በመስጠት የሚጎናፀፉት እርካታ ወደር የለውም:: አዎ! በመስጠት የሚገኝ ደስታ ልኬታው የከፍታ ጣራ ይደርሳል፡፡ ምላሽ ሳይጠብቁ ዝም ተብሎ የሚቸር በጎነት ያለ ክፍያ የሚሰጥ መልካምነት ከሁሉ ይልቃል፡፡ ያለ ቀስቃሽ ለበጎነት መሰለፍ መታደል ነው፡፡ ያለ ጎትጓች አገርና ወገንን ለመርዳት መነሳት፤ በራስ ተነሳሽነት ለበጎ አላማ መትጋት ትልቅነት ነው፡፡
ክረምት የበዙ በጎ ፍቃደኞች በበጎ ፍቃድ ተግባር ተሰማርተው ቀዝቃዛውን አየር በመልካም ሥራቸው ምክንያት ከማህበረሰቡ በሚያገኙት ፍቅር በሙቀት የሚያሸንፉበት ወቅት ነው፡፡ በበጎ ፍቃድ በጎን መስራት በበጎ ምግባር መሳተፍ የላቀ ትርፍ ያስገኛል:: መንፈስን የሚያረሰርስ ውስጥን ሰላም የሚሰጥ ትልቅ ትርፍ፡፡ በጎ ለመስራት ወይም በጎ ተግባር ላይ ለመሳተፍ በጎ ሀሳብ ብቻ በቂ ነው፡፡
እናንተዬ! የዘንድሮ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች አስተምረውን አለፉ አይደል? ለዚያውም አቻ የሌለው ትምህርት፡፡ መስጠትን፣ ለወገን ማሰብን፣በጎነት በአንድነት አዋህደው የመስጠትን ትሩፋት ከእናንተ በላይ ገብቶናልና፤ መስጠት ከመቀበል ይበልጣልና ተማሩ ብለው በጎነት አስተማሩን፡፡
እንካችሁ እኛ ለእናንተ በጎ ነገርን አለን ብለው ቅንነትን አሳዩን፡፡ የዘንድሮውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቀድመው በበጎ ተግባር አስተኮሱት የዘንድሮውን መልካም ተግባር ባደረጉት ሰናይ ምግባር አቀጣጠሉት፡፡
ስላለ ብቻ መስጠትን አይታደሉትም፤ ኪስም ስለነጠፈ ብቻ የሚሰጡት ነገር አያጡም፡፡ ዋናው በጎ እሳቤ ነው፡፡ ያ በጎ ሀሳብ በጎ ነገርን ይወልዳል፡ ፡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ሥራ፣ ገቢ ይሉት ነገር እነርሱ ጋር የለም፡፡ግን ደግሞ እነርሱ ጋር ከፍ ያለ በጎነት የላቀ ሰብዓዊነት እንዳለ በጉልህ አሳዩ፡፡
ከሌላቸው ላይ በመስጠት የበጎነት ጥግን አመላከቱ፡፡ እያላቸው ጨምረው ከሌላ ለሚነጥቁት ስግብግቦች ትልቅ ትምህርትን ሰጡ፡፡ ፈተናቸውን ጨርሰው ሲወጡ አንድ ኢትዮጵያዊ በጎነት ያመላከተ ለወገን ያላቸውን ብርቱ ፍቅር የገለፁበት ተግባርን ፈፀሙ፡፡
የለበሱትን የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም)፣ እርሳስ፣ እስክሪብቶ፣ ደብተርና የተጠቀሙበት የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች ቀጣይ ዓመት ትምህርትን ፈልጎ በቁሳቁስ እጥረትና በደንብ ልብስ ማጣት ተማሪ ከትምህርት እንዳይቀር በማሰብ ያላቸውን አበርክተው በወገናዊ በጎ አድራጎት ተማሪዎቹ ሌሎችን አስተማሩ፡፡
በጎ ተግባር ላይ መሳተፍ አይደለም የተሰራ በጎ ተግባር ማጥላላት የሚቀናው ስንት አለ መሰላችሁ፡፡ ብሩህ ነገርን በጎደፈ መነፅር እየተመለከተ የሚያነትብ ስንት ጉደኛ አለ መሰላችሁ፡፡ ታዲያ እነዚህ ተማሪዎች መመልከት ከቻለ ልከኛ አስተማሪዎቹ አይደሉም?
አሁን አሁን በሀገራችን ክረምትና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተለመደ የመጣ መልካም ባህል ነው፡፡ በበጎነት ተሞልተው በራሳቸው በጎ ፍቃድ ለመልካም ሥራ የሚተጉ ወጣቶች ክረምት ላይ ቁጥራቸው ይበዛል፡፡ በጎ መስራት የራስን አሳልፎ ለሌላ መቸር ነውና በወጣትነት ከፍ ይላል፡፡ በተለይ የበጎ ፍቃደኝነት ተግባር በወጣትነት ጊዜ ሲሆን ይገዝፋል::
በአንድ ቤተሰብ ወይም ግለሰብ ላይ የሚፈጠር ችግር የቤተሰቡና የግለሰቡ ብቻ ሳይሆን የኅብረተሰብ ነው። በጎ ፍቃደኝነትም የማህበረሰቡን የተለያየ ችግሮች መቅረፊያ አንዱ መንገድ ነው፡፡
የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ችግኞችን መትከል፣ አካባቢን ማፅዳት፣ ህሙማንን ማስታመም፣ ደም በመለገስ፣ ለአቅመ ደካሞች ቤት መስራት፣ የመንገድ ትራፊክ ደንብ በማስከበር ኅብረተሰቡን ከመኪና አደጋ መታደግ፣ ችግረኞችን አስተባብሮ መርዳት የመሳሰሉት የክረምት በጎ አድራጊዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት ናቸው፡፡
አብሮነት መለያው ህብረት በጎነት በጋራ ማበር ልምዱ ነውና ኢትዮጵያዊነት ሕዝባችን የጋራ ችግሩ ላይ በጋራ መዝመት ያውቅበታል፡ ፡ አገሬው ኃላፊነት በጋራ የመውሰድ ባህል አለው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህል እንዲኖረው ያደረገው ከዚህ ኃላፊነትን በጋራ የመውሰድ ልማዱ ነው። የበጎ ተግባር ክፍያው የገዘፈ የመንፈስ እርካታ ነውና የተደላደል ውስጣዊ ሰላም ለራስ ትልቅ ሽልማትን መሸለም ነውና ሁሌም ይሄን ሽልማት ለመጎናፀፍ መጣር ግድ ይላል፡፡
በበጎ ዘውታሪ በመልካም ነገር ተጠሪ የሆኑ ሰዎች መኖራቸውን በየአጋጣሚው እንሰማለን፡፡ እርግጥም ዓመቱን ሙሉ በጎነትን ተላብሰው ሕዝብና አገራቸውን ለማቅናት ደፋ ቀና የሚሉ አገር ወዳዶች ዜጎች አገሬ አፍርታለች፡፡ ይህች ሀገር ከራሳቸው በላይ የሚወዷት መውደዳቸውን በተግባር ያረጋገጡላት በጎ ሰሪዎችን ደጋግማ አበርክታለች፡፡ ለሀገርና ለወገን ፍቅር ማሳያው መንገድ ደግሞ በጎ ነገር ማበርከት ነው፡፡
በጎነት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ መልካምነት መልኩ የበዛ አከዋወኑም የተለያየ ነው፡፡ ሀገር የሚለውጥ መልካም ሀሳብ ካለህ እሱን ለሀገርህ አበርክት፡፡ ያ በጎ ሀሳብህ አገርን ለማቅናት መንገድ ይሆን ይሆናል፡፡ እውቀት ካለህ ሳትሰስት ለሌላው አውረስ ምን አልባት ያ እውቀት በተሻለ መልኩ ተግባራዊ አድርጎት ለለውጥ መሠረት ይጥል ይሆናል፡፡
ወጣትነት በጎ ቦታ ላይ ሲያገኙት ደስ ይላል:: ይህ ትኩስ ጉልበትና አገር በሚለውጥ ሀገር በሚያሳድግ በጎነት ላይ ሲውል ትርፉ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ መሰማራታቸው የላቀ ጠቀሜታ ያጎናፅፋቸዋል፡፡
አንድም ከፍ ያለ የመንፈስ እርካታን ያገኙበታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ወጣቶቹ ማህበራዊ ቁርኝታቸውን ያሳድግላቸዋል፣ የሕይወት ተሞክሮዎቻቸውን ያሰፋላቸዋል፣ ማህበረሰባቸውን ቀርበው እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል፤ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ያጠናክርላቸዋል፡፡
ይህ ሁሉ ትርፍ ለወገን በጎ ነገር ላበርክት ብለው በሚውሉት በጎ ተግባር ነው፡፡ ለበጎ ነገር መቅረብ የበዛ በጎ ነገርን ወደራስ ማቅረብ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ክረምቱ ወጣቶች በትምህርት ቆይታቸው እረፍት የሚያደርጉበት ጊዜ ነውና ይሄንን ጊዜያቸውን በመልካም ነገር ማሳለፋቸው ተገቢ ነው፡፡
ወጣቶቻችን በየአካባቢው በበጎ ፍቃደኝነት ተሰማርተው በጎ ምግባርን በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ማህበራዊ ልዩ ልዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚታትሩ ናቸውና በጎ ሥራቸው በማበረታታትና ለሚሰሩት በጎ ሥራ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ከሁላችን ይጠበቃል፡፡
እጅግ የሚደንቀው ደግሞ ይህን በጎ ተግባር የሚኮንን ጥግ ሆኖ የሚሰራው ሰናይ ተግባር የሚወርፍ መኖሩ ነው፡፡ ይሄስ ለማውራትም የሚከብድ የጉደኞች ጉድ ነው! መልካምነት ተላብሰው ባይተገብሩት እንዴት በመልካም ተግባሮች ይቀልዳሉ? እርግጥ ነው አንዳንዱ ስሪቱ ሁሉ ግራ ነውና የሚመለከተው ህፀፆችን ብቻ እየለየ መኮነን መጥፎን ብቻ እያገዘፈ መተንተን ቋሚ ሥራው አድርጎታል፡፡
በመልካምነትና በበጎ ተግባር መዛበትን የመሰል የገዘፈ ስህተት ከተሳሳተ ሰው የሚጠበቅ ነውና አይደንቅም፡፡ ሰው እንዴት ቅን ባይሆን የቀና ነገር መመልከት ይሳነዋል፡፡ ወዳጄ ኧረ አያዋጣም ይሄ መንገድ እኮ የሚያስት መድረሻውም የሚያዳልጥ ነው፡፡ ይልቁንም ዓይንህን ግለጥ መልካምነትን ተለማመድ ቢያንስ ግን በጎ ተግባሮችን ባትረዳ ለመልካም ምግባራቸው ድጋፍ ባትሰጥ እንቅፋት ባለመሆን አስተዋፅዎን አበርክት፡፡
ዘመን በራሱ ምንም ነው ወዳጄ! ዘመን በጎ አልያ ደግሞ ክፉ የሚያሰኘው የዘመኑ ሰዎች ተግባር፤ እይታና እሳቤ ነው፡፡ በጎ ሰዎች በጎ ዘመንን ይፈጥራሉ:: ሌለኞቹ ደግሞ በተቃራኒው፡፡ ዘመንን በጎ ማድረግ የነዋሪዎቹ ድርሻ ዘመኑን በጎ ማለት ደግሞ የዘመኑ መርማሪዎች ፈንታ ነው፡፡
ወዳጄ የተገኘህበት ዘመን በጎነት ለመጠበቅ ትጋ ካልሆነ ግን ያ ዘመን መልካም አልነበረም ተብሎ ዘመንህ ይንኳሰሳል፡፡ ይህቺ ምድር ኖራ ያገኘናትና ጥለናት የምንሄድ ጊዜያዊ እንግዶቿ ነን፤ በቆይታችን በጎ ነገርን አበርክተን መልካም ነገርን ትተን እንለፍባት፡፡ አበቃሁ! በጎነት ለሚተገብሩ ሁሉ በጎነትን ተመኘሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ተገኝ ብሩ