ሊቢያ በሰሜን አፍሪካ የምትገኝ አገር ስትሆን ከሜድትራኒያን ባሕር፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ቻድ፣ ኒጄር፣ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ ጋር ድንበር ትጋራለች። ሊቢያን ለ42 ዓመታት እንደሰም አቅልጠው በመዳፋቸው ቁጥጥር ስር አድርገው እስከ 2003 ዓ.ም ሕዝባዊ አመጽ ተቀስቅሶ እስከተወገዱበት ድረስ አገሪቱን በብቸኝነት ቀጥቅጠው የገዟት ሙአማር ሙሀመድ አቡ ማይናር አል ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ድፍን ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የቀድሞው የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ በ2003 ዓ.ም ለ42 ዓመታት ከቆዩበት ዙፋናቸው በሕዝባዊ ዓመፅ ተወግዶ ከተገደሉ ማግስት ጀምሮ ታጣቂ ቡድኖች እንደቅርጫ ስጋ የተከፋፈሏት ሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች። በተለይ ደግሞ ምስራቃዊውና ምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍሎች እርስ በእርስ በሚዋጉ ታጣቂ አንጃዎች ስር መውደቃቸው ጦርነቱን የከፋ አድርጎታል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የተሰጠውና በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግለት ቡድን በፋይዘል አል-ሲራጂ የሚመራው ሲሆን መናገሻውን በትሪፖሊ አድርጎ ‹‹ገቨርመንት ኦፍ ናሽናል አኮርድ የተባለ ‹‹መንግሥት›› መስርቶ ተቀምጧል። በፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር የሚመራውና ራሱን ‹‹የሊቢያ ብሔራዊ ጦር›› ብሎ የሚጠራው ቡድን ደግሞ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሲራጂን መንግሥት አላውቅም›› ብሎ በምስራቃዊ ሊቢያ በምትገኘው ቶብሩክ ከተማ ላይ ተሰይሟል። ይህ ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዘል አል-ሲራጂ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር በትሪፖሊ ብቻ እንዲወሰን አስገድ ዶታል።
የፊልድ ማርሻል ከሊፋ ሃፍታር ቡድን ለፋይዘል አል-ሳራጅ ‹‹መንግሥት›› ያለው ጥላቻ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ቡድኑ የአል-ሲራጂን ‹‹መንግሥት›› ‹‹መንግሥትነትህን አላውቅም›› ብሎ በመናገር ሳይገደብ የትሪፖሊውን መንግሥት ፈንግሎ በመጣል ዋና መንግሥት ለመሆን ዋና ከተማዋን ለመቆጣጠር እየተፋለመ ይገኛል። የአል-ሲራጂ መንግሥት በበኩሉ ‹‹እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም›› ብሎ በሚወስደው የመከላከል እርምጃ ሊቢያውያን ፍዳቸውን እያዩ ይገኛሉ።
በዚህም ላለፉት አራት ዓመታት በሊቢያ ያለው የእርስበርስ ጦርነት ቆሞ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብዙ ጥረት እያደረገ ቢገኝም፤ አሁን ላይ በአገሪቱ ከሶስት ወራት በላይ የዘለቀ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል። የጄነራል ካሊፋ ሃፍታር ጦር ሰራዊት ዋና ከተማዋን ትሪፖሊን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጦርነት ከተማዋ እየወደመች ትገኛለች። በጦርነቱ ከስድስት መቶ ሰዎች በላይ ተገድለዋል፣ ከሶስት ሺ ሰዎች በላይ ተጎድተዋል እንዲሁም ከ90 ሺ በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ብዙ ህንፃዎችና የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል።
በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግጭቶች እንዲቆሙ የተለያዩ ሃሳቦችን በተደጋጋሚ ቢያቀርብም ሁለቱም ተዋጊ ሃይሎች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ጦርነቱን እያፋፋሙት ይገኛል። ብሄራዊ የስምምነት መንግሥት እና ሀፍታር በአካባቢው ተኩስ አቁም ለማድረግም አልተስማሙም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በሊቢያ ሰላም ለማምጣት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ በአገሪቱ ጉዳይ የተያዘውን ድርድር ማስጀመር አልቻለም። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የዓለም መንግሥታት በሊቢያ ጉዳይ ያላቸው አቋም የተከፋፈለ በመሆኑ ነው። በተጨማሪም የተለያዩ አገራት ሁለቱን ተፋላሚ ቡድኖች በመደገፍ ጦርነቱ እንዲባባስ እያደረጉ ይገኛሉ።
በአገሪቱ መረጋጋት ለማምጣት ጦርነት አማራጭ ተደርጎ በመወሰዱ አገሪቱ ከመፈራረሷ በተጨማሪ ንፁሀን ዜጎች እየሞቱ ይገኛሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ልዑክ ጋሳን ሳላሜ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩት ጉዳይ ቢኖር በትሪፖሊ አካባቢ እየተደረገ ያለው ጦርነት የረጅም ጊዜ ደም መፋሰስ እንደሚኖር ማሳያ ነው። ዓለም አቀፉ አገራት ጣልቃ በመግባት ነገሮች የማይለወጡ ከሆነ በሊቢያ የንፁሀን ዜጎች ሞትና ስቃይ እየበረታ የሚሄድ ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል።
ነገር ግን በሁለቱ ጦር ሰባቂ ኃይሎች መካከል በሚደረገው ፍልሚያ አገሪቷ ዜጎቿ የከፋ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ የተጋረጠባቸው ናቸው። የወንበዴ መፈንጫ በመሆን የተለያዩ ወንጀሎችም ተበራክተውባት ይገኛል። በተለይ ይቺን አገር እንደ ድልድይ በመጠቀም ሜድትራኒያን ባሕርን አቋርጠው ምዕራባውያኑን ለመቀላቀል በማሰብ በአገሪቱ የከተሙ አያሌ ስደተኞች ላይ የሚፈጸመው ዘግናኝ ግፍ ቀን ከቀን እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ይገኛል።
ስደተኞችም በህገወጥ ደላሎች አካላቸው እየተሸጠ ሰብዓዊ ክብራቸው ተዋርዶ ከዛሬ ነገ ይሻላል በሚል ተስፋ በአገሪቱ በሚገኝ በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፤ በየማቆያ ማዕከላቱ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች በጣም በተጣበበ ቦታ እንደሚኖሩና እጅግ አስደንጋጭ በሆነ የምግብ እጥረት ላይ እንደሚገኙ ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ገልጿል።
ስደተኞቹ በከፍተኛ የጤና ችግር ላይ እንደሚገኙና፤ ጉዳዩ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን የሚያትተው ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን «MSF» በተለይ እድሜያቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕጻናት በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲኖሩ በመገደዳቸው ለከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ችግር መዳረጋቸውን ቡድኑ ጠቁሞ፤ እነዚህ ሕጻናቶች ከመጠለያ ጣቢያዎቹ እንዲወጡ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪውን አቅርቧል።
የዓለም አቀፉ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን «UNHCR» በሊቢያ ያለው የስደተኞች አልያም የተገን ጠያቂዎች መጠለያ እንዲዘጋና ስደተኞቹ አጎራባች አገር ወደ ሚገኝበት የስደተኞች መጠለያ እንዲያመሩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል።
ይህ እንዳለ ሆኖ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በያዝነው ሳምንት ከወደ ሊቢያ የተሰማው ዜና በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት በትንሹ 44 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል። ጥቃቱ የደረሰው በትሪፖሊ ምስራቃዊ ክፍል በሚገኝ ታጆራ በሚባል ስፍራ ሲሆን፤ 80 ሰዎች በፍንዳታው መቁሰላቸው ተገልጿል። ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ስደተኞች ናቸውም ተብሏል።
የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆነው ኦሳማ አሊ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንደተናገረው ከሆነ በአየር ጥቃቱ የስደተኞች ማቆያው ሲመታ 120 ስደተኞች በውስጡ ነበሩ ብሏል። ቃል አቀባዩ አክሎ አሁን ያለውን መረጃ በቅድመ ዳሰሳ የተገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ‹‹መንግሥት›› ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ፋዬዝ አል ሴራ ራሱን የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ብሎ የሚጠራውን አማጺ ኃይል ለጥቃቱ ተጠያቂ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው እንደተናገሩት ‹‹ቀድሞ የታሰበበት እና ማቆያውን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ነው›› በማለት ድርጊቱን አውግዘዋል። ጥቃቱንም ‹‹ከባድ ወንጀል ነው›› ሲሉ ገልጸውታል።
በአንጻሩ በካሊፋ ሐፍታር የሚመራው አማፂ ቡድን ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን መንግሥት በመዋጋት ላይ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ ቡድኑ በያዝነው ሳምንት ሰኞ እለት ጠንከር ያለ የአየር ጥቃት እንደሚያደርግ ገልጾ፤ በኢላማውም የተመረጡ ያላቸውን ስፍራዎች እንደሚያጠቃ አሳውቆ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት በስደተኞች ማቆያ ላይ የደረሰውን የአየር ጥቃት ‹‹እጅጉን አሳሳቢ›› ሲል ገልጾታል። ጥቃቱ በደረሰበት የስደተኞች ማቆያ የተገኙት ዶክተር ቢን አታኢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ‹‹እዚህም እዚያም ህይወታቸው ያለፈና የቆሰሉ ሰዎች ይታያል፤ መጠለያውም ወድሟል፤ ሰዎች ያለቅሳሉ፤ የስነልቦና ቀውስ አለ፣ ጥቃቱ ሰቅጣጭ ነው›› ሲሉ በአይናቸው ያዩትን ሁኔታ ምን እንደሚመስል ገልጸዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ በሊቢያ ተሻግረው አውሮፓ ለመድረስ የሚያስቡ ስደተኞች የሚቆዩት መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የስደተኛ ማቆያዎች ሲሆን፤ እነዚህ አብዛኞቹ መጠለያዎች የሚገኙት ከአማፂያን ጋር ጦርነት በሚደረግባቸው ስፍራዎች በመሆኑ ስደተኞቹ በቀላሉ የጥቃቱ ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ። በዚህም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች አያያዝ ላይ ትችት እያቀረቡ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች በህይወት የመኖር ህልውናቸው አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ሲሆን፤ በተለይም በመጠለያዎች የሚገኙ ሕጻናት፣ እናቶች እና በሕመም ላይ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከተጋረጠባቸው የሞት አደጋ ሕይወታቸውን ማዳን የሚቻለው የጦር አውድማ ከሆነችው ሊቢያ ወጥተው ወደ ሦስተኛ አጎራባች አገር ማዛወር ሲቻል ብቻ በመሆኑ፤ ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ስደተኞቹ የሊቢያን ምድር ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ህይወታቸውን መታደግ እንዳለበት ከተለያዩ የዓለም ክፍል ጥሪ እየቀረበ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሊቢያ ወደ አውሮፓ መሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች መነሻ ሆና እያገለገለች ስትሆን፤ ሊቢያን ለረዥም ጊዜ ሲያስተዳድሯት የነበሩት ሙአመር ጋዳፊ እ.አ.አ በ2011 ከስልጣን ከወረዱ በኋላ አገሪቷ በእርስ በእርስ ግጭት እየታመሰች ነው። የተለያዩ የጦር አበጋዞች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎችም ሀገሪቱ ተከፋፍላ ትገኛለች።
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2011
ሶሎሞን በየነ