
ኢትዮጵያ ለዜጎች አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመክፈት ያለባትን የሥራ አጥ እዳ ወደ ምንዳ ለመቀየር እየሠራች ነው፡፡ መንግሥት በየዓመቱ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል እየፈጠረ ቢገኝም ሀገሪቱ ካላት ግዙፍ የሥራ አጥ ቁጥር አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ለሥራ አጥ ወጣቶች አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር በኩል እንዲሁም በሀገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ እዳ ወደ ምንዳ ለመቀየር ምን እየተሠራ ነው? እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ እድሎች የሥራ አጥ ቁጥርን ምን ያል እየቀነሱ ነው?
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በሰጡት አስተያይት፤ ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆን አምራች ዜጋ አላት፡፡ ይህንን አምራች ዜጋ ወደ ሥራ በማሰማራት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን በሀገር ወስጥና በውጭ ሀገር ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሠራ ነው፡፡
በሀገሪቱ ያለውን የሥራ ቁጥር ለመቀነስ እየተሠራ ባለው ሥራ በ2016 በጀት ዓመት ለሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዜጎች በሀገር ውስጥ እንዲሁም ለሶስት መቶ 45 ሺህ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ዜጎች በውጭ ሀገር የሥራ እድል የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥ እዳ አለባት፤ ያለባትንም የሥራ አጥ ቁጥር በመቀነስ ኢኮኖሚያዊ ምንዳ ለማምጣት ለዜጎች አዳዲስ የሥራ እድሎችን የመፍጠር ሥራ እየሠራች ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በየዓመቱ ሶስት መቶ ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ሳይንስ ከየዩኒቨርሲቲው ይመረቃሉ፤ እነዚህ በየዓመቱ የሚመረቁ ዜጎችን የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ እድል እንዲያገኙ፤ ሀገሪቱም ገቢ እንድታገኝ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለው ሥራ በቂ ቢሆንም ሀገሪቱ ካላት ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር አንፃር ሲታይ ግን በቂ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ዲጅታል ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚያለሙ፣ አገልግሎት የሚሰጡ፤ የቴክኖሎጂን ፈጠራ የሚሳድጉ ጀማሪ ቢዝነሶችን የማሳደግና የመደግፍ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የተለያዩ ጀማሪ ቢዝነስ ሥራዎችን በማበረታታትና በማሳደግ ለሥራ አጦች የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥራን በኢትዮጵያ በማሳደግ ሰፊ የሆነ የሥራ እድል መፍጠር፤ የቴክኖሎጂ እውቀትን ለውጭ ሀገራት ኤክስፖርት በማድረግ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው፤ እየተሠራ ያለው ሥራ በተፈለገው ልክ እያደገ ሲመጣ ለሀገር ውስጥ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ለሌሎች ሀገር ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በዓለም ገበያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የእውቀት ኤክስፖርት በዓመት ሶባት መቶ 30 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል፤ በዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ገበያ ከሚያስገኘው 730 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ የአውትሶርሲንግ ገበያ 350 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን ይይዛል ያሉት አቶ ሰለሞን ፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አውትሶርሲንግ ገበያ በየዓመቱ 50 ሚሊዮን ዶላር ነው የምታገኘው ሲሉ ገልጸውልናል፡፡
አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያ ኮደሮች ማለትም በሶፍትዌር እድገት፤ በዳታ ትንተና፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሳይበር ሴኩሪቲና በሌሎች የዲጂታል ልማት ለሥራ አጥ ዜጎች በነፃ ሥልጠና በመስጠትና የሠለጠኑትን የሰው ሃይል ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር የሥራ ገበያ በማዋል ሀገሪቱ ያላትን የሥራ አጥ ቁጥር እዳ ለመቀነስ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የሰዎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂን እውቀት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲቻል ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር መፍጠር ማለትም ምቹና ቀልጣፍ መሠረተ ልማት የማሟላት ሥራ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት በሀገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ እዳ ወደ ምንዳ ለመቀየር ኮደሮችን አደራጅቷል፤ አይ ሲቲ ፓርኮችን ከፍቷል፤ ይህም ኢንቨስተሮች ኢንቨስትመንት ሰፊ የሥራ እድል እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነው የሰው ሃይሏን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሥራ እድል የማሰማራት ሥራ መሥራቷ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን በእጥፍ ያሳድጋል፡፡ ሥራ አጥ ዜጎችን ወደ ሥራ በማሰማራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ የተለያዩ የሥራ እድል አማራጮችን የመጠቀም፤ ፖሊሲዎችን የማሻሻያ ሥራ እየሠራች ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አውትሶርሲንግ አሶሲየሽን ፕሬዚዳንት አቶ ወንደወሰን ዘውዴ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ያለውን የሥራ እድል ጫና ለመቀነስ ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አውትሶርሲንግ ኢንዱስትሪ፤ በአይሲቲ ዘርፍ በየዓመቱ ለአንድ ሚሊዮን ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር ሥራ እየከናወነ ነው፤ ይህም ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡
የሀገሪቱን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ አዳዲስ የሥራ እድሎችን መፍጠር ያስፈልጋል፤ ዜጎችን በሥራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ከተቻለ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ትሆናለች ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በሀገሪቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሌላም ተሰጥኦ ያላቸው ሥራ አጦችን በማሰልጠን ለውጭ የሥራ ገበያ የማቀረብ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ይህም ለሀገር ጥቅም ሁለተናዊ ፋይዳ አለው ሲሉ ገልጸውልናል፡፡
የሀገሪቱን የሥራ አጥ ቁጥር ጫና ለመቀነስ ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር በመዘርጋት፣ የግል ዘርፎች በሥራ እድል ፈጠራ እንዲሳተፉ ማገዝ፤የእውቀት የገበያ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው፤ መሰረተ ልማት የማስፋፋት ሥራ ከተሠራ፤ ሀገሪቱ ያላትን የተማረና ባለተሰጥኦ የሰው ሃይል ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከተቻለ የስራ አጥ ቁጥርን መቀነስ ብቻ አይደለም፤ በዘላቂነት መቅረፍ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለሥራ አጥ ዜጎችን የስራ እድል መፍጠር ወጣቶች ራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲያሳድጉ፤ አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ያደርጋል፤ በሀገርም ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት ያስችላል፤ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው የሀፍ ሶፍትዌር ፕሮፊሽናል ድርጅት ማናጀር አቶ ዘውዱ ዘበርጋ ፤ በኢትዮጵያ የሚታየውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እየተሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ለሥራ አጥ ዜጎች ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር መሠረተ ልማትን በመዘርጋት፤ ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር መፍጠር፤ ጀማሪ ቢዝነሶችን ማበረታታት፣ አዳዲስ የስራ እድል አማራጮችን መዘርጋት፤ ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ሃይል ወደ ስራ ማሰማራት ከቻለች በኢኮኖሚው ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል፡፡
በየዓመቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የግል ዘርፉ ከመንግሥት፣ መንግሥት ከግሉ ዘርፉ በቅንጅት መሥራት፤ በከፍተኛ ቁጥር የሥራ እድል የሚፈጥሩ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮችን መሳብና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ማበረታታት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ.ም