ተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል አባት መባል ቢያንስባቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደሉም:: ምክንያቱም በኢትዮጵያ መጀመሪያ ፊደል በካርቶን ላይ ፅፈው ለማሰራጨት የሞከሩ ታላቅ አባት መሆናቸውን የትኛውም በተስፋ ገ/ሥላሴ ፊደል የተማረ ኢትዮጵያዊ የሚዘነጋው አይደለም::
ጥበበ ተስፋ ገ/ሥላሴ ደግሞ የተስፋ ገብረሥላሴ 5ኛ ልጅ ናቸው:: አቶ ጥበበ የተወለዱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ፋክልቲ 4 ኪሎ ጊቢ ነው:: በአራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ በ1935 ዓ.ም እርሳቸው ይህችን ዓለም ሲቀላቀሉ፤ የአሁኑ ቅድስት ሥላሴ አካባቢ ያለው ህንፃ በዛ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ሕንፃ ነበር::
የአሁኑ የስድስት ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) ከመቋቋሙ በፊት፤ የአሁኑ የአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሆኖ እንዲቋቋም እቅድ ተያዘ:: ስለዚህ አቶ ጥበበ ልክ እንደተወለዱ አባታቸው ተስፋ ገ/ሥላሴ የወቅቱ የልማት ተነሺ ሆነው ኮሌጁ እንዲቋቋም ቦታቸውን ለቀቁ:: በምትኩ ከአራት ኪሎ ብዙም ሳይርቁ ከአሁኑ ትምህርት ሚኒስቴር ጀርባ 7ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጣቸው:: የአሁኖቹ የአራት ኪሎ ሕንፃዎች ባሉበት አካባቢ ሰፊ ቦታ የተሰጣቸው ቢሆንም፤ አሁን ላይ 2ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ውጪ ሁሉም ቦታ በተለያየ ጊዜ እየተገፋ ተወስደውባቸዋል::
‹‹የላይኛው የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ይባል ነበር:: በኋላ በደርግ ጊዜ ስሙ ተቀይሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባለ:: ከዛ በፊት ግን የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተቋቋመው እኔ በተወለድኩበት በአባታችን በተስፋ ገ/ሥላሴ ጊቢ ነው::›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ጥበበ፤ አባታቸው የአሁኑ የተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት ባለበት አካባቢ መኖሪያ ቤት ገንብተው ኑሯቸውን ከመመሥረት አልፈው ማተሚያ ቤት ከፍተው አሁን ድረስ የሕትመት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገለፁልን::
አቶ ጥበበ ምንም እንኳ ለቤታቸው ሁለት ታላላቅ ሴት እህቶች እና ሶስት ታላላቅ ወንድሞች ቢኖሯቸውም፤ አሁን ላይ ሶስቱም ወንድሞቻቸው በሕይወት የሉም:: ስለዚህ አቶ ጥበበ ለ47 ዓመታት ከኖሩባት ሀገረ አሜሪካ መጥተው የተስፋ ገ/ሥላሴን ማተሚያ ቤት እየመሩ ይገኛሉ::
የፊደሉ ታሪክ
ተስፋ ገብረሥላሴ በቡልጋ ሸንኮራ አካባቢ የሚኖሩ ካህናትን የተዛመዱ ብቻ ሳይሆኑ የካህን ዘር ናቸው:: የቡልጋ ሕዝብ ደግሞ አለቃ እገሌ፤ አለቃ እገሌ የሚባባል ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪ ከ80 በመቶ በላይ ፊደል የቆጠረ ነው:: ስለዚህ ተስፋ ገብረሥላሴም የተወለዱበት አካባቢ ፊደል ለመቁጠር ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረላቸው ፊደላትን በደንብ አወቁ:: ነገር ግን በዛ አላበቁም:: ዳዊት መድገም ቻሉ፤ ድቁና ላይ ደረሱ:: ተስፋ ከድቁና አልፈው ወደ ቄስነት ሊሄዱ አልወደዱም:: ቄስነት ይቅርብኝ አዲስ አበባ ከተማ መግባት ይሻለኛል ብለው ወንድማቸው ብርሃኑ ቤት መጥተው ተቀመጡ::
ሌላ ሥራ መሥራት ስለማይችሉ መነገድ ጀመሩ:: የመጀመሪያው ንግዳቸው ሽቶ መሸጥ ነበር:: ሽቶ አልሸጥላቸው ብሎ ተቸገሩ:: ሽቶ መሸጥን ትተው፤ ጋዜጣ መሸጥ ጀመሩ:: በሌላ በኩል ደግሞ የጋዜጣ ሽያጫቸውም አዋጭ አልሆነም:: ምክንያቱም ሰዎች መግዛት ቢፈልጉም ማንበብ ስለማይችሉ ጋዜጣ መሸጥ ፈተና ሆነባቸው:: አንዳንዶች ደግሞ ‹‹እንግዛህ እና አንብብልን::›› እያሉ መጠየቅ ጀመሩ:: ተስፋ ገበያ በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን ሰዎች ማንበብ ስለማይችሉ፤ ‹‹ለምን ሰዎች ማንበብ አቃታቸው ?´ ብለው ራሳቸውን ጠየቁ:: ለጥያቄያቸው ራሳቸው ምላሽ አገኙ:: ምክንያቱም ፊደል የሚያውቁት እና ማንበብ የሚችሉት ልክ እንደሌላው ዓለም ሁሉ የቤተ ክህነት እና የቤተመንግሥት ሰዎች ብቻ በመሆናቸው ነው ሲሉ ለራሳቸው ምላሽ ሰጡ:: በእርግጥ የመንግሥት ሥራን የሚሠሩ ሰዎችም ፊደል ለይተው ማንበብ ይችሉ ነበር:: ነገር ግን እነርሱም ከቤተ ክህነት እና ከቤተመንግሥት ብዙም የራቁ አልነበሩም::
ስለዚህ ተስፋ ጋዜጣው እንዲሸጥላቸው ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ማንበብ መቻል አለበት ብለው ማሰብ ጀመሩ:: መላ ዘየዱ:: በእርግጥ እርሳቸው በቤተክህነት ሲማሩ ፊደል በቆዳ ተቀርፆ ይቆጥሩ ነበር:: ያንን ማድረግ እና ለሕዝብ ማዳረስ ከባድ መሆኑን ተረድተዋል:: ስለዚህ ከዕፅዋት ቀለም እየቀመሙ ካርቶን ላይ ፊደሎቹን በቅደም ተከተል ፃፏቸው:: ሀ ሁ ሂ …ከሚሉት በተጨማሪ ኣ ቡ ጊ ዳንም ፃፉ:: ተስፋ ይህንን ያደረጉት በ 1910 ዓ.ም ነበር:: ፊደላቱን በብዛት ፅፈው የካቲት 23 ቀን የዓድዋ ድል ሲከበር አራዳ ጊዮርጊስ መሸጥ ጀመሩ:: በዛ ጊዜ ብዙዎች ፊደል ማወቅ ይፈልጉ ስለነበር የፃፉትን በሙሉ ገዟቸው:: ከዛ ወዲያ ፊደላቱ በመላ ከተማዋ እየታወቁ ሔዱ:: ነገር ግን በእጅ እየፃፉ መሸጥ ቀላል አይደለም::
ስለዚህ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ወሰኑ:: በዛ ጊዜ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ያቋቋሙት መርሃፅድቅ ማተሚያ ቤት ሄዱ:: ‹‹ቤተክህነት ፊደል አምጥቷል:: እናንተ ደግሞ ማተሚያ አላችሁ:: ፊደል እናትምና ሕዝቡን ፊደል እንዲለይ እናግዘው:: እባካችሁ ፊደላቱን እንዳትም ፍቀዱልኝ::›› በማለት ለማተሚያ ቤቱ ሃላፊ ጥያቄ አቀረቡ:: ማተሚያ ቤቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሰው ‹‹ይቻላል›› ብለው ፈቀዱላቸው:: በኋላ መሃል ላይ መልዕክተ ዮሃንስ አካተው:: በግራ ሀ ሁ ሂ ሃ … በቀኝ አ ቦ ጊ ዳ … አሳትመው መሸጥ ጀመሩ:: በመጨረሻም የአማርኛ ፊደል ብቻ ሳይሆን የእንግሊዝኛ ፊደል እና ቁጥሮች ተካተውበት በስፋት እየታተመ እንዲሸጥ ማድረግ ቻሉ:: በኋላም ራሳቸው ማተሚያ ቤት አቋቋሙ ሲሉ የፊደሉን ታሪክ የነገሩን ልጃቸው አቶ ጥበበ ተስፋ ናቸው::
የተስፋ ገ/ሥላሴ ትዳር
ቀኝ አዝማች ተስፋ ከመጀመሪያው ትዳራቸው ሁለት ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ ወልደው ነበር:: ወንዶቹ አሁን አርፈዋል:: የእነርሱ እናት ደግሞ የሞቱት በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው:: ጣሊያን ማይጨው ላይ የጦርነቱን ሳይሆን የጦር ሜዳውን ሲያሸንፍ፤ ሰዎች ከአዲስ አበባ ተነስተው ይሸሹ ነበር:: አንዳንዶች ደግሞ ሸፍተው ይዋጉ ነበር:: ቀኝ አዝማች ተስፋም ከነራስ አበበ አረጋይ ከእነሃይለማሪያም ማሞ ጋራ ቡልጋ ሸፈቱ:: ቀኝ አዝማች ተስፋ ሲሸፍቱ ባለቤታቸው በወረርሽኙ ተያዙ:: በቂ ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ:: ከዛ ከነፃነት በኋላ የእነጥበበ ተስፋን እናት አገቡ::
ሁለተኛዋ ሚስታቸው ወ/ሮ አለሚቱ ንጉሤ የመጡት ከጎጃም ነው:: ፊደል ስለማይለዩ ማንበብ እና መፃፍ አይችሉም ነበር:: ስለዚህ ቀኝአዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ሚስታቸውን በደንብ ፊደል እንዲቆጥሩ ከማስተማር ባሻገር፤ ልጆች እየወለዱና እያሳደጉ ዳግማይ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው እንግሊዝኛም ማንበብ እና መፃፍ እንዲችሉ አገዟቸው:: በኋላም የተስፋ ገብረሥላሴ ሚስት ከማህይምነት ወጥተው የራሳቸውን መኪና እስከመንዳት ደርሰው ነበር::
ሕይወት እስከ ተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት
አቶ ጥበበ እንደሚናገሩት፤ እርሳቸው እና ታናናሾቻቸው ተወልደው ጭምር እናታቸው ትምህርት ቤት እየተመላለሱ ሲማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ:: አቶ ጥበበ አራት ዓመት ሲሞላቸው ፊደል ቆጠሩ:: ቀኝ አዝማች ተስፋ ከቡልጋ ቄስ አስመጥተው አቶ ጥበበ ዳዊት እንዲደግሙ አደረጉ:: የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመቋቋሙ በፊት የድቁና ትምህርት ነበር:: እዛም ቀጠሉ:: በኋላ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ገቡ:: በኋላም አባታቸው እና እናታቸው ተመካክረው ‹‹ፈረንሳይኛ ከሚማር እንግሊዝኛ ቢማር ይሻላል::›› ብለው አጠና ተራ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት አስገቧቸው:: ፈተናቸውን አልፈው ጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተምረው ጨረሱ::
በወቅቱ የተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት በደንብ እየሠራ ነበር:: የመጀመሪያውን ሃይሊንበርግ የተባለ ትልቅ ሲሊንደር ያለው የማተሚያ ማሽን ከውጭ አስመጥተው ነበር:: ማሽኑ ትልልቅም ሆነ ትንንሾቹ ወረቀቶች ላይ የሚያትም አውቶማቲክ ማሽን ነበር:: ያንን ማሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጡት ተስፋ ገብረሥላሴ ናቸው:: እናም አቶ ጥበበ ከትምህርት ቤት መጥተው መጀመሪያም ከወንድሞቻቸው ጋር ይሠሩ የነበረበት የአባታቸው ማተሚያ ቤት ገቡ:: የማተሚያ ማሽኑ ሲበላሽ የፈረንሳይ መካኒክ ያስተካክለው ይባል ነበር:: ማሽኑን የሚሠራው ሰው ከፈረንሳይ ከመጣ በኋላ የሚነጋገረው ከአቶ ጥበበ ጋር ብቻ ሆነ:: ምክንያቱም አቶ ጥበበ ፈረንሳይኛ ስለሚያውቁ ከፈረንሳዩ መካኒክ ጋር አብረው ማሽኑን መሥራት ቀጠሉ:: አቶ ጥበበ በኋላም የማሽኑን መመሪያ (ማንዋል) እያነበቡ ማሽኑን በደንብ አወቁት:: አቶ ጥበበ በማተሚያ ቤቱ ከመሥራት አልፈው ስለህትመት መማር ፈለጉ::
የአቶ ጥበበ እናት ደግሞ ለቀኝ አዝማች ተስፋ እ.አ.አ በ1966 ዓ.ም፤ ‹‹ጥበበ ጀነራል ዊንጌት ተምሮ 12ኛ ክፍል አጠናቋል:: ዩኒቨርሲቲ ከመግባት ይልቅ ውጪ ሔዶ ቢማር ይሻላል:: ብለው አማከሯቸው:: ይህንን ሃሳብ ተከትሎ አቶ ጥበበ የህትመት ሳይንስ ለመማር ጀርመን ሔዱ:: በዛ ጊዜ ጀርመን ውስጥ ብዙ ኢትጵያውያን አልነበሩም:: ከአቶ ጥበበ በፊት ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ:: በሚኖሩባት ከተማ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ወንጀል ሰራ ቢባል የሚጠየቁት እርሳቸው ብቻ ነበሩ:: በጀርመን የቴክኒክ ትምህርት ቤት ገብተው የሕትመት (ፕሪንቲንግ) ሳይንስተ ተማሩ:: ቀጥለው በ1968 ዓ.ም እንደገና አንድ ማሽን ላይ ጥናት ለማካሔድ ኬንያ እና እንግሊዝ ሄደው ጥናታቸውን አጠናቀቁ:: በኋላም ለትምህርት አሜሪካን የሔዱ ሲሆን፤ እዛም በድጋሚ የሕትመት ሳይንስን ተማሩ:: ዛሬ ነገ ወደ አገሬ እመለሳለሁ ሲሉ፤ ከአንድ አሜሪካዊት ጋር በፍቅር ወደቁ:: ልጆች ወለዱ፤ በኋላም በዛው ቀሩ፡፡
አቶ ጥበበ አራት ልጆች ወልደው አሳደጉ:: ልጆቹ ተመርቀው ራሳቸውን ችለው እየኖሩ ናቸው:: አንደኛው የአሜሪካ ወታደር ሆነ:: ሁለቱ ዳግሞ ባዮኬሚስት ናቸው:: አንደኛዋ ደግሞ ሕይወቷ አልፏል:: እንደአቶ ጥበበ ገለፃ፤ አሜሪካ ለመኖር ምቹ ናት:: አንድ ሰው ከሠራ ቤተሰብ መመሥረት ይችላል:: ቤተሰቡን በደንብ ለማስተዳደር አይቸገርም:: በአሜሪካ በቂ የጤና አገልግሎት አለ:: አንድ ሰው ከሠራ በአሜሪካ ምድር የፈለገበት መድረስ ይችላል:: በአብዛኛው የአሜሪካ ሕዝብ በጣም ጥሩ ሕዝብ ነው::
ከስምንት ዓመት በፊት ግን ለ47 ዓመታት ከኖሩባት ከአሜሪካን መጡ:: አሜሪካ ጡረታ ሲወጡ ወደ ሀገራቸው ገቡ:: ወደ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ መጥተው የአባታቸውን ተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤትን ማስተዳደር ጀመሩ:: አሁን በማተሚያ ቤቱ በተለይ የቤተክህነት መፅሃፍትን እያሳተሙ ይገኛሉ:: ከ300 በላይ ዓይነት የቤተክህነት መፅሐፍትን እያሳተሙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መሃል ተዓምረ እየሱስ፣ ተዓምረ ማሪያም፣ መዝሙረ ዳዊት እና ሌሎችም ይገኙበታል:: አሁን ግን የወረቀት ዋጋ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመሆኑ ፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀውልናል::
የአሜሪካ ኑሮ
አቶ ጥበበ በአሜሪካ ትዳር መሥርተው ልጅ ወልደው ሲኖሩ፤ አንዷ ልጅ በጣም ታመመችባቸው:: ሐኪም ቤት ስትሔድ ገና በሶስት ዓመቷ የሥኳር በሽተኛ መሆኗ ታወቀ:: ከፍተኛ ክትትል ስለሚያስፈልጋት ሆስፒታሉ ውስጥ መተኛት አለባት ተባለ:: አቶ ጥበበ በበኩላቸው ሆስፒታሉ የሚያስከፍለው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ‹‹አቅም የለኝም፤ ልጄን ወደ ሌላ ሆስፒታል እወስዳለሁ›› አሉ:: ሐኪሙ ግን የገንዘቡ ጉዳይ ከልጅቷ ሕይወት አይበልጥም፤ ስለዚህ ቅድሚያ ልጅቷ ትትረፍ ብሎ ሕክምናው ተሰጣት እናም ተሽሏት ወደ ቤት ገባች:: አቶ ጥበበ በአራት ወር ውስጥ ሠርተው ልጃቸውን ያሳከሙበትን ዕዳ ለሆስፒታሉ ከፈሉ::
‹‹አሜሪካ ሀኪም በጭራሽ ክፍያ ካልተፈፀመ አላክምም ማለት አይቻልም:: ታካሚው ወይም የታካሚው ቤተሰብ ሠርቶ ይከፍላል:: ከዛ ውጪ በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ሰዎችን የህክምና አገልግሎት ሰጥቶ ማዳን ብቻ ነው::›› ይላሉ:: አያይዘውም አሜሪካን ትምህርት ቤት በነፃ ነው:: ልጆች ምሳ የሚበሉት እዛው ትምህርት ቤት ነው::
አቶ ጥበቡ እንደሚገልፁት፤ ወደ ውጪ ከመሔዳቸው በፊት አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ 23 ሚሊዮን ብቻ ነበር:: የአዲስ አበባ ነዋሪም 100 ሺህ አይሞላም:: ስለዚህ በሁሉም መስክ ኑሮ የተሻለ ነበር:: የሕዝቡ ቁጥር ውስን ቢሆንም የህክምና አገልግሎት ንግሥት ዘውዲቱ ሆስፒታል ነበር:: ሐኪሞቹ እና ነርሶች ከውጪ የመጡ ነበሩ:: ደጅ አዝማች ባልቻ ሆስፒታልም ራሺያዎች ነበሩ፤ የጣሊያን እና የግሪክ ዶክተሮች የኢትዮጵያንም እነፕሮፌሰር አስራትን ጨምሮ ምርጥ ሐኪሞች ነበሩ:: በዛ ወቅት ሕዝቡ ጥቂት በመሆኑ ሐኪሞቹም ሆኑ ሆሲፒታሎቹ በቂ ነበሩ:: ዶክተሮች በበቅሎ ገጠር ሔደው ቤት ለቤት ሳይቀር ያክሙ ነበር::
አሁን የሕዝቡ ቁጥር እጅግ ጨምሯል:: በእርግጥ ብዙ ሐኪሞችም አሉ:: ሆስፒታሎች ግን ቁጥራቸው ውስን ነው:: የካቲት 12 ሆስፒታል በፊትም ነበር:: ራስ ደስታ ሆስፒታል እና ሌሎችም ነበሩ:: የሆስፒታል ቁጥር ብዙ አልጨመረም:: በቂ ዶክተሮችም የሉም:: ዶክተሮቹም ልምዳቸው ውስን ነው::
መልዕክት
አቶ ጥበበ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንካራ ነው:: ብዙ ነገር ሲሠራ ይታያል:: ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ላይ ይሠራሉ:: ‹‹ከጠረፍ እስከ ጠረፍ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ስሜት አሁን እየወረደ ነው:: በእኛ ጊዜ ይሔ አማራ ነው፤ ይሔ ኦሮሞ ነው፤ ይሔ ትግሬ ነው የሚባል ነገር የለም::›› ይላሉ:: እንደአቶ ጥበበ ገለፃ፤ በፊት እነርሱ ልጆች እያሉ የሚወራው ስለጀግንነት ነው:: ተደጋግሞ የሚነሳው ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉት ጦርነት ወይም ይሔኛው ብሔር ከዚህ ብሔር ጋር ብሎ መለየት አልነበረም:: ጣሊያንን እንዴት እንዳሸነፉ ይወራ ነበር::
ያው ከጣሊያን ጋር በነበረው ጦርነት ደግሞ ቀኝ አዝማች ተስፋ ገ/ሥላሴ ተሳትፈው ስለነበር፤ እርበኞች በቤታቸው አቅራቢያ ተገናኝተው ያወሩ ነበር:: ብዙም ሳይቆይ ያንን ተከትሎ በ1933 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር ተቋቋመ::
የማህበሩ ሊቀመንበር ማን ይሁን? ሲባል አንዳንዶች ‹‹የምንወዳቸው እና የምናከብራቸው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ይሁኑ›› ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ እርሳቸው በጣሊያን ወረራ ጊዜ ተሰደዋል እርሳቸው አይሆኑም አሉ:: አልጋ ወራሽ እከሌ ሲባል ሁሉም ተሰደዋል:: እኛ እንምረጥ ብለው እንቁ ስላሴ፣ በኋላ አበበ አረጋይም አርበኛ ነበሩ:: አበበ አረጋይ የራስ ጎበና የልጅ ልጅ ናቸው:: ነገር ግን የቡልጋን አርበኛ ሲመሩ እርሶ ኦሮሞ ነዎት እኛ በእርሶ አንመራም አላሉም:: በፊት በጠቅላይ ግዛት ነበር:: ጠቅላይ ግዛት ማለት ደግሞ በገንዘብ መግዛት አይደለም:: ለግዛት ያመች ዘንድ አካባቢውን በግዛት ማስቀመጥ ስለነበር የብሔር ልዩነት ጉዳይ እንደአሁኑ ከሮ የሚታይ አልነበረም::
የተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ ማተሚያ ቤቱ ከተቋቋመ 100 ዓ.ም ሆኖታል:: የሚሉት አቶ ጥበበ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ይህ ማተሚያ ቤት የጀርባ አጥንት ሆኖ ቆይቷል:: አሁንም ማገልገላችንን እንቀጥላለን ሲሉም ሃሳባቸውን ቋጭተዋል::
52 ዓመታትን በማተሚያ ቤት
በ1945 ሰሜን ሸዋ እንሳሮ አውራጃ የተወለዱት አቶ ንጉሤ ቃቂሳም፤ መጀመሪያ ፊደል የለዩት በተስፋ ገ/ሥላሴ የፊደል ገበታ መሆኑን በመግለፅ ኮከበ ፅብሃ ገብተው እስከ 12ኛ ክፍል መማራቸውን ይናገራሉ:: በ1964 ዓ.ም የተቀጠሩ ሲሆን፤ ለ52 ዓመታት በዛው ማተሚያ ቤት ውስጥ ሲሠሩ ቆይተዋል:: ሙያም የተማሩት እዛው አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ::
አቶ ንጉሤ እንሳሮ ተወልደው ወደ አዲስ አበባ የመጡት አያታቸው ቤት ለማደግ ነበር:: አያትየው የቤተመንግሥት ፈረስ ቤትን ይጠብቁ ነበር:: ስለዚህ ከአያታቸው ጋር ሲኖሩ፤ አያት የልጅ ልጃቸውን አቶ ንጉሤን ትምህርት ቤት አስገቧቸው:: በ1953 ዓ.ም ደግሞ እናት እና አባታቸው ከገጠር በመምጣታቸው፤ ወደ አባታቸው ቤት ገቡ:: አባታቸው አቶ ቃቂሳ ለአቶ ተስፋ ገብረሥላሴ የጭቃ ቤት ሠርተው ሲጨርሱ፤ ‹‹ምን ላድርግልህ?›› ሲሉ ጠየቋቸው:: ልጄን ሥራ አስቀጥሩልኝ አሏቸው:: በዛ አጋጣሚ አቶ ንጉሤ በተስፋ ገብረሥላሴ ማ/ቤት ለመቀጠር ዕድል አገኙ:: ደሞዛቸው 15 ብር ሆኖ መሥራት ጀመሩ::
ማሽን ሲበላሽ ለመሥራት እየሞከሩ በሒደት ራሳቸውን ችለው መሥራት ቀጠሉ:: በኋላም የህትመት ማሽን ጥገና ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ቢሆኑም፤ በትምህርታቸው እና ባላቸው ሙያ ልክ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ይናገራሉ:: በተስፋ ማተሚያ ቤት ብቻ ሳይሆን አርትስቲክ ማተሚያ ቤት ገብተው ሠርተዋል:: የማተሚያ ቤት ሥራ በፈረቃ በመሆኑ አርትስቲክ ማተሚያ ቤትም ለ33 ዓመታት ሲሠሩ፤ ጎን ለጎን በተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤትም ያገለግሉ ነበር:: አንዱ ማተሚያ ቤት ጠዋት ሠርተው ከወጡ፤ እስከማታ ደግሞ ሌላ ማተሚያ ቤት ይሠሩ እንደነበርም ይናገራሉ::
ከተስፋ ገ/ሥላሴ ጋር ልዩ ቅርበት እንደነበራቸው የሚናገሩት አቶ ንጉሤ፤ በ1990ዎቹ ሲያርፉ በምትካቸው ልጆቹ ማስተዳደር መጀመራቸውን እና በዛ ማተሚያ ቤት ምክንያት ብዙዎች እንጀራ እንደወጣላቸው ምስክርነት ሰጥተዋል:: እርሳቸውም በተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት በቀሰሙት ሙያ ሰሜን ጎንደር፤ ባህርዳር እና ወሎ ድረስ ሔደው ማሽን እየሠሩ ገቢ እያገኙ ሲያገለግሉ ቆይተዋል:: በምስራቅ ሱማሌ አርጌሳ ድረስ ማሽን ለመትከል እና ለመጠገን መሔዳቸውንም ነግረውናል::
አንድ ሰሞን ከተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት ራቅ ብለው ነበር:: በዛ አጋጣሚ አንድ ማሽን ተበላሽቶ ብዙ ተሞክሮ ሊሠራ አይችልም ከተባለ በኋላ፤ አቶ ንጉሤ ግን በተወሰነ ሰዓት ውስጥ እንዲሠራ አድርገውታል:: ይህ ማሽን አሁንም እያገለገለ ይገኛል ብለውናል:: ‹‹የተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት ብዙ ዋጋ አግኝቼበታለሁ:: ስለዚህ ለማተሚያ ቤቱ እቆረቆራለሁ:: የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆኔ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ባህል ቱሪዝም ድረስ እየሔድኩ የተስፋ ታሪክ መታወቅ አለበት እያልኩ እሞግታለሁ::›› ብለውናል::
እንደአቶ ንጉሤ ገለፃ፤ ቀኝ አዝማች ተስፋ ተቀጣሪዎችን ሠራተኞቻቸውን የማይበድሉ ነበሩ:: በፍፁም አያባርሩም ነበር:: ሀገር ወዳድም ነበሩ:: በጣም ፈጣን ጭንቅላት ያላቸው ሰውም ነበሩ:: ከዕፅዋት ቀለም እያወጡ ይፅፉ ነበር:: በጣሊያን ጊዜ የቅስቀሳ ወረቀት እያተሙ ይበትኑ ነበር:: ተስፋ የሀገር ባለውለታ ናቸው:: ነገር ግን ከ7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ውስጥ የቀራቸው እጅግ በጣም ጥቂት ነው:: የልጃቸው ቤት እና መጋዘናቸው ተገንብቶ የነበረበት ቦታ በሌላ ሰው ተወስዶ ሕንፃ ተገንብቶበታል:: የአትክልት ሥፍራቸውም በሌሎች ሰዎች ተወስዶባቸዋል:: ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ ማሽን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ያደረጉት ተስፋ ገብረሥላሴ ናቸው:: አሁን ግን የነበራቸው ይዞታ ተቀንሶ ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠሩ ማሽኖች መቀመጫ አጥተዋል::
አቶ ንጉሤ አልወለድም፣ ኦሮማይ፣ ሰመመን እና ሌሎችም ታዋቂ መጽሐፎችን ማተም ብቻ ሳይሆን ከደራሲን ጋርም የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው ይናገራ:: በተለይ ከአቤ ጎበኛ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበራቸውም ይናገራሉ:: ኮምፒውተር ባልነበረበት ዘመን፤ ብዙ የመፅሃፍ አንባቢ ነበር የሚሉት አቶ ንጉሤ፤ እርሳቸውም ጋዜጦችን በተለይም አዲስ ዘመን ላይ የጳውሎስ ኞኞን አምድ እንደሚያነቡ ይናገራሉ:: 15 ብር ደሞዝ ሲከፈላቸው አዲስ ዘመንን እና የዛሬይቱን ጋዜጣ በ20 ሳንቲም በየሳምንቱ እየገዙ ያነቡ ነበር::
አቶ ንጉሤ ስለአቶ ተስፋ ሲናገሩ፤ ‹‹ ቀኝ አዝማች ተስፋ የአመጋገብ ሥርዓታቸው ጥሩ ነው:: ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፤ ተስፋ እስከ መጨረሻው ቀና ብለው ይሔዱ ነበር:: ጥራጥሬ በተለይም ገብስ እና ሽንብራ ያዘወትሩ ነበር:: አልኮል ከመጠጣት ይልቅ የሚያዘወትሩት ቆሎ ብቻ ነው:: ለማንኛውም ሰው ዓርአያ መሆን የሚችሉ አባት ነበሩ›› በማለት ሃሳባቸውን አጠናቀዋል
ከልጅነት እስከ ዕውቀት በተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት
ወይዘሮ ፅጌ በየነም ለአምስት አስርት ዓመታት በተስፋ ገ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት ሲሠሩ ቆይተዋል:: ወይዘሮ ፅጌ አዲስ አበባ ሰሜን ሆቴል አካባቢ የተወለዱ ሲሆን፤ መጀመሪያ ወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት ገብተው እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማሩ:: 7ኛ ክፍል ሲደርሱ ግን የ1966 ዓ.ም ለውጥ መጣ:: መማር አልቻሉም፤ ስለዚህ ትምህርት አቋረጡ:: በድጋሚ በ1968 እና በ1969 ዓ.ም ተምረው የ8ኛ ክፍል ፈተናን ተፈትነው ሲጨርሱ፤ለቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የሚሠሩ አጎታቸው ለክረምት ትስራ ብለው አምጥተው ወይዘሮ ፅጌን አስቀጠሯቸው::
ወረቀት ማጠፍ እና ሌላውንም ይሠራሉ:: በሂደት መፅሃፍ መስፋት እና መጠረዝ ጀመሩ:: ፊደል ማጠፍ፣ አስሮ ማስቀመጥ እና ሌሎች ሥራዎችንም መሥራት ቀጠሉ:: በዕድሜ ገና ልጅ በመሆናቸው ሙሉ ደሞዛቸውን ለቤተሰቦቻቸው ይሠጡ ነበር:: በ1970 ዓ.ም የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ሲጨመር፤ የእርሳቸውም ደሞዝ ወደ 50 ብር አደገ:: በዛ ጊዜ 50 ብር ብዙ ነበር:: ነገር ግን ሙሉ ደሞዛቸውን ሰጥተው ምሳቸውን ተቀብለው በማተሚያ ቤቱ ውስጥ እየሠሩ ሕይወትን መግፋት ቀጠሉ::
በኋላም ቀን ማተሚያ ቤት እየሠሩ የማታ መማር ጀመሩ:: 12ኛ ክፍል ቢደርሱም ወደ ሌላ ቦታ ሥራ ለመቀየር አልፈለጉም:: ምክንያቱም ትዳር መስርተው ልጆች መውለድ ሲጀምሩ፤ አለቆቻቸው ብዙ አይጫናቸውምና እዛው ማተሚያ ቤት እንደተቀጠሩ መቆየትን መረጡ:: ልጆች እስኪያድጉ ነፃነቱ አለና በተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት እየሠሩ ሁለት ወንድ ልጆች እና አንድ ሴት ልጅ ወልደው አሳደጉ::
ወይዘሮ ፅጌ ስለተስፋ ገብረሥላሴ ሲናገሩ፤ ቀኝ አዝማች ተስፋ ሕይወታቸው ሥራ እና ሥራ ብቻ ነበር:: ለመሠረተ ትምህርት ፊደል በነፃ አትመው ይሰጡ ነበር:: ለትምህርት ሚኒስቴርም ብዙ መፅሃፍ ያትሙ ነበር:: የሃይማኖት መፅሃፎችን በተለይም የፀሎት መፅሃፍ ሥርዓቱን እንደጠበቀ እንዲሠራ አድርገው እስከ አሁን እንዲቆይ መሠረት የጣሉ ትልቅ ባለውለታ ናቸው ይላሉ:: በመጨረሻም ወይዘሮ ፅጌ እኚህ አባት መረሳት የለባቸውም መሥሪያ ቤቱም ከመፍረስ ይልቅ አድጎ ሰፊ ቦታ ላይ ትልቅ ሆኖ መገንባት እንዳለበት ተናግረዋል::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 12 ቀን 2016 ዓ.ም