የረፈደ ሩጫ

ጠባቧ ክፍል የተለያየ ቀለም ባላቸው አምፖሎች ደማምቃለች፣ ቦግ እልም በሚለው የብርሃን ፍንጣቂ ውስጥ አንዲት ተስፋ ቢስ ሴት ትታያለች። ፊቷ ላይ ሰላሳ ሁለተኛ ዓመቷን የሚያሳብቅ ሻማ ከነጭ ቶርታ ኬክ ጋር ተሰይሟል። የተለያዩ አይነት መጠጦች እንደ ክብር ዘበኛ የሙዚቃ ባንድ የእድሜዋን ቁጥር አጅበውታል። ማርታ ወደ ኋላ መለስ ብላ የመጣችበትን የሰላሳ ሁለት ዓመት የሕይወት ጎዳናዋን አየችው። ያልተኖረ ወጣትነት፣ ታይቶ የጠፋ ልጅነት ግሳንግሱን ይዞ ፊቷ ድቅን አለባት። ሁሌ ትናንትን ስታሰብ ራሷን ትጸየፈዋለች። ምድር ላይ በኖረችባቸው ሰላሳ ሁለት ዓመታት ውስጥ አንድም የሚያኮራ ነገር አለማድረጓ ያበሳጫታል። ጊዜ የእሷን የእድሜ ቁጥር ከማግዘፍ ባለፈ የፈየደላት አንድም ነገር አልነበረም ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ ሁሉ ጉዞዋ ውስጥ የኔ የምትለውን የነፍስ አጋር አለማግኘቷ ያስከፋታል።

የእጅ ሰዓቷን አየች.. ሰላሳ አምስት ደቂቃዎች ቀርተዋታል። ሳምሶን ሊመጣ.. አስረኛው ወንድ ሆኖ ወደ ሕይወቷ ሊገባ እየጠበቀችው ነው። ሳምሶን ምድር ላይ ከተፈጠሩ ወንዶች ሁሉ አስፈሪ ፊት ያለው ወንድ ነው። ሲበዛ ጥቁር ነው፣ በጭስ የጠቆረ የባላገር ግርግም የመሰለ። ሁሉም ሴቶች መርጠው የተዉት የሚመስል አስቂኝ ፍጥረት፣ በጥቁር ጸጉሩ መሀል እንደ ጋን ስር እንጉዳይ ያቸፈቸፈ ሽበት የወጣበት አጭርና ዘርፋጣ ወንድ። ዘጠኝ ወሯ እንደደረሰ ነፍሰጡር ሴት ሆዱ ወደ ፊት የተነረተ ቦርጫም። ጥርሶቹ በሲጋራና ጫት የበለዙ ለንቦጫም..ሳምሶን ይሄን ሁሉ ነው። ይሄን ወንድ ልታገባው ነው..። እድሜው ስንት ይሆን? ጠፋባት። ብቻ ግን አንቱ አትበይኝ እያለ ሲቆጣት እንደነበር ታስታውሳለች። ከፊቱ አቀማመጥ ተነስታ ብትገምት እንኳን የእሷን እድሜ ሁለት እጥፍ ቀርጥፎ እንደሚበላ እርግጠኛ ነበረች። አባቷን ልታገባ ነው።

ከተቀመጠችበት ተነስታ ወደ በሩ ተራመደች። አፍላነት የከዳቸው ጡቶቿ እንደ ንጉሥ አሽከር አንገታቸውን ወደ መሬት አጉብጠው እንደ እሷ በትካዜ ተውጠዋል። የበሩን ጉበን ተደግፋ በሃሳብ ጭልጥ አለች። ትናንትን ገላ መቅበር ያቃታት ሴት ናት.. ትናንት ዛሬ ቢሆን ትላለች.. በትናንትናዋ ውስጥ የምታስተካክላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ትናንትና ሲበዛ ኩራተኛ፣ ሲበዛ ፌዘኛ ነበረች። ውበቷን ሳታስቀድም የተራመደችው አንድም ጎዳና አልነበረም። በሩ ላይ እንደቆመች ዛሬ ቢሆን ወደምትሻም አምና ተጣደፈች። የመጀመሪያው የፍቅር ጥያቄ ያቀረበላት ወንድ ምሳሌ ነበር.. በሩ ጉበን ላይ እንደቆመች ምሳሌ ትዝ አላት። ያኔ ገና አስራ ስምንት ዓመቷ ነበር..። አቤት! ድምጹን ስትወድለት ድምጹ ዛሬም ድረስ ከነውበቱ ይታወሳታል። ግን ናቀችው.. ሂድና ቢጤህን ፈልግ ስትል በጓደኞቹ ፊት አዋረደችው። ያ ማን ነበር ደግሞ የአንደኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ እያለች አላስወጣ አላስገባ እያለ ሲያስቸግራት የነበረው? ትዝ አላት ፍስሀ ነው። አሁን እሱ ምኑ ይጠላል? ምኑን ጠልታ እንዳባረረችው እሷም አታውቀውም። በሕይወቷ ከባድ ጥፋት ያጠፋችው የፍሰሀን የፍቅር ጥያቄ አለመቀበሏ ይመስላታል። ዛሬ ላይም ሆነ የትናንቱ መልከመልካሙ ፍሰሀ ይናፍቃታል።

ልቧ ወደሌላኛው ወንድ በሃሳብ ተሽቀነጠረ፣ መልህቅን ሳትጥል እዛም እዚም ዋዠቀች። ያ ማን ነበር ፊቱን ከዝንጆሮ ላይ የሰረቀው የሚመስለው፣ በቤት መኪናው እየመጣ ካልሸኘሁሽ እያለ የሚጨቀጭቃት? አስታወሰችው ማስረሸ ነው። ይሄን ፊት ይዘህ እኔን ማግባት ያምርሀል? መጀመሪያ መስፍን እንጅነሪንግ ሄደህ ፊትህን አስቀይረህ ተመለስ ነበር ያለችው። አቤት ግፏ..።

ይስሀቅ ትዝ አላት..በልቧ ውስጥ እውነት ቢኖር ኖሮ ይስሀቅ የእሷ ባል ይሆን ነበር። የትኛውም ወንድ እንደ ይስሀቅ እውነትን ይዞ የቀረባት አልነበረም። ‹የእውነት ነው የማፈቅርሽ፣ ሕይወቴን ሙሉ ካንቺ ጋር ማሳለፍ እፈልጋለሁ› እያላት ነበር የገፋችው። ‹የኔ ነፍስ ላንቺ ነው የተፈጠረችው፣ካንቺ ሌላ ማንንም ማፍቀር አልችልም› እያላት ነበር የናቀችው። ሌላው ይቅርና እየሰደበችው የሚከተላት፣ እየናቀችው የሚያከብራት የነፍሱ የእውነት ጠል አይረሳትም። አሁን ላይ ስታስበው ይስሀቅ ወደ ሕይወቷ ፍቅርን ብቻ ይዞ አልነበረም የመጣው..ብዙ ነገሮችን ይዞላት ነበር። ትናንት ይሄን ሁሉ ነበረች። ፍቅርን በንዋይ የምትመዝን ሴት።

የመጣላትን በረከት ስትገፋ፣ የቀረባትን ስትሸሽ ሃያ አምስተኛ ዓመቷን አከበረች። የፍቅር ታሪኳ ግን አልቆመም። ሃያ አምስተኛ ዓመቷ በአሮን ፍቅር ተጀመረ። በፍቅርሽ ላብድ ነው፣ አንቺን ማግባት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ሲል አሮን አማላጅ ላከባት። በቤተሰቡ ሀብትና በሚነዳው መኪና ሊያማልላት ሞክሮ አልቻለም በመጨረሻ ብዙ ጥሮ ምሳ ሊጋብዛት ቀጠራት ከዛን ቀን ወዲህ ግን ደግማ አላገኘችውም። ትናንትና እንዲህ ነበረች.. በኩራትና በማንአለብኝነት የተሞላች። በነፍሷ ውስጥ ፍቅርና እውነትን አንቃ የገደለች። የሰዎች እንግልት ያስደስታታል፣ አፍቅረዋት ሲያጧት፣ ተመኝተዋት ሲከተሏት ነፍሷ ሀሴት ታደርግ ነበር። መፈለጓን፣ መወደዷን የምትለካው በሰዎች ጭንቀትና መከራ ነበር።

በሆነ አጋጣሚ ደጀኔ ከሚባል ሰው ጋር ተዋወቀች። ከብዙ ውትወታ በኋላ ሊገናኙ ተቀጣጠሩ። ከእሱ ጋር መታየት የሰማይን ያክል ከብዷት ነበር። ስትቀርበው ግን እንደምታየው አይነት አልነበረም። ማንም የሌለው ብዙ ነገር ነበረው። ሲበዛ ደግ ነበር። እሱ ጋ ያየችውን መልካምነት እስካሁን ድረስ የትኛውም ወንድ ጋ አላየችውም። ግን ምን ያደርጋል አትመጥነኝም ብላ አባረረችው።

እድሜዋ ሄደ። የሰፈሩ ሰው ቆሞ ቀር እያለ ይሰድባት ጀመር። ከብዙ ጊዜ በኋላ የእድሜዋ ማምሻ ላይ ለአርባ አራቱ ተስላ እንደምንም ብላ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቀች። በዝናብ ስትደበደብ አይቶ መኪና አቆመላት። እንደ ድሮው ቢሆን ዞራም አታየውም ነበር። ሳታመነታ ገባች.. ቤቷ አደረሳት። ዝም ብሎ መለያየት ነውር ሆኖ ስልክ ተለዋወጡ። ሁለት ቀን ተደዋወሉ.. በሶስተኛው ቀን አብረን እንደር አላት… ካላገባኸኝ አብሬህ አላድርም ብላው ተለያዩ። በሌላ ቀን ሱፐር ማርኬት ውስጥ ገባች.. ትርፍ ጊዜዋን የምታሳልፈው ወንድ በመፈለግ ሆኗል። ለይምሰል ጉዳይ ያላት ትምሰል እንጂ በምትሄድበት ሁሉ ፍላጎቷ ባል የሚሆን ወንድ መተዋወቅ ነበር። ቶሎ ተዋውቃ ቶሎ ማግባት ትሻለች.. ቆሞ ቀር ከመባል ለመዳን። ግን እንዳሰበችው የሆነ ምንም ነገር አልነበረም ሰላሳኛ ዓመቷን ለብቻዋ አከበረች።

አንድ ቀን ራሷን ጠልታ ስለሞት እያሰበች ለብቻዋ ቁጭ ብላ ነበር..

ከኋላዋ አንድ ድምጽ አስደነበራት ወደ ኋላዋ ዞረች ሲጋራ ከሚያጨስ አንድ ሰው ጋር ተገናኘች። ከሳምሶን ጋር.. በሰላሳ ሁለተኛ ዓመቷ ላይ እመጣለሁ ብሏት እጠበቀችው ነው… ይመጣ ይሆን?

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You