ዜና ትንታኔ
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው አዲሱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጿል፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎም የውጭ አገር የምንዛሪ ተመን በገበያው ዋጋ እንዲተመን በመደረጉ በርካታ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ ዘርፎች ሊሰማሩ እንደሚችሉ የምጣኔ ሀብት ምሑራን ይናገራሉ፡፡
ይህ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በኢኮኖሚው ላይ ለውጦች እንደሚያመጣም እሙን ነው።፡ ማሻሻያው በተለይ ለወጣቱ ምን ዕድሎች ይዞ ይመጣ ይሆን? ኢኮኖሚው ላይስ ምን አይነት ለውጦች ያመጣል? እንዲሁም ምን ጥንቃቄዎች መደረግ አለበት? በሚሉት ጉዳዮች ላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የተለያዩ ዕይታዎችን አካፍለውናል፡፡
የፐብሊክ ፖሊሲና የምጣኔ ሀብት ምሑር ቆስጠንጢኒዮስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ ለውጥ ይዞ እየመጣ ነው ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በመከፈቱ ምክንያት ብዙ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በኢንዱስትሪ እና በማዕድን ልማት ሊሳተፉ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መኖሩን የሚናገሩት ምሑሩ፤ ይህም ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ይገልጻሉ::
ከሰሞኑ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ከዚህ በፊት የነበረውን የጥቁር ገበያን ሕገ ወጥ ሥራ የሚያስቆም በመሆኑ ትልልቅ የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ገብተው በንግድ ሥራ እና በኢንቨስትመንት እንዲሠማሩ ዕድል ይሰጣል የሚሉት ምሑሩ፤ ይህም ከፍተኛ የሰው ኃይል ቅጥር የሚፈልግ በመሆኑ ለወጣቱ ጥሩ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡
ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል ወጣቶች የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ ሥራ በመሥራት በርከት ያለ ካፒታል ወደ ሀገሮቻቸው ማምጣት እንደቻሉ አውስተው፤ በሀገራችንም የቴሌኮም ዘርፉ ነፃ ሆኖ እየመጣ በመሆኑ ወጣቶች ይህን በመጠቀም ትልቅ ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡
ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደ ሀገር መደረግ ከነበረበት ጊዜ ዘግይቶ ተግባራዊ የተደረገ ቢሆንም ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረው፤ በኢትዮጵያ በአግሮ ኢንዱስትሪው፣ የውሃ ሀብት እና ሰፊ የእርሻ መሬት፣ ጥሩ መሠረተ ልማት በመገንባቱ እንዲሁም ከፍተኛ የወጣት ኃይል በመኖሩ ምክንያት ስኬታማ እንደሚሆን ይናገራሉ ፡፡
በተደረገው ማሻሻያ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብቶች በማቀናጀት በብድር ሳይሆን በራሷ ምርታማነት የምትኖር አገር እንድትሆን ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡
ናይጄሪያ እና ግብፅ በየዓመቱ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከዲያስፖራዎቻቸው ያገኛሉ የሚሉት ምሑሩ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር ሲታይ ከዲያስፖራዎቿ የምታገኘው በጣም አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የጥቁር ገበያው ኢትዮጵያ ከዲያስፖራዎቿ ማግኘት የሚገባትን እንዳታገኝ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን የሚገልጹት ምሑሩ፤ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሪ በገበያው እንዲወሰን የተደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያ በቀጣይ ማግኘት የሚያስችላትን ጥቅም እንድታገኝ ዕድል እንደሚፈጥርም ይገልጻሉ፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገትም በራሱ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ይናገራሉ፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማ እንዲሆን እየታዩ ያሉትን የሙስና ችግሮችን ማረም እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ቆስጠንጢኒዮስ (ዶ/ር)፤ በአገልግሎት አሰጣጥ በኩልም የሚታዩ ችግሮች ካልተፈቱ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች መጥተው ሥራ ለመሥራት እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ፡፡
ሙስና ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጥ ረገድ ሚዲያዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው የሚሉት ምሑሩ፤ የምርምራ ዘገባዎች ላይ በማተኮር የአገልግሎት አሰጣጡን ችግሮችን ማጋለጥ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የሥራ ዕድል እንዲበራከት መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በበኩላቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ማሻሻያውን ከትክክለኛ ጊዜው ትንሽ ቀደም ብሎ እንደጀመረው የሚናገሩት ተንታኙ፤ የኅብረተሰቡ የመወዳደር አቋም እና የመንግሥት የውጭውን ዲፕሎማሲ የመቋቋም አቅም ሲዳብር ማሻሻያው ቢደረግ ይበልጥ የተሻለ ይሆን እንደነበር ይገልጻሉ፡፡
ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ካፒታላቸውን ካፈሰሱ መሠረታዊ የሚባሉ ፈተናዎች መካከል ከሆኑት መካከል ሥራአጥነት፣ የዋጋ ግሽበትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን የመፍታት ዕድል ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
አቶ ሸዋፈራሁ ወጣቶችም በተለይ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በባንክና በጅምላ ንግድ በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። ይህ ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሌሎች ሀገራት ኢንቨስተሮች የካፒታል የመጥለቅለቅ ችግር እንዳያመጣ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ይመክራሉ፡፡
ግብርናው ለአጠቃላይ የሀገሪቱ ምርት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍ ማለት እንዳለበት የሚገልጹት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ሀገራት ልትሸጠው የምትችለው ነገር የግብርና ውጤቶችን በመሆኑ ግብርናው ላይ በማተኮር አርሶ አደሩን ማበረታታት እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ፡፡ ይህም ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ተጨማሪ መስክ ነው ይላሉ፡፡
መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ጨረታ በማውጣት ለባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሲሰጥ በጥቁር ገበያ ላይ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ስወራ ይቀንሳል የሚሉት ተንታኙ፤ ይህ የጥቁር ገበያውን አቅም በማዳከም ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣም ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ሸዋፈራሁ በሕገወጥ መንገድ ሲሠራ የነበረው የጥቁር ገበያ አሁን በማሻሻያው በነፃ ገበያ ክፍት ሲደረግ የምርትና አገልግሎት ነፃነት ሊኖረው ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የአቅርቦት እና የፍላጎት መጠን የተጣጣመ ባለመሆኑ ኅብረተሰቡ ምርትና አገልግሎቱን ከቦታ ቦታ እንደፈለገው አንቀሳቅሶ በፈለገው ዋጋ እንዲሸጥ ሠላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር መሠራት እንዳለበት የሚገልጹት ተንታኙ፤ ለተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው ይላሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ምሑራኑ እንደሚሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ቢሆንም ስኬታማነቱ እንዲረጋገጥ በምሑራኑ እንደ ስጋት የተቀመጡት የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንቅፋት እንይሆኑ በትኩረት ቢሠራባቸው መልካም ነው ሲሉ ይመክራሉ፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት፤ ቱሪዝም በማነቃቃትና የባንክ ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ በማድረግ ረገድ የሚፈጥረው ምቹ ሁኔታም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡
መዓዛ ማሞ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም