በክልሉ 285 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል ዝግጅቶች ተጠናቀዋል

– ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፦ በአማራ ክልል 285 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምሕረት ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ ዓመት ለሚከናወነው የአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር በአማራ ክልል ከ285 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በ28 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ በአንድ ጀንበር ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀው እለቱ እየተጠበቀ ነው፡፡

በዚህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በክልሉ የሚገኙ 22ቱም ዞኖች ተሳትፎ ያደርጋሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከላይኛው ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መዋቅር መልዕክት መተላለፉንና ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተሳትፎ ያደርጉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመትም ለየት ባለ ሁኔታ ከዚህ ቀደም የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብና የመተካት ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ እስመለዓለም ገለጻ፤ በደጋ፣ በቆላ፣ በወይና ደጋና በሌሎችም እንደየአከባቢው የአየር ሁኔታ ተስማሚነት ያላቸው ችግኞች የሚተከሉ ይሆናል፡፡ በዚህም የግራር፣ ባሕርዛፍ፣ የወይራ፣ የሀበሻ ፅድ እንዲሁም እንደአቮካዶ፣ ማንጎና ሌሎችም ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች ይተከላሉ፡፡

ለተከላውም በአብዛኛው ለደን፣ ለጥምር ግብርና፣ ለውበትና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ መርሐ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ የመረጃ ቅብብሎሹን ሊያሳልጥ የሚችል ቴክኒካል ኮሚቴ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ በማዋቀር እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

አቶ እስመለዓለም፤ በ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በ201 ሄክታር መሬት ላይ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ፤ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ሰኔ 26 ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ያለው የዝናብ ስርጭት የተሻለ በመሆኑ መርሐግብሩ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር በርካታ ለውጦችን እያስገኘ እንደሚገኝ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የተተከሉም ሆነ የሚተከሉ ችግኞች የፅድቀት መጠናቸው እንዲጨምርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማግኘት እንዲቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ትልቅ ሀሳብ በመሆኑ ለችግኝ ተከላው የሚወጡ ዜጎች ችግኞቹን በምን አይነት መልኩ በመንከባከብ ለፍሬ ማብቃት እንደሚቻል መወያየት አለባቸው። እንዲሁም ግንቦት ሲመጣ ችግኝ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ከችግኝ የማፍላት ሂደት ጀምሮ ተሳትፎ ማድረግ አለበት፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You