ዜና ሐተታ
አቶ ተስፋዬ ኡይገለች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ነዋሪ ናቸው፡፡ ከክልሉ ነዋሪነትም ባሻገር በአርብቶ አደርና ቆላማ ጉዳዮች ቢሮ የአርብቶ አደር የአደጋ ሥጋት ቅነሳ እና አካታች የኢኮኖሚ ዕሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሆነው ያገለግላሉ፡፡
በክልሉ በሬና ላሞችን፣ ፍየልና በጎችን የሚያረቡ በተለይ በአርብቶ አደርነት ብቻ የሚተዳደሩ እንዳሉ የሚጠቅሱት አቶ ተስፋዬ፤ በግለሰብ ደረጃ ከ800 እስከ አንድ ሺህ የቁም እንስሳት ያሏቸው አርብቶ አደሮች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡
ሆኖም የቁም እንስሳት ደኅንነት አጠባበቅ ላይ ተለምዷዊ እንጂ በዘመናዊነት የታገዘ አካሄድ እንዳልነበረ ጠቁመው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አርብቶ አደሮች ላይ በተፈጠረ ግንዛቤ የቁም እንስሳት መድን መግባት መጀመራቸውን ያብራራሉ፡፡
በክልሉ ስምንት የሚደርሱ የአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ወረዳዎች መኖራቸውን የሚጠቅሱት አስተባባሪው፤ የአደጋ ሥጋት ቅነሳ እና አካታች የኢኮኖሚ ዕሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት በስምንቱም ወረዳዎች እየተተገበረ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡
በወረዳዎቹ የሚገኘው የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ቁጥር ከ750 ሺህ በላይ እንደሆነ ጠቁመው፤ የቁም እንስሳት መድን የመግባት ባሕል ገና እየዳበረ ያለ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በክልሉ መጠነኛ ድርቅ ተከስቶ 537 አርብቶ አደሮች ላይ ሥጋት ተደቅኖ ነበር፡፡ እንደወትሮው ቢሆን ብዙ እንስሳት ሊሞቱ እና ለጉዳት ሊዳረጉ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡
አርብቶ አደሮቹ የቁም እንስሳት ኢንሹራንስ የገቡ በመሆናቸው፤ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ የውሃና የመኖ አቅርቦት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የቁም እንስሳታቸውን ከሞት ራሳቸውን ከኪሳራ አድነዋል ይላሉ፡፡
ማኅበረሰቡ ከመድኅኑ በሚያገኛቸው የቁጠባ ጉርሻ አገልግሎቶችም የእንስሳት የውሃ አቅርቦት እና የመኖ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ በአርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች ዘንድ በተፈጠረ ግንዛቤ ከ530 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ለቁም እንስሳቶቻቸው መድን ( ኢንሹራንስ) መግባታቸውን ያስገነዝባሉ፡፡
ሆኖም ይህ ቁጥር በቂ እንዳልሆነ የሚጠቅሱት አስተባባሪው፤ ማኅበረሰቡን ከሥጋት እንስሳቱን ከሞት ለማዳን ሲባል የቁም እንስሳት መድን ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት የቁም እንስሳት መድን ፕሮጀክቶችን ትኩረት ሰጥተው የአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደሩን የሕይወት ዘይቤ ሊቀይሩ ይገባል ሲሉም ይመክራሉ፡፡
በሬዕ አብዱርሃማን መሐመድ በሱማሌ ክልል የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር የአደጋ ሥጋት ቅነሳ እና አካታች የኢኮኖሚ ዕሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ናቸው፡፡ በክልሉ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመቱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ በሬዕ፤ በተለይ የቁም እንስሳት(መድን) ኢንሹራንስ ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ያመላክታሉ፡፡
ማኅበረሰቡ እንደ ግመል እና ፍየል ያሉ ተፈላጊነት ያላቸው የቁም እንስሳትን የሚያረባ ቢሆንም የአካባቢው የአየር ንብረት አስተማማኝ እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም የቁም እንስሳት መድን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው፤ በክልሉ የአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ዘንድ ያለው የቁም እንስሳት ግንዛቤ እየጨመረ መምጣቱን ያብራራሉ፡፡
በክልሉ 85 በመቶ የሚጠጋው ነዋሪ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ነው የሚሉት አቶ በሬዕ፤ ሁሉም አካባቢዎች የቁም እንስሳት መድን ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎት ቢኖራቸውም በክልሉ ከሚገኙ 95 ወረዳዎች 24 ወረዳዎች ብቻ ፕሮጀክቱ እየተተገበረባቸው እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡
ፕሮጀክቱ እየሠራባቸው ከሚገኝባቸው 24 ወረዳዎች 66 ሺህ አርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች የቁም እንስሳት መድኅን መግዛታቸውንም ይናገራሉ፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ በክልሉ ያሉ የቁም እንስሳት 50 ሚሊዮን ይጠጋሉ፡፡ የቁም እንስሳት (መድን) ኢንሹራንስ በመግባት በድርቅ ጊዜ የእንስሳት መኖ እና ውሃ አቅርቦት ማግኘት የግድ የሚባል ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2021 እና በ2022 ዓመታት ብቻ ከአምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ እንስሳትን በድርቅ ምክንያት አጥታለች የሚሉት ደግሞ የአደጋ ቅነሳ እና አካታች የኢኮኖሚ ዕሴት ፕሮጀክት ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ጀማል አልይ ናቸው፡፡
መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የእንስሳት መድን (ኢንሹራንስ) እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው፤ አሁንም በመላ ሀገሪቱ ለ140 ሺህ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደሮች ተደራሽ የቁም እንስሳት መድን መሸጡን ይናገራሉ፡፡
የቁም እንስሳት መድን ዘርፉን ከስጋት ነፃ ለማድረግ እና ለማዘመን የሚረዳ መሆኑን ጠቁመው፤ የቁም እንስሳት መድኅን አርብቶ አደሩን ከስጋት እንስሳቱን ከሞት የሚታደግ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ከኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በተውጣጡ 187 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
ፕሮግራሙ የሚተገበረው በደቡብ ኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ስድስት ወረዳዎች፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ቀብሪ ደሐር እና ጅርቲ በሚገኙ 95 ወረዳዎች፤ በኦሮሚያ ያቤሎ፣ ባሌ ሮቤ እና ጭሮ በሚገኙ 45 ወረዳዎች ነው። በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ምዕራብ ኦሞ እና ከፋ በሚገኙ ስምንት ወረዳዎች እንዲሁም በአፋር አዋሽ ሰባት በሚገኙ 35 ወረዳዎች ይተገበራል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2016 ዓ.ም