አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የክህሎት ማህበረሰብ አባል ሆና መቀላቀሏ የወጣቶችን ክህሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚረዳ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የክህሎት ማህበረሰብ አባል መሆኗን አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፤ ላለፉት ዓመታት የዓለም አቀፍ የክህሎት ማህበረሰብ መስፈርቶችን አዘጋጅቶ የተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ሀገራትን በአባልነት ሲቀበል ቆይቷል። በዚህም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የክህሎት ማህበረሰብ 88ኛ አባል ሀገር ሆና ተቀላቅላለች።
ኢትዮጵያ አባል መሆኗ በክህሎት ምህዳር ውስጥ ትልቅ ፋይዳና ትርጉም እንዳለው በመጥቀስ፤ ወጣቶች ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እገዛ እንደሚያደርግ አመልክተዋል። በተለይ የወጣቶች ሙያና ክህሎት ቦታ እንዲኖራቸው የሚያስችል መድረክ በመሆኑ ለወጣቶች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለጥቁርና ለመላው ግፉዓን ሕዝቦች ነጻነት ፋና ወጊ የሆነች ሀገር ናት ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፤ አባል መሆኗ ጠቀሜታው አፍሪካዊ ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል። የአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳን ቀርጾ እንደ አህጉር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በክህሎት ዐሻራ ማሳረፍ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ የራሷን ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ አባልነቱ ከተቀረው ዓለም የሚፈጠሩ ተጨማሪ እድሎችን ለማግኘት የሚያስችል እና አዲስ አውድ የሚፈጥር ነው። ከመላው ዓለም የሚመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየሁለት ዓመቱ በአንድ ላይ ተገናኝተው የሚያካሂዱት መድረክ በመሆኑ የክህሎት ሽግግር፣ ወጣቶች የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችሉ እድሎችን ይፈጥራል።
አባል ለመሆን ከሁለት ዓመት በላይ ጠንካራ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰውም፤ በዚህም ጥሩ ውጤትም ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ የክህሎት ማህበረሰብ ውስጥ ከአባልነት በላይ በአመራርነት የምታገለግልባቸው መድረኮች እንዳሉም አመላክተዋል።
የ2024 የዓለም ክህሎት ውድድር በፈረንሳይ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ የውድድር ኮሚቴ ውስጥ በቋሚ ኮሚቴነት መወከሏን ተናግረዋል። እንዲሁም በአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ተወክላ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች ብለዋል።
ፈረንሳይ በሚካሄደው የክህሎት ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በሶስት መሠረታዊ የሥራ መስኮች ለመወዳደር ዝግጅት እያደረገች ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በጣውላ ሥራ ዘርፍ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) እና በማሽን ማምረት ዘርፎች ላይ ሙያተኞች ዝግጅት እያደረጉ ነው። ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ መድረክ በመሆኑ በቂ ልምድና ትምህርት እንደሚቀሰምበት ጠቁመዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም