የቱሪዝሙ አባት

በሀገራዊ ውለታቸው ልክ አልተዘመረላቸውም:: ኢትዮጵያን በዓለም አስተዋውቀዋል:: ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበትን 13ኛ ወር በዓለም አቀፉ ቋንቋ እንግሊዘኛ አስተዋውቀዋል:: እኚህ የቱሪዝም አባት ሀብተሥላሴ ታፈሰ ናቸው:: የታሪክ አጋጣሚ ሆነና የዓመቱ 12ኛው ወር በሆነው በወርሐ ነሐሴ የመጀመሪያ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል:: በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን እኚህን የቱሪዝም አባት እናስታውሳለን:: ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ታሪካዊ ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ::

ከ62 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 29/ 1954 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይና ፖለቲከኛ ኔልሰን ማንዴላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ታሰሩ:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ማንዴላ 27 ዓመታትን እስር ቤት ውስጥ አሳልፈዋል:: በመጨረሻም ከእስራት ነፃ ወጥተው፣ የታገሉለት ዓላማ ድል አድርጎ፣ እርሳቸውም የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል::

ከ79 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 30 ቀን 1937 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር 1945) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጃፓኗ ሂሮሽማ ከተማ ‹‹ሊትል ቦይ›› በተባለው የአሜሪካ ጦር ኃይል ቦምብ ተደበደበች:: ከሂሮሽማው ጥቃት ሁለት ቀናት በኋላ (ነሐሴ 3 ቀን 1937 ዓ.ም ማለት ነው) ደግሞ ናጋሳኪ የተባለችው ሌላኛዋ የጃፓን ከተማ ‹‹ፋት ማን›› በተባለው የአሜሪካ የጦር ኃይል ቦምብ ተደበደበች:: ሁለቱ ድብደባዎች ከ129 ሺህ እስከ 226 ሺህ ለሚሆኑ ጃፓናውያን ህልፈት ምክንያት ሆነዋል::

ከ35 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ነሐሴ 1 ቀን 1981 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መንገድ እንዲሁም አስኮ አካባቢ ደግሞ በስማቸው የመኖሪያ ሰፈር የተሰየመላቸውና የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት ጆርጅ ቶማስ ሚኪ ሌላንድ እንዲሁም ሌሎች አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን በአውሮፕላን አደጋ ሞቱ::

አደጋው የደረሰባቸውም ስደተኞችን ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ (ጋምቤላ) በአውሮፕላን ሲጓዙ የተሳፈሩበት አውሮፕላን ተከስክሶ ነው:: ጆርጅ ቶማስ ሚኪ ሌላንድ በሰብዓዊ እርዳታ ተግባራት ታዋቂ የነበሩ ፖለቲከኛ ስለመሆናቸውም ታሪክ ያስረዳል::

በዝርዝር ወደምናየው የቱሪዝም አባት ሀብተሥላሴ ታፈሰ ታሪክ እንለፍ::

የነሐሴ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ እንገኛለን:: የነሐሴ ወር በኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ክስተቶች የሚበዙበት ነው:: ብዙ የባህልና ቱሪዝም ሁነቶች የሚከናወኑበት ነው:: ወዲህ ደግሞ የአዲስ ዘመን መቀበያ ዋዜማ ነው:: የተሰናባች ዓመት የመጨረሻው ወር ነው:: በዚህ ወር ውስጥ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴዎች አሉ::

ይህን የኢትዮጵያን መለያ ቱሪዝም ያስተዋወቁ ጀግና ሀብተሥላሴ ታፈሰ ናቸው:: የታሪክ ግጥምጥሞሽ ሆኖ ሕይወታቸው ያለፈው በዚሁ ነሐሴ ወር መጀመሪያ ሳምንት ነው::

በተለይም ‹‹Thirteen Months of Sunshine›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ኢትዮጵያን ለዓለም አስተዋውቋል:: የእንግሊዘኛ ፕሮግራሞች ማስጀመሪያ ነበር:: ይህን የእንግሊዘኛ ቃል አስገብተው ወደ በይነ መረብ ጎራ ቢሉ ኢትዮጵያን በዓለም ያስተዋወቁ ብዙ አይነት ጥናቶች፣ መጣጥፎች፣ ዜናዎችና መጻሕፍትን ያገኛሉ::

ይህ ቃል ለ50 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ መሪ ቃል ሆኖ አገልግሏል:: አሁን ‹‹ምድረ ቀደምት›› በሚል ተተክቷል:: ዳሩ ግን ኢትዮጵያን ለዓለም አስተዋውቋልና እነሆ ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል::

ሀብተሥላሴ ከአባታቸው ከፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተሚካኤል እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሙላቷ በላይነህ በ1919 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ:: ሀብተሥላሴ ገና ሕፃን ሳለ አባቱ ፊታውራሪ ታፈሰ የጠረፍ አካባቢ አስተዳዳሪ ሆነው ተመደቡ:: በዚህም ምክንያት ፊታውራሪ ሀብተሥላሴ ጎረቤታቸው የሆኑ የውጭ ሀገር ጥንዶች (ሩስያዊት ሚስት እና ግሪካዊ ባል) ሕፃኑን ሀብተሥላሴን ለጥቂት ጊዜያት ያህል እየተንከባከቡ እንዲጠብቁላቸው በአደራ ሰጥተዋቸው ወደተመደቡበት ሥራቸው ሄዱ:: ሀብተሥላሴን በአደራ የተቀበሉት የባህር ማዶ ሰዎች ሁለት ልጆች ነበሯቸው::

ሀብተሥላሴ ከወላጆቻቸው የተለዩት ገና በሁለት ዓመት ዕድሜያቸው ነበር:: ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረሯ ሀብተሥላሴን ለመንከባከብ በአደራ የተቀበሉት ባልና ሚስት ሕፃኑን ሀብተሥላሴን ይዘው ወደ ግሪክ ሄዱ:: ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተቀስቅሶ ግሪክ በፋሺስት ኢጣሊያና በናዚ ጀርመን መዳፍ ስር ወደቀች:: በዚያ የጦርነትና የመከራ ዘመን ባለአደራዎቹ የሀብተሥላሴ አሳዳጊዎች ሀብተሥላሴን ከልጆቻቸው እኩል እየተንከባከቡ ማሳደጉን ቀጠሉበት:: ሀብተሥላሴ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ንቁ፣ ታታሪና ብልህ ስለነበር ንቃቱንና ታታሪነቱን ተጠቅሞ አሳዳጊ ቤተሰቦቹን ያግዝ ነበር::

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሀብተሥላሴ አባት ፊታውራሪ ታፈሰ በስደት አውሮፓ ውስጥ ነበሩ:: ፊታውራሪ ታፈሰ ልጃቸውን ሀብተሥላሴን በቀይ መስቀል አማካኝነት አፈላልገው ስላገኙት በጦርነቱ መገባደጃ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ይዘውት ተመለሱ::

ብላቴናው ሀብተሥላሴ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው ግሪክ ውስጥ ነው:: ዕድሜው 15 ዓመት እስኪሆን ድረስ የሚናገረው የግሪክና የሩስያ ቋንቋዎችን ነበር:: ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በመግባት ለአንድ ዓመት ያህል የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ተማረ::

በመቀጠልም ግብፅ ወደሚገኘው ቪክቶሪያ ኮሌጅ በማቅናት ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ እ.አ.አ በ1950 አሜሪካ ሄዶ ከሚኒሶታው ካርልተን ኮሌጅ በስነ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ተመርቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ::

ወጣቱ ሀብተሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ የተመደበው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር:: እስከዕለተ ሞታቸው ድረስ ካልተለዩት የቱሪዝም ሥራ ጋር የተዋወቁት በዚህ ወቅት ነበር:: በወቅቱ የሥራ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከወጣቱ ሀብተሥላሴ ጋር ለሥራ ጉብኝት ወደ አውሮፓ ተጓዙ:: በአውሮፓ የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ የተደነቁት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በቱሪስቶች ዘንድ ተወዳጅ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት እንደሆነችና በዘርፉ ጠንክሮ ከተሰራ ብዙ ሀብት ማፍራት እንደሚቻል ለወጣቱ ሀብተሥላሴ ገለፁለት::

ከአውሮፓ እንደተመለሱም ሚኒስትሩ ልዑል ራስ መንገሻ ሃሳባቸውን ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በአጭር ማስታወሻ አቀረቡ:: ንጉሠ ነገሥቱም ሃሳቡን ወዲያው ተቀብለው ለሥራው የሚመጥን ሰው ሚኒስትሩ እንዲያቀርቡ ነገሯቸው:: የሚኒስትሩ ምርጫ ሀብተሥላሴ በመሆኑ ወደ ቤተ መንግሥት ተጠርቶ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያቋቁም በንጉሰ ነገሥቱ ታዘዘ::

ሀብተሥላሴ ግን በቱሪዝም ዘርፍ የትምህርትም ሆነ የሥራ ልምድና ዝግጅት እንደሌለው ለንጉሰ ነገሥቱ በትህትና አስረዳ:: ሥራው ለወጣቱ ሀብተሥላሴ እንደማይሳነው የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ‹‹ … ግዴለም ትችላለህ! ስራው ቶሎ ይጀመር!›› በማለት አጭር መመሪያ ሰጡት:: የንጉሰ ነገሥቱን ትዕዛዝ ተቀብለው ሥራ የጀመሩት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ ውሎ አድሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ታዋቂ ያደረጋቸውን ሙያ የጀመሩት ይህን በመሰለ አጋጣሚ ነበር::

አቶ ሀብተሥላሴ ሥራውን ከግብ እንዲያደርሱ የተጣለባቸው ኃላፊነት ቀላል አልነበረም:: በዘርፉ የትምህርትም ሆነ የሥራ ልምድና ዝግጅት አለመኖር ከዘርፉ አዲስነትና ከሌሎች ችግሮች ጋር ተደምሮ ሥራውን ሲጀምሩት ከባድ አድርጎባቸው ነበር:: ስለጉዳዩ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ‹‹ … በዘርፉ ከመጀመሪያው (እ.ኤ.አ. ከ1954) ጀምሮ አገልግያለሁ:: በወቅቱ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እሠራ ነበር:: ከዚያም በግድ ይህንን የቱሪዝም ሥራ እንድሠራ አዘዙኝ:: ገባሁበት:: ከባድ ሥራ ነው:: ያን ጊዜ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ አይገባም ነበር:: ሲገባም ጉምሩክ ይይዘዋል:: ፈቃድ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ማውጣትም ያስፈልግ ነበር:: በዚህ ሰበብ ሁለት ጊዜ ታስሬያለሁ:: ፎቶግራፍ ለምን ታነሳለህ ብለው ነው ያሰሩኝ:: ያን ጊዜ ፎቶግራፍ የሚያነሳ ሰው ሰላይ ተደርጐ ይታሰብ ስለነበር ነው …›› ብለዋል::

ሀብተሥላሴ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ የማቋቋሙን ተግባር ከዳር ለማድረስ ጥረታቸውን ጀመሩ:: ቦታ፣ ቅርስ፣ ባህልና ሌሎች ሀብቶችን አስጎብኝቶ ገንዘብ ማግኘት መቻል በወቅቱ ቀልድ ይመስል ነበርና ስለስራው ስኬታማነት የተጠራጠሩ ብዙዎች ነበሩ::

ይሁን እንጂ የአቶ ሀብተሥላሴ ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ አስቻለ:: ስራውም ከድርጅቱ እድገት ጋር እየሰፋና እያደገ በመሄዱና ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘቱ አቶ ሀብተሥላሴም የማዕረግ እድገት አገኙ፤ በመጀመሪያ የድርጅቱ ምክትል ሚኒስትር ቀጥሎም ሚኒስትር ዴኤታ ሆኑ:: የድርጅቱን የሥራ መመሪያዎች አዘጋጅተው ፈር ከማስያዛቸው በተጨማሪ ኢንዱስትሪው ዘመናዊ አደረጃጀት እንዲኖረው አደረጉ::

ስራው ዕድገት እያሳየ ቢሄድም ብዙ መሰናክሎች መኖራቸውም አልቀረም:: የበጀት እጥረትና የግንዛብ ማነስ ተጠቃሽ ችግሮች ነበሩ:: ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩም ‹‹ … ሁልጊዜም እየተጠራሁ ወቀሳ ይቀርብብኝ ነበር:: ቤተ ክህነት ተጠርቼ ‹በቴሌቪዥን ለምን እንዲህ ተናገርክ?› እባላለሁ፤ የሀገር ውስጥ ገቢ ይጠሩኝና እወቀሳለሁ:: በዚያን ጊዜ ከቀረጥ ነፃ ሱቅ ከፍተን ነበር::

የእኛ ቢሮ ከመንግሥት ቢሮዎች ሁሉ ሀብታም የሚባለው ነበር:: በወቅቱ የቱሪዝም በጀት 220 ሺህ ብር ስለነበር ‹በዚህ በጀት እንዴት ሀገርን ማሳደግ ይቻላል?› እያልኩ ከጃንሆይ ጋር እጨቃጨቅ ነበር:: አንድ ጊዜ ቁልፉን ይዤ ሄድኩና ጃንሆይ ይህንን መሥሪያ ቤት ለሒሳብ ሹም ይስጡት፤ ደመወዝ ከመክፈል ውጪ ሌላ ሥራ መሥራት አልቻልኩም አልኳቸው:: የቀረጥ ነፃ ፈቃድ ስጡኝ ብዬ ጃንሆይን ጠየቅሁ:: በኋላ የገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና ‹እኛ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር አቅቶናል፤ ሀብተሥላሴ ደግሞ አናታችን ላይ ኮንትሮባንድ ለመፍጠር ይፈልጋል› አሉኝ:: ንጉሡም ‹ሥራህ መቆጣጠር ነው እንጂ ሥራ አይሥራ ነው የምትለው ወይስ መቆጣጠር አልችልም ነው?› ብለው ጠየቋቸውና ተፈቀደልኝ::

ሥራው ሊጀመር ሲል ደግሞ ገንዘብ ስለጠፋ የአባቴን ካርታ ወስጄ አምስት ሺ ዶላር ተበደርኩ:: በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማግኘት ተቻለን:: በአንድ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ የእኛ መሥሪያ ቤት ነበር ሀብታም የነበረው:: አንድ ሚኒስትር ሲሾም በጊዜው እንዲነግድ አይፈቀድለትም ነበር:: ለእኛ ተፈቅዶ ነበርና ብዙ ገንዘብ አስገብተናል:: የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ተሠርቶ ሥራ ሲጀምር የእኛ መኪናዎች ነበሩ የሚያገለግሉት:: 46 መኪናዎች ነበሩን:: እኔ እንደ ሾፌር፣ እንደ አስጐብኚ፣ እንደ ፎቶግራፍ አንሺ እየሆንኩ ሠርቻለሁ:: በኋላ ምቀኛ በዛና ‹የቀረጥ ነፃ ገንዘብ ወደ መንግሥት ይግባ› አሉ:: ያ አሠራር በርካታ ሰዎች በዘርፉ መሰማራት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው …›› በማለት ገልጸዋል::

የኢትዮጵያ መለያ ሆኖ ለብዙ ዓመታት ያገለገለውን ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› ስያሜውን እንዴት እንደመረጡት ሲያስረዱ እንዲህ ብለው ነበር::

‹‹ … እኔ ያደግሁት ውጭ ሀገር ነው:: የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም:: ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው:: አይፈል ታወር ሲታይ ፈረንሣይ ነው:: የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ:: እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር:: ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር:: ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ ‹የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን› ብዬ ጠየቅሁ:: ወዲያው ይህንን ሃሳብ ወደ ቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ:: ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር:: ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት:: የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም:: ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም … ››

አቶ ሀብተሥላሴን የተለዩ የሥራ መሪ የሚያደርጋቸው የነበረን ወይም ያለን ተቋም ወይም ድርጅት ተቆጣጥሮ ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ሥራ የመፍጠር ችሎታቸው ነው:: የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት ለውጭና ለሀገር ቤት ተመልካቾች ማሳወቅ (ፕሮሞሽን)ን መሰረታዊ ዓላማው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቱሪዝም ድርጅት ሥራውን ለማከናወን አቅም ባነሰው ወቅት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን አቋቋሙ:: ዛሬ ይህ ድርጅት የአገሪቱን ቅርስና ባህል ከማስተዋወቁ በተጨማሪ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ተቋም ሆኗል:: በመቀጠልም ከፕሮሞሽኑ ሥራ ጋር ተደጋጋፊ የሆነውን የሀገር ባህል ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅትን አቋቋሙ:: የመኪና ኪራይ ድርጅት እንዲመሰረት ያደረጉትም እርሳቸው ናቸው:: እነዚህ ድርጅቶች ገቢ ከማስገኘታቸው ባሻገር ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ናቸው::

በስራቸው ምክንያት ያልደረሱበት የኢትዮጵያ አካባቢ እንደሌለ የተናገሩት አቶ ሀብተሥላሴ፣ ‹‹ … በእግር፣ በፈረስ፣ በግመል፣ በሄሊኮፕተር፣ በአውሮፕላን ሁሉ ተዘዋውሬ ከ100 በላይ ሰው ያልረገጣቸው የኤርትራ ደሴቶችን አይቻለሁ:: ትልቅ ሀብት ናቸው:: ቢያውቁበት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር:: በጋምቤላ በኩል ጂካው ድረስ ሄጃለሁ:: የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ነው:: በኤርትራ በኩል ቤንአመር ድረስ ወዳለው የጠረፍ ቦታ ደርሻለሁ:: ቤንሻንጉልን በሙሉ እስከ ሱዳን ድረስ አዳርሻለሁ:: መሥራት ካስፈለገ ማየትና ማወቅ ግድ ይሆናል:: ካየንና ካወቅን በኋላ ማውራት ይቻላል … ›› በማለት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል::

የሒልተን ሆቴልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ምግብ ዝግጅት ኢንስቲትዩት እንዲሁም ለፕሮሞሽን ሥራ የዋሉ አያሌ ዲዛይኖች እና መፅሔቶች አቶ ሀብተሥላሴ በቀጥታ ተሳትፈውባቸው ሥራ ላይ ከዋሉ በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው::

በአሁኑ ወቅት ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› የሚለው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መጠሪያ ‹‹ምድረ ቀደምት (Land of Origins)›› በሚል ስያሜ ተተክቷል:: ‹‹ … ‹የ13 ወር ፀጋ› የሚለው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ለብዙ ጊዜያት ያገለገለ ነው:: አሁን መቀየር አለበት› የሚሉ ሰዎች አሉ:: ይቀየር ቢባል ምን ይሰማዎታል?›› ተብለው ተጠይቀው አቶ ሀብተሥላሴ ‹‹ … ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲፈጠርና የሚበልጠው ሲገኝ ያንን ማየቱ ተገቢ ነው:: አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ደግሞ ቶሎ መተካት ነው:: ምንም ችግር የለውም›› ብለዋል::

አቶ ሀብተሥላሴ በርካታ ሽልማቶችንም አግኝተዋል:: በ2009 ዓ.ም የዋንጫና የወርቅ የደረት አርማ (Pin) ሽልማት በወቅቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተበርክቶላቸዋል:: የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ የገንዘብ ሽልማትና እውቅና ሰጥቷቸዋል:: ከዚህ በተጨማሪም በቅርስና ባሕል ዘርፍ የ2007 ዓ.ም ‹‹የበጎ ሰው ሽልማት›› ተሸላሚ ሆነዋል::

እኝህ የቱሪዝም አባት ባደረባቸው ሕመም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው ነሐሴ ሦስት ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል:: ሥርዓተ ቀብራቸው ነሐሴ ሰባት ቀን 2009 ዓ.ም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል::

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You