ስለቁንጅናቸው በእጅጉ ይጨነቃሉ፤ ሴቶች። በዚህ የተነሳ ቁንጅናቸውን ለመጠበቅ፣ ቁንጅና ለመጨመር ወይም እንደ አዲስ ቆንጆ ለመሆን የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ ይባላል። ጥቂቶች ካልሆኑ በቀር የተማሩትም ቢሆኑ «ዞሮ ዞሮ ሴት ነኝ» በሚል እሳቤ ነው መሰል፤ ብዙ ጊዜያቸውን ለመቆነጃጀት ባያውሉም፤ ብቻ በሆነ መልኩ ቁንጅናቸውን ለመጠበቅ ይጥራሉ።
ቁንጅናን የመጠበቅ አልፎም የመጨመር ሥራ በታዳጊነት የእድሜ ክልል የሚጀመር ይመስላል። በዚህ በኩል ቤተሰብ የራሱን ድርሻ ሲወጣ ታዳጊዎቹም ያዩትን ሁሉ በራሳቸው ላይ ለመተግበር ሲጣጣሩ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ የተለመደና ተፈጥሯዊ ሊባል የሚችል ሂደት ነው።
ከዚህ በመለስ ግን ቁንጅናን የመጠበቅን እና የመጨመርን ተግባር የእንጀራ ያህል የሚያከናውኑ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። እንደውም የቁንጅና ውድድርስ ማን ዘንድ ነው ያለው? ሴቶች ዘንድ አይደል?
ይህ ቁንጅናን የመጠበቅና የመጨመር ተግባር ታዲያ ብዙ ዋጋም ያስከፍላል። የቀደሙትስ «ሲያጌጡ ይመላለጡ» ማለታቸው ለዚህ አይደለ? ያኔስ ሹሩባውም ጠበቅ ተደርጎ የተሠራ እንደሆነ፣
የጆሮ ጌጥ ለማድረግ ጆሮ ላይ ቀዳዳ ማበጀቱ ህመም ያለው በመሆኑ፣ ጥርስን መነቀስም ቀላል የማይባል ህመም ስላለው ነው። አሁን ደግሞ ለቁንጅና መጠበቂያና መጨመሪያ በሚል ኮስሞቲክ ቅባቶችን በእጅጉ መጠቀም አለ።
በነገራችን ላይ በእነዚህ ለውበት ተብለው በተዘጋጁ ቅባቶች ውበትን መጠበቅም ሆነ መጨመር፤ «ሲያጌጡ ይመላለጡ» ብቻ ሳይሆን «…መዋዕለ ነዋይዎትን ያውጡ» የተባለ ያህል ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅም ነው። ዋናው ግን ጤና ነውና፤ የጤና ጉዳይ ላይ ስናተኩር በቀዶ ህክምናና በተለያዩ ቅባቶች ሳቢያ ሊመጣ የሚችል ጉዳት በፊታቸውና በመሳሰሉት የአካል ክፍሎቻቸው ላይ እያጋጠማቸው ፊታቸው የተገለበጠ የሚመስል ሰዎች የሚያጋጥሙበት ሁኔታ ጥቂት የሚባል አይደለም።
ኦዲቲ ሴንትራል በድረ ገጽ ላይ ሰሞኑን ከዚህ ጋር የተያያዘ ዜና አስነብቧል። አንዲት ጃፓናዊት ናት አለ፤ በሥራዋ የአውሮፕላን አስተናጋጅ (ሆስተስ) እና ሞዴሊስት ናት። ይህቺ ሴት ላለፉት 21 ዓመታት ለመቆነጃጀት ስትል 30 ሚሊዮን የጃፓን ገንዘብ (የን) ወይም 280 ሺ ዶላር አፍስሳለች፤ ወጪ አድርጋለች።
ይህ ሁሉ ተደርጎም ታዲያ የዚህች የጃፓናዊት ሴት እናት ልጃቸው እርሳቸው የሚያስቡትን ያህል ልትቆነጅላቸው አልቻለችም። ጹባኪ ቶሞሚ የተባለችው ይህች ሞዴሊስት የእናቷን ፍላጎት ለማሟላት ብላ በ18 ዓመቷ ልክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ነው የመጀመሪያ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ያደረገችው። በ20 ዓመቷ ጥርሶቿን እና የአይኗን ቅርጽ በፕላስቲክ ቀዶ ህክምና አቃንታለች፤ የጡት ንቅለ ተከላም አድርጋለች።
ቅርጽዋን በማስተካከል በኩል ለአፍታም አርፋ የማታውቀው ጹባኪ ቶሞሚ፤ ይህንንም እስከ ህይወቷ ፍጻሜ ድረስ እንደምትቀጥልበት ትገልጻለች። ጹባኪ ወጣት ለመምሰል በሚል የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና የምታደርግ ሲሆን፣ ቁንጅናን ብላ በምታከናውናቸው ተግባሮች ክፉኛ የተለከፈችው ገና በጨቅላነቷ መሆኑንም ነው የምትናገረው።
ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው ላይ የጹባኪ እናት ሁሌም ስለ ልጃቸው መልከጥፉነት ሁልጊዜ ይናገሩ ነበር ብሏል። እንደውም ለልጃቸው አንዳች ርህራሄ ባለማሳየት ሰው ፊት ሳይቀር ቆንጆ አለመሆኗን በግልጽ ይነግሯት ነበር። እንግዲህ ይህ በልጅቷ አእምሮ ውስጥ ክፉኛ ዘልቆ ኖሮ፤ ጹባኪ የእናቷን ፍላጎት ለማሟላት በሚል ያላደረገችው እንደሌለ ራሷ ትናገራለች።
መቼም ሰው እድሜው መገስገሱ ያሳስበው ይሆናል እንጂ ጊዜ አይቆምም። እናም ጹባኪም የእድሜዋ እየጨመረ መምጣት የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማድረግ እንደማያስችላት ትረዳለች። እናም ሞዴሊስቷ ለቁንጅናዋ ስትል 30 ሚሊዮን የን ማውጣቷንም ትናገራለች።
ጹባኪ ቶሞሚ ከጃፓኑ የሆስቴሶች መጽሔት «ካባ» ጋር ባደረገችው ቆይታ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ከሆነችበት ጊዜ አንስታ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃን ጨምሮ እናቷ ሁሌም ቁንጅናዋ ሙሉ እንዳልሆነ ስታስብበት መኖሯን ገልጻለች። በየአዲስ ዓመቱ ዋዜማና ቦን የተሰኘው ፌስቲቫል በመጣ ቁጥርም እንዲሁም ዘመድ አዝማድና ጓደኞቻቸው ወደ ጹባኪ እናት ቀረብ ብለው «ወይ ጊዜ! ልጅሽ እንዴት ትልቅ ሆነች?!» ሲሏቸው፤ እናቷ ግን ከማደጓ የልጃቸው መልክ አለማማር ነበር የሚያሳስባቸውና የሚናገሩትም።
ጹባኪ እናቷን አክብራ ዝም ትበል እንጂ፤ ይህን ከማድረግ እንዲቆጠቡ ነግራቸዋለች። እናቷ ግን ከሚሰጡት አስተያየት ለመቆጠብ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ታስታውሳለች፡፡ በዚህ የተነሳ እናቷ የሚሏትን በአእምሮዋ ይዛ ማደጓን እና ራሷን ለፕላስቲክ ቀዶ ህክምና አሳልፋ መስጠቷን አስታውሳለች።
በእርግጥ ነገሩ ለወጪ የዳረጋት ቢሆንም ያገኘችው ገቢም ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ለመጀመሪያ ቀዶ ጥገና ሥራ ከቁጠበዋ አንስታ የከፈለች ሲሆን፣ ከዛ በኋላ በሃያዎቹ እድሜ ታዋቂ ሆስቴስ ለመባል ከመብቃትም ባሻገር በርካታ መጠን ያለው ገንዘብ አግኝታበታለች። ምን ዋጋ አለው! በምታገኘው ገንዘብ «ኑሮዬን ልለውጥ! ቤት ልሥራ!…» አላለችማ!
ከምታገኘው ገቢ ውስጥ አብዛኛውን ገንዘብ ከአገጭ እንስታ አፏን፣ አፍንጫዋን፣ ፊትዋን ለማስተካከል ለተደረጉ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምናዎች ነው ያዋለችው። ባለፉት 21 ዓመታትም 300 ጊዜ የአካል ማስተካከያ ሥራዎች ተደርገውላታል። በቅርቡም ኢንቲማ የተሰኘ እና 160 ሺ የን ወይም አንድ ሺ 500 ዶላር ወጪ የተደረገበት ሌሰር ዘመናዊ የቀዶ ህክምና ተደርጎላታል።
ፕላስቲክ ቀዶ ህክምና በጃፓን በዚህ ዘመን እየተለመደ መምጣቱንም ጠቅሳ፤ እሷ ቀዶ ህክምናውን በጀመረችበት ዓመት ግን ህዝቡ በእጅጉ ያወግዘው እንደነበር ታስታውሳለች። እርሷ ግን ይበልጥ መቆንጀትን በመምረጥ ለህብረተሰቡ አስተያየት ስፍራ ሳትሰጠው ቆይታለች።
ጹባኪ አሁንም ሞዴሊስት በመሆን ተጽእኖ ፈጣሪ እስከ መሆን መድረሷን ዘገባው አመልክቶ፣ በኢንስታ ግራም፣ ፌስ ቡክና ትዊተር ገጾች ሁሉ የማትጠፋ በጃፓን የተለያዩ ድረ ገጾች በመጻፍም እንደምትታወቅ ይጠቁማል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
ዘካርያስ