ሰዎች በሚሰሯቸው ወንጀሎች ምክንያት እንደየጥፋታቸው ፍርዳቸውን ተቀብለው ዘብጥያ ይወርዳሉ።አንዳንዶች በሁኔታዎች አነሳሽነት በወንጀል ተጥርጥረው በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌሎች ደግሞ እንደ ቀላል የወሰዱት ድርጊት ለአስር ሲዳርጋቸው ይታያል። ስካይ ኒውስ ከሰሞኑ ያወጣው ፅሁፍም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
በሀገረ አሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ በየጊዜው ለሚካሄደውና ዳጎስ ያለ ትርፍ ለሚያስገኘው የወፎች ማዘመር ውድድር የሚውሉ ወፎች መግዛት የተለመደ ነው።ለእዚህ ውድድር
የሚቀርብ አንድ ወፍ እስከ 2ሺ 400 ፓውንድ ያወጣል።ይህን የተገነዘበው የሃገረ ጋያና ግለሰብ ታዲያ ለዚሁ ውድድር የሚበቁ ወፎችን ለማቅረብ እቅድ ያወጣል።
ፍራንሲስ ጉራሆ የተሰኘው የ39 ዓመት ግለሰብ 34 ወፎችን በፕላስቲክ የፀጉር መጠቅለያ ውስጥ በመደበቅና የእጅ ሻንጣ ውስጥ በመክተት ከሃገረ ጋያና ተነስቶ አሜሪካ ጆን ኦፍ ኬኔዲ አየር ማረፊያ ይደርሳል።ግለሰቡ ምንም እንዳልተፈጠረ አርጎ በሻንጣ ውስጥ ደብቆ የያዛቸውን ወፎች ከአውሮፕላኑ ያወርዳል።ይሁንና በለስ ሳይቀናው ይቀርና ወፎቹን ለማሳለፍ ሲል በአየር መንገዱ የፍተሻ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ይውላል።
ጉዳዩን የተመለከተው የከተማዋ ፍርድ ቤትም ግለሰቡ ወፎቹን በሻንጣ በመደበቅ ለዚህ ውድድር እያንዳንዳቸውን በ2 ሺ400 ፓውንድ በአጠቃላይ በ81 ሺ 500 ፓውንድ ሊሸጣቸው አቅዶ እንደነበር በማረጋገጥ ፍርድ ሰጥቷል።
የጋያን ወፎች ከአሜሪካ ወፎች በዝማሬ የተሻሉ መሆናቸው የሚነገር ሲሆን፣ በዚህ የተነሳም በኒውዮርክ በሚደረገው የወፎች ማዘመር ውድድር ላይ በብዛት ይቀርባሉ።በዚህ ውድድር ሁለት ወፎች በፓርክ ውስጥ እንዲለቀቁ ከተደረገ በኋላ ዝማሪያቸውን ሰምተው ዳኞች ውሳኔ እንደሚሰጡም የፍርድ ቤቱ የክስ ሰነድ አረጋግጧል። ተወዳዳሪው ካሸነፈ የወፎቹ ዋጋ እስከ 4ሺ ፓውንድ ከፍ እንደሚልም በሰነዱ ተገልጿል።
በ2018 የአሜሪካ የጉምሩክና ድንበር ጠባቂዎች 200 የሚጠጉ ወፎች በሌሎች ግለሰቦች ወደ አሜሪካ ሲሻገሩ በአየር መንገዶች መያዛቸውን የገለፁ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በታህሳስ ወር አንድ ግለሰብ ከጋያና ወደ ኒውዮርክ 70 ወፎችን በሻንጣ በመደበቅ ሊያሳልፍ ሲል በአየር መንገዱ ፈታፈሾች መያዙን ዘገባው አስታውሷል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
አስናቀ ፀጋዬ