እነሆ! ዛሬ ቀኑ ልዩ ነው:: ዕለቱን በጉጉት ሲናፍቁ የቆዩ ሕፃናት በትምህርት ቤቱ አጸድ ማልደው ተገኝተዋል:: የአካባቢው ነዋሪ፣ ጥሪ የደረሳቸው እንግዶች፣ መምህራንና ሌሎችም ስፍራውን እያደመቁት ነው:: በተለይ ትንንሾቹ ልጆች ሌቱ የነጋላቸው አይመስልም:: አብዛኞቹ ወፍ ሲንጫጫ ጀምሮ ሲዘጋጁ መቆየታቸው ያስታውቃል::
ዓመቱን ሙሉ ዕውቀት ሲፈስበት የቆየው ይህ ስፍራ ዛሬ በተለየ ዓላማ ተገልጧል:: የማንነቱ ምልክት የሆኑ ተማሪዎች የልፋት፣ ድካማቸውን ውጤት ሊያዩ፣ በሽልማት፣ በምስጋና ሊመረቁ ጊዜው ደርሷል:: ይህ እውነት የመጀመሪያቸው ለሆነ ሕፃናት ደግሞ ስሜቱ በእጅጉ ይለያል::
በመመረቂያ ልብሳቸው ከወዲያ ወዲህ የሚሉት ሕፃናት የ‹‹ኦርቶተ›› አካዳሚ ፍሬዎች ናቸው:: በወላጆቻቸውና በእኩያ ባልንጀሮቻቸው ታጅበው ልዩ ደስታን ተጎናጽፈዋል:: ለአብዛኞቹ ከወዳጅ ዘመድ የሚበረከትላቸው አበቦችና ስጦታዎች ተዘጋጅተዋል:: የትምህርት ሀሁን የጀመሩበት ትምህርት ቤትም ስለ ውጤታቸው ዝም አላለም:: እንደ የጥረታቸው የሚገባቸውን ማበረታቻ ‹‹እነሆ›› ሊላቸው ዝግጁ ነው::
የ‹‹እንኳን ደስ አላችሁ›› ህብረ ዝማሬ ደምቆ መሰማት ይዟል:: ይህ መዝሙር በትምህርት ዓለም ተጉዞ ከፍጻሜ ለደረሰ ሁሉ ልዩ ስሜትን ያቀብላል:: ዛሬን በዚህ ዝማሬ የታጀቡት ሕፃናት ደግሞ ስለነጋቸው በእያንዳንዱ ስንኝ ይሻገራሉ:: በሚያልፉበት ጎዳናም የስኬት ድልድያቸውን ይገነባሉ:: ይህ ዓይነቱ እውነት እስከ አሁን እልፎችን አጎልብቶ ለፍሬ አድርሷል::
ሰዓቱ እየሮጠ ነው:: የክረምቱን ዝናብ አሸንፋ የደመቀችው ፀሐይ ለቀኑ ያገዘች ይመስላል:: ተመራቂ ሕፃናት፣ ተሸላሚ ተማሪዎች፣ እንግዶችና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ቦታቸውን ይዘዋል:: የዕለቱ መርሀ ግብር በታለመለት ዕቅድ መካሄዱን ቀጥሏል:: የምክክር መድረክ፣ የተማሪዎች ድንቅ ችሎታ፣ የሥነ ጽሑፍና የምርቃቱ ሥነ ሥርዓት እየተከወነ ነው::
በድንኳኑ የፊተኛው ረድፍ ካሉ እንግዶች መሀል ሁሉን ትዕይንት በአንክሮ የሚያስተውል አንድ ትንሽ ልጅ እይታን ይስባል:: አለባበሱ ንጹህና ጠንቃቃ፣ በዕድሜውም ደግሞ ገና እምቦቃቅላ ነው:: እያንዳንዱን ትዕይንት በአንክሮ እያስተዋለ ይደመማል:: በየአጋጣሚው ለመሳቅ አይቸኩልም:: እራሱን እየወዘወዘ በሚያስገርመው ይደነቃል፣ በሚያስደንቀው እጁ እስኪግል ያጨበጭባል::
እሱ ካሻው ቦታ ተራምዶ አያልፍም:: እንደ ሌሎች ፈጥኖም አይሮጥም:: ካለበት እየመጡ የሚያቅፉ፣ የሚስሙት ግን በርካቶች ናቸው:: ያገኙት ሁሉ ስሙን እየጠሩ ፍቅራቸውን ይገልጹለታል:: አክብሮቱ ደግሞ እንደ አዋቂ ነው:: ለእያንዳንዱ የሚሰጠው ምላሽ ልብ ይነካል:: ከተቀመጠበት ዊልቸር የአቅሙን ያህል ተንቀሳቅሶ ምስጋናውን ለመግለጽ አይዘገይም::
ማነው?
እኔ የዚህ ሕፃን ማንነት አልጠፋኝም:: ስለእሱ የራሴን ታሪክ ያህል አሳምሬ አውቃለሁ:: ሁሌም ቢሆን በውስጤ ውሎ ያድራል:: ስለእሱ ዘወትር እያስታወስኩ እተክዛለሁ:: የልጅነት አእምሮው፣ ስለሌሎች ያለው ፍቅርና አክብሮት ሁሉ ከእኩዮቹ ይለያል:: ይህን ልጅ ሳስብና ሳስታውስ ግን ስለወላጅ እናቱ የተለየ ብርታት መዘንጋት አይቻለኝም:: ጥንካሬዋ ሁሌም እንዳስደነቀኝ ነው:: ስለዚህ ልጇ የከፈለችው መስዋዕትነት የእናትነት ወርቃማ ምሳሌ ያደርጋታል::
እሷ ማለት ስለልጇ መኖር፣ ሕይወትና እስትንፋስ ናት፣ ስለእሱ መማርና ማወቅ እንደሻማ ቀልጣ ብርሃን የሰጠች ልዩ ሴት:: ካሰበችው ለመድረስ ብዙ ደክማ ዝላለች:: በልፋቷ መሀል ያየችው ታሪክ መልከ ብዙ ነው:: የእሷ መንገዶች መቼም አልጋ በአልጋ አልነበሩም:: ያለፈችባቸው የሕይወት ጎዳናዎች ፍጹም እሾሃማና ሻካራማ ናቸው:: ልጇን ወልዳ ካቀፈችበት የመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ ሕይወቷ በጭንቅ የተሞላ ፈታኝ ነበር::
ከዓመታት በፊት…
በሶስት ልጆች የተባረከው የጥንዶቹ ጎጆ ዓመታትን በፍቅር ዘልቋል:: መተሳሰብ የሞላው ትዳር ለሌሎች መልካም አርአያ ነው:: ባልና ሚስቱ በፍቅር ውለው ያድራሉ:: አሁን ደግሞ አራተኛው ልጃቸው ሊመጣ በጉጉት እየተጠበቀ ነው:: ለቤቱ እንግዳ የሆነው ይህ ሕፃን ለቤተሰቡ መልካም ስጦታ ነው:: ሁሉም በስስት፣ በጉጉት ይናፍቁታል::
ወይዘሮ ልኬለሽ ተፈሪ በወር ደሞዝ የምታድር የመንግሥት ሠራተኛ ናት:: ዘወትር የባለቤቷን ሰርቶ መግባት፤ የልጆቿን ተምሮ መመለስ ትናፍቃለች:: እንደ እናት፣ ለልጆቿ የዋህ፣ እንደሚስት ለባሏ አሳቢ ነች:: ሁሌም ቢሆን ቤቷን አጉድላ አታውቅም:: በመሥሪያ ቤቷም ትጉህና ጠንካራ መሆኗ ይነገርላታል::
ልኬለሽ እንደማንኛዋም ነፍሰጡር ክትትሏን አቋርጣ አታውቅም:: ቀጠሮ ባላት ጊዜ ከሐኪም ፊት ትቀርባለች:: የምትባለውን አድምጣ ትዕዛዝ ለመፈጸም አትሰንፍም:: እርግዝና ለእሷ አዲስ አይደለም:: ሌሎቹን ስትውልድም በዚሁ መንገድ አልፋለች::
አሁን ልኬለሽ የመውለጃ ጊዜዋ ቀርቧል:: እንደ አራስ ቤት የሚያስፈልጋትን ማሟላት አለባት:: ለአዲሱ እንግዳ፣ ለልጆቿ ወንድም የሚበጀውን ማድረግ ግድ ይላታል:: ከጥቂት ጊዜ በኋላ አዲሱን ጨቅላ ትታቀፋለች:: ከዚህ ባሻገር ለሚሆነው ደግሞ ነገ መልስ ይኖረዋል::
ከቀናት በአንዱ …
ዛሬ ልኬለሽ ከሐኪሟ ዘንድ ቀጠሮ አላት:: ቀኑን ሳታዛባ በዕለቱ ተገኝታለች:: እንደ ሁልጊዜው የምትባለውን ሰምታ ለመሄድ ራሷን አዘጋጀች:: ምርመራዋ ከወትሮው የተለየ ነበር:: ምክንያቱ ባይገባትም መደንገጧ አልቀረም::
ከደቂቃዎች በኋላ የሰማችው እውነት ከአቅሟ በላይ ሆነ:: ሐኪሙ በእጁ የገባውን የአልትራሳውንድ ውጤት እያስተዋለ ያለማወላወል ዕቅጩን ነገራት:: ይህ ከመሆኑ በፊት እናት ልኬለሽ ስለእሷ ሕይወት ቅድሚያ እንደሚሰጥ አባብሎ የነገራትን ሀቅ በወጉ አልሰማችም::
አሁን ጆሮዋ ምን እያቀበላት እንደሆነ አልገባትም:: ሐኪሙ ስለእሷ ሕይወት ብቻ ደጋግሞ የሚናገረው ጉዳይ እንቆቅልሽ ሆኖባታል:: ለመውለድ አስራ አምስት ቀን ብቻ እንደቀራት ታውቃለች:: በሰላም ወልዳ ልጇን ለማቀፍ የነበራት ህልም ዕውን አለመሆኑ እየገባት ነው::
ወይዘሮዋ በሆዷ ያለው ጽንስ ጤናማ አለመሆኑን እንዳወቀች ጤናዋ ተቃወሰ:: የደም ግፊቷ ጨምሮ ልቧ ያለቅጥ ፈጠነ:: ሐኪሞቹ እንዳሏት ችግሩ የተከሰተው በእርግዝና ወቅት ‹‹ፎሊክ አሲድ›› የተባለው መድኃኒት በአግባቡ ባለመወሰዱ ነው:: በዚህ ሳቢያ በጽንሱ ላይ የጀርባ ላይ ክፍተት አጋጥሟል:: ልኬለሽ እየተነገራት ያለው እውነት በእሷም በሌሎችም ላይ አጋጥሟት አያውቅም:: እንደምንም ራሷን ለመግዛት ሞከረች::
ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ በሕይወት ከቀጠለ በቀዶ ሕክምና እንደሚታገዝ ተነግሯታል:: በውስጧ ሁለት ተቃራኒ ስሜቶች ሙግት ገጠሙ:: ‹‹በሕይወት›› ከቀጠለ›› የሚለውን ቃል ልትቀበለው ከአቅሟ በላይ ሆነ:: ቀዶ ሕክምና ይሉት አማራጭ ደግሞ የቆሰለ ውስጠቷን ስስ ተስፋ ዘራበት:: አሁን ሁሉን ለፈጣሪዋ ትታ የሚሆነውን ልትቀበል ነው:: አስጨናቂዎቹን ቀሪ ቀናት አንድ፣ ሁለት… ስትል መቁጠር ያዘች::
ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ…
እነሆ! ጊዜው ደረሰ:: የተረገዘው ሊወለድ እናት ልኬለሽ ምጥ ጀመራት:: ለእሷ ይህ ጊዜ ፍጹም ልዩ ነበር:: ከተለመደው ህመም የዘለለ ጭንቀት፣ እስከ ዛሬ ከምታውቀው ምጥ የተለየ ስቃይ አስተናገደች:: ‹‹ምን ዓይነት ልጅ እወልድ ይሆን? ››በሚል ስጋት መንፈሷ ታወከ:: አዲሱ እንግዳ ዓለምን በለቅሶ ሲቀላቀል ዓይኖች ሁሉ በሁለመናው አረፉ:: የሐኪሞቹ እውነት በማሳያዎች ተረጋገጠ:: ሕፃኑ የተወለደው ከነርቭ ዘንግ ክፍተት ጋር ነበር::
የነርቭ ዘንግ ክፍተት በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹ስፓይና ቢፊዳ›› በሚል ይታወቃል:: በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥም የፎሊክ አሲድ እጥረት ጋር ተያይዞ በሕፃናት ላይ የሚደርስ ችግር ነው:: ለአብዛኞቹ ሕፃናት አካላዊ ጉዳት ምክንያት የሆነው ይህ ህመም ተደጋጋሚ የቀዶ ሕክምና የሚያስፈልገው በመሆኑ ፈተናውን ከባድ ያደርገዋል::
ልኬለሽ ከወለደች በኋላ የአራስነት ወግን አላየችም:: መላ ቤተሰቧን ከቤት ትታ ለወራት ከጨቅላው ጋር በሆስፒታል አልጋ ከረመች:: ስለ ትንሹ ልጅ ህመሙን ተጋርታ፣ ጭንቀቱን ተካፈለች:: በጥረት ልፋቷ ሕይወቱን የታደገችው እናት ‹‹በቃ›› እስክትባል እግሮቿ አልራቁም:: ዓይኖቿ ከልጇ ዓይኖች አልተነቀሉም::
እዮስያስ ተወዳጁ ጨቅላ…
‹‹እዮስያስ›› ማለት ትርጉሙ ‹‹እግዚአብሔር፣ ያግዛል፣ ይደግፋል›› እንደማለት ነው:: እውነትም እንደ ቃሉ ሆኖ እናት ልኬለሽ በፈጣሪዋ ድጋፍ ትንሹን እዮስያስ ይዛ ከቤቷ ገብታለች:: ቤተሰቡን ከተቀላቀለ ወራትን የቆጠረው ሕፃን በእህት ወንድሞቹ ተናፋቂና ተወዳጅ ሆኗል::
ዮሲ እንደማንኛውም ሕፃን ሊሆን የሚቻለው አይደለም:: ቀዶ ሕክምናውን ያስተናገደ አካሉ ጥንቃቄን ይሻል:: ሕክምናው በዚህ ብቻ አይበቃምና በየጊዜው በሐኪሞች ይጎበኛል:: ዕድገቱ በጨመረ አካሉ ባደገ ቁጥር ተያያዥ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለእናት ልኬለሽ ተነግሯታል:: ከዚህ ችግር ጋር የሚወለዱ ልጆች ባብዛኛው ከቤተሰብና ከማህበረሰቡ መገለል ያገኛቸዋል:: በወጉ ለመንቀሳቀስ፣ ተምሮ ለመለወጥ የሚኖራቸው ዕድልም የጠበበ ነው::
እናትነት ከቃል በላይ…
ዮሲ ከወገቡ በታች አካሉ አይንቀሳቀስም:: የህመሙ ተጽዕኖም ሕፃንነትን የሚሻገር የዳይፐር ተጠቃሚ እንዲሆን ያስገድደዋል:: ይህን የተረዳችው እናት ስለልጇ መኖር ራሷን አዘጋጀች:: ለዓመታት ትሰራበት የነበረውን ቋሚ ሥራ ለቃ የቤት እመቤት ሆነች:: ስለ ትንሹ ልጅ ራሷን ጣለች፣ ከሳች፣ ተጎሳቆለች:: ይህ ሁሉ ሲሆን ልጇ እንዳይከፋ፣ እንዳያዝን ፈገግታዋ ከፊቷ ነበር::
አሁን እዮስያስ ዕድሜው እየጨመረ አካሉ እያደገ ነው:: ትምህርት ቤት የመግቢያ ዕድሜው ቢደርስም ከመሬት ችሎ አይነሳም፣ ለመራመድ ለመሮጥ አይሞክርም:: ዮሲ አስተውሎቱ የዳበረ፣ ግንዛቤው የተለየ ልጅ ነው:: እኩዮቹ፣ ከትምህርት ውለው ሲመጡ ስለራሱ ያስባል:: የእህት ወንድሞቹን ደብተር ሲያይ እናቱን በጥያቄ ያፋጥጣል::
ትምህርትን ፍለጋ…
ትንሹ ልጅ ስለትምሀርት በትኩረት እያሰበ ነው:: የእሱ ከሌሎች ተለይቶ ከቤት መቅረት እየገባው አይደለም:: በየጊዜው ለምን ሲል ራሱንና ሌሎችን መጠየቁን ቀጥሏል:: እናት ልኬለሽ አሁንም ስለእሱ ዝም አላለችም:: የልጇን ፍላጎት ለመሙላት፣ በዕድሜው የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ አበከራ መታገሏን ይዛለች::
ዮሲ እንደሌሎች ልጆች ራሱን ችሎ አይሄድም:: እሷም እጁን በእጇ ይዛ ምሳ ዕቃውን ቋጥራ ወስዳ አትመልሰውም:: እንዲህ መሆኑ ተስፋዋን አላጨለመም:: ልጇን አዝላ ትምህርትን ፍለጋ ተጓዘች:: ነገሮች ሁሉ እንደታሰቡት አልሆኑም:: በር ያንኳኳችባቸው ትምህርት ቤቶች ሁሉ ፊት ነሷት::
እነሱ በእግሩ ሮጦ የሚገባ እንጂ ታዝሎ የሚመጣ ተማሪ አጋጥሟቸው አያውቅም:: ዳይፐር የሚጠቀም፣ የሌሎች እገዛን የሚሻ ሕፃንም አይፈልጉም:: እናት ልኬለሽ ተስፋ አልቆረጠችም:: በየቦታው እያንኳኳች፣ እየጠየቀች፣ በድካም ባዘነች:: ጥቂት ቆየት ብሎ አንድ ትምህርት ቤት ሊቀበለው ፈቀደ:: የልጇ ፍላጎት ሞላ:: በእጅጉ ደስ አላት::
‹‹ለላም ቀንዷ አይከብዳትም››
አሁን ልኬለሽ በየቀኑ ልጇን አዝላ ትጓዛለች:: የእሷ መንገድ ወደ ዕውቀት ያደርሳል፣ የልጇን ምኞት ይሞላል:: አካባቢዋ የእግር መንገድ አለው:: ከቤት ትምህርት ቤት ለመድረሰ ወጥታ የምትወርደው የድንጋይ ደረጃ ተቆጥሮ አያልቅም:: እሱን አልፋ ታክሲ ለመያዝ ደግሞ ብዙ መታገል፣ መጋፋት ይጠብቃታል:: የታዘለውን ትልቅ ልጅ የሚያዩ ባለታክሲዎች ከሌሎች እሷን ሊያሳፍሩ አይፈቅዱም:: እንዳላየ ዘግተዋት ያልፋሉ::
የልኬለሽና የልጇ እንክርት ከአቅም በላይ ሆኗል:: እሷ በየቀኑ አዝላው መዞሩ ቢያደክም እንጂ አላሰለቻትም፣ ስለ እሱ ደስታና ፍላጎት የእናትነት ፍቅሯን እየከፈለች ነው:: ውሎ ሲያድር ልኬለሽና ቤተሰቦቿ መከሩ:: የነበረቡትን አካባቢ ለቀው ቢሄዱ ለትንሹ እዮስያስ እንደሚበጅ ገባቸው::
አዲሱ ሰፈር…
አሁን የእነዮስያስ መኖሪያ ተቀይሯል:: ከከተማ ወጣ ብለው የገቡበት ሰፈር ውጣወረድ የሌለበት ፀጥተኛ ነው:: እንዲህ መሆኑ ትንሹን ልጅ ለማንቀሳቀስ፣ ከትምህርት ቤት አውሎ ለመመለስ ያመቻል:: ይህ መልካም አጋጣሚ የዮሲን ፍላጎት አሟላ:: በአካባቢው የሚገኝ ትምህርት ቤት ሊያስተምረው ፈቀደ::
ጎበዙ ዮስያስ ዛሬም በእግሩ አይራመድም:: ልክ እንደ ትናንቱ ዳይፐርና የሌሎች እገዛን ይፈልጋል:: የሁልጊዜው አጋር ውድ እናቱ ዛሬም ከጎኑ ናት:: በማለዳው ገላውን አጥባ፣ ዳይፐሩን ቀይራ ለትምህርት ታዘጋጀዋለች:: ዮሲ ዛሬ ላይ የዘጠነኛ ዓመት ዕድሜውን እየተሻገረ ነው:: አካሉ ጎልብቷል:: አስተሳሰቡ ከእኩዮቹ የላቀ ነውና የሚጽፋቸው ግጥሞች ከእሱ የሚጠበቁ አይመስሉም:: ሁሌም የሚያየውን አይዘነጋም:: ቁም ነገር ሲጫወት፣ የወዳጅ ዘመድ ጤናን ሲጠይቅ ልጅ መሆኑን ያስረሳል::
በአዲሱ ሰፈር ኑሮ ከተጀመረ ወዲህ እዮስያስ ትምህርቱን በወጉ እየተማረ ነው:: እገዛ ቢያሻውም በዊልቸሩ ለመንቀሳቀስ ይሞክራል:: ከጥቂት ጊዜ ወዲህ መለስ ቀለስ የሚልበት የጤና ችግር ግን አንዳንዴ ከትምህርቱ ያስቀረው ይዟል:: መላው ቤተሰብ ጭንቅ ውስጥ ነው:: ቤቱን በፍቅር ሙሉ የሚያደርገው ትንሽ ልጅ ውሎው ከሆስፒታል መሆኑ ለሁሉም ሰላም አልሰጠም::
ዮሲ ከዚህ ቀድሞ የነበረው የሕክምና ክትትል አልተቋረጠም:: ዘንድሮ ጀርባው ላይ ያደረገው ቀዶ ሕክምና ግን ቂም ቋጥሮ ያሰቃየው ጀምሯል:: የልጅነት አካሉ ስቃዩን መቋቋም አልቻለም:: ለስምንት ወራት በኢንፌክሽን ቁስል ተሰቃየ:: በቀላሉ ወደቤቱ አልተመለሰም:: ከሚወደው ትምህርቱ ተቆራረጠ::
እነሆ! ዛሬ ትንሹ እዮስያስ በተማሪዎች የምርቃት ቀን ከፊት ተቀምጦ ዝግጅቱን እየቃኘ ነው:: ለወራት ርቆት የቆየው ትምህርት ትውስ ያለው ይመስላል:: የኦርቶተ አካዳሚ ፍሬዎች የዕለቱ ድምቀቶች ሆነዋል:: አምና ይህን ጊዜ ዮሲ ተሸላሚ ተማሪ ነበር:: ዘንድሮ ደግሞ እንደ ተጋባዥ እንግዳ ከፊት ተቀምጧል::
የዕለቱ ዝግጅት በተያዘለት ዕቅድ እየተከወነ ነው:: በድንገት ዮሲ የመርሀ ግብሩ አንዱ አካል ሆኖ ወደ መድረኩ ተጋበዘ:: ወዲያው ዊልቸሩን የሚሸከሙ፣ እጆች ተረባረቡ:: ትንሹ ልጅ በእርጋታ ንግግሩን ጀመረ:: ትምህርት ቤቱ የመማር ዕድል ስለሰጠው፣ ጓደኞቹ ፍቅርና አክብሮት ስለለገሱት ከልብ አመሰገነ:: ለዕለቱ ያዘጋጀው ግጥም ጆሮ ገብ ነበር::
ስለእሱ የሚናገሩ አንደበቶች ዝም አላሉም:: ማንነቱን ሊተርኩ ቃላት አወጡ:: ጥንካሬው፣ ጉብዝናው ተወሳ:: የእናት ልኬለሽ ብርታትም እንዲሁ:: ዮሲ ዛሬም ድጋፍን ይሻል:: ዳይፐር ያስፈልገዋል:: የትምህርት ቤት ክፍያና ሌሎች ወጪዎች ይጠብቁታል:: በስፍራው የነበሩ እንግዶች ስለእሱ ባወቁ ጊዜ በዓይኖቻቸው ዕንባ ሞላ:: አብዛኞቹ በትካዜ አንገታቸውን ደፉ::
ዕንባ ሲታበስ..
ከአፍታ ደቂቃዎች በኋላ አንድ አስገራሚ እውነት ወደ መድረኩ ደረሰ:: የኦርቶተ አካዳሚ የቦርድ አባላት ፈጣን ውሳኔን ይዟል:: ሕፃን እዮስያስ ኃይሉ የትምህርት ቤቱ ድንቅ ፍሬ ነው:: እስከዛሬ በብዙ ችግሮች መሀል ተመላልሷል:: ከአሁን በኋላ ግን ይህ ፈተናው አይደገምም::
ለእዮስያስ የትምህርት ክፍያው ነፃ ይሆንለታል:: የመማሪያ ቁሳቁስ ይሟላለታል:: የዳይፐር ወጪውም ይሸፈንለታል:: በጭብጨባ የደመቀው መድረክ በአድናቆትና ክብር ተሞላ:: የዮሲ ፊት በፈገግታ ደመቀ፤ የእናት ልኬለሽ አንደበት ለምስጋና ተከፈተ:: ልበ ሙሉው ብላቴና ለራሱ ቃል ሲገባ አደመጥኩት:: ከዚህ በኋላ ትምህርቱን ያለ አንዳች ችግር እንደሚቀጥል ሲናገር በተለየ ተስፋ ተሞልቶ ነበር::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 ቀን 2016 ዓ.ም