ወላጅ ለልጁ ከሚወደው፣ ካጋጠመው አሊያም ከሁኔታዎች ጋር አያይዞ ስም ያወጣል። አንዳንዴም ስም ከመጠሪያነት ባለፈ የማንነት መገለጫ፣ የተስፋ ማሳያ እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎችን ጠቋሚ ሊሆንም ይችላል። ከወደ ኢንዶኔዢያ የተሰማው ዜና ደግሞ ያልተለመደ ስም ለህጻን ልጁ ያወጣው አባት መሸለሙን ነው። አባት ለሽልማት የበቃው ደግሞ ልጁን «ጉግል» ብሎ በመሰየሙ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
እንደሚታወቀው፤ ዘመናችን የኢንተርኔት አብዮት ላይ ይገኛልና አንድን ነገር ለመረዳት እንደ ቀድሞ መጽሃፍትን ማገላበጥ እና አዋቂዎችን ማፈላለግ ቀርቷል። ይልቁንም በዘመናዊ የእጅ ስልኮቻችን ወይም በኮምፒዩተሮች ደቂቃዎችን ብቻ በማጥፋት ስለፈለግነው ነገር ሙሉ መረጃ ማግኘት እንችላለን። በዚህ ረገድም ጉግል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ታዲያ አባትም አንዳች ነገር ተፈልጎ በማይታጣበት ጉግል ልጃቸውን መሰየማቸው ከመነጋገሪያነት ባለፈ ለዕውቅና አብቅቷቸዋል።
በምድር ላይ ስምንት ወራትን ብቻ የኖረው የህጻኑ ጉግል አባት የ31ዓመቱ አንዲ ቻያ ሳፑትራ፤ ለልጁ ይህንን ስም ያወጣው ህጻኑ ከመወለዱ አስቀድሞ የሰባት ወራት ጽንስ ሳለ መሆኑን ለሃገሩ መገናኛ ብዙሃን ገልጿል። ባለቤቱ መጸነሷን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በሚኖርበት አካባቢ የተለመደውን አልብራ ዲርጋንትራ ፑትራ የሚል ስም አሊያም በቁርዓን ያሉ ስሞችን ለልጁ ሊያወጣለት አስቦ እንደነበርም ያስታውሳል። ነገር ግን የትኛውም ስም የአብራኩ ክፋይ ለሆነው አዲስ ህጻን የሚስማማ ሆኖ አላገኘውም።
በዚህ ምክንያትም ሁሉን ትቶ ልጁን፤ ዊንዶ፣ አይ ፎን፣ ማይክሮሶፍት፣ አይኦኤስ በመሳሰሉ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ተቋማት መጠሪያ ለመሰየም ተነሳ። በመጨረሻም ቀልቡ ከጉግል ላይ አረፈ፤ ለልጁም ይህ ስም ትክክለኛና ተስማሚ ሆኖ አገኘው። እናት ግን በወቅቱ በዚህ ስም ባትስማማም፤ ቀስ በቀስ እርሷም ተቀብላው የልጃቸውን ስም በዓለም ላይ ታላቅ በሆነው የኮምፒውተር መፈለጊያ አንቀሳቃሽ ሊሰየም ችሏል። በዚህም ወላጆች «በዓለም ያልተለመደ ስም» ሽልማት (ምስክር ወረቀት) ባለቤት ሆነዋል።
የ27ዓመቷ እናት ኤላ ካሪን በህጻኑ ስም ተደምመው ለጥየቃ ወደእርሷ ለሚያቀኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስሙን ከመጥራት ይልቅ «ህጻኑ ልጄ» ማለት ይቀናት እንደነበርም ዘገባው ያትታል። ህጻኑ ሶስት ወራትን እስኪያስቆጥር ድረስም ከስሙ ጋር ሳትለማመድ ነበር የቆየችው፤ አሁን ግን በኩራት ልጇ የበርካቶች አለቃ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላት ትገልጻለች።
በሌላው ዓለም ለሰዎች ስም የመጀመሪያ እና ተከታይ ስም ማበጀት የተለመደ ቢሆንም፤ ጉግል ግን ነጠላውን ይጠራል። ይህ ለምን እንደሆነ አባት ሲጠየቅም የልጁን የተለየ ስም ከሌላ ስም ጋር መከለስና መበረዝ እንደማይፈልግ ነው የገለጸው። አክሎም «ጉግል በዓለም ላይ ቀዳሚውና በበርካታ ሰዎች የሚጎበኝ ሳይት ነው። ትልቅ ትርጓሜ ያዘለ ስምም ነው፤ ጉግልም አድጎ በርካቶችን እንደሚጠቅምና እንደሚረዳ ተስፋ አደርጋለሁ» ማለቱ ተደምጧል።
የህጻኑ ጉግል እናት ኤላ በበኩሏ፤ ሰዎች እርሷና ባለቤቷ ለልጃቸው ባወጡላቸው ስም እንደሚዘባበቱባት ትገልጻለች። እርሷ ግን ለሚቀልዱባት «እንዲያውም አዲስ የምትወልዱትን ህጻን ‘ዋትስአፕ’ ብላችሁ ሰይሙት» በማለት ምላሽ ትሰጣለች። ነገሩ እንደማያስከፋትና የጉግልን ትርጉም ባለማወቃቸው እንደሚያሾፉባት ነው የምታብራራው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ብርሃን ፈይሳ