ሰዎች በስራና ሌሎች ጉዳዮች በሚጠመዱበት በዚህ ወቅት ምግብን አብስሎና አዘጋጅቶ መመገብ አስቸጋሪ መሆኑ ይታወቃል። በተለይ በከተሞች አካባቢ ኑሮው በውጥረት የተሞላ እንደመሆኑ የተዘጋጁና መሰረታዊ የሆኑ ፍጆታዎችን ጭምር ከገበያ መግዛት በእኛም ሃገር ይሁን በሌላው ዓለም የተለመደ ነው። በቀላሉ ወደ ገበያ አዳራሾች በመሄድ ማብሰል የማያስፈልጋቸውን ምግቦችና መጠጦች በመሸመት መጠቀምም አሁን ላለንበት የአኗኗር ሁኔታ አማራጭ ሆኗል።
የታሸጉ ምግቦችን በብዛት መጠቀም ጉዳቱ በሂደት የሚያይል መሆኑ በባለሙያዎች ይነገር እንጂ፤ በርካቶች ግን ይጠቀሙታል። ክልከላው የመነጨው ምግቡ ጣዕሙን እንደያዘ ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ሲባል ኬሚካሎች ስለሚጨመሩበት እንደሆነም ይነገራል። በተለይ በማሸጊያው ላይ የሚለጠፈው የምግቡን አሊያም የመጠጡን የቆይታ ጊዜ ሳያረጋግጡ መግዛት በጤና ላይ ከባድ እክል ሊያደርስም ይችላል።
ይህ በባለሙያዎች ዘንድ ይነገር እንጂ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ግን «ካላየሁ አላምንም» የሚል ቁማር በህይወታቸው ይጫወታሉ። በእንዲህ ዓይነት ቁማር (ጀብድ) ከሚሳተፉት መካከል አንዱ የሆነው የአሜሪካዋ ሜሪላንድ ነዋሪ ከሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል። ስኮት ናሽ የተባለው ግለሰብ «የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምግቦች መመገብ እንደሚባለው ለጉዳት ይዳርጋል?» የሚለውን ማውጠንጠን የጀመረው ከሶስት ዓመታት በፊት መሆኑን የኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ ዘገባ ያስነብባል።
አስደናቂው ነገርም፤ ሃሳቡን በተግባር አስደግፎ የአፈታሪክ መሰሉ ንግርት ባለቤት ለመሆንም የመሞከሪያ አይጦችን ሳይሆን ህይወቱን ነበር በማስያዣነት ማቅረቡ ነው። ለተግባራዊነቱም በቅድሚያ ከአንድ የገበያ ማዕከል ያረጀ የዕቃ መደርደሪያ ያገኘውንና ተረስቶ ከገበያ ላይ ቆይታ ጊዜው ስድስት ወራትን ያሳለፈ እሽግ የረጋ ወተት በመጠጣት ሙከራወን ጀመረ። የወተቱ ጣዕም መልካም የሚባል አይሁን እንጂ ለህመምም ሆነ ለከፋው ሞት እንዳላጋለጠው አረጋገጠ። በዚህም የታሸጉ ምግቦችን አምራች ድርጅቶች ለምን የቆይታ ጊዜውን በእሽጉ ላይ ይጽፋሉ የሚል ጥርጣሬ አዘል ጥያቄ ማንሳት ጀመረ።
ትዝብቱንም «ግልጽ አይደለም፤ የገበያ ላይ የቆይታ ጊዜ ምን ማለት ነው? ከዚህ እስከዚህ ባለው ጊዜ ተጠቀሙ ማለት ትክክል አለመሆኑን ተገንዝቤያለሁ። እንዲያውም ግራ ሊያጋቡን ስለፈለጉ ብቻ ነው ይህንን የሚሉት» ሲል ይገልጻል። እርሱ ይህንን ይበል እንጂ፤ ዕሽግ ምግቦች እና መጠጦች ግን የተመረቱበት እንዲሁም ለምን ያህል ጊዜ መቆየት እንደሚችሉ ማሳሰቢያ መስጠታቸው አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር ከምርት ጥራት መገለጫዎች መካከል አንዱ ነው። እንደ ጨው፣ የህጻናት ንጽህና መጠበቂያዎችና ሌሎች በቆይታ ሊበላሹ ከሚችሉ ምርቶች በቀር።
ስኮት ናሽ ግን ከመጀመሪያ ሙከራው በተረዳው መሰረት ከራሱ አልፎ ላለፈው አንድ ዓመት ቤተሰቦቹንም ጭምር ከገበያ ላይ የቆይታ ጊዜያቸው ሳምንታትና ወራትን ያሳለፉ ስጋ፣ ክሬም እና መሰል ምግቦችን ሲመገቡ መቆየታቸውን ዘገባው ተመላክቷል። በማቀዝቀዣ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተረስቶ በቆየ የገበታ ቅቤ ምግባቸውን ቢያበስሉም ቤተሰቡ ላይ የደረሰ አንዳችም እክል እንደሌለም ተረጋግጧል።
ናሽ በሙከራው ይህንን ያረጋግጥ እንጂ ለረጅም ጊዜ መቆየት በማይችሉ ምግቦች ላይ ግን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሳይጠቁም አላለፈም። ምግቡ ጠረን ከፈጠረ አሊያም ተፈጥሮአዊ ጣዕሙን ከቀየረ አለመጠቀም አማራጭ እንደሌለውም ያምናል። ከዚህ ባለፈ ግን አምራቾች ተጠቃሚዎች ላይ በሚፈጥሩት ማስፈራሪያ ወደኋላ ማለት እንደሌለባቸውም ያሳስባል።
እንዲያውም አምራቾች በጊዜ የገደቡትን ምርት ሻጮችና ተጠቃሚዎች ሲያስወግዷቸው አምራቾቹ ወደ ጥቅም እንደሚቀይሩትም ነው የሚጠቁመው። በማብራሪያውም «የሚበላሹ እና በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የምግብ ዓይነቶች ይኖራሉ፤ አብዛኛዎቹ ግን ፍርሃትን የሚፈጥሩ ብቻ ናቸው» ይላል።
ግለሰቡ ይህንን የሙከራ ውጤት በግል ድረ- ገጹ ለዘመናት የቆዩ በጠርሙስና ቆርቆሮ የታሸጉ ምግቦችን ሲጠቀም ለተከታዮቹ ያሳያል። ነገር ግን ተጠቃሚዎች ምቾት የሚነሳቸውን ነገር እንዳይጠቀሙ ከማሳሰብ ወደኋላ አይልም። የእርሱን የሙከራ ውጤት ሙሉ ለሙሉ መቀበል አዳጋች ቢሆንም፤ በእርሱና በቤተሰቡ ህይወት መወራረዱን ድፍረት ወይስ ምን እንበለው?
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ብርሃን ፈይሳ