በፓሪስ ይደምቃሉ ተብለው የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን ከዋክብት

ኦሊምፒክን ለሶስተኛ ጊዜ የማስተናገድ ዕድል ባገኘችው ፓሪስ ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል። እስካሁንም ሀገራት በተለያዩ ስፖርቶች ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ እየተፎካከሩ ይገኛሉ። ግብጽ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገራትም ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚዎቹ መሆን ችለዋል። በመጪው ሐሙስ በሚጀምሩት የአትሌቲክስ ውድድሮች ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአህጉሪቱ ጠንካራ ተፎካካሪዎችም ወደ ሜዳሊያ ሽሚያው እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ዘንድሮ 15ኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን የምታደርግ ሲሆን፤ የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድሯንም ከነገ በስቲያ በሚካሄደው የወንዶች 20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ የምትጀምር ይሆናል። በውሃ ዋና እና በአትሌቲክስ ስፖርቶች ተሳትፎዋን የምታደርገው ኢትዮጵያ በ43 በሚሆኑ አትሌቶች (ከእነተጠባባቂዎቻቸው) ትወከላለች። እነዚህም ርቀቶች በ800 ሜትር ሴቶች፣ 20 ኪሎ ሜትር የወንዶች ርምጃ እንዲሁም በሁለቱም ጾታ በ 1 ሺህ 500 ሜትር፣ 3ሺህ ሜትር መሰናክል፣ 5ሺህ ሜትር፣ 10ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን ናቸው። ባለፉት ተሳትፎዎቿ 23 የወርቅ፣ 12 የብር እና 23 የነሃስ በጥቅሉ 58 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ የቻለችው ኢትዮጵያ፤ በዚህ ኦሊምፒክም በምትታወቅባቸው የመካከለኛ እና የረጅም ርቀት ውድድሮች ተጨማሪ ክብሮችን ታስመዘግባለችም ተብሎ ይጠበቃል።

ከአራት ዓመታት በፊት ቶኪዮ ላይ በተካሄደው ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በወንዶች 10ሺህ ሜትር በአትሌት ሰለሞን ባረጋ በተገኘው ብቸኛ የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁም 1ብር እና ሁለት ነሃስ በጥቅሉ 4 ሜዳሊያዎች መመለሷ ይታወሳል። የፓሪስ ኦሊምፒክን ተከትሎ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስቀድሞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቡድኑ ሊያስመዘግብ ያቀደውን ሜዳሊያ በቁጥር በይፋ አለመናገሩ የሚታወስ ነው። ይሁንና ቡድኑ እንደተለመደው በሚሳተፍባቸው የተለያዩ ርቀቶች ሜዳሊያዎችን ያስመዘግባል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበታል። ኢትዮጵያ የኦሊምፒክ እና የዓለም ቻምፒዮናዎችን እንዲሁም የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆኑ ምርጥ አትሌቶችን መያዟ የዚህ ተስፋ ምክንያት ነው።

ከታላቁ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ ቀዳሚው የወርቅ ሜዳሊያ አንስቶ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ስም የሚነሳው በጠንካራ አትሌቶቿ ነው። ከሀገር አልፈው በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ አዳዲስ ታሪክ እንዳጻፉት አንጋፋዎቻቸው አሁንም የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ የወጣት አትሌቶቹን ብቃት ሊያይ ይጓጓል። ቶኪዮ ላይ ጠንካራዎቹን የዩጋንዳ አትሌቶች ጆሹዋ ቺፕቴጊን እና ጃኮፕ ኪፕሊሞን አስከትሎ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ፓሪስ ላይም እጅግ ተጠባቂው አትሌት ነው። የ 10 ሺህ ሜትር ርቀትን የሚመራው ወጣቱ አትሌት ባለፉት የዓለም ቻምፒዮናዎች ላይ እንደተጠበቀው ባይገኝም በዚህ ዓመት ካለበት አቋም አንጻር ለሜዳሊያው የሚፎካከር ይሆናል። የቡድን አጋሮቹ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊም ለተፎካካሪዎቻቸው የማይመለሱ አትሌቶች መሆናቸው ይታወቃል።

በሴቶች በዚሁ ርቀት ባለፈው ዓመት ቡዳፔስት ላይ የዓለም ቻምፒዮና የሆነችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይም ቡድኑ ካካተታቸውና ለተፎካካሪዎቻቸውም ስጋት ከሆኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል አንዷ ናት። አትሌቷ በ5ሺህ ሜትር ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ነሃስ ማጥለቋ የሚታወስ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ደግሞ የዓለም ክብረወሰንን በመስበር የርቀቱ ምርጥ አትሌትነቷን አስመስክራለች። ጠንካራዋ አትሌት በ1 ሺህ 500 ሜትርም የቤት ውስጥ ክብረወሰን ባለቤት ስትሆን በሁለቱ ርቀቶች ሀገሯን ወክላ ኦሊምፒክ ላይ ትሮጣለች። በእርግጥ ከኬንያ እና ኔዘርላንድ በኩል እጀግ ፈታኝ ፉክክር እንደሚገጥማት ቢጠበቅም ከወጣቶቹ የቡድን አጋሮቿ ጋር በመሆን ሁለትና ከዚያ በላይ ሜዳሊያዎች ለኢትዮጵያ ይመዘገባሉ በሚል ይጠበቃል።

ሌላኛው የዓለም ክብረወሰወን ባለቤትና በርቀቱም ተስፋ ከሚጣልባቸው አትሌቶች መካከል የሚመደበው የ3ሺህ ሜትር መሰናክል አትሌቱ ለሜቻ ግርማ ነው። ኢትዮጵያ ከጥቂት ሜዳሊያዎች ያለፈ ስኬት ባላስመዘገበችበት በዚህ ርቀት የተገኘው ይህ አትሌት በቶኪዮ የብር ሜዳሊያን ያጠለቀ ቢሆንም፤ ከሶስት ተከታታይ የዓለም ቻምፒዮና ተሳትፎ በኋላ በመድረኩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ለራሱና ለሀገሩ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል።

በዚህ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የምትጠበቅበት ሌላኛው ርቀት ማራቶን ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች የሚኖረው ፉክክርም ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል። በሴቶች የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችውን ትዕግስት አሰፋ እና የዓለም ቻምፒዮናዋ አማኔ በሪሶ ያሉበት ይህ ቡድን በጠንካራነቱ ምናልባትም በርቀቱ ተሳታፊዎች ቀዳሚው ሊያደርገው ይችላል። በተመሳሳይ በወንዶች በኩልም የቀድሞው የኦሊምፒክ ኮከብ ቀነኒሳ በቀለ ወደ መድረኩ መመለስ እንዲሁም የኬንያዊው ድንቅ አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በአንድ ውድድር መገናኘት በአትሌቲክ ስፖርት ታሪካዊ ሁነት ተብሎም ሊመዘገብ የሚችል ነው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You