አንድ ወጣት ሶስት ጉልቻ ሊያቆም አስቦ ከህይወቱ ረጅሙን ዘመን በምርጫ ያሳልፋል። የሚያማልለውን መልክ ሲያስስ የባህሪ ነገር ያሳስበዋል፤ መልኳም ባህሪዋም የተስተካከለውን ሲያገኝ ደግሞ የሙያዋ ነገር አልሳካ ይለዋል። እነዚህን ሁሉ አሟልታለች ብሎ ያገኘ ግዜ ደግሞ ቤተሰቦቿ እሱ እንደሚፈልገው የተመረጡ ፣ የከበሩና የተከበሩ አይሆኑም። እንዲህ ግራ በመጋባት በሰፊ የምኞት ጀልባ የሚቀዝፈው ውቅያኖስ አልገፋ ሲለው የቤተሰቡ የንሰሀ አባት ወደ ሆኑት አንድ መነኩሴ ጥያቄውን፣ የጨነቀውን ሊያካፍልና መንፈሳዊ ከሆኑት ግራ ቀኙን አይተው ምክር ይለግሱኛል ብሎ ወደተማመነባቸው አባት ያመራል።
የተለመደውን ሰላምታ ሰጥቶ ቡራኬ ያቸውን ከተቀበለ በኋላ ከጎናቸው አረፍ ብሎ አይን አይናቸውን ተመለከተ።
አባ ? “አቤት ልጄ ምን እግር ጣለህ”? ጥያቄያቸው አስቀደሙ ከአፉ የሚወጣውን ለመስማት አንገታቸውን ጎንበስ አድርገው እየጠበቁ። እሱም ምን ብሎ እንደሚጀምር ግራ ገብቶት ትንሽ መሰላሉን ቀጠለ።
ወጣቱ ቀጠለ”ሚስት ላገባ ፈልጌ ነበር ?” አባት ፈጠን ብለው” እንዴ ይሄማ ጥሩ ነው፤ የፈጣሪን ትእዛዝ መፈፀም እኮ ነው።”
ወጣቱ “አይ አባ ግን ሊሳካልኝ አልቻ ለም። አባ” “ለምን ?”
ወጣቱ”እኔ የምፈልጋት አይነት ሴት ማግኘት አልቻልኩም።” አባ”አንተ ምን አይነት ሴት ነው የምትፈልገው?”
ወጣቱ ”ቆንጆ ፣ደግ ፣ የተማረች፣ ስነምግባር ያላት ፣ሀብት ያላት…” ቀጠለ ከልቡ ያለውን ፍላጎት ሁሉ ዘረዘረላቸው።
አባ ከአጎነበሱበት ቀና ብለው ”አይ ልጄ እንዲህ አይነት ሴት ብትኖር ኖሮ እኛም ባልመነኮስን ነበር”። አሉ። ይሄውልህ ሰው ሁሉ በተፈጥሮ በሁሉ ነገር ሙሉ አይደለም። በአንዱ ስታመሰግነው በአንዱ ይጎልብሃል፤ በዛ ላይ ሰዎች እኛ እንደምንፈልገው እንዲሆኑ በተመኘን ቁጥር የበለጠ ጎዶሎ ሆነው ይታዩናል። ስለዚህ አንተ በሁሉም ነገር ወደመረጥካት ለመቅረብ ራስህን አስተካክል እንጂ የተስተካከለ ለማምጣት አትሞክር። ፍፁማዊ ሰው ፍፁማዊ ህይወት የለምና ይሄን አትመኝ። አንተም በሌሎች ሰዎች ብዙ ጉድለቶች አሉብህ። ሆኖም ከሰው ጋር ለመኖር የጎደለው እየሞሉ እየተቻቻሉና እየተደጋገፉ ነው ብለው ምክር ለገሱና ሸኙት። ይህን የቆየ ትርክት ያቀርብኩላችሁ አታውቁትም ብዬ ሳይሆን ለሀሳቤ መንደርደሪያ ቢሆ ነኝ ብዬ ነው እንጂ የኔ ነገር ወዲህ ነው።
ከቀናት በፊት ነው የመሬት ካርታ ጉዳይ ለማስፈፀም በአዲስ አበባ ከሚገኝ ክፍለ ከተሞች በጠዋት የተገኘሁት። በክፍለ ከተማው መሬት አስተዳደር ቢሮ የተገኘሁት ለአምስተኛ ግዜ ቢሆንም የነበረው አካሄድ ያለጥርጥር ደጋግሜ እንደምመላለስ የሚያሳብቅ ነበር። እናም ምሬትም ተስፋ መቁረጥም መበሳጨ ትም የታከለበትን ውይይት አብረውኝ ካሉት ተገልጋዮች ጋር ጀመርን። ሁላችንም በሚሰጠው አገልግሎት ደስተኞች አልነበርንም። የየራሳችንን ችግር ውጣ ውረድ እያነሳን አሰራሩ እንዴት መስተካከል እንዳለበትም የግል አስተያየታችንን ሰነዘርን።
ትንሽ ቆይተው የተቀላቀሉን አንድ አዛውንት ግን ችግሩ ዛሬ ባሰበት እንጂ እዚህ ሀገር ሁሌም መጉላላት እንዳለ ማብራራት ጀመሩ። በንጉሱ ዘመን ከየትምና የእከሌ ልጅ ነው ካልተባለ የሚሰማህ የለም። ለእነሱ የሆነ እንደሁ የባላምባራስ ልጅ ነው፤ የነጋድራስ ልጅነው አንዳንዴም የእከሌ ዘመድ ነው ካልተባለ ጉዳይህን የሚሰማ የለም። እጅ መንሻም አቅርበህ እንኳ የምትገፋበት ግዜ ነበር።
ደርጉም ያው ነው የጄነራል እከሌ፤ የኮሎኔል እከሌ እየተባለ ማእረግ ስልጣን ካልተጠራ ከመስከረም እስከ መስከረም ብትመላለስ ዞር ብሎ የሚያይህ የለም። አቤት ለማለት እንኳ የሚፈራበት ግዜ ነበር። ይቆጡሃል፤ ትገለመጣለህ ፤ትሰደባለህ።
አሁንም ያው ነው ለስሙ ዲሞክራሲ መብት ምናምን ይባላል እንጂ ለደሀው የተረፈው ስብሰባና ወሬ ብቻ ነው። ድሮ ተቆጥተው፣ ገላምጠው፣ አገጫብረው አመት ሁለት አመት ያመላልሱ ነበር። አሁን ደግሞ ፈገግ ብለው እየሳቁ አመት ሁለት አመት ያመላልሱናል። ደግሞ እኮ እንደአህያ መልክ ሁሉም መስሪያ ቤት ያሉት ሰራተኞች በክፋት አንድ ናቸው። ሀኪም ቤት ሂድ፤ ውሃ ፍሳሽ ሂድ…. ምን አለፋህ ህዝብን በደሉ፣ አንገላቱ፣… ተብለው የተቀመጡ ነው የሚመስሉት።
አዛውንቱ ቀጠሉ፤ እስካሁን ያለችውን ኢትዮጵያን ያለበሷት ማቅ አልበቃ ብሏቸው ወደ ፊቷም ጀመሩ። እናንተ ልጆች ናችሁ ብቻ ፈጣሪ እድሜ ሰጥቶ ያሳያችሁ እንጂ የዛሬ አርባ አመትም እዚች ሀገር ምንም የሚቀየር ነገር የለም። አያያዙ ሁሉ ያስታውቃል።
አንዱ ወጣት ጣልቃ ገብቶ ከሞቀ ወሬያቸው አናጠፋቸው እርስዎ ምንድ ነው የሚሰሩት ?
አሁንማ ምን እሰራለሁ ጡረታ ከወጣሁ አስር አመት ሊሞላኝ ነው።
ድሮስ
ድሮማ ምን ያልሰራሁበት ቦታ አለ አለ መዘጋጃ ቤት ብትል፤ መብራት ሀይል ብትል፤ ውሃና ፍሳሽ ብትል ምን አለፋህ በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ዘመን ከንግድ ስራ ኮሌጅ በዲፕሎማ ከተመረቅኩበት ግዜ አንስቶ ጡረታ እስክወጣ ድረስ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ስር ያልነካሁት ቦታ ያላየሁት ጉድ የለም እያሉ በጣፋጭ አንደበታቸው ትረካውን ምሬቱን እያቀ ላቀሉ ያቀርቡልን ጀመር። እኛም ለማድ መጡ ጆሮ ሰጥተናል። ማንም ያጥፋ ማን ተወቃሹ ትውልድ እኛ አይደለን?
ወጣቱ በስጨት ብሎ አዛውንቱን አስከፍቶ ውይይቱን ለመበተን ያበቃውን ንግግር ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ።
ከተረት ውጪ ያለ ድካም ማርና ወተት የምታቀርብ ሀገር የለችም። እኔ እርሶዎን ብሆን ዲፕሎማዬን እንደያዝኩ ሀገሪቱን እለቅ ነበር። አሁንም ግን እንደማትቀየር እርግጠኛ ከሆኑ የሚሄዱበት ሌላ ሀገር ፈልገው ቢሄዱ ጥሩ ይመስለኛል። ተስፋ መቁረጥ አንድ ነገር ነው ሰውን ተስፋ ማስቆረጥ ግን ለማንም አይበጅ። ስለዚህ እያንዳንዳችን እየሰራን ብንጠይቅ ለኛም ለሀገርም ለህዝብ ይበጃል አለ። ሁላችንም በዚህ ሀሳብ ተስማማን። በያለንበት በየደረስንበት ያለፈን ታሪክ ከመተረክ አሁን በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መስራት፤ ወጣቱን ተስፋ ከማስቆረጥ ወጣቱን በተስፋ መሰነቅ፤ ስነልቦናውን ማነሳሳት፣ ሰርቶ ማሰራት… ያኔ የጎደለው ይሞላል። የሰነፈው ይንቀሳቀሳል፤ ሙሰኛው ያፍራል፤ ለዚህ ግን ሰጪም ተቀባይም እጁን መሰብሰብ አለበት ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ