ኢትዮጵያ ልክ እንደ አውሮፓና ሌሎች የዓለም ሀገራት ሁሉ ለሺህ ዘመናት በንጉሣዊ ሥርዓት ስትተዳደር ቆይታለች። በእነዚህ ነገሥታቶቿ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት እና የሀገር ግንባታ የተለያየ ቅርጽ ሲይዝ ቆይቷል። በእነዚህ ነገሥታቶቿ ታፍራና ተከብራ፣ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ኖራለች።
በዘመን ሂደት ዓለም አዲስ ቅርጽ እየያዘች መጣች። ንጉሣዊ ሥርዓት ዘመን ሊሽረው ግድ ሆነ። ባላባት እና ገባር የሚባል ነገር ዘመኑን የማይመጥን ኋላቀር ሆነ። የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጣዊ ሂደት የተለያዩ ዕድሳቶችን እየያዘ ይሄዳልና የአኗኗር ዘይቤውን ከዋሻ ወደ ቤት መሥራት፣ ከአደን ወደ እርሻና ሌሎች ሥራዎች እንደተለወጠው ሁሉ የአስተዳደር ሥርዓቱንም በዚያው ልክ እያሻሻለ፣ መብቱን እየጠየቀ መምጣት ላይ ደረሰ። በመሆኑም የፊውዳል ሥርዓት በቃህ ተባለ፡፡
በዓለም የተፈጠረው አብዮት ጊዜውን ጠብቆ ወደ ኢትዮጵያ መጣና ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን በታሪክ የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉሥ አደረገ። የንጉሣዊ ሥርዓት ታሪክ ሲነሳ ቀድሞ የሚነሳው ስም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም የመጨረሻው ንጉሥ ናቸው። ሌሎች ነገሥታት እንደየታሪክ አጋጣሚያቸው የሚነሱበት ምክንያት ብዙ ቢሆንም በንጉሣዊ ሥርዓት ታሪክ ግን ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹የመጨረሻው›› እየተባሉ ይነሳሉ። ወዲህ ደግሞ ረጅም ዘመናት የገዙ እና ረጅም ዕድሜ የኖሩም መሆናቸው ንጉሣዊ ሥርዓትን ያጎላዋል።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ የመጨረሻው ንጉሥ የሆኑት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የተወለዱበትን ሐምሌ 16 ቀን ምክንያት በማድረግ እናስታውሳቸዋለን። ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውስ።
ከ24 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 16 ቀን 1992 ዓ.ም የበርካታ የታሪክ መጻሕፍት ጸሐፊው አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ አረፉ። የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን ጨምሮ የኢትዮጵያን ነገሥታት ታሪክ የጻፉት ተክለጻድቅ መኩሪያ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በተወለዱበት ቀን አርፈዋልና ታሪካቸው በአንድ ቀን ሊታወስ ይችላል፡፡
ከ60 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 18 ቀን 1956 ዓ.ም ከአፖሎ 11 መንኮራኩር ጋር ወደ ጨረቃ ተወስዶ የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከጨረቃ ከመጣው ድንጋይ እንዲሁም ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ሪቻርድ ኒክሰን መልዕክት ጋር ለንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ተበረከተ። ሰንደቅ ዓላማውንና ድንጋዩን ከመልዕክቱ ጋር ለንጉሠ ነገሥቱ ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ነበሩ፡፡
ከ108 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 20 ቀን 1908 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እና የእቴጌ መነን አስፋው ልጅ የሆኑትና የወሎ ጠቅላይ ግዛት ገዢ የነበሩት ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ተወለዱ፡፡
ከ147 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 20 ቀን 1869 ዓ.ም ስመጥር የሙዚቃ ባለሙያ፣ ባለቅኔ፣ ቀራፂ፣ ሠዓሊ፣ ነጋዴ፣ መኪና አሽከርካሪ፣ መካኒክ፣ ፖለቲከኛ፣ ፎቶ አንሺ… በአጠቃላይ የበርካታ ሙያዎችና ተሰጥኦዎች ባለቤት የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ተወለዱ።
ከ44 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 20 ቀን 1972 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የሞስኮ ኦሊምፒክ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድርን በማሸነፍ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አደረገ።
ከ28 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 21 ቀን 1988 ዓ.ም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋጡማ ሮባ በአትላንታ ኦሊምፒክ የሴቶች የማራቶን ውድድርን በማሸነፍ ኢትዮጵያን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ማድረግና በሴቶች የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድርን ያሸነፈች የመጀመሪዋ አፍሪካዊት መሆን ቻለች።
አሁን በዝርዝር ወደምናየው የኢትዮጵያ የመጨረሻው ንጉሥ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ታሪክ እንሂድ።
ከ132 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም፤ ኢትዮጵያን ከ1910 ዓ.ም እስከ 1921 ዓ.ም በአልጋ ወራሽነትና በንጉሥነት፣ ከጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም እስከ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ድረስ በንጉሠ ነገሥትነት የመሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ተወለዱ።
አጼ ኃይለሥላሴ የመጨረሻው ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የመጨረሻው የሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት ንጉሠ ነገሥትም ያደርጋቸዋል። ምክንያቱም ከ13ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩት ሥርዎ መንግሥታት ሌላ ነበሩ። ሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት ከ13ኛው ክፍለ ዘመን (1270) እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን (1967 ዓ.ም) ድረስ ለ700 ዓመታት አካባቢ የኖረ ነው።
ሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት ከኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ እና ከእስራኤሉ ንጉሥ ሰለሞን ከተገኘው ቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ እንደሆነ በአፈ ታሪክም በጽሑፍ ታሪክም ይነገራል። ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ የነገሡ ነገሥታትም ራሳቸውን የሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት ቤተሰብ አድርገው ነበር ቅብዓ መንግሥት የሚያገኙት። ይህ ሥርዎ መንግሥት በኢትዮጵያ ለ700 ዓመታት ያህል ሲያገለግል ኖሮ፤ በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰ አብዮት በወታደራዊው ደርግ ፍጻሜውን አግኝቷል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴም የሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት የመጨረሻው ንጉሥ ተብለው በታሪክ እንዲቀመጡ ሆኗል።
የምናስታውሳቸው የልጅነት ታሪካቸውን ‹‹ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ ርምጃ›› ከተሰኘው ከራሳቸው መጽሐፍ፣ አስተዳደራዊ ታሪካቸውን ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983›› ከተሰኘው የፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ መጽሐፍ፣ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ከተለያዩ ድረ ገጾች ባገኘነው መረጃ ነው።
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ (የያኔው ተፈሪ) ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም ከሐረር ከተማ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኤጀርሳ ጎሮ በተባለች ቦታ ተወለዱ። ሕጻኑ ተፈሪ ከራስ መኮንን ወልደሚካኤል እና ከወይዘሮ የሺእመቤት ዓሊ ጋምቾ ከሐረር ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኤጀርሳ ጎሮ በተባለች ቦታ ነው የተወለደው፡፡
አባታቸው የአጼ ምኒልክ የአክስት ልጅ ናቸው። እናታቸው ወይዘሮ የሺእመቤት ዓሊ ከተፈሪ በፊት ስድስት ልጆች ወልደው የነበረ ቢሆንም፤ ሁሉም እንደተወለዱ ሞተውባቸዋል። አሁንም ሰባተኛውን ልጅ ተፈሪን ለመውለድ ሁለት ወራት ቀርቶኛል ብለው ሲያስሱ ድንገት በከባድ ምጥ ይያዙና ፈጣኑ ተፈሪ በተረገዙ በሰባተኛው ወር ይወለዳሉ፡፡
ልጅ ተፈሪ እንደተወለዱ ቤተዘመድ ‹‹እናቱ ካዩት እንደተለመደው ይሞታል›› በማለት ህፃኑን እናቱ ሳያዩት ይዘውት ይሄዳሉ። ይህ ክስተት በባህላዊ አገላለፅ ‹‹ሾተላይ›› የሚባል ሲሆን፤ ሰው ላይ ሊኖር የሚችለው ኃይለኛ የዓይን ጨረር ሌላ ሰው ላይ ሲያርፍ እስከሞት የሚያደርስ ጉዳት እንደሚያስከትል ይታመናል። በሳይንሳዊ ገለፃ ደግሞ የእናት ወይም የአባት የደም አይነት ‹‹RH Negative›› ሆኖ የሌላኛው RH Positive ይሆንና የሁለቱ ወላጆች ደም ሳይጣጣም ሲቀር የሚከሰት ችግር ተደርጎ ይገለፃል፡፡
በዚህ ምክንያት ህፃኑ ተፈሪ ከእናቱ ወዲያው መለየት ነበረበትና ከወላጆቹ ቤት ወጥቶ ዘመድ ቤት ማደግ ይጀምራል። እናቱ የህፃኑን ሁኔታ በመልዕክት ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ፤ በድጋሚ አርግዘው ነበርና ከ20 ወራት በኋላ መጋቢት 6 ቀን 1886 ዓ.ም በዚሁ በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው አለፈ። ልጅ ተፈሪ የእናትን ጣዕም ሳያውቀው ቀረ። ከህፃንነቱ ጀምሮ የአጎቱ የደጃዝማች ብሩ ኃይለማርያም ባለቤት ወይዘሮ ትሰሜ አባይርጋ ከእምሩና ከልጃቸው ጋር አሳደጉት፡፡
በዚያም ሳሉ አባታቸው ራስ መኮንን የፈረንሣይኛ ትምህርት እንዲማሩ መምህር ቀጠሩላቸውና ልጅ ተፈሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አደጉ። በ10 ዓመታቸው በ1894 ዓ.ም ከሐረር ወደ አዲስ አበባ መጥተው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአጼ ምኒልክ ጋር ተገናኝተው ተዋውቀው ተመልሰው ወደ ሐረር ሄዱ፡፡
አባታቸው ራስ መኮንን በ1898 ዓ.ም ህዳር 10 ቀን የደጃዝማችነት ማዕረግ ሰጥተው ‹‹ጋራ ሙለታ›› የተባለውን አውራጃ ሾሟቸው። ‹‹ተከታይ ልጄ ደጃዝማች ተፈሪ ነው›› ብለውም ለመኳንንቶቻቸው ይፋ አደረጉ። ልጅ ተፈሪ በ14 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ እንዳገኙ ወዲያው በ1898 ዓ.ም መጋቢት 13 ቀን አባታቸው ራስ መኮንን አረፉ።
በዚህ ጊዜ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ተፈሪን ከሐረር ወደ አዲስ አበባ አስመጥተው ደጃዝማችነታቸው እንደፀና ቀረብ የሚለውን የሰላሌን ግዛት ሾሟቸው። ተፈሪ ግን ለተሰጣቸው ግዛት ሌላ እንደራሴ ወክለው በኢትዮጵያ ብቸኛ ትምህርት ቤት በነበረው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው ሐረር እያሉ የጀመሩትን ትምህርታቸውን ቀጠሉበት፡፡
ከዚያም በ1899 ዓ.ም የባሶ በጌምድር ግዛትን፤ ቀጥሎ በ1900 ዓ.ም ሲዳሞን ተሾሙ። ከሁለት ዓመት በኋላም ሲዳሞን ትተው የአባታቸውን ግዛት ሰፊውን ሐረርጌንና አውራጃዋን እንዲያስተዳድሩ ተደረገ። የሐረርጌ ሕዝብም በደስታ ተቀበላቸው። በ1903 ዓ.ም በዚሁ በሐምሌ ወር የንጉሥ ሚካኤልን የልጅ ልጅ ወይዘሮ መነንን አግብተው መኖር ጀመሩ።
ደጃዝማች ተፈሪ በ19 ዓመታቸው ወይዘሮ መነንን አግብተው፣ በ1905 ዓ.ም የመጀመሪያ ልጃቸውን ልዕልት ተናኘወርቅን ወለዱ። ከዳግማዊ ምኒልክ ሞት በኋላ ሥልጣን የያዙት ልጅ እያሡ በ1907 ዓ.ም ደጃዝማች ተፈሪን ከሐረርጌ ግዛት ሽሯቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው እንዲቀመጡ ተደረገና ወዲያው የከፋን ግዛት ሾማቸው። ሆኖም ደጃዝማች ተፈሪ አልሄዱበትም። ተፈሪ የአውሮፓ ቋንቋ የሚያውቁ፣ ከአውሮፓውያኑ ጋር ያለአስተርጓሚ በቀጥታ የሚነጋገሩ ጨዋ፣ ዝምተኛ … እየተባሉ ቆዩ፡፡
በ1909 ዓ.ም አቤቶ ልጅ እያሱ ከሥልጣን ተወግዶ ዘውዲቱ ሲነግሡም በወቅቱ አዲስ አበባ የነበሩት ደጃዝማች ተፈሪ፣ ‹‹ራስ›› በሚል ማዕረግ አልጋወራሽ ሆነው የራስ ወርቅ አሠሩ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ንጉሠ ነገሥት እስከሆኑበት እስከ 1923 ዓ.ም ድረስ በተከታታይ ልዑል አስፋወሰንን፣ ልዕልት ዘነበወርቅን፣ ልዕልት ፀሐይን፣ ልዑል መኮንንን እና ልዑል ሳህለሥላሴን ወልደዋል፡፡
ንጉሡ እንደሚሉት፤ በልጅነታቸው እንደ ቀደሙት ነገሥታት ልጆች በቅምጥል ሳይሆን እንደ ተራ ግለሰብ ልጆች ነው ያደጉት። የእርሳቸው ልጆች ግን በቅምጥል እንዳደጉ በሌሎች ወገኖች የተጻፉና የሚነገሩ ታሪኮች ያሳያሉ።
በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈው የተፈሪ ሕይወት አሁን ወደ ንጉሠ ነገሥትነት እየመጣ ነው። መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን ተሽረው ዘውዲቲ ምኒልክ (የዳግማዊ አጼ ምኒልክ ልጅ) ንግሥት ሲሆኑ፤ ተፈሪ ደግሞ አልጋ ወራሽ ሆኑ። ከዚያ በኋላ ‹‹እጅግ በጣም ውስብስብ ነበር›› በሚባል አካሄድ ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም ‹‹ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ለ44 ዓመታት ነገሡ። ይህ ታሪካቸውም የመጨረሻው ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ረጅም ዓመት (ለግማሽ ክፍለ ዘመን የተጠጋ) ያስተዳደረ ንጉሥ እንዲሆኑም አድርጓቸዋል። አንዳንድ የታሪክ ተንታኞችም ለንጉሣዊ ሥርዓት መውደቅ ምክንያት የሆነው የእርሳቸው እስከ እርጅና ዘመን ሙጭጭ ማለት ነው እንዲሉ አድርጓል፡፡
ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርትን በማስፋፋት ይመሰገናሉ። ለዘመናዊ ትምህርትም ብዙ ተማሪዎች ወደ አውሮፓ ተልከዋል። እነዚህ በንጉሡ ጊዜ የተላኩ ተማሪዎች ሀገራቸውን ከሠለጠኑት ሀገራት ጋር በማወዳደር የንጉሡን ሥርዓት አምርረው መጥላትና መቃወም ጀመሩ። ይህን ለመግለጽ ይመስላል ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ስለዘመናዊ ትምህርት የሚከተለውን ብለዋል።
‹‹.. በንጉሠ ነገሥትነት አደራ ከተቀበልንበት ከ፲፱፻፱ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ያገሩን ውስጥ ሥራ በየጥቂቱ ለማሻሻል፤ የምዕራባውያንንም የሥልጣኔ ሥራ ባገር ውስጥ አስገብተን ሕዝባችን ወደ ትልቅ ደረጃ የሚደርስበትን በሚቻለን ሁሉ ጀምረናልና ሕሊናችን አይወቅሰንም።
በየጥቂቱ ማለት ሕፃንን ልጅ በማባበልና በማስለመድ ካልሆነ በቀር በእጁ የያዘውን ነጥቆ ቢወስዱበት ደስ አይለውም ። በማሳየትና በማቅመስም ካልሆነ ማናቸውንም ምግብ ቢሰጡት ሊመገበው አይፈቅድም ። ጥርስም እስቲያበቅል ወተት ወይም ሌላ ለስላሳ ምግብ ካልመገቡት ዳቦ ወይም ሥጋ ቢያቀርቡለት ሊመገበው አይችልም።
እንደዚሁም በትምህርት ቤት ሳይማርና በዦሮውም የዕውቀትን ነገር ሳይሰማ በዓይኑም ሳይመለከትና ሳይመረምር በልማድ ብቻ የሚኖረውን ሕዝብ ብዙ ዘመን የኖረበትን ልማዱን በትምህርት አስለቅቆ አዲስ ልማድ እንዲቀበል ለማድረግ በመቸኰልና በጭካኔ ሥራ ሳይሆን በትዕግሥትና በትምህርት በየጥቂቱ በቀን ብዛት ማስለመድ ያስፈልጋል ማለት ነው።››
ከዚህ መግቢያ ሥር ‹‹የካቲት ፲፱፻፳፱ ዓ.ም ተጻፈ።›› ይላል። 1929 ዓ.ም ገና አብዮቱ ያልተጀመረበት ነው። በተለምዶ የ60ዎቹ ትውልድ የሚባሉ አብዮተኞች የውጭ ትምህርትን በአንድ ጊዜ ካልተጋትን በማለታቸው ይወቀሳሉ። ንጉሡ የምዕራባውያንንም ሆነ የምሥራቃውያኑን ትምህርት በአንድ ጊዜ መጋት ትክክል እንደማይሆን ቀድመው አስበው ነበር ማለት ነው። ምክንያቱም ለረጅም ዘመን በልማዳዊ አኗኗር የኖረ ማህበረሰብ አንድ ጊዜ የሌላ ሀገር ባህል ቢጭኑበት ውጤታማ አይሆንም።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሤን ንግሥና እና ጥቅል መለያ ርዕዮት ከገለጹባቸው አንቀጾች የሚከተለውን ቃል በቃል እናስቀምጥ፡፡
‹‹… የተፈሪ የፖለቲካ ቁመና መለወጥ የጀመረው ግን ገና ንጉሠ ነገሥት ከመሆኑ በፊት ነው። በ1921 ዓ.ም ንጉሥ ከተባለ ወዲህ ጋዜጦችም የቀድሞ ነፃታቸው እየኰሰሰ ተፈሪን ማወደስ ጀምረዋል። ሥርዓተ ንግሡ የተፈጸመበት ጥምት 23፣ 1923 የሂደቱ ማሳረጊያ እንጂ መጀመሪያ አልነበረም። እንደዚህ ፍጹማዊ ሥልጣን ከጨበጠ በኋሳ የዘመነ መሳፍንት ቅሪቶችን የማስወገዱን ጉዳይ ሥራዬ ብሎ ተያያዘው።
ቴዎድሮስ አሐዳዊ መንግሥት ለመመሥረት ሞክሮ እንደከሸፈበት ይተናል። ዮሐንስና ምኒልክም ከዚህ ትምህርት ወስደው ነው ይመስላል ከክልላዊ አገዛዝ ጋር ታርቆ መኖርን መርጠዋል። የተናቁትንና የተጠሉትን አቀርባለሁ የሚለው ለጊዜው እንግዳ የሆነው የኢያሱ ሙከራም ዙፋኑን እስከማጣት አብቅቶታል። ከዚህ ሁሉ አንፃር ኃይለ ሥላሴ በታሪክ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ቴዎድሮስ ያለመውን አሐዳዊ መንግሥት እውን ማድረጉ ነው።
ይህም ሁኔታ ነው ከሕይወት ታሪኩ (ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ) እንደምንረዳው ንጉሠ ነገሥቱ ራሱን እንደ ፀረ ፊውዳል ታጋይ እንዲቆጥር ያደረገው። ይህም የፊውሊዝምን መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ ይዘት ካለማጤን የመጣ አስተሳሰብ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኃይለ ሥላሴ ይታገል የነበረው ፊውዳሊዝምን ለማስወገድ ሳይሆን ባንድ ወገን የንጉሡን ሥልጣን አጠናክሮ በሌላ ወገን ደግሞ የመሳፍንቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስከብሮ ፊውዳሊዝምን በአዲስ መሠረት ላይ ለማቆም ነው። በኢትዮጵያ የፍጹማዊ አገዛዝ ዓይነተኛ ባሕርይም ይኸው ሆነ፡፡››
ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 23 ንግሥናቸውን አውጀው ከስምንት ወራት በኋላ ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም የመጀመሪያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት አውጀዋል። ያም ሆኖ ግን እየዋለ እያደረ ሲሄድ የንጉሡ ሥርዓት ውጫዊና ውስጣዊ ጫና በዛበት። በተለይም ከ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ‹‹የመሬት ለአራሹ›› ጥያቄ አድጎ አብዮቱ ተቀጣጠለ። በመጨረሻም 1966 ዓ.ም ንጉሣዊ ሥርዓቱ ያለቀለት መሆኑ ታወቀ። መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ለ44 ዓመታት ያህል የኖረው የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥትነት፣ በኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት የኖረው ንጉሣዊ ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ አከተሙ። እነሆ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጨረሻው ንጉሥ ሆኑ፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም