
የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ በነሐሴ መጨረሻ ወደ ዩክሬንን እንደሚጎበኙ ተነገረ፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ በመጀመሪያ ይፋዊ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸው በቅርቡ ሩሲያ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዩክሬን እና በሩስያ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኬቭ ያቀናሉ።
ሞዲ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ባዘጋጁት የተለያዩ የሠላም ጉባኤዎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቢቀርብላቸውም ሳይታደሙ ቀርተዋል፡፡
ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሩስያ ላይ ጫና ለማሳደር እና ማዕቀብ ለመጣል በተደረጉ የተመድ እና የሌሎች የባለ ብዙ ወገን ጉባኤዎች ላይ ገለልተኛ ሆነው ዘልቀዋል።
አሜሪካ እና ምዕራባውያን በጦርነቱ ምክንያት ሩስያ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንድትገለል እንዲሁም በኢኮኖሚያዋም ላይ ጫና ለመፍጠር ላሰቡት እቅድ ሕንድ እና ቻይና እንቅፋት የሆኑ ይመስላል፡፡
የተለያዩ የአውሮፓ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት መሪዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ በዩክሬን ተገኝተው አጋርነታቸውን ሲገልጹ ሞዲ ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ አንድም ጊዜ ወደ ስፍራው አላቀኑም፡፡
በቅርቡ በሩስያ የነበራቸውን ጉብኝት ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በኤክስ ገጻቸው የዓለም ትልቁ ዴሞክራሲ ከዓለም ትልቁ ወንጀለኛ ጋር ሲተቃቀፍ ማየት ያሳፍራል የሚል ጽሑፍ አስፍረው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም በሕንድ የሚገኙት የዩክሬን አምባሳደር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በሕንድ መንግሥት ታዘው ነበር፡፡
በሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉት ምዕራባውያን ሁለቱን ሀገራት ከማቀራረብ እና ከማደራደር ይልቅ ለዩክሬን ይፋዊ ውግንናቸውን ገልጸው ጦርነቱን መደገፍ መርጠዋል በዚህ መካከል ጦርነቱ ሦስት ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ጊዜያት ቀርተውታል፡፡
የተለያዩ የዓለም አቀፍ ሠላም እና ደኅንነት ተመራማሪዎች የዩክሬን ግጭት ወደ እጅ አዙር ጦርነት ከተቀየረ መሰነባበቱን ያነሳሉ፡፡
ይህን ጦርነት ለመቋጨት የአሜሪካ እና ምዕራባውያን የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንዲሁም ተፅዕኖ የሠራ አይመስልም በመሆኑም ግጭቱ ይቆም ዘንድ ወይ እንደ ሕንድ እና ቻይና ያሉ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ላይ በጎ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ አካላት ወደ ፊት መምጣት ይኖርባቸዋል ካልሆነም ደግሞ አንዱ ሀገር እስኪሸነፍ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን ሁለቱን ሀገራትን ለማቀራረብ አድርገውት የነበረው የዲፕሎማሲ ጉዞም ከአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ሲኤንኤን ላይ ትንታኔ የሚጽፈው ሳይመን ማካርቲ ምዕራቡ የተሳነውን አልያም ችላ ያለውን የማሸማገል ሥራ ቻይና ተሳክቶላታል ሲል ጽፏል፡፡
በዚህ ሳምንት የፍልስጤም ተቀናቃኞቹን ፋታህ እና ሃማስ አብረው እንዲሠሩ እና ከግጭት እንዲወጡ ያስማማችው ቤጂንግ ከዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚተሮ ኮሊባ ጋር ተወያይታለች፡፡
በቻይና ከፍተኛ የዩክሬን ባለሥልጣን ከጦርነቱ በኋላ ጉብኝት ሲያደርግ ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ቤጂንግ እና ኒውደልሂ ሩስያ እና ዩክሬንን ለማደራደር አብረው ቢሠሩ ሁነኛ ውጤት ላይ ሊደርሱ እንደሚችል ይገመታል ለዚህም የአሁኑ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩክሬን የሚያደርጉት ጉብኝት ወሳኝነቱ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም