‹‹ያለንን ፀጋ መለየት፣ መጠቀምና መጠበቅ ከቻልን ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን›› አቶ ኡስማን ሱሩር

አቶ ኡስማን ሱሩር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለውጡን ተከትሎ በአዲስ መልክ ከተደራጁ ክልሎች አንዱ ነው። ክልሉ ከተደራጀ አጭር ጊዜ ያስቆጥር እንጂ የሚታየው የልማት እንቅስቃሴና የሚነፍሰው የሰላም አየር በአርአያነት መጠቀስ የሚችል ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዛሬው የወቅታዊ ቃለ ምልልስ አምዱ በክልሉ ስላለው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የሌማት ቱርፋትና በጥቅሉ የግብርና ልማት ሥራው ምን እንደሚመስል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ከአቶ ኡስማን ሱሩር ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮግራሞች ምን ይመስላሉ?

አቶ ኡስማን፡- ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተደራጀ ወደ አንድ ዓመት እየተጠጋው ነው። ሲደራጅ የአስተባባሪው ቀዳሚና ቁልፍ አጀንዳ የመጀመሪያው ሰላም ነው። ከዛ ቀጥሎ ግብርና ልማት ነው። የሰላማችንም የመልካም አስተዳደር ጉዳያችንም የትምህርት የጤና ጉዳይም መልስ የሚያገኘው ግብርናችንን ስናለማው እና ስናዘምነው ነው። የግብርናውን ቁልፍ አጀንዳ የሕብረተሰብ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ልማት እውን ማድረግ ነው። ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ግብርናን ማዘመን ነው ብሎ ነው የክልሉ መንግሥት በግልጽ ያስቀመጠው።

ግብርናን በማዘመን ቀድሞ ከነበረበት ኋላቀር የአሠራር፣ የአስተራረስና አያያዝ ዘዴ ወጥቶ መሬትን የላቀ ጥቅም ሊያመጣ በሚችል መንገድ ማልማትና ሕብረተሰቡን መጥቀም፤ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታም ማህበራዊ ልማትም ክልሉ የራሱን ድርሻ ከፍ ማድረግ አለበት ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ከዚህ አንጻር ግብርናችንን አዘምነን በዓመት አንዴ ከማልማት ሁለት ሦስት ጊዜ ውሃ ተኮር ግብርናን በመተግበር እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን እውን በማድረግ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማምረት አለብን ነው የገባነው። ይህን መነሻ በማድረግ በሴክተሩ አቅጣጫ ከተቀመጠ በኋላ ሴክተሩ ደግሞ ስድስት የሚደርሱ ጉዳዮችን ለይቷል።

አንደኛው ግብርናችንን አዘምነን በቴክኖሎጂ የታገዘ አድርገን የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠ ቤተሰብ መፍጠር ነው። ሁለተኛው ግብርናችንን አዘምነን ምርትን በጥራት፣ በብዛት እና በዓይነት አስፍተን ከተለመደው ውጭ የአመራረት ሥርዓት ወጥተን የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የሚል ነው።

ምን ይተካል ሊባል ይችላል። በሀገር ውስጥ ለምሳሌ አፕል ከውጭ እናስገባለን። ውሃ ልከን፣ አፈርና ሌሎች ነገሮችንም ልከን አፕል እናስገባለን። ስለዚህ ቢያንስ የአፕልን ሀገራዊ ፍጆታ መሸፈን እንችላለን። ሁለተኛው ወተት ከውጭ እናስገባለን። የወተት ልማት ሥራችንን አጠናክረን አስፍተን የወተትን ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት ማሟላት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ የድርሻችንን ሚና ማበርከትም ሌላኛው ትኩረታችን ነው።

ሦስተኛው ግብርናን በማዘመን ምርትን በብዛት፣ በጥራት እና በዓይነት ተወዳዳሪ ምርት በማምረት ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ድርሻ በማሳደግ ለአምራቹ የተሻለ ገቢ ማምጣት የሚል ነው። በዚህ ውስጥ የሥራ እድል መፍጠር ለሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ የሚል ዓላማ ነው የያዝነው።

አራተኛው ደግሞ የግብርና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በመጠቀም ዳጣ ከማዘጋጀት እስከ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ማቋቋም የሚደርስ ሥራን በገጠር ማስፋፋትና አሁን ላሉ ኢንዱስትሪዎችም ዓመቱን ሙሉ ግብዓት ማግኘት የሚችሉበትን እድል በመፍጠር ውጤታማነታቸውን ማሳደግ በሚል ነው ያስቀመጥነው።

ይህን ስንሠራ የግብርናው ዘርፍ ከግብዓት አቅርቦት እስከ ገበታ ባለው ሂደት በገጠርም በከተማም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ምንጭ ይሆናል።

በተለይ ገጠሩ ዜጎች ወደውትና መርጠውት የኑሯቸው ማዕከል፣ ሕይወታቸውም የሚቀየርበት አካባቢ ማድረግ የሚሉ እሳቤዎች አስቀምጠን ነው ወደ ሥራ የገባነው።

እነዚህን ነገሮች ደምረን ስንሠራ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በክልል ደረጃ ድህነትን ቀድሞ ያሸነፈ መንደር፣ ቀበሌ ወረዳ ብሎም ክልል ለመፍጠር አልመን ነው እየሠራነው ያለነው።

የግብርናውን ዘርፍ የሚያግዙ የተለያዩ አጋር አካላት አሉ። ሀብታቸውን ሥራ ላይ ሲያውሉ ከእነዚህ ስድስት ጉዳዮች የትኛውን ነው የሚያሳኩት የሚለውን አውቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያስፈልጋል። ይህን አውቀው እንዲገቡ የዘርፉ የልማትና እድገት ፍኖተ ካርታ ተቀምጧል።

ዛሬ ላይ አንዳንድ አርሶ አደሮቻችን ደሳሳ ጎጆ ውስጥ እየኖሩ ክረምት ሲመጣ በዝናብ የሚቸገሩ ናቸው። ነገ እነዚህ ሰዎች ምን አይነት ቪላ ቤት ውስጥ ነው መኖር ያለባቸው የሚለው ዲዛይን ተደርጓል። ዛሬ ላይ የተሻለ ኑሮ ለሚኖሩት እንዲሁ ወደ መካከለኛ ደረጃ ከፍ እንዲሉ በሞዴልነት ደረጃ የሚገኙትም ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲያድጉ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ይህን ተከትሎም አብዛኛው መሬት ወደ እርሻ እንዲቀየር ማድረግ ያስፈልጋል።

ብዙ አልሄድንበትም እንጂ አንድ ፕሮግራም ጀምረናል። አረንጓዴ፣ ድዱና የበለጸጉ አርሶ አደሮች መንደር የሚል። በመላው ክልላችን እንዲህ ዓይነት መንደሮችን ፈጥረን ገጠር ላይ ማህበራዊ መሠረተ ልማት ከተሟላ ማንም ከገጠር ወደ ከተማ የሚሰደድ የለም። ገጠሩ ተመራጭ ተወዳጅ ሊኖሩበት ብቻ ሳይሆን ሊዝናኑበትም የሚሄዱበት ቦታ ማድረግ የሚል እሳቤ ያለው ነው። በቀጣይት ትኩረት ሰጥተን የምንሠራበት ይሆናል።

የክልሉ መገኛ ከማዕከል አዲስ አበባ፣ ከድሬዳዋ፣ ከአዳማ፣ ሶዶና አርባ ምንጭንም ጨምሮ ለብዙ አካባቢዎች ማዕከል ነው። ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ስንሄድም ከጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን በቅርበት ላይ ይገኛል። ወደፊት ምስራቅ አፍሪካን የሚያገናኙ መንገዶች ሲፈጠሩ ማታ ተመርቶ ለጠዋት ቁርስ ወደ እነዚህ ሀገራት ማድረስ የሚቻልበት እድል ያለው ነው። ሕብረተሰቡም በተፈጥሮው የሥራ ባሕሉና ፍላጎቱ ከፍተኛ፣ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያለው ዝግጁነትም በጣም ጥሩ ነው።

በመሆኑም እነዚህን አስቻይ ሁኔታዎች ተጠቅመን ምን ብናመርት የተሻለ ጥቅም እናገኛለን ከሚለው ተነስተን ነው ፍኖተ ካርታውን የቀረጽነው።

ሥራዎቻችን መንግሥትን እየመራ ያለው ብልጽግና ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች የሚነሱ ናቸው። በዚህም ውሃ ባለበት አካባቢ አንድም መሬት ጦም እንዳያድርና በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠናል።

የበጋ መስኖ፣ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ አረንጓዴ ዐሻራ እና የሌማት ቱርፋት እንደ ሀገር በትልቅ ትኩረት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ናቸው። እኛ ደግሞ እነዚህን ሥራዎች በማቀናጀት የተቀናጀ የግብርና ልማት የቤተሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሠራን ነው። በርግጥ ጉዳዩ ከምግብ ዋስትና ማረጋገጥም የተሻገረ መሆን እንዳለበትም ታሳቢ ተደርጓል።

ይህም 30፣40፣30 የሚባል ኢንሼቲቭ አለ። በውስጡ ብዙ ነገሮችን ይይዛል። ሥራውም የአረንጓዴ ዐሻራ አካል ነው። የልማት ቱርፋትም አካል ነው።

በዚህ ኢንሼቲቭ መሠረት አንድ ቤተሰብ በመጀመሪያው ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40 እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት 30 የፍራፍሬ ዛፎች ይተክልና በሦስት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 100 የፍራፍሬ ዛፎች እንዲኖሩት ማስቻል ነው።

ክልሉ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተመቸ ነው። ለእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማትም ምቹ ነው። የገበያ ትስስር ለመፍጠርም የተመቸ አካባቢ ነው። ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ ልማት ስትራቴጂን በመጠቀም ሁሉንም ዓይነት የግብርና ሥራዎች በአንድ ቦታ ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

እነዚህ ልማቶች ደግሞ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ፣ ገቢ ምርትን የሚተኩና ወጪ ምርትን የሚያሳድጉ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው።

እንደ ክልል አምስት የፍራፍሬ ዓይነቶች ተለይተዋል። ደጋማው አካባቢ አፕልና አቮካዶ ይመረትበታል። በዚህም 16 አፕልና 44 አቮካዶ አምራች ወረዳዎች ተለይተዋል። በወይና ደጋና በቆላማው አካባቢ ደግሞ አቮካዶ፣ ሙዝና ፓፓያ ለይተናል። ማንጎ አምስተኛው የፍራፍሬ ዓይነት ሲሆን አንዳንድ የበሽታ ችግሮች እያጋጠሙን ስለሆነ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ ትንሽ ያዝ ተደርጓል። ሎሚ፣ ዘይቱን፣ ጊሽጣና ሌሎችም ፍራፍሬዎች ክልሉ ላይ በስፋት ይገኛሉ።

ትኩረታችን ፍራፍሬ ላይ ብቻ ሳይሆን የዶሮ ልማትም አለ። ለዶሮ ደግሞ አምስት፣ አስር፣ ሃያ አምስት የሚል ኢንሼቲቭ አለን። ምንም አቅም የሌለው ቤተሰብ አምስት ዶሮ ትንሽ ሻል ያለው አስር ከዚህ ከፍ ያለው ደግሞ ከ25 ጀምሮ አቅሙ በፈቀደው ልክ ዶሮዎች እንዲኖሩት ታስቦ የሚሠራ ሥራ ነው። ከዚህ ጋር በቅንጅት የሚሠራው ደግሞ ሦስት በሰባት የሚባል የንብ ማነብ ሥራ ነው። አንድ ቤተሰብ ሦስት ዘመናዊና ሰባት ባህላዊ ቀፎ እንዲኖረው ማድረግ ነው። በሂደት ደግሞ አቅሙን እያሳደገ ወደ ሃያ ሠላሳ እንዲያሳድግ ይደረጋል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ የተሻሻለች ጊደር ትኖረዋለች። ለዚህ ሥራ የሚሆን ደግሞ አንድ የውሃ አማራጭ ይኖረዋል።

የእንስሳት ልማት ካለ ያለ መኖ ሥራው አይታሰብም። በመሆኑም አንድ ቤተሰብ በትንሹ 250 ካሬ ሜትር፣ መካከለኛ ደረጃ ያለው ከ450 እስከ 500 ካሬ ሜትር አለፍ ሲልም አንድ ሺህ ካሬ ሜትር መኖ እንዲያለማ ይጠበቃል።

መኖው ለከብቶቹ ቀለብ ነው። የተረፈው ደግሞ ለገበያ ይቀርባል። ስለሆነም መኖው ስናለማው አካባቢ ይጠብቃል፤ ለከብቶች ቀለብ ይሆናል፤ ለገበያ ቀርቦም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ መቶ ካሬ ሜትር አትልክት ይኖራል። ለአካባቢው ተስማሚ የሆነ ቅመምም ይጨመርበታል።

ከዚህም ሌላ 40፣ 40፣ 20 የተባለ እንሰት ፕሮጀክት አለ። ይህም በመጀመሪያው ዓመት አርባ በሁለተኛው ዓመት አርባ እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት ደግሞ ሃያ እንሰት ይተክልና በጥቅሉ 100 የእንሰት ተክል ይኖረዋል።

በዚህ 30፣40፣ 30 ውስጥ ስምንት ነገሮች አሉ። እነዚህ ደግሞ የሌማት ቱርፋትንም አረንጓዴ ዐሻራንም አቀናጅተው የያዙና በጥቂት መሬት ላይ ለምተው የአንድን ቤተሰብ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ናቸው፡ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና መፍጠርንም ዓላማው ያደረገ ነው።

በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በርካታ ሥራ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጥረናል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መሬቱ ባህር ዛፍን ጨምሮ በተለያዩ ነገሮች ተይዟል። በመሆኑም ባህር ዛፍን ወደ አትክልትና ቡና የመቀየር ሥራ እየተሠራ ነው። በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተገኘበት ነው።

አንዳንዶቹ ሐይቅ ዳር ሰፊ ባህር ዛፍ ከነበረበት ሕብረተሰቡን አወያይተን አሳምነን በሙዝ ተክል የመለወጥ ሥራ ሠርተናል። ለዚህ በስልጤ ዞን ምስራቅ ስልጢ ወረዳ ስልጤ ሐይቅ ላይ የተሠራው ሥራ ትልቅ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው። ባህር ዛፉ ለሐይቁ ሳይቀር አደጋ ፈጥሮ ነበር። አሁን ላይ ግን ቦታው የተትረፈረፈ ሀብት መፍጠሪያ ሆኗል። ይህን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።

በተጀመሩ ኢንሼቲቮች ለብዙ አካባቢዎች አዳዲስ ምርት ማስተዋወቅ ተችሏል። ሀላባ የሚታወቀው በበርበሬ ነበር። አሁን ግን በሙዝና በሐብሐብ በደንብ መታወቅ ጀምሯል። ቀደም ሲል ሐብሐብ ከጂቡቲ ወይም ከጂግጂጋ ነበር የሚመጣው። አሁን ላይ ግን ሀላባ፣ ስልጤና ጉራጌ አካባቢ በስፋት ይመረታል። አዳዲስ ምርቶች በአዳዲስ አካባቢ ማምረት ተችሏል።

ፓፓያም ከዚህ በፊት በማይታወቅባቸው 24 ወረዳዎች ውስጥ ማምረት ተጀምሯል። ለብዙዎች የሀብትና ሥራ እድል መፍጠሪያ እየሆነ ነው። በጥቅሉ ግብርና ማደጊያ፤ መበልጸጊያ ነው የሚል ትልቅ የአመለካከት ለውጥ መጥቷል።

በወጣቶች ዘንድም ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ መጥቷል። ዓይናችን ተጋርዶ ነበር። አዳዲስ ሃሳብ መጥቶ ዓይናችንን ገልጦታል። ይህ ደግሞ ጸጋችንን እንድናውቅና እንድናለማ ምክንያት ሆኖናል እያሉ ነው።

የተማሩ ወጣቶች ሰብሰብ ብለው ኢንተርፕራይዝ ፈጥረው ወደ አትክልት ልማት በመግባት አዳዲስ ምርቶችን እያመረቱ ነው። ለምሳሌ ጉራጌ ላይ ያየነው አምስት ወጣቶች ከ120 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል። ይህ የሚያመላክተው ግብርናን በአግባቡ ከመራነውና ከሠራነው የሀገሪቱ የማደግና የመበልጸግ ተስፋ መሆኑን ነው።

ያለንን ፀጋ መለየት፣ መጠቀምና መጠበቅ ከቻልን ድህነት ታሪክ የሚሆንት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። በየደረጃው ያለው አመራር ባለቤት ሆኖ የተጀመሩ ሥራዎችን በቀጣይነትም አጠናክረን መሄድ ከቻልን ከነበርንበት ድህነት ወጥተን ወደ ብልጽግና ማማ መውጣት እንችላለን።

በጥቅሉ ስናየው በሴቶች፣ በወጣቶችና በአርሶ አደሮች ዘንድ የሚታየው ሠርቶ የመለወጥ ተስፋ ነው። በሴቶች ላይ የተጀመሩ የሌማት ቱርፋት ሥራዎች በጣም የሚያበረታቱ ናቸው።

እንደ ሀገር የሌማት ቱርፋት አምስት ነገሮችን ይይዛል። እነዚህም እንቁላል፣ ወተት፣ ሥጋ፣ ማርና ሰም እንዲሁም ዓሣን ያካትታል። በእኛ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ዘጠኝ ነገሮችን ይዟል። እነዚህም አትክልት፣ ሥራ ሥር፣ እንሰት፣ ፍራፍሬ አክለንበታል። አንድ ሰው ከአስሩ ቢያንስ ስድስቱ ሊኖሩት ይገባል ብለን ነው እየሠራን ያለነው።

በዚህ ሂደትም በርካታ የዶሮ፣ የንብ፣ የወተትና የሙክት መንደሮችን መፍጠር ተችሏል። የተገኙ ውጤቶችና የታዩ ለውጦች ብዙ ወጣቶችን ያነሳሱና እስካሁን የት ነበርኩ የሚል ቁጭት የፈጠሩ ናቸው።

በተለይ ሀላባ ዞን ላይ የሌማት ቱርፋት ትግበራ ከአመራሩ ነው የተጀመረው። በዚህም ብዙ አመራርና ሠራተኞች የዶሮ ባለቤት ሆነዋል። ብዙ ሰዎች ወደ ዶሮ ልማት ሲገቡ ለሌሎች ደግሞ ዶሮ ቤቶችን በመሥራት የሥራ እድል አግኝተዋል። አንድ ሥራ ስንሠራ ሌላ እድል እየፈጠረ ይሄዳል ማለት ነው።

የወተት መንደሮችን ስንመለከት በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠርም እየተፈጠሩ ነው። ብዙ ወተት በተመረተ ቁጥር ደግሞ የወተት ማቀነባበሪያ ፍላጎት እየተፈጠረ ነው። ለዚህ ምላሽ የሚሆኑ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው። መጀመሪያ ላይ አይብ፣ ክሬምን እርጎን ማምረት ይቻላል። በቀጣይነት ደግሞ ወደ ዱቄት ወተት መሄድ ይኖርብናል በሚል ነው እየተሠራ ያለው። ይህ ደግሞ ገቢ ምርትን ይተካል፤ ወጪ ምርትንም ያሳድጋል።

ዓሣ ላይ ሥራዎች ተጀምረዋል። ነገር ግን ከሌሎች ሥራዎች አንጻር ገና ነው። ወደፊት አጠናክረን የምንሄድበት ይሆናል። ሌሎቹን በማቀናጀት ከፍራፍሬ፣ ከአትክልት፣ ከሥራ ሥር እና ከእንሰት ጋር እየሠራናቸው ያሉ ሥራዎች በጣም ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል። ፡ አንዳንዶቹ ከጠበቅነውም በላይ ውጤት የተገኘባቸው ሆነዋል።

እንደ ማሳያ ብናነሳ ሀላባ ዞን ላይ ፍል ውሃ አለ። ለዘመናት ውሃው፣ ባለሙያውና አመራሩ ነበር። ነገር ግን እዚህ ግባ የሚባል ጥቅም እየሰጠ አልነበረም። አሁን ላይ በተፈጠሩ የአመለካከትና እይታ ለውጦች መሰል ሀብቶችም ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል። አንድ ባለሀብት ውሃውን ወደ ኩሬ ወስዶ ካቀዘቀዘ በኋላ አትክልት እያለማበት ነው። በዚህ ሂደትም ለራሱ ሀብት ከመፍጠር ባሻገር ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። ገበያው ላይ የነበረውን ጫናም በብዙ እንዲቀንስ አድርጓል።

የሌማት ቱርፋት ሲመጣ ዕይታችንን ለውጦታል። በዚህም አትክልትና ፍራፍሬ ለምቶባቸው በማያውቁ አካባቢዎች ጭምር ትልልቅ ውጤት እየተገኘ ነው።

በዚሁ በሀላባ ዞን ውስጥ ሲምቢጣ የምትባል ቀበሌ አለች። የምትታወቀው በችግር ነበር። ለዞኑ፣ ለክልሉና ለሀገርም እዳ ነበረች። ዝናብ በመጣ ቁጥር ጎርፍ የሚያጠቃው ትልቅ ችግር የነበረበት አካባቢ ነበር። አሁን ግን የምርጥ ተሞክሮ ማስተላለፊያና የበለጸጉ አርሶ አደሮች የተፈጠሩበት ቀበሌ ሆኗል። ይህ ሌላ አካባቢ ያሉ ቀበሌዎችንም አነሳስቶ ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ አድርጓል።

በጥቅሉ ስንመለከተው በመንግሥት በተቀመጡ ፖሊሲ አቅጣጫዎች መነሻነት የክልላችን መንግሥት ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ድህነትንም በቤተብ፣ በመንደርና በቀበሌ ደረጃ ለማሸነፍ የጀመርነው ጉዞ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው። ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን።

አሁን ላይ የፈጠርናቸው ፍላጎቶች አሉ። እየሠራን ያለነውን ሥራ ተከትሎ በርከት ያሉ ፍላጎት መጥተዋል። አንዱ ፍላጎት ገበያ ነው። ሁለተኛው ፍላጎት ግብዓት ነው። ለምሳሌ እንስሳት ላይ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህ ደግሞ በግብዓት የሚያስፈልጉ ነገሮች አሉ። የባለሙያዎችን ክህሎትና ተደራሽነትን ማሳደግም ይጠበቃል።

ከዶሮ ልማት ጋር ተያይዞ ደግሞ የዶሮ መኖ ፍላጎት በእጅጉ ጨምሯል። የፋይናንስ አቅርቦትና ቴክኒካል ድጋፍ የማቅረብ አቅማችንም ማደግ ይኖርበታል። ስለሆነም አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ግብዓትና ድጋፍ የማቅረብ አቅማችንን ማሳደግ ነው። ምክንያቱም መኖ የሚቀርብበትና እንቁላል የሚሸጥበት ዋጋ ተመጣጣኝ አይደለም። የመኖ ዋጋ በጣም ውድ ነው። ስለሆነም በሁሉም መስክ እሴት የመጨመር አቅማችን ማደግ አለበት።

በቀጣይ መሥራት ያለብን የቤት ሥራ እንዳለ ሆኖ አጠቃላይ ጉዟችን ግን ተስፋ ሰጪ ነው። ድህነት ሊሸነፍ የሚችልበት ጊዜም ሩቅ እንደማይሆን ርግጠኛ መሆን ይቻላል። ነገር ግን ሥራው እምነት፣ ጽናትና ትጋት ይጠይቃል። እምነት፣ ጽናትና ትጋት ከሌለን ግባችንን ማሳካት አንችልም።

አሁን ላይ ተስፋ ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ ውጤት እጃችን ላይ አለን። ይህን መነሻ በማድረግ በቀን ቢያንስ 15 ወይም 16 ሰዓት መሥራት ከቻልን ድህነትን ማሸነፍ የምንችልበት እድል ሰፊ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የለውጥ አመራር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ያለው አንዱ ጉዳይ የአረንጓዴ ዐሻራ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ በክልሉ ያለው አተገባበር ምን መልክ አለው?

አቶ ኡስማን፡- የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራችን በጣም ውጤታማ ነው። ውጤታማ ያደረገውም ሕብረተሰቡ አምኖበት በሰፊው እየተሳተፈ በመሆኑ ነው። በክልላችን አረንጓዴ ዐሻራ ሁለት ገጽታ አለው። አረንጓዴ ዐሻራ በሁለት መልኩ ነው የምናከናውነው። የመጀመሪያው የወል መሬትና ተራሮች ባሉበት አካባቢ ዓላማ ተኮር የሆኑ ደኖችን እናለማለን። ዓላማ ተኮር ስንል ዓላማው ለማገዶ፣ ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት አልያም ለአካባቢ ጥበቃ ሊሆን ይችላል።

በዚህ መነሻነት ቀርቀሃን ጨምሮ ከላይ ለተገለጹት ዓላማዎች የሚውሉ ደኖችን እያለማን ነው። በዚህም የተራቆቱና ከአገልግሎት ውጭ ሆነው የነበሩ መሬቶች አገግመዋል። መሬቱ በመራቆቱ ምክንያትም ከታች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ስጋት ውስጥ ይጥሉ የነበሩ አካባቢዎችን ችግር መፍታት ተችሏል። አስቀድመን የተፋሰስ ሥራዎችን ሠራን በመቀጠልም እርከን የመሥራትና የመትከል ሥራውን እያስከተልን ውሃው ባለበት እንዲቀር ማድረግ ተችሏል።

አፈሩ ባለበት ቀርቶ በተለይ የወል መሬቶች ለተደራጁ ወጣቶች ፍራፍሬና አትክልት እያለሙ የሀብት መፍጠሪያነት እያገለገለ ይገኛሉ። ከወል መሬት ውጭ ያሉ ቦታዎችንም በአብዛኛው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ተክሎች እንዲሸፈኑ እያደረግን ነው። ክልሉ ባስቀመጠው የ30፣ 40፣ 30 ንቅናቄ ጋር በማስተሳሰር ሕብረተሰቡ በባለቤትነት እየፈጸመው ይገኛል።

በተያዘው ዓመት በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት 147 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደን 219 ሺህ ሄክታር መሬት ማሳካት ችለናል። በሥራው ላይም አንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ተሳትፈዋል። ከዚህ ውስጥ 49ነጥብ5 በመቶው ሴቶች ናቸው።

አረጋውያን፣ ሴቶች፣ ሕፃናትና ሌሎችም ማህበረሰብ ክፍሎች በንቃት ተሳትፈዋል። ማንም ቀስቅሷቸው ሳይሆን ጥቅሙን በማየታቸው በባለቤትነት ነው እየተሳተፉ የሚገኙት። የተራቆቱና ነዋሪዎችም ለስደት ይዳረጉባቸው የነበሩ አካባቢዎች አሁን ለም ሆነዋል።

ይህን ሥራ አጠናክሮ ለመቀጠል በዚህ ዓመት እንደክልል ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅቷል። ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ኢኮኖሚዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ናቸው። ይህም ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ መኖና እንሰትን ያጠቃልላል።

ለተከላ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል። 40 ሺህ 902 ነጥብ 34 ሄክታር ፖሊጎን ካርታ ማዘጋጀትና 245 ሚሊዮን 341 ሺህ 46 ጉድጓዶችን ማዘጋጀት ሥራም ተከናውኗል። አሁን ላይ ዝም ብሎ ጉድጓድ መቆፈር ሳይሆን የትኛው ቦታ ላይ ምን ያህል ችግኝ እንደተተከለ የሚያመላክት ሳይንሳዊ አሠራርን የተከተለ ነው የሚሆነው። ለአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላም ቦታዎችን የመምረጥ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

ጥቅምት መጀመሪያ ላይ የተቀናጀ የግብርና ልማት ንቅናቄ አካሂደን ነበር። ንቅናቄው የተካሄደው የተለያዩ ጉዳዮችን ታሳቢ አድርጎ ነው። የመጀመሪያው አረንጓዴ ዐሻራ ነው። በዚህ የተከልናቸውን ችግኖች መንከባከብ፣ ለዘንድሮ ተከላ ዝግጅት ማድረግን ያጠቃልላል። በበልግ ወቅት በተከናወነ ንቅናቄም 10 ሚሊዮን ቡና ጨምሮ 14 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።

በአጠቃላይ አረንጓዴ ዐሻራችን የሕብረተሰቡን የመኖርና የማደግ ተስፋን እያለመለመ ነው። በቀጣይነትም ሁላችንም በባለቤትነት የምናከናውነውና አጠናክረን የምንቀጥለው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ላይ ያለው ሰላም ለልማት ሥራዎች መሳካት የነበረው ሚና እንዴት ይገለጻል? በቀጣይነትስ ይህን ሰላም አጽንቶ ከመቀጠል አንጻር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ኡስማን፡– ክልሉ ሲመሠረት የአስተባባሪው የመጀመሪያ አጀንዳ የነበረው ሰላም ነው። ሰላም ከሌለ የግብርና ልማት የለም። ትምህርት፣ ጤናና ገቢ አይኖርም። ስለዚህም ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥተን የተንቀሳቀስነው ሰላም ላይ ነው። ይህን ስናደርግ ደግሞ የሰላሙ ባለቤትም ጠባቂም ሕብረተሰቡ መሆን አለበት። ሕብረተሰቡን ባለቤት ማድረግ አለብን ብለን ነው የገባነው።

በዚህ መነሻነት እዚህም እዛም የሚነሱ በሕብረተሰቡ መካከል ያለውን የእህትማማችነትና ወንድማማችነት፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚሸረሽሩ ነገሮችን በሚያራምዱ አካላት ላይ የማያዳግም ርምጃ እየወሰድን ነው።

ለምሳሌ ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው በሕዝቦች መካከል ቁርሾን የሚፈጥሩ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ የሚያደርጉ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚሰብኩ አካላትን የማስተማር እና አልታረም ያሉ የዚህ እኩይ ተግባር አንቀሳቀሾች ላይም ርምጃ የመውሰድ ሥራ ተሠርቷል።

ሕብረተሰባችንም በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። ሰላም ካለ ኢኮኖሚያዊም ማህበራዊ ልማትንም ማሳካት ይቻላል። ሕብረተሰቡ ለዚህ ባለቤት እንዲሆን የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። በቀጣይነትም ይህንን ልማታችንን እያጠናከርን የክልሉንም ሰላም አጽንቶ የመቀጠል ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ በጣም እናመሰግናለን።

አቶ ኡስማን ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You