አዲስ ላይ ኑሮ ተወዷል፤ ሸገር ላይ ህይወት ከብዷል። መዲናችን ለኔ ቢጤ ድሃ ጥሩን ለብሶ ማጌጥ ድንቁ፤ እህል ጎርሶ ማደር ብርቁ ሆኗል። ወገን በወገን ላይ ጨክኗል። ነጋዴው ደንበኛው (ሸማቹ) እንጀራው መሆኑን ረስቶ ዛሬ ኪስህን ካላጠብኩ እንቅልፍም አይወስደኝ፤ ተኝቼም አላድር ብሏል።
ከገበሬው 1 ሺህ 500 ብር የገዛው ጤፍ ከተማ አምጥቶ ከ3,500 ብር ፍንክች አልልም ይላል። “ምነው ወዳጄ! ይሄ ደግም አይደል እንተዛዘን እንጂ ይሄን ያህል መጨካከን ተገቢ ነው?” ስትለው “ዶላር ጨምሮ ነው። ምን እናድርግ?” ይልሃል። ጤፉን በውጭ ምንዛሬ ከሩቅ ምስራቅ አስጭኖ ያስመጣው ይመስል። ነጋዴው ሸምሱ ከወይዘሮ ጫልቱ በ100 ብር የገዛው ቅቤ በ300 ብር መሸጡ ከዶላር መጨመር ጋር ምን አገናኘው? በሞቴ እስቲ አስረዱኝ።
ነጋዴዎች ኧረ ተዉ! ወዴት እንሄድባችዋለን? ቀስ እያላችሁ ብትነጥቁን አይሻልም? ከበረገግን እኮ ለእናንተም መጥፎ ነው። የኛ ገቢ አድሮም ውሎም መድረሻው ወደ እናንተው ነው፤ ምን መሄጃ አለው ?
ቆዩማ! እጀራችሁ እኛ መሆናችንን እየዘነጋ ችሁ ይሆን እንዴ? እኛ ከሌለን እናንተስ በምን ታድራላችሁ? ሰው እንጀራውን ይገፋል? እንጀ ራው ላይ ይጨክናል? ጭካኔያችሁ ደግሞ መክ ፋቱ ደግማችሁ እንዳትደርሱብኝ የማለትን ያህል “ስንት ነው?” ብለን ስጠይቅ ለመቁጠር ቀርቶ ለመጥራት የሚከብድ የገንዘብ መጠን መንገራችሁ አያስተዛዝበንም?
ለኛ ባታዝኑ ለወገን ባትራሩ እንኳን ይሄ ለኛ ብረቅ የሆነው ገንዘብ እንዴት ነው የናቃችሁት? ቢያንስ ያስከበራችሁ ያህል ክብር ሰጥታችሁት አብሮዋችሁ እንዲቆይ ብታደርጉ አይሻልም? ገንዘብ አንዴ ካኮረፈ አኮረፈ ነው እንደኛ መሄጃ ያጣ አይደለም ጥሎዋችሁ እብስ ይላል።
ንገሩኝማ ውድ ነጋዴዎች የወገንስ ኪስ ማጠብ፤ ያለአግባብ በትርፍ ላይ ትርፍ መሰብሰብ እንደው ደስታን ያጎናፅፍ ይሆን? እኔ አይመስለኝም። እውነተኛ ደስታ የራስን አሳልፎ ከመስጠት ጋር የሚያያዝ በመቸር የሚገኝ ልዩ ጉዳይ ነው። ይህ በድርሰት አለም ውስጥ የሚሰበክ አይደለም እውን ነው። እውነተኛ ደስታ በውስጣችን ለመፍጠር ቀድመን ማስደሰትን እንወቅ። እናም ነጋዴዎች ለወገን ማሰብ መልካም ነው፤ እንተሳሰብ። የደንበኛዬን እድሜ ያቆይልኝ ገቢውንም ያሳድግልኝ እያላችሁ ፀሎት አድርጉ እሱ ነው የሚያዋጣችሁ።
የኔ ቢጤ ለፍቶ አዳሪዎች በነጋዴዎች የተፈጠረብን ጫና እያንገዳገደን ነው። እንደኔ አይነቱማ ብቻ መኖሩ አልቻል ሲለው አጋር ፍለጋ መባዘን ጀምሯል። ኣኣ..አጋር ያልኩት ትዳርን አይደለም ወዳጆቼ እሱማ አከራዮች ማቀብ ጥለዋል! መባሉን ሰምቶ የማግባት ሀሳቡን ተከራይ ሰርዟል። አከራዮች ለባለ ትዳር አናከራይም ለላጤ እንጂ ብለዋል አሉ። ጉድ ነው ላጤ አድርገው ሊያስቀሩን እኮ ነው።
እናም የማወራው ከትዳር ውጪ የሆነ ደባልነትን ነው። እናላችሁ እኔና የኔ ቢጤው የኑሩን ዳገት ለብቻ አልገፋ ቢለው አብሮ የሚያጋፋው መላ በመዘየድ ላይ ነው። እኔም ከሌሎች ጋር አብሮ በመሆን ኑሮን ለማሸነፍ አሰብኩ።
መኖር ቢያቅተኝ ጓደኞቼን ጠራው ለመመካከር፤ እንደው ምን ይሻል ይሆን ብሎ ስለ መፍትሄው ለማውራት። እነሱም እንደኔው ከጫፍ ደርሰው ነበርና “ባንድ አፍ!” አሉኝ። ሀሳቤን ቅዱስ ብለው ተቀበሉት።
እናም ኑሮው ትንሽ ቢቀለን ብለን አንድ ላይ በመኖር ወጪም ለመጋራት ተስማማን። አራት ባራት በሆነች አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ለመኖር። አራት ነን በአንድ ቤት የምንኖር፤ አንድ ክፍል የምንጋራ፤ መሆን ሳንፈልግ የኑሮ መወደድ ያቆራኘን፤ ነፃነታችንን ማወጅ እየፈለግን ችግር ያዋደደን ጓደኛሞች።
አስማተኛ ሆነን ምናዘግምባት አዲስ አበባ (የምናወጣው ወጪ ገቢያችንን ስለሚበልጥ አመጣጡ እንዲሁ ግርም ስለሚለኝ ነው)፣ ኑሮን ማየት እንጂ ማኖር በማትፈቅደው በዚህች ጉደኛ ከተማ አዲስ አበባ (ለደሃ ማለቴ ነው) አንዱን በጠኔ ክርችም ሌላውን በተቃራኒው በቁንጣን በምታጨናንቀው አዲስ አበባ እንኖራለን ኣኣ…ተሳሳትኩ እንኖራለን ነው ያልኩት ማለቴ እናኗኑራለን።
ሰሞኑን ብርድም አይደል? ሲበርደን አንድ ሀሳብ መጣልንና ጃኬት ለመግዛት ተስማማን። አንድ ጃኬት ለአራት ነው። እንግዲህ ለመግዛት ያሰብነው። አንድ ጃኬት ለአራት በተራ ለመልበስ። በአንድ ጃኬት በተራ ለአራት ለማጌጥ። አራታችንም በጃኬቱ መገዛት ላይ ድምፅ ለመስጠት ተሰባሰብን በሙሉ ድምጽ ጸደቀና በመዋጮ ተገዛ።
በነገራችን ላይ የኛ ቤት ይለያል። አንድ ሰው ቢጎልም ምላዕተ ጉባዔው ስለተሟላ ስብሰባው ይደረግ ወይም ድምፅ ይሰጥ የሚለው ፍልስፍና እኛ ቤት አይሰራም። ምክንያቱም የጎደለው ሰው ሙሉ የቤቱ አባል ካልተሟላ ምንም ርእስ ተነስቶ ውይይት አይደረግበትም። ምክንያቱ ብዙውን ጊዜ የምንወያየው በመዋጮ ጉዳይ ስለሆነ ስብሰባው ላይ ያልተገኘው አላዋጣም እንዳይለን በመስጋት ነው።
እኔ ነኝ ጃኬቱ እንዲገዛ ሀሳብ ያቀረብኩ። ምክንያት ስጠየቅ አንድም ብርድ ነው በሚል ሁለትም አብሮን በተማረ የሌላ መስሪያ ቤት ሰራተኛ (ጥሩ ደመወዝ የሚከፈልበት መስሪያ ቤት የሚሰራን ሰው ጠቅሼ) ተለብሶ ማየቴን እንዳማረበትና እኛም በዙር ቢያምርብን ብዬ መሆኑን አስረዳሁ።
“አዎ እኛ ከሱ በምን እናንሳለን አራት ሆነን መግዛት እንዴት ያቅተናል።” በሚል ፉከራ ይገዛ ተባለ። “አዎ በእርግጥ በደመወዝ እንጂ በጋራና በፍቅር በመኖርም እኛ የተሻልን ነን” አንዱ ጓደኛችን የጃኬቱ መገዛት እርግጥ እንዲሆን ለማፅናት በዛቻ መሰል መልክ ያሰማው ፉከራ ነበር።
በዚህ እልህ የተገዛው ጃኬት ለመልበስ እጣ ወጣና ለገረመው ደረሰው። በመዋጮ ለአራት የተገዛው ጃኬት የመጀመሪያ ሳምንት የገረመው ማጌጫ ሊሆን በቃ። ድምጽ የሚከበርበት ቤት ነውና ጸደቀለት። አይናችን እያቁለጨለጭን ፈቀድንለት። ኦ በነገራችን ላይ ይቅረታ ጓደኞቼን (ደባሎቼን) ሳላስተዋውቃችሁ። የኛ ቤት ልዩ ነገር የሁላችንም ስምና ባህሪ መመሳሰሉ ነው፤ ካንዱ በቀር። ጓደኞቼ ስማቸውና ባህሪያቸው በትንሹ ልንገራችሁ።
ዜና፡- ቤታችንን በመረጃ ሙሉ የሚያ ደርግልን ጓደኛችን ነው። እኛ ቤት የመረጃ ችግር የለም። ዜና ባይኖር ከመረጃ ርቀን ቀርተን ነበር። ሬድዮ የለን፤ ቴሌቪዥን የለን። እናም ዜና መረጃዎችን እያነፈነፈ እንደ ጉድ ያዘንብልናል። ችግሩ ዜናዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ሲግናላቸው በተበላሸ ሳተላይት ቲቪ እና ጣቢያቸው ባልተሰናሰለ ሬድዮ እየሰማ ነው መሰለኝ የተሟላ መረጃ አይነግረንም። ብዙው ዜና ጀምሮ ይተወዋል። ለነገሩ እኛም አሟላ ብለን አናስጨንቀውም። ባልተሟላ ኑሮ የተሟላ መረጃ ምን ያደርጋል።
ገረመው፡- አቤት ነገሮች ሁሉ የሚገርሙት ሰው፤ ገረመው መገረም ዋንኛ ስራው ነው። በአንደኛው ጓደኛችን የሺጥላ የሺጥላ ተብሎ እራሱን እንኳን ማስጠለል ተስኖት ከኛ ጋር ተጠግቶ መኖሩ ያስገርመዋል፤ በእኛ ደህነትና በቢል ጌት ሀብታም መሆን ይደነቃል፤ በኤሊ መንቀርፈፍና በዩዜን ቦልት ፍጥነት ሲደነቅ፤ በጨርቆስና በቦሌ ልጆች የኑሮ ልዩነት ሲመሰጥ ብዙ ጊዜውን ይፈጃል። እኛም እየተመለከትነው ባለነው የገረመው መገረም ይገርመናል። አንዳንዴ ሳስበው ገረመው ለመገረም የተፈጠረ ሁሉ ይመስለኛል፤ ተገራሚው ገረመው።
የሺ ጥላ ምስኪን ራሱን የማይችለውን ሰው የሺ ሰው ጥላ አሉት። እኔም እንደገረመው በየሺ ጥላ በጣም እገረምበታለሁ። አራት ወራት በጋራ ስንኖር አንድ ቀን ምግብ የማብሰል ተግባር ብቻውን ተወጥቶ አያውቅም። አድርግ የተባለውን ሁሉ ገረመው እስኪገርመው ድረስ አልችልም ብሎ ያልፋቸዋል። ለነገሩ እሱ ምን ያድርግ ቤተሰቦቹ ናቸው የማይችለውን ያሸከሙት።
እኔን ጓደኞቼ በሰኔ ይሉኛል፤ ሰኔን አልወደውም፣ ደጋግሞ ሰኔ ላይ መጥፎ ገጠመኝ ስለገጠመኝ ሰኔን እጠላለው። ከ13ቱ ወራት ሰኔን ቀንሰው አኔን ከመሳቀቅ ቢታደጉኝ እላለው። ምንም ነገር በሰኔ ቢጠይቁኝ እለፉኝ ባይ ነኝ። ጓደኞቼም በሰኔ ያሉኝ ለዚያም ነው። በቃ እኔ እና ሰኔ እንዲህ ነን፤ የተወለድኩት በሰኔ ነው። ምን አልባትም እንትን የምለው በሰኔ ይመስለኛል። እንትን ያልኩት አስፈሪ ቃል ሰኔ ላይ ማውራት ስለማልወድ ይቅርታ እለፉኝ ሰኔ ባይሆን ኖሮ አወራችሁ ነበር። ለዛሬ ይብቃኝ ሰላማቹሁ ይብዛልኝ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2011
ተገኝ ብሩ