የአለምን ኢኮኖሚ በበላይነት የተቆናጠጠች ሀገር አሜሪካን ባልታሰበና ባልተጠበቀ መልኩ ብቅ ብለው አለምን ሲያነጋግሩ አሜሪካዊያንን ሲያነታርኩ የቆዩ መሪዋን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመረጠችው እአአ በ2016 ነበር።
አነጋጋሪው ሰው ድጋሚ ሀያልዋን ሀገር “አሜሪካ ለመምራት ዝግጁ ነኝ፤ በቀጣይ አመት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ለፕሬዚዳንትነት በድጋሚ እወዳደራለሁ።” ማለታቸውን ተከትሎ አለም የቆዩበትን መዘርዘርና መፃኢ ቆይታቸውን መተንበይ ተያይዞታል። የሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በፍሎሪዳ ግዛት ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ለደጋፊዎቻቸው ለ2020 ምርጫ ዝግጁ እንደሆኑና ዳግም እንዲመረጡ ጠይቀዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ እና በባለቤታቸው ቀዳማይ እመቤት ሜላንያ ትራምፕ ታጅበው በምርጫ ወቅት በትንሽ የድምፅ ልዩነት ያሸነፉበት ግዛት ፍሎሪዳ የተገኙትና የምርጫ ቅስቀሳቸው ከወዲሁ የጀመሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ዘወትር እንደ ሚያደርጉት ፓሪቲያቸው ሪፐብሊካን የሚቀና ቀነው ዲሞክራቶችን “እነርሱ ሀገር ሊበታትኑ የተዘጋጁ” ናቸው በማለት አጥላልተዋል።
በዚህ ቅስቀሳቸው ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የፕሬዚዳንቱ አድናቂዎች ተገኝተው ድጋፋቸው የሰጡ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ቅስቀሳ ካደረጉበት አካባቢ ብዙም ሳይርቅ የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሰልፈኞችም ነበሩ። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የአሜሪካንን ጠንካራ የምጣኔ ሀብት ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ፣ህገ ወጥ ስደተኞችን ከሀገራቸው እንደሚያባርሩና ሀገራቸውን በተለያየ መስክ የሚገዳደሩ ሀገራት ድል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ድጋፍን ከተቃውሞ ጋር ተቀብለው ሲሸኙ የከረሙት ሰው ምርጫውን ድጋሚ ያሸንፉ ይሆን ወይስ በፕሬዚዳንትነት የከረሙበትን ነጩ ቤተ መንግስት ተሰናብተው የአራት አመት ቆይታቸወን በመቋጨት ይሰናበቱ ይሆን የሚለው ትንቢያና መላምት በአለም ሚዲያዎች በስፋት እየቀረበ ይገኛል።
ሰውዬው ያሻቸውን ተናጋሪ የሚፈልጉትን አድራጊ ናቸው። ለዚያውም ስሜት የተቀላቀለ በት ውሳኔና ብዙዎችን “ምን ነካቸው እኚህ ሰው?” የሚያስብሉ። ሰውዬው እስከአሁን በቆዩበት የስልጣን ዘመናቸው የአሜሪካ ኢኮኖሚ እንዳይንገታገት በማድረግ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል፣የስራ እድሎችን በመፍጠር ብዙ ሰርተዋል ቢባልም እጀ ረጅም የሆነችው ሀገር በየአቅጣጫው የዘረጋችው እጆችዋን በወጉ ተጠቅማ የአሜሪካንን ጥቅም በማስጠበቁ በኩል ፕሬዚዳንቱ ነጥብ ያስጣሉ ጉዳዮች ተብሎ ተቀምጧል።
ያኔ የይምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ ሲጀምሩ ያቀርቡት የነበረው ሀሳብ በአለም መገናኛ ብዙሀን መብጠልጠል ጀመረ። ሰውዬው ወይ ፍንክች አቋሜ የማያወላዳና ፅኑ ነው በማለት ሞገቱ። ‹‹አሜሪካዊያን አሜሪካዊያን ናቸውና ጅምር ላይ ልክ ኖት›› ያሉ ውስን ተከታዮችን አፈሩ። እውን ጤነኛ ሰው ይሄን ያደርጋል? በብዙዎች የተሰጠባቸው ትችት ነበር። የሰው ልጆችን በቀለምና በእምነት ከፍሎ “ከዚህች ምድር ርቀው መሄድ አለባቸው። ታላቅዋ አሜሪካ ለእነሱ የሚሆን ቦታ የላት። እናንተ አሜሪካንን የምታሳንሱ ናችሁ” ማለታቸው በእርግጥም “እኚህ እብድ ሰው ለአሜሪካም ሆነ ለተቀረው አለም አይበጁም።” አሰኝቷቸውም ነበር።
ደጋፊዎቻቸው ግን ‹‹አዎ እኛም አብደናል›› በማለት ይከተሉዋቸው ጀመር። በቁጥርም በረከቱ፤ እኛም የእሳቸውን ሀሳብ እንደግፋለን ባዮች በዙ። ትራምፕ በአጃቢዎቻቸው በየ ቅስቀሳ አደባባይ ደምቀወና ገነው ታዩ። እናም የምርጫው ወቅት እየቀረበ ሲሄድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ስለሳቸው በስፋት ማውራትን ያዙ። ሰውዬው ከሚያቀርቡት ጥቁርና ሙስሊም ጠል ንግግራቸው ጋር አያይዘው “አሜሪካ ትቅደም” የሚለው መርህ መሰል መፈክራቸው ብዙ አሜሪካዊያንን አማለሏቸው።
በተለይ ከብዙ የእስልምና እምነት ተከታይ ሀገራት ለመጡ ሙስሊሞችና ጥቁሮች “ፊት አልሰጥም እነሱ ለአሜሪካን አይበጁም ድምፃችሁን ከሰጣችሁኝ የመጀመሪያ ተግባሬ ከዚህች ተስፋይቱ ምድር እነሱን ማባረር ነው።” በማለት በግልፅና በድፍረት በየምርጫ ቅስቀሳቸው ለደጋፊዎቻቸው መንገሩን ቀጠሉበት። ለአሜሪካና ለአሜሪካዊያን አይበጅም ያሉት ሀሳብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “እኔን ምረጡኝ! የሚል ፉከራ በይምረጡኝ ዘመቻቸው ላይ ደጋግመው አሰሙ።
ከምርጫው መካሄድ ቀደም ብሎ መገናኛ ብዙሀኑ ስለ ትራምፕ ብዙ ቢሉም ያነሱት ለየት ያለ ሀሳብ ከማተት ባለፈ ይመረጣሉ የሚል ግምት ግን አልነበራቸውም። ምን አልባትም በወቅቱ ለፕሬዚዳንትነት ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት ሂላሪ ክሊንተን የቅርብ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ የሚለው ግምት በአንዳንዶቹ ከመሰጠቱ በቀር።
ከሁለት አመት በፊት የተካሄደው ምርጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን አመጣ። ምንም እንኳን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ይፎክሩበት የነበረው ሙስሊም ጠል የሆነና ጥቁሮችን ያገለለ መርሀቸው ከምርጫው በኋላ ረገብ ቢያደርጉትም፤ሰውዬም ከመመረጣቸው ማግስት አንስቶ የየዕለቱ መነጋገሪያ በመሆን የአለምን መገናኛ ብዝኋን ትኩረት ሆነው ቆይተዋል።
በበዙ አሜሪካዊያን ድጋፍ ወደ ስልጣን የመጡት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ከሀገሬውም ከአለምም ውግዘትና ምስጋና፣ አድናቆትና ውረፋ ሲፈራረቅባቸው ቆይተዋል። ሀገሪቱ አሜሪካ ናትና የተቃና አስተዳደራዊ መዋቅር የተዘረጋባት፣ የሰለጠነ ህዝብ የተትረፈረፈባት፣ መብቱን በወጉ አክብሮ የሚያከብር ዜጋ የበረከተባት ናትና ሀገሪቱ ትራምፕም ሆነ ሌላ ወደ ስልጣን አምጥታ ብታወርድ የግለሰቡ መጠነኛ አተያይ ፍልስፍና የሚያስቀይራቸው ጥቂት ነገሮች ካልሆኑ በቀር እንደ ሀገር አሜሪካ የማይንገዳገድ ስርዓት ዘርግታለች።
የልዕለ ሀያሏ ሀገር ነዋሪ ምክንያታዊ ነው። ሲያሻው በምክንያት ከፍ አድርጎ ያነግሳል፤ ምክንያት ካገኘ የዝቅታን አድራሻም አሳምሮ ማሳየት የሚችል፣ እቅድ ወጥኖ በጥንቃቄ የሚያሳካ፣ መጪው ዘመንን ተንብዮ ቀድሞ የሚዘጋጅ ለዚያም ምላሽ የሚሰጥ ብቁ ዜጋ በዝቶ የሚገኝባት ሀገር ናት-አሜሪካ።
በመካከለኛው ምስራቅ ባካሄደቻቸው ሰፋፊ ጦርነቶች ያሰበችው ውጥን ማሳካት የተሳናት እንዳለመችው ያልሰመረላት አሜሪካ ዛሬም በብርቱ ለፍላጎቷ ስምረት በዶናልድ ትራምፕ መሪነት ጥረትዋን ቀጥላለች። የአለም ልዕለ ሃያልነትዋ ላለማስነጠቅ የሀይል ሚዛንዋን ጠብቃ ለመቆየት አሁን ላይ አለን ብለው ከሚገዳደርዋት ሀገራት ጋር በብዙ ፍልሚያ ላይ ትገኛለች።
ስሜታዊ ናቸው የሚባሉት የሀያልዋ ሀገር መሪ ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸውን ያህል የገዛዘፉ ጉዳዮችን እየመሩ እስከዛሬ ቆይተዋል። በቆይታቸውም በአሜሪካዊያን አንዴ ሲብጠለጠሉና ጥርስ ሲነከስባቸው መለስ ብለው “ሚስተር ፕሬዚዳንት ደግ አደረጉ እኛ የምንፈልገው ይሄንን ነው።” ሲያስብሉ “በነጩ ቤተ መንግስት የነበረኝ ቆይታ በዚህ ማብቃት የለበትም፤ ማስቀጠል እፈልጋለሁ። ለዚህም ተዘጋጅቻለሁ።” ማለታቸውን በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።
በፈጣን እድገትዋ የአለምን ኢኮኖሚ ለመቆናጠጥ አለሁ መጣሁልሽ እያለች የምትገዳደረዋን ቻይና ጋር የኢኮኖሚ ፉክክር መርተው፣ ከሰሜን ኮሪያና ከኢራቅ ጋር ያለውን የኒኩሌር ሰጣ ገባ ላይ ተነታርከው፣በቀደምት መሪዎች የተጀመሩ የመካከለኛው ምስራቅ ጦራቸውን መርተውና የበዛው የሀገራቸውን ጥቅም አስጠብቀው በበዛ የስራ ውጥረት የተፈ ቀደላቸው የስልጣን ዘመን በማገባደድ ላይ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ አለም ቀጣይ እርም ጃና መድረሻቸው በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
እውን በባህሪና ተግባራቸው ብዙ ሲያሰኙ የቆዩት ሰው ዋሽንግተንን በድጋሚ የመምራትን እድል በአሜሪካዊያን ተጎናፅፈው የአለም መነጋገሪያነታቸው የየቀን ቁንጮ ርዕስ መሆና ቸው ይቀጥል ይሆን?
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2011
ተገኝ ብሩ