እውን ፈረንጅ ልቅ ነው?

አንዳንድ ኢ-ስነ ምግባራዊና ኢ-ሞራላዊ ነገሮችን የሚያደርግ ሰው ከፈረንጅ እንደኮረጀው ተደርጎ ይነገራል። በትልልቅ መንግሥታዊ ተቋማት በሚዘጋጁ መድረኮች ‹‹መጤ ባህል›› ተብሎ ውይይት ይደረጋል። ከባህልና ሞራል ያፈነገጡ ነገሮችን ባለቤትነቱን ለነጮች በመስጠት ‹‹የምዕራባውያን የባህል ወረራ›› ሲባል ይሰማል። ልክ እኛ ሐበሾች የሰለጠንን፣ በሞራል የታነጽን ሆነን፤ መጥፎ ነገሮችን ግን ፈረንጆች እንደጫኑብን ተደርጎ ይነገራል።

በነገራን ላይ በሞራል የታነጸ ማለት ሌሎች ቢጭኑበትም የማይቀበል ማለት ነው። ስለዚህ የመጥፎ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ፈረንጆች ቢሆኑ እንኳን እኛ ኩሩ ነን ካልን መቀበል የለብንም፤ ሎጂኩ ራሱ አያስኬድም። ኩሩ ማለት ማንም መጥፎ ነገር ልጫንብህ ሲለው የማይቀበል ማለት ነው።

ለመሆኑ ግን ፈረንጅ እኛ ሐበሾች በምንለው ልክ ልቅ ነው? በነገራችን ላይ ፈረንጅ የሚለው ቃል በልማድ የምንጠቀመው ነው። ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ እንደገለጽነው ፍረንች (ፈረንሳይ) የሚለውን ነው ፈረንጅ ያልነው። ቋንቋ ማህበረሰባዊ ስምምነት ነውና ነጭ የሆነውን ሁሉ ‹‹ፈረንጅ›› ስለምንል ያስማማናል። ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ፈረንጅ ስንል ነጮችን ማለታችን ነው። በሌላ አገላለጽ ምዕራባውያን ይባላሉ፤ ምዕራባውያን ማለት በዋናነት አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ማለት ነው። በአጭሩ ግን ፈረንጆች የሚለው ያግባባናል።

ፈረንጆችን የልቅነት ምሳሌ ማድረግ የተሳሳተ ነው። በጣም ሞራል ያላቸው፣ በህግና ደንብ ብቻ የሚመሩ ናቸው። ምንም እንኳን እዚህ ላይ ለመጥቀስ አስፈላጊ ባይሆንም ብዙ መጥፎ ነገሮች ቢኖሯቸውም ስነ ሥርዓትና ህግ አክባሪነት ግን ለማንም አርዓያ የሚሆኑ ናቸው።

ችግሩ አንዳንዱ ከኢትዮጵያ ባህል ጋር ስናነፃፅረው ተቀባይነት አይኖረውም። ለምሳሌ፤ ሐበሻ አብሮ መብላት ይወዳል፤ ፈረንጆች ግላዊነት የተጠናወታቸው ናቸው። ይህን እንደ ሥልጣኔ ቆጥሮ ከእነርሱ መኮረጅ አይጠበቅብንም፤ ምክንያቱም ሁለቱም ማንነትና መለያ ነው።

ከፈረንጆች ልንኮርጀው የሚገባው ግን ‹‹እገሌ ምን በላ? ምን ጠጣ? ምን ለበሰ?›› የሚለው አያስጨንቃቸውም። የግለሰብ መብት ያከብራሉ። ‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አያድርም›› የሚለው አባባል የሐበሻ ቢሆንም በትክክል ተግባር ላይ የሚያውለው ግን ፈረንጅ ነው። የእገሌ ልጅ ሲመረቅ ይህን ያህል ድግስ ተደገሰለት የሚለው አያስጨንቃቸውም። ሐበሻ ግን ተበድሮ ድል ያለ ድግስ ይደግሳል። ከዚያም ልጁ በሥራ ፍለጋ ሲኳትን ይከርማል። ይህ ልማድ እንደ ሀገር ድሃ ያደርገናል ማለት ነው። ስለዚህ ይሄኛው ባህላቸው ብንኮርጀው የሥልጣኔ ምልክት ነው።

የፈረንጅ እንቅስቃሴ በህግ የሚመራ ነው። ለእኛ ነውር የሚባለውን ነገር ሲያደርጉ የህግ ማዕቀፍ አውጥተውለት ነው። ህጋቸው ከፈቀደ ይደረጋል፤ ህጋቸው የማይፈቅድ ከሆነ ግን አይደረግም።

ፈረንጆች ውስጥ ሁሉ ነገር ልቅ ይመስለናል፤ ግን አይደለም። በመጽሐፎቻቸውም፣ በመድረክም የአውሮፓ አገራት ገጠመኞቻቸውን በተደጋጋሚ የሚናገሩት የደን ስነ ምህዳር ተመራማሪውና ደራሲ አለማየሁ ዋሴ (ፒ. ኤች. ዲ) ሲናገሩ የሰማሁትን አንድ ገጠመኝ ልጥቀስ። የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ሆነው ለምርምር በቡድን እየተንቀሳቀሱ ነው። አንዲት ከተማ ውስጥ ሲገቡ ማደሪያ ቦታ ተሰጣቸው። የተሰጣቸው ክፍል ውስጥ ሴቶችም አብረው እንዲገቡ ተደረገ፤ ሴቶቹ ነጮች ናቸው።

በእነ አለማየሁ ዋሴ ሀገር ሴትና ወንድ አንድ ክፍል ውስጥ የተለመደ አይደለም፤ ስለዚህ ግርምት ተፈጠረ። አንዳንዶቹ ሐበሾችም ‹‹እኔ እዚህ አላድርም›› ማለት ጀመሩ። ምክንያቱም ‹‹ሴቶቹ ምን አስበው ነው?›› የሚል ስሜት ተፈጥሮባቸዋል። እንደምንም ተመካክረው ልክ በወጣቶች ቋንቋ ‹‹ያስፎግረናል›› በሚል ስሜት ምንም እንዳልገረማቸው ሆነው አብረው ሆኑ። አንድ ክፍል ውስጥ ቢሆኑም ሁሉም የየራሳቸው አልጋ አላቸው። ሴቶቹ እዚያው ከወንዶች መሃል ልብሳቸው እየቀየሩ ተገኙ።

ይህን ነገር በሐበሻ ባህል ልብ እንበለው። ‹‹ምን አይነት ስድ አደጎች ናቸው!›› መባሉ አይቀርም። የልቅነት መለያ ነው። ነገሩ ግን ወዲህ ነው። በፈረንጆች ባህል የግለሰብ መብት በጣም ይከበራል። ከግለሰቡ ፈቃድ ውጭ ምንም የሚደረግ ነገር የለም። ይህ ማለት ግን አልፎ አልፎ ኢሞራላዊ ነገሮች አያጋጥሙም ማለት አይደለም፤ ቢያንስ እንደ ባህል ግን መለያቸው ህግና ደንብን ማክበር ነው።

የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የሚበዛው እንደ ህንድ ባሉ ወግ አጥባቂ ሀገራት ነው። በሀገራችን በተደጋጋሚ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የምንሰማው ‹‹ሴት ልጅ ከወንድ ፊት እግሯን ዘርግታ መቀመጥ የለባትም›› በሚባልበት ሀገር ነው። ያም ሆኖ ግን የግድ ከእነርሱ ጋር እንመሳሰል ማለት አይደለም፤ እነርሱ የደረሱበት ግለሰባዊ መብት ሞራል ላይ እስከምንደርስ ከባህላችን ጋር የሚሄድ ህግና ደንብ መኖሩ የግድ ነው። ዳሩ ግን ፈረንጆችን የልቅነት ምሳሌ ማድረግ ስንፍና ነው።

‹‹መጤ ባህል›› የሚባሉትን ልብ እንበል። አደንዛዥ ዕፅ የሆነ ነገር ሁሉ ‹‹መጤ›› ይመስለናል። ‹‹መጤ›› የሚባለው ከፈረንጆች የመጣ ማለት መሆኑ ነው። ትምባሆ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ አይበቅልም? ጫት የማን ነው? በዘመናዊ መንገድ ከተሰራው ሲጋራ በፊት የሐበሻ አባቶች የደረቀ ትምባሆ እሳት ላይ አድርገው ያጨሱ አልነበረም ወይ?

እልም ያለ ገጠር ውስጥ፣ ፈረንጅ የሚባል ነገር አይተው የማያውቁ፣ ፊልም እና ቴሌቭዥን የሚባሉ ነገሮች በማይታወቁበት በዚያ በጥንቱ ዘመን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅል የሚዘጋጅ የሺሻ ዕቃ የሚመስል ነገር ነበር። የማስቀመጫ ዕቃው ከቅል የሚዘጋጅ ሲሆን የሚሳብበት ነገር ደግሞ ከሸንበቆ ይዘጋጃል። ትምባሆ እና እሳት ጨምረው ካቀነባበሩ በኋላ ያንን እየማጉ ጭስ በአፋቸው ይትጎለጎላል። ያንን ያደረጉት ፈረንጅ አይተው ነው?

ነገርየው ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጣዊ ሂደት ጋር የመጣ ነው። የሰው ልጅ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ነገሮችን አድርጓል። የሚጠቅሙትን አስቀጥሎ የጤና ጉዳት የሚያስከትሉትን ጥሏል፤ የሚሻሻሉትንም አሻሽሏል። ስለዚህ ፈረንጆች ቀድመው ስለነቁ ጎጂ የሆኑ ነገሮችን ጎጂ ናቸው ብለው ማስተማር ጀመሩ። ሲያስተምሩ ግን እነርሱ የፈጠሩት በማስመሰል ‹‹መጤ›› ብለን የፈረንጆች አደረግነው።

ራቁት መሄድ የፈረንጅ ባህል ይመስለናል። ግን እነርሱም ጋ ነውር ነው። ለምሳሌ፤ ከአምስት ዓመታት በፊት በሊቨርፑልና ቶተንሃም አንድ ጨዋታ ላይ አንዲት ሞዴሊስት ድንገት ከታዳሚው አምልጣ ራቁቷን ወደ ጨዋታው ሜዳ ገባች። ለዚያውም ሙሉ ራቁቷን አይደለችም። ያ ክስተት ከጨዋታው በሻገር መነጋገሪያ ሆነ። እሷም የፈለገችው ማስታወቂያውን ነበር። ወዲያውኑ በፖሊስ ተይዛ ወጣች።

ለምን እንደዚያ አደረገች? ብለን ልብ ካልን ራቁት መሄድ በእነርሱ ሀገርም ነውር ነው ማለት ነው። ያልተለመደ ድርጊት ነው ማለት ነው፤ ትኩረት እንደሚስብ ገብቷታል ማለት ነው። ፈረንጅ በዚያ ልክ ይገረምበታል ብየ አልገመትኩም ነበር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ራሱ ከዚያ በላይ የሚያስገርም አይመስለኝም።

ከአሥራ ምናምን ዓመታት በፊት ይመስለኛል አንድ ኢትዮጵያዊ በአንዲት አውሮፓ ሀገር ውስጥ ሀፍረተ ስጋውን አሳየ ተብሎ ታስሮ መነጋገሪያ እንደነበር አስታውሳለሁ። አውሮፓ ሀገር ውስጥ ሀፍረተ ሥጋ እያሳዩ መሄድ ነውር ነው ማለት ነው፤ ነውር ብቻ ሳይሆን በህግ ያስጠይቃል ማለት ነው።

በአጠቃላይ ለህግና ለሞራል መገዛት ሲያቅተን ‹‹ፈረንጅ የጫነብን ነው›› እያሉ ማሳበብ ስንፍና ነው። ፈረንጆች እኛ በምንለው ልክ ልቅ አይደሉም!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 3/2016

 

 

Recommended For You