ድሮ ላይ የቆሙ አንዳንድ ሰዎች “አዬ ክፉ ዘመን! ሰው የለም፣ መተዛዘን መተሳሰብ ጠፍቷል…” ይሉናል፡፡ ዙሪያችንን የከበበንን መልካም ያልሆነ ነገርና መልካም ያልሆኑ ሰዎች ብቻ አጉልተው እያሳዩ መልካሙን ያርቁብናል፡፡ ሰው ግን ሞልቷል። ለዚያውም በጎነትን የተላበሰ፣በሰናይ ምግባሩ የተወደሰ ሰው ! የሰውነት ውሃ ልክ የሆነ መመልከቱን ማስተዋሉን ካደለን ሰው በጠፋበት ሰው ሆኖ የሚገኝ ሰውማ አለ፡፡ በክፉ ቀን ስለሰው ብለው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ፤ከኔ ይልቅ ሌላውን ብለው ሰውን ለማዳን መስዋዕት የሆኑ ሰዎች ደጋግመን አይተናል፡፡
አቤት! የሰው ልጅ ክፋት ባሰኙን ሰዎች ምትክ ለሰዎች በጎ ውለው “ሰው ነው ለሰው መድኃኒቱ” ያልንበት ገጠመኞች ይበዛሉ። የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ መልካምነት ነው ብለን ስላመንን ብዙ መልካም ነገሮች ልብ ብልን አናይም፡፡ ይልቁንም ሰዎች የሚሰሩት ስህተት ገኖ ይታየናል ልክ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጻፈው “የሰውን ጉድፍ ከምታይ እራስህ ላይ ያለውን ምሶሶ አስወግድ” ከሰዎች ፍፁምነት መጠበቅ ደግሞ ደግ አይደለም፡ ፡ የሰው ልጅ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሳሳትም ፍጥረት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ዛሬ ስህተታቸው እና ችግራቸው ሁሌም ጎልቶ የሚታየንና እያነሳን ከምድር የምንቀላቅላቸው ታክሲዎች መልካም ስራቸውን ለማየት መነፅራችንን ፀዳ ፀዳ አድርገን ብንመለከት ብዬ አሰብኩ፡፡ ሲሰሩት እና ሲኖሩት ያየሁት መልካም ነገርን እያነሳሁ ላወጋችሁ ወደድኩ ፡፡መልካም ነገሮችን አይቶ ይህንን ያብዛልን የማለት ከልብ የመነጨ ምኞት በጎውን ነገር ይበል ደስ የሚያሰኝ ነው ብሎ ከመግለፅ ይጀምራል፡፡
ከስራ ቀኖች በአንዱ እንደተለመደው ከመስሪያ ቤት ወጥቼ ወደ ቤቴ የሚያደርሰኝ “ሚኒባስ” ታክሲ ያዝኩ። የተቀመጥኩት ከሹፌሩ ወንበር ኋላ ነው። ታክሲ ውስጥ ጥቅስ ይበዛል እኔ ደግሞ የተሰቀሉ ጥቅሶችን ማንበብ ልማዴ ሆኗል። እንደ ልማዴ የተሰቀሉ ጥቅሶችና ፅሁፎች ማንበቤን ተያያዝኩት። ጋቢና ከሹፌሩ ጎን ከተቀመጠው ሰው ከፍ ብሎ የመኪናው ጣሪያ ተጣብቆ ቁልቁል በተለቀቀው በፕላስቲክ የታሸገ ወረቀት አንድን መልዕክት ለተሳፋሪዎች ያስተላልፋል፡፡
ይሄንን መልዕክት ግን እንደ ሌሎቹ ጥቅሶች በመቻኮል ሳይሆን በአግራሞትና በተመስጥዖ አነበብኩት፡፡ “ዓለም የተገነባችው በእውቀት ነው፡፡ የዕውቀት አባቶች ደግሞ መምህራን ናቸው፡፡ እኔ መምህርነትን እጅግ አከብራለሁ፡ ፡ መምህራን በዚህ መኪና ሲሳፈሩ መታወቂያ በማሳየት ብቻ ያለ ክፍያ መሳፈር ይችላሉ” ይላል። አጠገቤ ከነበረው ተሳፋሪ በአንድ ጊዜ ቀና ብለን ተያይተን ፈገግታ ተገባበዝን፡ ፡ የተለጠፈው በጎ መልዕክት በጎነት በእኩል አግባብቶን፤ የባለ ታክሲዎቹን ሰናይ ተግባር ደስ አሰኝቶን፡፡
ከጥቂት አመታት በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለወላድ እናቶች ወደ ሆስፒታል ነፃ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጥ በጎ አድራጊ አንድ ወጣት ባለ “ላዳ” ታክሲ ሹፌር በአርአያነት ቀርቦ ተመልክቻለሁ፡፡ በወቅቱ የግለሰቡ ሰናይ ተግባር በብዙዎች የተወደሰና መነጋገሪያም የሆነ ጉዳይ ነበር፡፡
ወደ ጀመርኩት ወግ ልመልሳችሁ ረዳቱ ሂሳብ መሰብሰብ ሲጀምር በድጋሚ ለመምህራን ሂሳብ እንደማያስከፍሉ ገልፆ በትህትና ከሌሎች ተሳፋሪዎች ሂሳብ መቀበሉን ቀጠለ፡፡ ተሳፋሪው በሙሉ የረዳቱን መግለጫ ከሰማ በኋላ ስለተግባሩ በጎነት እርስ በእርስ ይጨዋወት ጀመር፡፡ ታክሲው ውስጥ ሁለት መምህራን ያለ ክፍያ ወደፈለጉት ቦታ የመድረስ አጋጣሚ አገኙ፡፡
ከኋላ አንድ በእድሜ ጠና ያሉ አባት የስራውን በጎ መሆን በመመስከር ለሹፌርና ረዳቱ ምርቃት ማዝነቡን ተያያዙት። “አምላክ ክብሩን ያጎናፅፋችሁ… ማንኛውንም ሰው ስታከብሩ ትከበራላችሁ። ስለዚህም መምህር እንዳከበራችሁ ክበሩ! … መልካምነትን ያላብሳችሁ …. የሰራችሁትን መልካም ተግባር በእጥፍ ይከተላችሁ ……” ቀጥለዋል ምርቃታቸው እኛም አሜን … ማለታችንን ቀጠልን፡፡ የዚህ በጎ ተግባር ተሳታፊ ሆኜ ከክፍያ በላይ የሆነውን ምርቃት እኔም በተመረኩ ያሰኛል፡፡
በዚሁ መነሻነት የታክሲው ተሳፋሪ ሳይተዋወቅ ተግባብቶ እርስ በእርስ መጨዋወቱን ተያያዘው፡፡ የታክሲዎች በጎ ስራ ተነስቶ አንዱ የሚያውቀውና ያየውን ለሌላው ይነግር ጀመር፡፡ በዚህ ታክሲ ውስጥ የታየ በጎ ተግባር ሌሎች መሰል ተግባሮችን ለማንሳትም ምክንያት ሆነ፡፡
ሳሪስ አካባቢ የእድሜ ባለፀጎችን በነፃ የሚያገለግል ሚኒባስ ታክሲ መኖሩን ከአንድ ተሳፋሪ ተነገረን፡፡ አሰብኩት የዚህ ታክሲ ባለቤት አቅማቸው የደከመ ጉልበታቸው የዛለ አዛውንቶችን ያለ ክፍያ አገልግሎት ሲሰጥ የሚመርቁት ምርቃት፡፡ ከክፍያው በላቀ የሚሰማው የህሊና እርካታ፡፡ በበጎ ምግባሩ የሚያገኘው የውስጥ ሰላም፡፡ የደስታው ዳር ድንበሩ ሁሉ ግልጥ ብሎ ታየኝ። ቀናሁ!። መንፈሳዊ ቅናት፤ እኔስ እንደዚህ ያለውን ምርቃት በምን ማግኘት እችላለሁ? ምን በጎ ተግባር ለማን ላድርግ እያልኩ ማሰቡን ቀጠልኩ ኧረ እንደነዚህ ያሉ በጎ በጎውን የሚያስቡ ሰዎችን ያብዛልን።እኔም በጎ በጎውን እያሰብኩ በጎ የሰሩትን እያመሰገንኩ ወደፊት ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ስንቶቻችን ነን በምንችለውና በአቅማችን መልካም ተግባራትን የምናዘወትር? ዓለም ላትሞላ ነገር አስሩን ግሳንግስ ሰብስበን አንዱን እንኳን በወጉ መጠቀም ሳንችል ለመኖር የተሰጠን ጊዜ ያበቃል፡፡ አለማዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ሌሎችን በድለን የግል ፍላጎታችንን ለመሙላት ስንስገበገብ ፤ ስንባዝን እርካታችን ላይ ሳንደርስ ጊዜው ያልፋል፡፡ እውነተኛና ዘላቂ መንፈሳዊ እርካታ የምናገኘው በምንሰራው በጎ ምግባር እንደሆነ ለማወቅ በጎን ስራ ሞክሮ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ቸር ያሰማን ነው! ወዳጆቼ ዛሬ በተሳፈርኩበት ታክሲ ሰናይ ተግባራት በተሳፋሪዎች መስማቱን ቀጥያለሁ፡፡ ውይይትና ጭውውቱ ቀጥሏል፡፡ ጨዋታዎች ሁሉ መልካም ስራ ላይ የተሰማሩ የታክሲ አሽከርካሪዎች በጎ ተግባርን ማውሳት ሆኗል፡ ፡ የተሳፈርንበት መኪና ረዳት እንዲህ አለን። “አብነት አካባቢ አንድ የላዳ አሽከርካሪ የኩላሊት እጥበት (ዲያሊስስ) ለሚያደርጉ የኩላሊት ህመምተኞች በነፃ የታክሲ አገልግሎት ይሰጣል።“አለ ሁኔታው ተገቢነት ያለው ሰዋዊ ተግባር ቢሆንም ብዙ መጥፎ ነገር ከሚነሳባቸው የታክሲ አሽከርካሪዎች በኩል መሆኑ ግን በጣም አስገረመን አስደነቀን በዛው ልክም በሰማነው ብቻ ምስጋናችንን ምርቃታችንን ቸር ናቸው።
ወዳጆቼ! እነዚህ በጎ ሰሪዎች አያስቀኑም? ሰው ሞልቶ ሰው ጠፋ በሚባልበት ዘመን ሰው ሆኖ መገኘት ምንኛ መታደል ነው፡፡ በነገራችን ሰውነት የሚለካው በበጎ ምግባር አይደል እንዴ ? አዎ! ሰው መሆንን የሚያላብሰን ሰዋዊ ባህሪያችን ነው፡፡ ሰዋዊ ባህሪ ደግሞ በመተሳሰብ ፍቅርን በመጋራት፣ በመደጋገፍ ይገለፃል፡፡ ልክ እንደእነዚህ የታክሲ ላይ በጎ ሰሪዎች፡፡
በእርግጥ እነዚህ በጎ ሰሪዎች ከሌሎቻችን የተሻለ የገቢ ምንጭ ስላላቸው አይደለም። መልካም ስራው የሚሰጣቸው የመንፈስ ጣፋጭ ምግብ ጥሟቸው እንጂ፡፡ ራሳቸውን አሸንፈው “ከራስ በላይ ንፋስ” የሚለው ብሂል እኔ ጋር ድርሽ አይልም ቅድሚያ ለወገኔ በሚል መርህ እየኖርኩ ላኑር በሚል በጎ እሳቤ እንጂ፡፡ በየሙያና ችሎታችን መሰል በጎ ተግባራት ላይ ብንሰማራ ሰላማችን ተጠብቆ ኑሮአችን ምንኛ በአማረ፡፡ አብሮነታችን ምንኛ በጠነከረ፡፡
የበጎ ተግባር አድናቆታችን እያየለ የተሳፈርንበት ታክሲ የሚያደርገውን መልካም ተግባር መነሻነት እንዲህ የሚያስደምም ተግባር በሚከውኑ ታክሲዎች ላይ ማውራትን ያስቆመን የተሳፈርንበት ታክሲ ከምንፈልገው ቦታ አድርሶን ስንቆም ነው፡፡ ባለ ታክሲውን ምንም ወጣት ብሆንም እኔም መረኩት ከስንት ዝባዝንኬ የታክሲ ወሬዎች አላቆ በጎ ነገር ሲያሰማን ሰፈሬ ድረስ ያደረሰኝን የበጎ ተግባር ባለቤት እንዴት ዝም ብዬ ልውረድ? ኧረ በፍፁም እመርቀዋለሁ፡፡ለሰጠኸው ነፃ አገልግሎት በምላሹ ፈጣሪ ያሰብከውን ያጎናፅፍህ አቦ!
ወዲያ ግድም ደግሞ አሉ፡፡ ከእነዚህ በተቃራኒው የቆሙ የታክሲ ሹፌርና ረዳቶች፡ ፡ እነዚህኞቹ ግን መች ይሆን ተገልጋያቸውን የሚያከብሩት? በሚሰጡት አገልግሎት ብልሹነት ተማረን፣በታሪፍ ጭማሪያቸው ተጨቃጭቀን፣”መልሴን ስጠኝ!”.. “አልሰጥም!” ተጎሻሽመን፣ “መጨረሻ ነው ውረዱ..!” “ ገና ነው አንወርድም” በማለት ተሟግተን እስከመቼ እንዲህ ባለ ሁኔታ እንዘልቅ ይሆን? እነዚህኞቹ ከላይ ካሉት ሹፌር እና ረዳት እጅግ የራቀ እና የተቃረነ ስብዕና ያላቸው ናቸው፡፡ ሳይለመኑ፣ የተሳፋሪን መልስ መልሰው ሳያንጓጥጡ ፣ጭነው ሳይገላምጡ አድርሰው ስርዓቱን አክብረው ቢያቀርቡልን አገልግሎታቸው በራሱ ትልቅ ልገሳና በጎነት እኮ ነበር፡ ፡ ለማንኛውም እነዚህኞቹ ከላይ በብዙ ካነሳናቸው በጎ ሰሪዎች መልካምነትን፣ መረዳዳትንና መከባበርን ፈጣሪ በኪነ ጥበቡ ያድላቸው ! እኛንም ያድለን፡፡ መልካም ሰንበት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2011
ተገኝ ብሩ