በህይወት ሰንብቶ ያሰቡትን ለመፈጸም ህልምንም ለመኖር ወሳኙ ነገር ጤና ነው። በምድር ላይ እንድንኖር የተወሰነልን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ባናውቀውም፤ ራሳችንን ግን ከአደጋም ሆነ ከጤና እክል የቻልነውን ያህል እንጠብቃለን። አይበለውና ህመም ሲገጥመንም ከቤት አፈራሽ ህክምና እስከ ሃኪም ቤቶች ዘልቀንም መላ እናፈላልጋለን።
ስልጡን ሃኪሞች ጤናችንን መልሰው በጤና እንድንኖር ይረዱናል። አልፎ አልፎ ግን የዚህ ተቃራኒ የሆነ ነገር ይገጥማል፤ «ልታከም ሄጄ በሽታ ሸምቼ መጣሁ» ሲባልም ሰምተን ይሆናል። «ከብረት ዝገት ከሰው ስህተት አይጠፋም» እንዲል ብሂሉ፤ ባለሙያዎችም ስህተት ይሰራሉ። በስህተት መድሃኒት ማዘዝ፣ የታመመውን ትቶ ያልታመመውን ማከም፣ የህክምና መሳሪያዎችን አካል ውስጥ መዘንጋት፣… ጥቂቶቹ ናቸው።
መቼም ዓይነቱ ይለያይ ይሆናል እንጂ ታሞ የማያውቅ ሰው አለ ለማለት አያስደፍርም። ታዲያ በዚህ ስህተት ለዓመታት መታመም ቀርቶ ትንሿ ቁስል የምታስከትለው ስቃይ ምን ያህል እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። ከህክምና ስህተት ጋር በተያያዘ እየታመሙ መኖርን ግን አስቡት።
ሩሲያዊቷ ባልቴት የገጠማቸው ይኸው ነው፤ አትሙቺ ያላት ነፍስ ሆነችና ከእነ ህክምና እንከናቸው ሁለት አስርት ዓመታትን ሰነበቱ እንጂ። የ62 ዓመቷ ወይዘሮ ኢዜታ ጎቤቫ ሲሰኙ፤ ነዋሪነታቸውም በሩሲያ ሰሜናዊው ክፍል ነው። ታዲያ ሴትየዋ እአአ በ1996 ቀዶ ጥገና ካደረጉ ጀምሮ ጤናቸው ተመልሶ አያውቅም። የሚያሰቃያቸውን የሆድ ህመም ለማስታገስ በተደጋጋሚ ሃኪም ቢጎበኙም መላ ግን አልተገኘላቸውም።
ሃኪሞችም ወይዘሮዋን ከመረመሩ በኋላ የጉበት ህመም እንደሆነ እየነገሩ የማስታገሻ መድሃኒቶችን ብቻ ሲያዙላቸው ዓመታት ተቆጥረዋል። ከሰሞኑም ህመሙ ስለጠናባቸው በድጋሚ ሃኪም ዘንድ ቀረቡ፤ ሃኪምም ሆዳቸው በኤክስሬይ እንዲታይ አዘዙ። ውጤቱ ግን እጅግ አስደንጋጭ እንደነበር ኦዲቲ ሴንትራል በድረገጹ ያስነብባል።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ ወይዘሮዋ ከ23ዓመት በፊት ቀዶ ጥገና ባደረጉበት ወቅት የህክምና መቀስ መሰል መሳሪያ ሆዳቸው ውስጥ ተረስቷል። የሆነው አስደንጋጭና የአንድ ወጣት ዕድሜን ለሚስተካከል ጊዜ በሆዳቸው ውስጥ መቆየቱ አስገራሚ ቢሆንም፤ የሴትየዋ የረጅም ጊዜ ህመም መንስኤ ግን ሊታወቅ ችሏል። ወይዘሮ ጎቤቫ ስለ ሁኔታው ሲገልጹም፤ «ባለሙያዋ መቀስ መሰል ነገር ሆዴ ውስጥ መታየቱን ስትነግረኝ፤ የምን መቀስ? ስል ነበር የጠየቅኳት። ምክንያቱም ምንም የማስታውሰው ነገር አልነበረም፤ ምስሉን ስታሳየኝ ግን ደንግጬ አለቀስኩ፤ ለረጅም ዓመታት ሲያሰቃየኝ ነበር እኮ» ብለዋል በብሶት።
ይህንን ተከትሎም መሳሪያውን ከባልቴቷ ሆድ ለማውጣት ቀን ተቆርጧል። ዜናው ከተሰማ በኋላም የጤና ሚኒስትር ጉዳዩ ላይ ማጣራት እንዲደረግ አሳስቧል። የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ እንዳሉት ከሆነም መንግስት ራሱ ጉዳዩን ይመረምራል፤ ከዚህ ባሻገርም ባልቴቷ መሳሪያው እንዲወጣላቸው የሚያደርገውን የቀዶ ጥገና ወጪ እንደሚሸፍን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2011
ብርሃን ፈይሳ