መነሻውን እኤአ1979 ያደረገው የዋሽንግተንና ቴሄራን ሽኩቻ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከነግለቱ ቀጥሏል። ከዚህ ጊዜ በኋላም ሁለቱ አገራት በአይነ ቁራኛ ከመጠባበቅ ባለፈ አንዳቸው ለአንዳቸው እጃቸውን በቅጡ ለሰላም ዘርገተው አያውቁም።
የኢራን መንግስት ድጋፍ ያላቸው ሚሊሻዎች አሜሪካን ከቀጠናው ለማስወጣት ለዓመታት ብርቱ ትግል አድርገዋል። በቀጠናው በተሰማሩ የዋሽንግተን ወታደሮች ላይ ተደጋጋሚና ከባድ ጉዳት አድርስዋል፤በዚህም የበርካቶችን ህይወት ነጥቀዋል።
አሜሪካም ብትሆን በተለያዩ ጊዜያት በቴሄራንና ዜጎቿ ላይ ጉዳት አድርሳለች። በኢንፎርሜሸን ድህንነት ላይ ያነጣጠረ የሳይበር ጥቃት ከመፈፀም የኢራን መርከቦችን ወደ ባህር ከማስመጥ አንስቶ በስህተት ነው በሚል በአገሪቱ አውሮፕላን ላይ ጥቃት መፈፀሟም ይነገራል።
ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ነጩ ቤተ መንግስት በገቡትና በአሜሪካ ትቅደም መርሃቸው አገራቸው የዓለም መሪና አስተባባሪ እንድትሆን አጥብቀው በሚመኙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአስተዳደር ዘመንም በሁለቱ አገራት መካከል የቆየው ትኩሳት ይበልጡኑ ተጋግሏል።
ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳቸው ቃል በገቡት መሰረት እ አ አ በ2015 በኢራንና በስድስቱ የዓለማችን ኃያላን አገራት በአሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩስያ፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያና ፈረንሳይ መካከል የተፈረመውን የኒውክሌር ስምምነት ቴሄራን እንዳላከበረች በመግለፅ አገራቸውን ማስውጣታቸው ግንኙነቱን ከድጡ ወደ ማጡ አሸጋግሮታል። የዋሽንግተኑ አስተዳደር በዚህ ብቻ ሳይወሰን ተጨማሪ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በኢራን ላይ ማወጁም ነገሮች ይበልጥ መልካቸውን እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል።
አገራቸው ያልፉትን ዓመታት የስምምነቱን ቃል ጠብቃ ሰለመቆየቷ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ የቆዩት የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሮሃኒም፥የዋንሽግተን መንግስትን ከማውገዝ ባለፈ «ውሳኔው ህጋዊነት የሌለውና ዓለም አቀፍ ህግን የሚጻረር፤ ቴሄራን በስምምነቱ የገባችውን ቃል እንደታጥፍ የሚገፋፋ ነው»ሲሉም ተደምጠዋል።
በተለይ አንድ ዓመት ሁለቱ አገራት እንዳቸው እንዳቸውን ሲወንጀሉ የቆዩበት ነው፡፡ ይሁንና ልዩነታቸው እያደር እየሰፋ ቢመጣም፣ ፍጥጫቸው ግን ቦታ ለይተው ጦር እንዲማዘዙ የማድረግ እቅም ሳያገኝ ቆይቷል። ያለፈውን አንድ ወር ግን በቃላት ከመወራረፍ ተሻግረው በጡንቻ ለመለካካት እየዳዱ ስለመሆናቸው ፍንጭ ሰጥቷል።
ወቅታዊውን የሁለቱ አገራት ውጥረት መሰረት በማድረግም የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ከጡዘቱ ስር መሰረት ተነስተው አሁን የሚነሱ ጥያቄዎችን በማታት ላይ ይገኛሉ።
የወቅታዊ ውጥረት መነሾ
ሁለቱ አገራት የዚህ ዓመት ውጥረት በሚያዝያ ወር መጨረሻ ሳምንት የአሜሪካው የደህነንት አማካሪ ማይክል ቦልት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ስፍራው እንደሚልኩ ማሳወቃቸውን ተከተሎ የተጀመረ ነው። የዋሽንግተንን ውሳኔ ያስተዋለችው ኢራንም ከሶስት ቀናት በኋላ «ከእንግዲህ በኋላ በጎርጎሳውያኑ 2015 የኒውክለር ፕሮግራሜን ለመቀነስ የገባሁትን ስምምነት ለማክበር አልገደድም» ስትል አሳውቃለች።
ሁለቱን አገራት እልህ በማጋባት ለጠብ አጫሪነት እጃቸውን እንዲሰበስቡና በመካከለኛው ምስራቅ የወታደራዊ ፍልሚያ ሊያስጀምር እንደሚችልም የተገመተው ይህ ክስተት ከተፈጠረ ከቀናት በኋላ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ሁለት የሳውዲና አንድ የተባበሩት አረብ እመሬትስ እንዲሁም አንድ የኔርዌይ ኩባንያ ንብረት የሆኑ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ዋሽንግተንም«ጥቃቱ የቴሄራን ስራ ነው» በሚል ክፉኛ ኮንናዋለች። ይህም አገራቱ «ጦር የሚማዘዙበት ትክክለኛው ሰዓት ላይ ደርሰዋል» የሚሉ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ተንታኞች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።
ይባስ ብሎ የዚህ ጥቃት እሳት ሳይበርድ በቀናት ልዩነት በዖማን ባሕረ-ሰላጤ ውስጥ በሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ዳግመኛ ጥቃት መፈፀሙን ወትሮም ቢሆን «አላማርሽኝም» የተባባሉትን አገራት ይበልጥ እንዲፋጠጡ ገፋፍቷቸዋል።
የዋሽንግተን አስተዳደር የዓለማችን የነዳጅ ምርት በሚዘወርበት በዚህ ቀጠናው በሚመላለሱት መርከቦች ላይ በሚደርሰው ጥቃት ቴሄራን ዋነኛ ተዋናይ ናት በሚል ሲከስ፤ ኢራኑ በበኩሏ «ውንጅላው መሰረት ቢስና ትንኮሳ ስሜት የወለደው ነው፤እኔ ከደሙ ንፁህ ነኝ» ስትል ተደምጣለች።
ለነጩ ቤተመንግስት ግን ይህ የቴሄራን መልስ በቂና አሳማኝ አልነበረምና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ኢራን እያሳየችው ለምትገኘው «የጠብ አጫሪነት ባህሪ ምላሽ ለመስጠት» ነው በሚል ከወራት በፊት ተጨማሪ 1ሺህ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የማሰማራት ውሳኔ አሳልፏል።
ይህ ውሳኔ ከተላለፈ ከቀናት በኋላም የኢራን አብዮት ዘብ ጠባቂ ወታደሮች በሀገሪቱ የአየር ክልል ውስጥ ቅኝት ስታደርግ በነበረች የዋሽንግተን ሰው አልባ የስላለ አውሮፕላን (ድሮን)መቶ መጣሉን ያስታወቀ ሲሆን፤ ይህ ክስተትም ከሁሉም በላይ ሁለቱ አገራት ምናልባትም ራሳቸውን ለጦርነት እያሟሟቁ ስለመሆኑ በርካቶች እንዲገመቱ በቂ ምክንያትን መሆን ችሏል።
የጦርነት አይቀሬነት
ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ሁለቱን አገራት ወደ ጦርነቱ የሚወስዱ መንገዶች ክፍት መሆናቸው እርግጥ ቢሆንምና አገራቱን በቀላሉ ስህተት ለመፈጠር ከፍተኛ እድል እንዳላቸው ቢያስግምቱም፣ በአንዳንድ መረጃዎች መሰረት ደግሞ አገራቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ፈጥነው ወደ ጦርነቱ ይገባሉ ተብሎ እንዳይጠበቅ ማድረጋቸውም ተመላክቷል።
በተለይ አሜሪካ ሃያልነቷን ለማስመስከር ፈጥና ወደ ጦርነት ትገባለች ተብሎ እንደማይጠበቅ ያመላከቱት መገናኛ ብዙሃኑ፤ ለዚህ እሳቤአቸውም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ስለጦርነቱ አይቀሬነት ሲጠየቁ፤«ጦርነቱ ይሆናል የሚል ተስፋ የለኝም፤እኛ ከኢራን ጋር ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎቱ የለንም፤ግጭት ከተከሰተ ግን አውዳሚ ይሆናል» ማለታቸውን በዋቢነት አመላክተዋል።
ይህ ማለት ግን ሁለቱ አገራት አሁንም ቢሆን ወደ ጦርነቱ እየተንደረደሩ አይደለም አሊያም አንዳቸውም በሌላኛቸው ላይ ያልተገባ ውሳኔ በመወሰን ጦር የሚያማዝዝ ስህተት አይስሩም ማለት አይደለም፤ ሆኖም ግን በተለይ ልዕለ ሃያሏ አገር የጦርነት ረሃብ ላይ አለመሆኗ ጦርነቱ በቅርብ ይሆናል የሚለውን እንዳናስብ እፎይታን የሚሰጠን ነውም ተብሏል።
ጦርነቱ ከሆነስ በምን መርህ ይሆናል?
የትራምፕ አስተዳደር አቋምና ቀደም ሲል በነበረው የአገሪቱ ፖሊሲ መሰረት ዋሽንግተን ወደ ጦርነቱ ልትገባባቸው የምትችላቸው መርሆች ተለይተዋል። ከሁሉም በላይ ግን ኢራን የኒውከሌር መርሃ ግብሯን አቀላጥፋ ከቀጠለች አሊያም በዋሽንግተን ላይ የሚሳኤል ጥቃት የምትፈፅም ከሆነ አሜሪካን ወደ ጦርነቱ ለመግባት የተገደድኩት በዚህ መርህ ነው በሚል ጡንቻዋን ለማሳረፍ እንድምትጓዝም ተመላክቷል።
ጦርነትን ምን አይነት መልክ ይኖራዋል
አስከፊ የተባለው የሁለቱ አገራት ጦርነት ከሆነስ ምን አይነት መልክ ይኖረዋል ለሚለው ጥያቄ መልስ ከሁሉ በላይ ዋሽንግተን ለማስፈፀም የፈለገችውን መጠን ይወሰናልም ተብሏል። ባለሙያዎችም ጦርነቱ የኢራን ኒውከሌር ጣቢያዎችን ኢላማው ያደረገ ሊሆን እንደሚችልና፤አሊያም ሙሉ በሙሉ ኢራንን በመውረር ሊካሄድ እንደሚችል ተመላክቷል።
ጦርነቱ እንዲካሄድ ፍላጎት ያለው ማነው በርካቶች መጪውን ጉዳት በመስጋት በቴሄራንና በዋሽንግተን መካከል ጦርነት እንዳይከፈት ቢማፀኑና ፍላጎታቸውም ከጠብ ይልቅ ሰላም መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም፤ አንዳንዶች በተለይም በስም ደረጃ በይፋ ያልተገለፁትና ከኢራን ጋር መልካም ወዳጅነት የሌላቸው አገራትና ግለሰቦች የጦርነቱን ይፋ መሆን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውና አስከፊ የተባለው የጦር ፍልሚያ በፍጥነት እንዲሆን መሻታቸው ስለመሆኑም ተጠቁሟል።
ፍጥጫው በዓለም የነዳጅ ኡደት ላይ ምን ያስከትላል?
እንደዘገባውና ባለሙያዎች ከሆነ ፍጥጫው በዓለም አቀፉ የነዳጅ ምርት ኡደት ላይ ያልተጠበቀና ከባድ የተባለ ጉዳት ማምጣቱ አይቀሬ ነው። በተለይ ሶስተኛዋ የዓለም ነዳጅ አቅራቢ አገር ኢራን ደቡባዊ ሃረሞዝ ግዛት በኩል የሚተላለፈውን የነዳጅ መስመር ልትዘጋው ትችላለችም ተብሏል። ይህም ዓለም አቀፍ የነዳጅ ጫናን መከሰቱ አይቀሬ ነው ተብሏል።
ቀደም ባሉት ቀናት በነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ ላይ የተቃጣው ጥቃትም ምናልባትም ቴሄራን የነዳጅ መስመሩን ለማቋረጥ አማራጭ እንዳላት ለማሳያት የተጠቀመችበት ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ ባለሙያዎች ቁጥር በርካታ ሆኗል።
በእርግጥ አሁን የጦርነቱ ይፋዊ የማወጅ ስልጣን በትራምፕ ላይ ተወስኗል። ሰውየውም ወደ ጦርነቱ የመግባት እቅድ እንዳላቸው በይፋ አልገለፁም። ይህም ለጊዜም ቢሆን ጦርነቱ ይሆናል ከመባል አይሆንም ላይ እንዲንጠለጠል አድርጎታል። መረጃው የቮክስ ኒውስ ሲሆን ዘጋቢው አሌክስ ዋርድ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2011
ታምራት ተስፋዬ