በሀገራችን ቤት የመስራት ነገር ሲታሰብ አንዱ የሚደረገው ቤቱ የሚሰራበትን አካባቢ ማጽዳት ነው፡፡አትክልት ፣ዛፍ ካለ መመንጠር ወይም መቁረጥ ይቀድማል፡፡በዚህም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩ ዛፎች፣ ባህላዊ እና ለአካባቢው ያላቸው ፋይዳ ግምት ሳይገባ መመንጠር ውስጥ ይገባል፡፡ይህ ተግባር በተለይ የቦታ ጥበት ከተማ አካባቢ በእጅጉ የከፋ ነው፡፡
የዛፉ ስር ለህንጻው መሰረት ጥሩ አይደለም፤ቤቱ ትንሽ ቆይቶ እንዲፈርስ ያደርጋል ይባላል፡፡በእርግጥ የዛፍ ስር የቤት መሰረት ቀስ በቀስ እንዲናጋ እያደረገ ለመፍረስ ሊዳርገው ይችላል፡፡ ይህ ታዲያ ለትንሹም ለትልቁም ህንጻ አደጋ ሆኖ መወሰድ አለበት ብዬ አላምንም፡፡መሰረቱ ጥልቅ የሆነ ግዙፍ ህንጻ በሚገነባበት አካባቢ ይህ የሚሰራም አይመስለኝም፡፡
በእርግጥ አንዳንድ አካባቢዎች ለዛፎች ካለው ባህላዊ ፋይዳ የተነሳ እንደ አድባር የሚቆጠሩ ዛፎችን መጠበቅ ላይ ጥሩ አመለካከት አለ፡፡ከዛፉ ፈንጠር ተብሎ ነው ቤቱ የሚገነባው፡፡ይሄ ዛፎችን ለመንከባከብ የሚያስችል ጥሩ ባህል ነው፡፡
አሁን አሁን ደግሞ መሀንዲሶቻችን የመኖሪያ ቤት ወይም ግዙፍ ህንጻ ለመገንባት ዲዛይን ሲሰሩ በቅድሚያ ቦታውን በሚገባ ይመለከታሉ፡፡አንዳንድ ዛፎችን የህንጻው ውበት አድርገው በመቁጠር ከዲዛይኑ ጋር ያካትቷቸዋል፡፡እነዚህ ዛፎች ግንባታው ሲያልቅ ለህንጻው ውበት ይሆናሉ፡፡ይህም በቀጣይም ሊጠናከር የሚገባው ተግባር ነው፡፡
የህንዷ ጃባልፑር ኬሻረዋኒ ቤተሰቦች ያደረጉትም ይህንኑ ነው፡፡እነዚህ ቤተሰቦች እኤአ በ1994 ቤታቸውን ለማስፋፋት ፍላጎት ያድርባቸውና ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡በአረንጓዴ ስፍራቸው ላይ የሚገኘው እድሜ ጠገቡ ግዙፍ ዛፍ ጉዳይ ግን ያነጋግራቸው ጀመር፡፡ቆርጠን አንጣለው ወይስ በአጠገቡ ባለአራት ፎቅ ህንጻ እንስራ ብለው መከራከር ይጀምራሉ፡ ፡በመጨረሻም ዙሪያውን ባለ አራት ፎቁን ህንጻ ለመገንባት ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ህንጻውንም ይገነባሉ፡፡
ይህ ህንጻም ይገነባል፡፡የኬሻርዋኒስ ህንጻ በመባል የሚታወቀው ይህ ህንጻ የጃባልፑር ከተማ ድንቅ ስፍራ ለመሆን መብቃቱን ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረ- ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡ ባለአራቱ ፎቅ ህንጻ የዛፉ የተለያዩ ግዙፍ ቅርንጫፎች በየወለሉ ፣በየክፍሎቹ መስኮቶች እና ኮሪደሮች ሳይቀር እንዲያልፉ ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፣ ጣሪያው እና ግድግዳው ሳይቀር የዛፉን ቅርንጫፎች ያገኛቸዋል፡፡ ህንጻው ነዋሪዎቹን ብቻ ሳይሆን ተመልካቾችንም እያስደመመ ነው፡፡
የዮዴሽ ኬሻርዋኒ ቤተሰቦች ከ25 ዓመት በፊት ለገነቡት ለዚህ ህንጻ ትልቅ ውበት የሆነው ዛፍ እድሜ 150 ዓመት ሲሆን፣ሁሌም አረንጓዴ ፣አበባ በአበባ እንደሆነ ነው፡፡ በየዓመቱም ያፈራል፡፡የህንጻው ነዋሪዎች በተንቀሳቀሱ ቁጥር በዛፉ የተለያዩ አካሎች ላይ ጉዳት ቢያደርሱበትም፣ ዛፉ እንዳማረበት ከመሆኑ በተጨማሪ የቤቱ ውበት ሆኗል፡፡ቤተሰቡም ዛፉን የቤተሰብ አባል ያህል እየቆጠረው መሆኑን ዘገባው ያመለክታል፡፡
‹‹እኛ ተፈጥሮን አጥብቀን እናፈቅራለን፤አባቴ ይህን ዛፍ እንድጠብቅ አደራ ሰጥቶኛል›› ሲል ዮጌሽ ኬሻርዋኒ ለኤኤፍፒ መግለጹን የጠቀሰው ዘገባው ‹‹ዛፍ ቆርጦ መጣል ቀላል ነው፤ተክሎ ለእዚህ አይነት ተግባር ማብቃት ግን ከባድ ፈተና እንደሆነ እናውቃለን››ሲል አስገንዝቧል፡፡
በህንድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በቆየው ፔፓል በተሰኘ ባህላዊ ስርአት ይህን አይነቱን ዛፍ መንከባከብ የግድ ያስፈልጋል፡፡በዚህ አይነቱ ዛፍ አካባቢ 350 አማላክት ይሰበሰባሉ ታብሎም ስለሚታመን ዛፉን ጠብቆ ማቆየት የግድ ነው፡፡እንደ እኛ የአድባር ዛፍ ማለት መሆኑ ነው፡፡
የኬሻርዋኒ ቤተሰብ ዛፉ ቤቱን ከመቀዝቀዙ እና ነፈሻ እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪ፣ በአማኞች ዘንድ ባለው ትልቅ ስፍራ የዮግሽ ባለቤት ለጸሎት ወደ ሌሎች የእምነት ስፍራዎች ከመሄድ እንድትቆጠብ አድርጓታል፡፡የዘወትር ጸሎቷን ከዛፉ ፊት ለፊት ባለው ስፍራ ላይ ሆና መፈጸም እንደምትችል ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
ይህን አይነቶቹ አመለካከቶች ምድር በደን መመንጠር ሳቢያ ክፉኛ ራቁቷን እየቀረች ባለችበት በአሁኑ ዘመን በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡
ቤቱ ተገንብቶ እንዳበቃ የአካባቢው የመሀንዲሶችና አርክቴክቶች ማሰልጠኛዎች አይን ውስጥ መግባቱን ዮግሽ ያስታውሳል፡፡አሁን ቤቱ ከጃባልፑር ዋና ዋና የቱሪስት መስህቦች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡‹‹ዛፉ እኛን የተጋፋበት ምንም አይነት ሁኔታ ባለመኖሩ ፣ዛፉ ስለመኖሩ ምንም አይሰማንም›› ያለው ዮግሽ ዛፉ በራሱ መንገድ የቆመ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2011
ዘካርያስ