ለሰው ልጅ ታማኝ ከሆኑ እንስሳት መካከል ውሻን የሚስተካከለው የለም ማለት ይቻላል፡፡በዚህም በዚያም የምንሰማው ፣ራሳችንም የኖርነው እውነታ እንደሚያመለክተውም ውሻ ታማኝ የቤት እንስሳ መሆኑን ነው፡፡ስለታማኝነቱ እንጂ ስለከዳተኛነቱ ብዙም የተባለ የለም፤ ለእዚህ ውለታው ምን ያህል ተከፍሎት ይሆን ? ‹‹ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ …›› እንዲሉ ለውለታው ተገቢውን ዋጋ ከመክፈል ይልቅ ሲያረጅ ፣ሲታመም ወይም ሌላ ጉዳት ሲደርስበት ከቤት ይባረራል፡፡
ሰሞኑን ከወደ ቻይና የተገኘ መረጃ ግን ውሾችን ለመንከባከብ ሲል መስዋዕትነት ስለከፈለ ግለሰብ አትቷል። ቻይናዊው “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እንደሚባለው የጎዳና ውሾች መንከራተት አሳዝኖት መስዋዕትነት ሲከፍል መረጃው አስነብቦናል።
ቻይናዊው አፍቃሪ እንስሳ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለቤት አልባ የጎዳና ተዳዳሪ ውሾችን ሲንከባከብ ቆይቷል፡፡ ለውሾቹ ሲል 600 ሺህ የን ወይም 87ሺህ ዶላር ዕዳ ውስጥ ቢገባም፣ ባለ አራት እግር ወዳጆቹን አሳልፎ መስጠት አልፈለገም።
የ41 ዓመቱ ዣን ካይ ከቼንጉዱ ቻይና ሰላማዊና ምቾት የተሞላበት ሕይወት ይመራ ነበር።የአንድ ሀገር በቀል ኩባንያ አስተዳዳሪ ሆኖ እያገለገለ የራሱን የጉዞ ወኪልም በመክፈት ሰርቷል።
ዣን ካይ ያሳደገውና ለ13 ዓመት አብሮት የቆየ ውሻው በድንገት ሲሞት ነገሮች ይለዋወጡበታል። አሳዛኙ ክስተት ሕይወቱን አናጋበት፤ከዚያም በከተማው ያሉ መጠለያ አልባ ውሾችን ትኩረት በመስጠት መሰብሰብ ጀመረ።በቅድሚያ ሁለት ውሾች ወስዶ በጉዞ ወኪል ቢሮው ማሳደግ ቢጀምርም፣ ስምንት ጎዳና ተዳዳሪ ውሾች እያሳደገ መሆኑን ያወቀው ዘግይቶ ነበር።ይህ አሀዝ 260 ይደርሳል፡፡
እነዚህን ውሾች በባንክ ብድርና በሌሎች ልገሳ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ለመንከባከብ መታገል ውስጥም ይገባል። ዣንግ በጉዞ ወኪል እየሠራ ስምንት ውሾች በነበሩት ወቅት ሥራው ላይ ጫና እንደፈጠረበት ሲገነዘብ በቼንግዱ መውጫ የሚገኝ አንድ ቤት ለእንስሶቹ ማሳደጊያ ይከራያል።ቤቱን የተወሰነ ጊዜ ቢገለገልበትም የውሾቹ ጩኸት ጎረቤቶችን ይረብሻል፡ ፡በዚህ የተነሳም ከቦታ ቦታ እያዘዋወረ ማኖር የግድ ሆኖበት ቆይቶ በመጨረሻ ከቤቱ 10 ደቂቃ አቅራቢያ በተከለለ ሥፍራ የራሱን አነስተኛ የእንስሳ መጠለያ ማዕከል ይከፍታል።
ስምንት ውሾችን አይደለም አንዱንም ማሳደግ ለአብዛኞቻችን ፈፅሞ የማይታሰብ ቢሆንም፣ ዣንግ ካይ ግን በአግባቡ ያኖራቸው ነበር፡፡በየጊዜውም ተጨማሪ የጎዳና ተዳዳሪ ውሾችን ይሰበስብም ነበር።
በቼንግዱ መውጫ ውሾቹን መመገብ ሲጀምር ብዙ የጎዳና ውሾች ሲንከራተቱ ይመለከታል፤ከውሾቹ መካከልም አንዳንዶቹ የህክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሆነው ያገኛቸዋል፡፡እነዚህን ውሾች ወደ መጠለያው ይወስዳቸዋል።ውሾቹን ለመጠበቅ የሚያደርገው ወጪ፤ ከሚያገኘው ክፍያና ከንግድ ድርጅቱ ገቢ በእጥፍ ለመብለጥ ረጅም ጊዜ አልወሰደበትም፤ ስለዚህ ከባንክ ብድር መውሰድ ውስጥ ይገባል።
ለዓላማው በከፈለው መስዋዕትነት የተደነቁ ሌሎች አፍቃሪ እንስሳት የተወሰነ ርዳታ መስጠት ቢጀምሩም፣ ይህም ቢሆን የውሾቹ ቁጥር በፍጥነት ሲጨምር በቂ አልሆን እያለ ይመጣል።በ2019 መጀመሪያ ዣንግ ካይ 300 ቡችሎችን ማሳደግ ውስጥ ይገባል፤ ይህም አሀዝ እስካሁን ከተንከባከባቸው ውሾች በጣም ከፍተኛው ነው።
ከእነዚህ ውሾች ከፊሎቹ እንዲያሳድጋቸው በጉደፈቻ የተሰጡት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 260 ውሾችን እየተንከባከበ ነው፡፡ባለፈው ግንቦት ዣክ ለዘጋቢዎች እንደተናገረው ዘወትር 40ኪግ ምግብ ይገዛል ፤በየወሩ ለውሾቹ ምግብና ለመሳሰሉት 20ሺ የን ያወጣል፤ ውሾቹን ለሚንከባከቡለት ሁለት ሠራተኞቹም ወደ 6ሺ የን በየወሩ ወጪ ያደርጋል።ይህም ወርሃዊ ወጪ ለውሾቹ ህክምና የሚያስፈልገውን ወጪ አያካትትም።
ከሁለት ዓመታት በፊት አፍቃሪ እንስሳት የመጀመሪያውን 200 ሺ የን የባንክ ብድሩን እንዲከፍል ገንዘብ ቢሰጡትም፣ ብድሩን የሚከፍልበት ጊዜ አልነበረውም፡፡የጎዳና ውሾቹን ቁጥር በጨመረ ቁጥር ዕዳውም እየጨመረ ሄደ። በመጀመሪያው ዓመት ብቻ 600ሺ የን ዕዳ ነበረበት፤ ወርሃዊ ወጪውን ለመሸፈን ከአባቱ በምስጢር 20ሺ የን እስከ መውሰድ ደርሶም ነበር ።
የዣንግ እናት ሁዋንግ ሚንግሹ”ውሾች እንደሚያረባ እናውቃለን፤ ቤተሰቦቹ ስለ ጉዳዩ ሲጠይቁት ምርጫ ስለሌለው ቁጠባውን በሙሉ ማውጣቱንና በዕዳ ውስጥ መዘፈቁን አረዳቸው።” ሲሉ ይናገራሉ።
ዕድሜያቸው 69 እና 70 የሆኑ የዣንግ ካይ ታላላቆቹ የቤተሰቡ አባላት እየተጦሩ መደሰት በሚገባቸው ዘመን ይህን ወጪ ለማገዝ በሚል ወደ ሥራ ለመሰማራት ተገደዋል። በዚህም ዕዳውን ለመቀነስ አስበው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ዣንግ ባለፈው ወር የባንክ ሂሳቡን ሲያጣራ እስካሁን ለባንኮች 510 ሺ የን ወይም 74 ሺ ዶላር መክፈሉን ተረድቷል።
“ውሾቹን ባያረባ ይሻል ነበር፤ ይህ ባይሆን ኖሮ ሁላችንም ሰላም እንሆን ነበር ፤አሁን ግን እሱ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡ በሙሉ በዕዳ ተዘፍቋል።”ሲሉ እናቱ ተናግረዋል።
የዣንግ ካይ የፋይናንስ ሁኔታ በአደገኛ ሁኔታ ስለመገኘቱ እሱም በአካባቢው ያሉትም ያውቃሉ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በውሾቹ ምክንያት እጁን መስጠት አልፈለገም፡፡
“ውሾችን ማሳደግ ስትጀምር በአጠቃላይ እንደ ሰው መሆናቸውን ትረዳለህ ።”ሲል ዣንግ ካይ ይናገራል።”ውሾችን ማንም አይፈልጋቸውም፤ እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ወስዶ መንከባከብ የኔ ኃላፊነት ነው።”ይላል። የሰበሰበበትን ዘመን በመግታት የተረጋጋ ኑሮውን ለመምራትና የራሱን ሥራ ለመጀመር በመጣር ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2011