የኢትዮጵያ እስላማዊ ቅርሶች

ኢትዮጵያ በዓለም በሀይማኖት፣ በባህልና በልዩ ልዩ እሴቶች ሀብት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት ትመደባለች። በተለይ በሀይማኖቱ ረገድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠሩና ጥንታዊ መሰረት ያላቸውን ተቋማት በውስጧ ይዛለች።

ከእነዚህ ሃይማኖቶች መካከል ሕዝባዊ መሰረታቸው ሰፊና ጠንካራ የሆኑት የክርስትናና እስልምና ሃይማኖች ይጠቀሳሉ። የእምነቶቹ ተከታዮች ቁጥር መብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በባህልና፣ በታሪክ፣ በቅርስ እንዲሁም በዜጎች የእለት ተእለት የኑሮ ዘይቤ ላይ ባሳደሩት በጎ ተፅእኖም በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ሀይማኖታዊ መሰረት አላቸው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ እስላማዊ ቅርሶች ይገኙበታል። እስልምና በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናትን የተሻገረ ታሪክና አሻራ ያለው መሆኑን አጥኚዎች በተለያዩ መረጃዎቻቸው፣ ምርምሮቻቸውና ማስረጃዎቻቸው ያመለክታሉ። ከአስተምሮቱ ባሻገርም ለታሪክ ለትውልድ የሚተላለፉ የአገር ሀብቶችና የእስልምናን መሰረት የሚያወሱ ቅርሶች በኢትዮጵያ ለዓለም ማበርከት እንደተቻለ እነዚሁ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ በሃይማኖትና ባህላዊ ይዘቱ የሚታወቀው በምስራቁ የሐረሪ ክልል በድምቀት በየዓመቱ የሚከበረውን ሸዋል ኢድ በአልን በዚህ ዓመት የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ አድርጎ መመዝገቡ ይታወሳል። ይህ ስኬት ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ እስላማዊ ቅርሶች በስፋት እንዲታወቁ በር እንደሚከፍት ይጠበቃል። በመሆኑም ምሁራን፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና ዘርፉን የሚመራው የመንግስት ባለድርሻ አካል ቅርሶቹ እንዲለሙ፣ እንዲተዋወቁና የጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆኑ በስትራቴጂ የተደገፈ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ምርምር የሚያደርጉ፣ ጥናታዊ ፅሁፎችን በልዩ ልዩ ጆርናሎች ላይ የሚያትሙ እንዲሁም የመስህብ ሀብቶቹ የዓለምን ትኩረት እንዲስቡ ባገኙት መድረኮች ላይ የሚሞግቱ ምሁራንም አሉ። ከእነዚህ መካከል እስላማዊ ቅርሶች ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው ለዓመታት የሰሩም ይገኛሉ።

ባሳለፍነው ወር የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አንደኛውን የኢትዮጵያ ዓመታዊ ቅርስ ምርምር ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት የጥናት ውጤቶቻቸውን ካቀረቡት መካከል አንደኛው በኢትዮጵያ የሚገኙ እስላማዊ ቅርሶች ላይ ስራቸውን አቅርበው ነበር።

ረዳት ፕሮፌር አህመድ ዘካሪያ የታሪክ ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም በእስልምናና በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ቅርሶች ላይ የሰሩ ምሁር ናቸው። ረዳት ፕሮፌሰሩ በተለይ የኢትዮጵያን የእስልምና ቅርሶች በሚመለከት ሰፋ ያሉ ጥናቶችና ምርምሮችን አድርገዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አፍሪካ ውስጥ አሉ ከሚባሉት ጥንታዊና የመጀመሪያ መስኪዶች መካከል አል ነጃሺ ቀዳሚው ነው። ይሁን እንጂ ይህንን ቅርስ ለመጠበቅ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅ በቂ ስራዎች አልተሰሩም። በዚህ ምክንያት ሌሎች አገራት የታሪክ ሽሚያ ውስጥ መግባታቸውን ያነሳሉ። በተለይ በሱዳን፣ በሶማሊያ እና በኤርትራ ውስጥ የመጀመሪያው መስጂድ አል-ነጃሺ እንደሚገኝ በመግለፅ የተሳሳተ ትርክት መኖሩ የዚህ ማሳያ ነው።

‹‹እስልምናና ኢትዮጵያ ተጨባጭ ትስስር አላቸው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በምሳሌነት በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያውን አዛን ያሰማውን (የሶላት ጥሪ) ያሰማውን ቢላል አል-ሀበሺን ይጠቅሳሉ። ይህንን ታሪካዊ ሀብት ለዓለም አጉልቶ በማስተዋወቅ በቅርስነት በመመዝገብ እና በሀይማኖታዊ መስህብ ሀብትነት ለመጠቀም መስራት ተገቢ መሆኑን ያስረዳሉ።

በውጪ አገር አጥኚዎች በ1920ዎቹ አካባቢ በተደረገ ጥናት ከሐረር እስከ አዲስ አበባ ባለው ቦታ ላይ በርካታ እስላማዊ የአርኪዮሎጂ ቅርሶች ተገኝተዋል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ፤ በተመሳሳይ ከዳህላክ እስከ ሐረር በርካታ የመቃብር ቦታዎች መገኘታቸውን ያመለክታሉ። በዓለም ላይ ያሉ አብዛኛዎቹ ታላላቅ ቅርሶችም (አክሱም፣ ግብፅ እና ሌሎች) ከመቃብር ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ያነሳሉ። በዚሁ መሰረት በኢትዮጵያ በሚገኙ የመቃብር ስፍራዎች የእስልምና ታሪካዊ መረጃና ማስረጃዎች መገኘታቸውን ይናገራሉ።

ረዳት ፕሮፌሰሩ ለበርካታ ዓመታት ባደረጉት ምርምር ጥንታዊ መስኪዶች፣ የመቃብር ስፍራዎች የእስልምናን ታሪክ፣ የሃይማኖቱ ተከታዮቹን አሰፋፈር እንዲሁም ሌሎች የታሪክ እና የባህል ሀብቶች መለየት መቻላቸውን ይገልፃሉ። በተለይ በአፋር፣ በሐረሪ፣ በድሬዳዋ፣ በሶማሌ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እነዚህ እስላማዊ ቅርሶች በስፋት እንደሚገኙም ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ስፍራዎች በቂ ጥበቃ፣ እንክብካቤ አለማግኘታቸውን ያስረዳሉ።

በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበው የሐረር ጀጎል ግንብና በከተማዋ ውስጥ ከ83 በላይ ጥንታዊ መስጂዶች እንደሚገኙ የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በክልሉ በአጠቃላይ እስላማዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ስፍራዎችና የመስህብ ቦታዎች በብዛት እንደሚገኙ ይጠቁማሉ። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ እንደ ድሬ ሼህ ሁሴን፣ የመውሊድ ክብረ በዓል እና ሌሎችም እስላማዊ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዓለም ቅርስነት የመመዝገብ አቅም እንዳላቸው በመግለፅ ኢትዮጵያን ሊያስተዋውቁ የሚችሉ እምቅ ሀብት መሆናቸውን ይናገራሉ። በተለይ ዛሬም ድረስ ውበት፣ ታሪክ እና ትውፊቱን ጠብቆ የቆመው ድሬ ሼህ ሁሴን በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ያለበት ታላቅ ቅርስ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ ይገልፃሉ።

መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ይህ ስፍራ ይህ ስፍራ በ11ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባ እና ዛሬም ድረስ በውበት ቆሞ የዚያን ጊዜውን እውቀት የሚናገር ቅርስ ነው። በጊዜው የእስልምና ሃይማኖት መሪ የነበሩት አባት ድሬ ሼህ ሁሴን ይህን ስፍራ በውብ ጥበብ ማስገንባታቸውንም መዛግብት ያስረዳሉ።

በድሬ ሼህ ሁሴን መስኪድ የእስልምና ሃይማኖትን በማስተማር ብዙ የእምነቱ ተከታዮችን በሃይማኖቱ ስርአት እና ሕግጋቶች እንደታነፁ መረጃዎች ያመለክታሉ። ሼህ ሁሴን የእስልምና ሃይማኖትን ከማስተማር ጎን ለጎንም በዚህ ስፍራ ላይ ሰው ሰራሽ ሃይቅን የመገንባት፣ በእርከን ስራ ተራሮችን የማልማት እና ከብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመተባበር እና በመዋደድ በአብሮነት የመኖር ብሂልን ይመሩ የነበሩ አባት መሆናቸውን፤ በተጨማሪ ሳይንስ አዋቂ እና አርቀው አሳቢ መሪ እንደነበሩ መዛግብት ያስረዳሉ።

‹‹የኢትዮጵያን ቅርሶች፣ ባህሎችና ታሪኮች ጠብቆ ለትውልድ ከማስተላለፍ ባሻገር ለቱሪዝም በምን መልኩ መጠቀም እንደሚገባ ስትራቴጂ ሊነደፍ ይገባል›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ አህመድ ዘካሪያ፤ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰነድ ከማዘጋጀት፣ እና ቅስቀሳ ከማድረግ ባሻገር በቅድሚያ ቀጥታ ማህበረሰቡ እንዲያውቀው፣ እንዲጠቀምበትና በሀብቱ የኔነት እንዲሰማው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። ይህንን መተግበር ከተቻለ በቀላሉ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ማስገባትና የቱሪዝም መስህብ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ ቀጣዩ ቀላል ስራ መሆኑን ይገልፃሉ። እስላማዊ ቅርሶችም ይህንን መንገድ እንዲከተሉ ማልማት፣ መጠበቅና ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

የእስልምና እምነት ተከታዮች ከመካ መዲና ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው በእስልምና እምነት ታሪክ ውስጥ ዋነኛው ሁነት እንደሆነ የሚያነሱት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ፣ ይህ እውነታ ኢትዮጵያን በእስላማዊ አስተምሮ፣ በታሪካዊና በሃይማኖታዊ ቅርስ እምቅ ሀብት ካላቸው አገራት ተርታ እንደሚያሰልፋት ይናገራሉ። ይህንን እድል ተጠቅሞ ቅርሶቹ ለቱሪዝም አስተዋፆኦ እንዲኖራቸው መላው ዓለምም በቂ እውቀት ስለ ኢትዮጵያ እስላማዊ ቅርስ እንዲኖረው መስራት ይገባል ይላሉ።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱት በመካ የነበሩ ሙስሊሞች ያጋጠማቸውን እንግልት ተከትሎም ነብዩ መሐመድ ምዕመኑ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ እንዲጠለሉ ምክር ሰጥተዋቸዋል። ይህ ሁኔታም ኢትዮጵያ በመላው ዓለም በሚገኙ ሙስሊሞች ዘንድ ልዩ ቦታ እንድታገኝ አስችሏታል። ኢትዮጵያ ጥንታዊ መስጊዶችን ጨምሮ፣ የቅዱስ ቁርአን፣ መድረሳ እና መንዙማዎችን እና የተለያዩ እስልምናን የሚገልጹ ቅርሶች ባለቤት ሆናለች። ይሁን እንጂ ልክ እንደሌሎቹ የዓለማችን ክፍሎች ጎብኚዎች በበቂ ሁኔታ ወደ አገሪቱ እየገቡ አይደለም።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚገልፁት ኢትዮጵያ ካላት ቀዳሚ እስላማዊ ቅርስ አንዱና ዋንኛው በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተገነባ እና በአፍሪካ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለትን የአል ነጃሺ መስጊድ ነው። ታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በእስልምና አስተምሮ ከፍተኛ ክብር የሚሰጣት አራተኛዋ ከተማ መሆኗን አንስተዋል፡፡ ምንም እንኳን ከተማዋ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበች ቢሆንም በአፍሪካ እና በመላው ዓለም ሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ መታወቅ ባለባት ልክ እንዳልታወቀችም ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም በመላው ዓለም ለሚገኙ ሙስሊሞች የሐረርን ባሕላዊ እና ማኅበራዊ ትስስር ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ማስተዋወቅ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ ለዚህም በያዝነው ዓመት በዩኒስኮ የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የሰፈረውን የሸዋል ኢድ እና ሌሎች ቅርሶች እንደ መልካም እድል መጠቀም ያስፈልጋል የሚል ምክረ ሀሳብ ይሰጣሉ።

እንደ መውጫ

ኢትዮጵያ ከእስልምና ሀይማኖት ጋር በተያያዘ በርካታ የመስህብ ሀብቶች ባለቤት ብትሆንም በሚፈለገው መጠን ጎብኚዎችን መሳብ እንዳልቻለች በተደጋጋሚ ይነሳል። ከእስላማዊ ቅርሶች ባሻገር በሌሎች የመስህብ ሀብቶች ላይም ተመሳሳይ ነገር ይስተዋላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንግስት የቱሪዝም ዘርፉን ከዋንኛ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ በማድረግ፣ ታላላቅ የመዳረሻ ልማት ስራዎችን በማከናወን ስር ነቀል የሚባል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ገብተው ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ማንነታቸውን የሚያንፀባርቁ የመስህብ ሀብቶችን እንዲጎበኙ፣ ከዚያም ባሻገር ለቀሪው ዓለም እንዲያስተዋውቁ የሚያስችል ንቅናቄ መፍጠር ነው። ባለፉት ዓመታትም ሀይማኖታዊ በዓላትን ተከትሎ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን በማድረግ ውጤት መታየት መጀመሩን መረጃዎች ያሳያሉ። በምሳሌነትም የረመዳንና ሌሎች መሰል በዓላትን በማስመልከት የሁለተኛው ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው መግባታቸው ይታወቃል። ይህ ጅምር እስላማዊ ቅርሶች እና መስህቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁና ትኩረት እንዲያገኙ መንገድ እንደሚከፍት ይጠበቃል።

ምህዳሩ ቢመቻች በመላው ዓለም የሚገኙ የሀይማኖቱ ተከታዮችም ሆኑ ሌሎች ጎብኚዎች ስለ ኢትዮጵያ ኢስላማዊ ቅርሶች ይበልጥ ማወቅ እንደሚሹ ጥርጥር የለውም፡፡ ይህን በማድረግ የሀገሪቷን የቱሪዝም ዘርፍ በሌላ ተጨማሪ አቅጣጫ ማሳደግ እንደሚቻልም እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ያሉ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲያስገነዝቡ ይደመጣል። ይህንን ምክረ ሀሳብ የሚመለከተው ባለድርሻ አካል ተግባራዊ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

ጎብኚዎችን ትኩረት ያደረጉ ልዩ መርሀ ግብሮች በማዘጋጀት የቱሪዝሙን ዘርፍ የበለጠ ማነቃቃት እንደሚቻል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባየናቸው ምሳሌዎች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ስላሉት ኢስላማዊ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስፍራዎች የበለጠ እንዲያውቁ በማድረግ በኩል መንግስት እና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መላው ዓለምም ኢትዮጵያ ሙስሊምና ክርስቲያኑ አብሮ ባህሉን እና ሃይማኖቱን የሚያከብርበት ሀገር መሆኑን እንዲገነዘብ ተከታታይ የማስተዋወቅ ስራዎች ሊተገበሩ ይገባል፡፡

ዳግም ከበደ

 

 

አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2016 ዓ.ም

Recommended For You