ሳምሰንግ በ55 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሠራተኞቹ የሥራ ማቆም አድማ መቱ

የደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሠራተኞቹን የደመወዝና ጉርሻ ጥያቄ ለመፍታት ቃል ገብቷል በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ የሳምንሰንግ ኩባንያ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ጀምረዋል።

በሥራ ማቆም አድማው ከኩባንያው የደቡብ ኮሪያ ሠራተኞች ሩብ የሚሆኑት (28 ሺህ ገደማ) እንደሚሳተፉ የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ማህበር አስታውቋል። በኩባንያው የ55 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያው ነው የተባለው የሥራ ማቆም አድማ ዋነኛው ምክንያት የደመወዝ እና ጉርሻ ወይም ቦነስ ጥያቄ አለመመለሱ ነው ተብሏል።

የኩባንያው የሠራተኞች ማህበር ከዓለማችን ቀዳሚው የስማርት ስልኮች አምራች ተቋም ጋር ሲያደርገው የነበረው ድርድር ውጤት ባለማምጣቱ ሠራተኞች በዛሬው እለት ፈቃድ ወጥተው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ማቅረቡን ሲኤንኤን ዘግቧል።

የማህበሩ ሊቀመንበር ሰን ወሞክ አብዛኞቹ ሠራተኞች አመታዊ ፈቃዳቸውን ተጠቅመው የሥራ ማቆም አድማውን መቀላቀላቸውን ያሳወቁ ሲሆን፥ በሴኡል በሚገኘው የተቋሙ መሥሪያ ቤትም ሠራተኞች ተቃውሟቸውን ማሰማት መጀመራቸው ተዘግቧል።

“ሠራተኞችን አክብሩ ! የ6 ነጥብ 5 ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ ወይም የ 200 ፐርሰንት ጉርሻ አይደለም ጥያቄያችን” ሲሉ መደመጣቸውንም ፍራንስ 24 አስነብቧል።

ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የሚውሉ ሚሞሪ ቺፕስ በማቅረብ ቁጥር አንድ የሆነው ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ከጥር ወር ጀምሮ ከሠራተኞች ማህበሩ ጋር በደመወዝና ዓመታዊ ጉርሻ (ቦነስ) ሲያደርጉት የቆዩት ድርድር ስምምነት አልተደረሰበትም።

የተጀመረው የሥራ ማቆም አድማም በኩባንያው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ያለመ ነው ተብሏል። የሳምሰንግ ቃልአቀባይ ግን ፈቃድ የወሰዱ ሠራተኞች ቁጥርን ባይጠቅሱም የሥራ ማቆም አድማው በኩባንያው የእለት ተዕለት ሥራ ላይ ምንም አይነት ጫና እንደማይፈጥር ነው የተናገሩት።

ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር የተጀመረው ድርድር ቀጥሎ ቅሬታውን ለመስፋት እንደሚሠራም ቃል ገብተዋል። የሳምሰንግ ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየገነነ መሄድ በስማርት ስልክም ሆነ በማይክሮ ቺፕ ገበያው ይበልጥ ተፈላጊነቱን ጨምረውለታል።

ባለፈው ወርም በ2024 የመጀመሪያ ሩብ አመት ገቢው በ10 እጥፍ ማደጉን መግለጹ የሚታወስ ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You