ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ ብርታት የሚያጥራቸው ሕፃናትና አረጋውያን፣ ለብዙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችም የበለጠ ተጋላጭ ናቸው። አካላቸውና አዕምሯቸው ያልጠናው ለጋ ሕፃናት እና ብዙ ደክመው በማምሻ እድሜያቸው ላይ አቅም የከዳቸው አረጋውያን፣ የቤተሰብና የዘመድ እንክብካቤ በሚፈልጉበት የእድሜያቸው ምዕራፍ ላይ ለችግር ተጋላጭ ሲሆኑ ችግሮችን የሚቋቋሙበት ብርታት አያገኙም። ‹‹የብርሃን ልጆች›› የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት የተመሰረተው የሀገር ተረካቢና የሀገር ባለውለታ የሆኑትን እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማገዝ ነው።
‹‹የብርሃን ልጆች›› የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ያሬድ ብርሃኑ እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ በጎዳና ላይና በቤተ-ክርስቲያን ዙሪያ የሚኖሩ ሕፃናትንና አረጋውያንን ሕይወት የማሻሻል ዓላማን ይዞ በ2012 ዓ.ም ነው የተመሰረተው። ሕፃናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች እንደመሆናቸው ከፊታቸው ብዙ እድሎችና ኃላፊነቶች ስለሚጠብቋቸው ገና እንደተወለዱ ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው አይገባም። በመሆኑም ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ከአስር ዓመት በታች የሆኑ፣ እናት ወይም አባት የሌላቸው እንዲሁም እናትና አባት ኖሯቸውም የሚረዳቸው የሌላቸው ችግረኛ ሕፃናትን ነው።
አረጋውያን የሚረዳው ደግሞ የሀገር ባለውለታዎች በመሆናቸው እድሜያቸውን መሰረት አድርጎ በሚመጣ እርጅና ምክንያት ለብዙ ችግሮች በመሆኑና በተለይ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋውያን መደገፍ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመኑ እንደሆነ ያስረዳሉ።
‹‹የብርሃን ልጆች›› በትምህርት፣ በጤና፣ በማኅበራዊ ድጋፍ፣ በአልባሳት እና በሌሎች ዘርፎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን የሚያከናውን መሆኑን ያመለክታሉ። ድርጅቱ ስራውን የጀመረው ለተቸገሩ ሰዎች አልባሳትን በመስጠት እንደሆነ አስታውሰው፤ ‹‹አልባሳት በመስጠት ጀምረን ሕፃናትንና አረጋውያንን ከጎዳና ላይ በማንሳት ቀጠልን። በወቅቱ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ድጋፍ እያሰባሰብን በሚገኘው ገንዘብና በመረጡት የስራ መስክ እንዲንቀሳቀሱ አድርገናል። ከጎዳና ላይ እያነሳን ቤት እየተከራየን፣ ስራ መስራት ለሚችሉት፣ በተለይም ሕፃናትን ለያዙ ወጣት ሴቶች የስራ እድሎችን በመፍጠር ራሳቸውን እንዲደጉሙ አድርገናል›› ይላሉ። ጎዳና ላይ ይኖሩ ለነበሩ 70 ሕፃናት ደግሞ ቤት የተከራዩላቸው መሆኑንና ብዙዎቹ ወደተከራዩላቸው ቤት ገብተው መኖር ጀምረው እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ብዙ ዓይነት ባህርያት አላቸው›› የሚሉት መምህር ያሬድ፣ ድርጅቱ ቤት ቢከራይላቸውም አንዳንዶቹ ልጆች ተመልሰው ጎዳና ላይ ያድሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹ለስራ መስሪያ የሰጠናቸውን ገንዘብ አባክነው በድጋሚ የሚጠይቁም ነበሩ። ስራውን ስንጀምር ጎዳና ላይ የሚኖር ሰው ሁሉ የተቸገረ ይመስለን ነበር። በእርግጥ የተቸገሩና ለመለወጥ ዝግጁ የሆኑ እንዳለ ሁሉ፣ የጎዳናን ሕይወት እንደምቾት ቀጣና (Comfort Zone) የሚቆጥሩትም እንዳሉ ታዝበናል። ተመልሰው ወደ ጎዳና የወጡም ነበሩ። ይህ ችግር የመጣው የጎዳና ሕይወት በሚያሳድረው ተፅዕኖ ምክንያት ነው›› በማለት ያብራራሉ።
ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ተግባራት ሕፃናት እንዲማሩ አስችሏል። በትምህርት ዘርፍ ስራዎችን ሲጀምር የትምህርት ቁሳቁስን ለሕፃናት በመስጠት ነበር። በችግር ላይ የሚገኙት ሕፃናት የቤተሰብ ክትትል ስለማይደረግላቸው የትምህርት አቀባበላቸው ደካማ ነው። ድርጅቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጎ ፈቃደኛ መምህራንን በማስተባበርና በአራዳ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ‹‹ኒው ኤራ›› ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር በክረምት ነፃ ትምህርት ሰጥቷል።
በዚህ መርሃ ግብር ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ 328 ተማሪዎች ተምረዋል። ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ዘንድሮም ይህ የትምህርት መርሃ ግብር ሐምሌ አንድ ቀን 2016 ዓ.ም ይጀምራል። መርሃ ግብሩ ተማሪዎችን ለቀጣዩ ዘመን የትምህርት ደረጃ እንዲያዘጋጃቸው ከማድረግ በተጨማሪ በትምህርታቸው ደካማ የሆኑትን እንዲበረቱ ያግዛቸዋል።
በጤናው ዘርፍ ደግሞ ሕፃናትና አረጋውያን ሲታመሙ ለሕክምናቸው የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ፣ 40 በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞችን በማስተባበር ሕፃናትና አረጋውያን ነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል። በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞቹ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ከአፍንጮ በር ጤና ጣቢያ፣ ከማሪስቶፕስ፣ አይኬርና ራስ ክሊኒኮች እና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሕክምና ባለሙያዎች ማህበር የተውጣጡ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በመጀመሪያው ዓመት 70፣ በሁለተኛው ዓመት 100 እንዲሁም ዘንድሮ 152 ሰዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል። የሚሰጡት የሕክምና ዓይነቶችም በየጊዜው እየሰፉ መጥተው በአሁኑ ወቅት ስምንት ዓይነት ሕክምናዎች (የዓይን፣ የጆሮ፣ የጡት ካንሰር፣ የማህፀን በር ካንሰር፣ የጥርስ፣ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ በሽታዎች፣ የውስጥ ደዌ ሕክምናዎች) በነፃ እየተሰጡ ናቸው። በማኅበራዊ ድጋፍ ረገድ ደግሞ ድርጅቱ በበዓላት ወቅት የአልባሳትና ሌሎች ድጋፎችን ያደርጋል። ጎዳና ላይ ከወጡት ይልቅ ወደ ጎዳና ለመውጣት ጫፍ የደረሱ ሰዎችን ለመርዳት ‹በጎ ማዕድ› የተሰኘ የስፖንሰርሺፕ ፓኬጅ አዘጋጅቶ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል።
ድርጅቱ በሦስት ዓመት ከአስር ወራት እድሜው በትምህርት፣ በጤናና በማኅበራዊ ድጋፍ ዘርፎች ከ4660 በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ብዙ የበጎ አድራጎት ተግባራትን አከናውኗል። በቋሚነት ከሚደግፋቸው 18 አረጋውያን እና 33 ሕፃናት በተጨማሪ በአልባሳት 2 ሺ 483፣ በማኅበራዊ ድጋፍ 1ሺ158፣ በትምህርት 645 እና በሕክምና 325 ሰዎችን ተጠቃሚ አድርጓል።
ድርጅቱ ያከናወናቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ብዙ አዎንታዊ ውጤቶችን ማስመዝገባቸውን መምህር ያሬድ ይናገራሉ። ‹‹የበጎ አድራጎት ስራዎቻችን በትምህርት፣ በጤና እና በማኅበራዊ ድጋፍ ዘርፎች ብዙ መልካም ውጤቶችን አስገኝተዋል። ለአብነት ያህል በአምስት ሺ ብር መነሻ ገንዘብ ጧፍ እንድትሸጥ ስራ ያስጀመርናት ልጅ ከ57ሺ ብር በላይ መቆጠብ ችላለች›› ሲሉም ይገልፃሉ።
‹‹የብርሃን ልጆች›› የያዘውን ዓላማ ለማሳካት የሕፃናትንና አረጋውያን መንደር እንደሚያስፈልገው መምህር ያሬድ በአፅንዖት ይናገራሉ። ‹‹የበጎ አድራጎት ስራና ምቹ ሰፊ ቦታ ይፈልጋል። ድርጅቱ ይዞት የተነሳውን ሕፃናትንና አረጋውያንን ዘላቂ በሆነ መልኩ የመደገፍ ዓላማን ለማሳካት ማዕከል ያስፈልጋልም ባይ ናቸው። ሰዎቹ ችግራቸው የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የስነ-ልቦናም ጭምር ነው። ስለሆነም ከስነ-ልቦና ችግሮቻቸው የሚያገግሙበትና እንክብካቤ የሚያገኙበት ማዕከል ያስፈልጋል። ይህን ማዕከል ለመገንባት ደግሞ 30ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ሊኖር ይገባል›› ይላሉ።
ይሁንና ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ስራዎቹን ሲያከናውን ከሚያጋጥሙት መሰናክሎች መካከል አንዱ የማዕከል አለመኖር ነው። ‹‹ዓላማችንን ለማሳካት ማዕከል መገንባት ያስፈልገናል። ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገውን የ30ሺ ካሬ ሜትር የቦታ ጥያቄውን በየደረጃው ለሚገኙ የአስተዳደር አካላት አቅርበናል። ወደ ዋናው ስራችን ለመግባት መንግሥት የምንሰራውን የበጎ አድራጎት ስራ አይቶ አምኖብን መሬት እንዲሰጠን እንፈልጋለን›› ሲሉም አስታውቀዋል።
<<አሁንም በኪራይ ቤት ውስጥ ነው ያለነው፤ በወር 11ሺ 500 ብር እንከፍላለን። እስካሁን ለቢሮ ኪራይ ብቻ ከ507 ሺ ብር በላይ አውጥተናል። የራሳችን ማዕከል ቢኖረን፣ ለቢሮ ኪራይ የምንከፍለውን ገንዘብ ለሌላ ተግባር እናውለው ነበር። ስራችንን ለማስፋፋት ማዕከል ያስፈልገናል። ስራ በቢሮ ደረጃ እና በማዕከል ደረጃ ሲከናወን የሰው አመለካከት የተለያየ ነው። ቢሮ ላይ ሲሆን ገንዘቡ ለግል ጥቅም ይውላል ተብሎ ይታሰባል፤ ሰው ወደ ማዕከል መጥቶ ሰዎችን ማየት፣ ከሰዎች ጋር ማውራት፣ ሰዎችን ማገልገል ይፈልጋል›› በማለት የማዕከሉን አስፈላጊነት ያስረዳሉ።
መምህር ያሬድ እንዳሉት፤ ይህ ማዕከል የመክፈት ፕሮጀክት እውን እስከሚሆን ድረስ ድርጅቱ ሁለት አማራጮችን አስቧል። አንደኛው አማራጭ ዋጋው ውድ ቢሆንም፣ አንድ ቤት/ሰፊ ግቢ/ ተከራይቶ ቢያንስ የሕፃናት ማቆያና መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት መክፈት ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ድርጅቱ ለስራው የሚሆነውን ገንዘብ የሚያገኘው ከአባላትና ከበጎ አድራጊዎች ከሚሰበሰብ መዋጮ ነው። በጤና ዘርፍ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ስራዎችን መስራት ነው።
‹‹ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሕፃናት ይለመንባቸዋል፣ በየቀኑ ምፅዋት ይጠየቅባቸዋል። እነዚህ ሕፃናት ወደ ማዕከል ገብተው እንክብካቤ ቢደረግላቸው ይማራሉ፤ ወላጆች ልጆቹን ከሚለምኑባቸው ስራ ፈልገው ሰርተው ማታ ወደ ቤታቸው መውሰድ ይችላሉ በሚል እሳቤ ማቆያና ትምህርት ቤት የመክፈት እቅድ አለን። ይህ የአጭር ጊዜ እቅዳችን ነው። በሁለተኛው አማራጭ ደግሞ መድኃኒት ቤት (Pharmacy) ከፍቶ መድኃኒት መግዛት ለማይችሉ ሰዎች የመድኃኒቱን ዋጋ 10 በመቶ ነፃ በማድረግ፣ 90 በመቶ ደግሞ ለድርጅቱ ገቢ የሚያስገኝ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም መካከለኛ ክሊኒክ መክፈት ናቸው›› በማለት ያብራራሉ።
መምህር ያሬድ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ድጋፍ የሚፈልገው ሰው ቁጥር መጨመሩ፣ የጤና አገልግሎት ክፍያ እየተወደደ መምጣቱ እና በደጋፊውና በተደጋፊው ዘንድ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ ሌሎች ፈተናዎች እንደሆኑም ይጠቁማሉ። ‹‹በፈተናዎች ውስጥ ሆነን የቻልነውን ሁሉ ለማድረግ እየሞከርን ነው››ሲሉም ይገልጻሉ።
መምህር ያሬድ ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ፈቃድ ከመስጠትና ክትትል ከማድረግ ባሻገር ለበጎ አድራጎት ተቋማት ድጋፎችን ማድረግ አለበት። በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለው የመደጋገፍ ልምድ ለውጥ ያስፈልገዋል። ሕብረተሰቡ ጠንካራ የመደጋገፍ ባህል ቢኖረውም ድጋፉ ዘላቂ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መሆን ይገባዋል›› በማለትም ይመክራሉ።
‹‹የብርሃን ልጆች›› የሕፃናትና የአረጋውያን መንደር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሏቸው የበጎ አድራጎት ተግባራትን ሲያከናውን በመቆየቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጨምሮ በየደረጃው ከሚገኙ የአስተዳደር አካላት የዕውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀቶች ተበርክተውለታል። በግንቦት 2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምስጋናና እውቅና ተችሮታል። በትምህርት፣ በጤናና በማኅበራዊ ድጋፍ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት አገልግሎት በመስጠቱ ከአራዳ ክፍለ ከተማ ሽልማት አግኝቷል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም