ፊልምና የፊልም ጥበብ ከሀገርኛ አገልግል ውስጥ ሲበሉት ይጣፍጣል። መዓዛውም ያስጎመጃል። ከዚያ በፊት ግን ማጀቱንም ማየት ያስፈልጋል። ምስጋና ለፊልም ጠቢባኑ ይግባና አመስግነን ወደ ጎደለው ስንክሳር ውስጥ ልንገባ ነው። ጥሩ ነገሮች እንዳሉ ሆነው ለበለጠ ጥሩነት የጎደለንን ፍለጋ ከኢንዱስትሪው ማጀት ስንገባ ለምን የሚያስብሉን ጉዳዮች ለጉድ ናቸው።
ከማጀቱ ከተያዘው የጥበብ አገልግል ውስጥ ላለው ለወጡ ጥፍጥና የጎደለው ከምኑ ላይ ነው? ከባለሙያው ወይንስ ከግብአት እጥረት? እንደ አንድ የፊልም ጥበብ ወዳጅ ሲያስደስቱን እጅ ስመን ሲያጠፉ ደግሞ እጅ ይዘን ከገባን ላይ ስናሳይ ለኢንዱስትሪው በሁለት እግር መቆም የሚገባንን እያደረግን ነው። ብዙውን ጊዜ ግን ከትችትና የማብጠልጠል ስሜት ሳንላቀቅ በግራ ነው የምናደርገው።
ትችት በወግ ወጉ ሲሆን ጥሩ መስመሮችን ያሰምርልናል። በግልም ሆነ በጋራ ውስጥ ውስጡን ከማንሾካሾክ ከሂሳዊ የቅንነት እሳቤ ጋር በግልጽ አውጥተን ብንማከርባቸው ኖሮ እስካሁንም ለመፍትሄዎች ባልዘገየንና በረሀውም በለመለመ ነበር። ከብዙ የሀሳብ ቃታ ትንሷን የጥበብ ጠብታ የለውጥ አድማስ ትሆናለች።
ከፊልም ወዳጆች የጎደለን ነገር ቢኖር በትችት የምናሳጣውን ያህል በሀሳብ ማዋጣቱ ላይ አለመኖራችን ነው። ስለ ፊልሞቻችን በተነሳ ቁጥር እንደ ሀሜት ጓዳ ጓዳውን ብቻ የሚያሳልጠው ብዙ ሆኖ ሳለ፤ እንዲህና እንዲያ ቢሆን እያሉና ከችግሩ ነቅሰው ከመፍትሄውም የሚያመላክቱ ግን ጥቂቶች ናቸው። ከፊልሞች ዳሰሳ ይልቅ ለአዳዲስ ሀሳብ አሰሳ መውጣትም ወሳኙ ነጥብ ነው። የፊልም ኢንዱስትሪውን ከፍ ለማደረግ ስናስብ ሁልጊዜም ጥቃቅን ከሚመስሉ ጉድለቶቻችን መጀመር ይኖርብናል፤ ነጠብጣቦች አንድነትን ፈጥረው እንከኖቹን ወደ አራት ነጥብነት ሳይቀይሩት።
ፊልም የማኅበረሰቡ የፊት መስታየት ነው እንላለን፤ ነገር ግን ፊልሞቻችንና ማኅበረሰቡ በቅጡ ይተዋወቃሉ? አንድም ከፊልም ኢንዱስትሪው ሁለትም ከማኅበረሰቡ ሁላችንም ከአንደኛው ጋር አንድ ነገር አጉድለናል። ከሁለት አቅጣጫ የሚሰነዘር ቡጢ እያረፈበትም ይመስለኛል።
እንደ ማኅበረሰብ ጫናው በዝቶበታል፤ ጥላቻ ባይኖርበትም በማኅበረሰቡ ውስጥ በነጻነት የመዘዋወሩ ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው። ከማኅበረሰብ አንጻር በሁለት ነገሮች የበደልነው ይመስለኛል። አንደኛ፤ ፊልሙ የወጣቱ ክፍል ብቻ ተደርጎ ከመቆጠሩም በአንዳንዱ ዘንድ እንደ አደንዛዥ እጽ መታየቱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ለፊልሞች ያለው አመለካከት ለመዝናኛ ጥቅም ብቻ መዋሉ ይሆናል።
ፊልሞች የማኅበረሰቡ ነጸብራቅ ናቸው ካልን ታዲያ ማኅበረሰብ ማለት የወጣቱ ክፍል ብቻ ነው? በእድሜ የገፋው ክፍል ፊልምን መመልከት ሥራ እንደመፍታት ከመቁጠሩም የክብር ሚዛንን የሚቀንስም ሆኖ ይታያል። ታዲያ የላይኛውን ኅብረተሰብ ያማከሉ ፊልሞች ስለማይሰሩ ወይንስ እነርሱ እንደሚሉትም አላስፈላጊ ነገር ሆኖ ነው? በእርግጥ ባህላችን ቁጥብነት የበዛበት ከመሆኑ የተነሳ ወደ ማኅበረሰቡ የሚወስዱን አብዛኛዎቹ መንገዶች ዝግ መሆናቸውም አይጠፋንም።
ባህል አክባሪነት ከፊልም አያግደንም የበዛ ወግ አጥባቂነት ግን መፈናፈኛ ፋታም አይሰጡንም። ለሁሉም ነገሮች መጀመሪያው የግንዛቤ እጥረት መሆኑ ይታወቀናል። ከቤታቸው ቁጭ ብለው ድራማዎቹን የሚከታተሉ ነገር ግን ፊልም ሲባል ጥሩ ነገር የማይታያቸው ሰዎች በግሌ ገጥመውኛል። ከራሳቸው አልፎ ልጆቻቸውም ጭምር ፊልም የሚባል ነገር እንዳይመለከቱ የሚመክሩ ብዙ ወላጆችም አሉ።
እንዲህ አይነቶቹን ክፍተቶች አጥበን ከማኅበረሰቡ ጋር የምንገናኝበትን መስመር መቅደድ ይኖርብናል። ለማኅበረሰብ ተብሎ የሚሠራው ፊልም በየአጥሩ እየተንጠላጠለ የአይጥና የድመት ጨዋታ እየተጫወተ እስከመቼስ ሊዘልቅ…ወጣም ወረደም ያለውን ተቀባይነት ለማሳመር ካልቻለ ያለማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ምንም ዓይነት ለውጥ ለማምጣት አይችልም። በመሀከል የተፈጠረውን ፍራቻ በማስወገድ እራሱን የሚያይበትን የፊት መስታየት የመሰለ ፊልም ሠርተን ልናሳየውና ልናሳምነው ይገባል። ፊልሙን ለማነቃቃት ማኅበረሰቡን ማንቃት ትልቁን ሸክም እንደማቅለል ነው።
ሁልጊዜም በየትኛውም ቦታና ማኅበረሰብ ውስጥ ፊልሞቻችን ለትውልዱ የመዳኛ መንገድ እንጂ የሞት መንኩራኩር ተደርገው መቆጠር የለባቸውም። አንዳንዴም የፊልሙን መልክ የሚያጠለሹት ቅጥ አልባ ግብርና እይታዎች ናቸው። ባህል ጥሶ ወግና ሥርዓትን ፈንቅሎ ማነውስ ተመልካቹ? መጽሐፍ ተመርጦ ይነበባል፤ የፊልምን ይዘት መምረጥ ግን የፊልም ባለሙያዎችም ኃላፊነትም ጭምር። ምክንያቱም ተመልካች ሁል ጊዜም እንደ ሕጻን ልጅ ነው፤ ድጋፍን ይሻል። ሁሉም ትዕይንቶች ለሁሉም አይቀርቡም፡፡
የሀገር ውስጥ ፊልም መመልከት የማይወደውን ወዳጃቹን ጠጋ ብላችሁ ለምንድነው? ያላችሁት እንደሆን የሚሰጣችሁ ምላሾች ተመሳሳይና ከብዙዎች የሰማችሁትን ዓይነት ነው። “ኤዲያ! ደግሞ የኢትዮጵያ ፊልም…ገና ፊልሙ ሲጀምር ሳላይ ከደራሲው እኩል ታሪኩን አውቄ ጨርሰዋለሁ።
መዋደድ…መጣላት እና መታረቅ…” ይላችሁ ይሆናል። በእርግጥ አሁን አሁን በቆንጆ የታሪክ ፍሰት ያማሩ ፊልሞችን ለመመልከት ብንችልም ነገሩን ግን ከእውነትነት የምናርቀው አይደለም። በፊልሞቻችን ውስጥ ያለው የተዋናይ መረጣስ? አንዳንድ ጊዜማ ለፊልሙ ታሪክ የሚሆን ተዋናይ ሳይሆን ለተዋናዩ የሚሆን ታሪክ የምንመርጥ ነው የሚመስለው። ትናንት በአንደኛው ፊልም ጎበዝ አባት ሆኖ የተወነው ሰው ሁሌም አባት ነው።
በኢትዮጵያ ፊልሞች ውስጥ የጨካኝነትና አስፈሪ ገጸ ባህሪያትን የሚጫወቱ ሰዎች በተለይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተሰፍረውና ተለክተው የተቀመጡ ተዋንያን አሉ። አስፈሪነትና ጭካኔን ባስታወሰን ቅጽበት ድቅን የሚልብን የጥቂት ሰዎች ፊት ነው። ሌላው ቀርቶ በአንደኛው ፊልም የበር ጠባቂ የነበረው ሰው የእውነትም እስኪመስለን በቀጣይም የምናገኘው እዚያው በር ላይ ይሆናል። ይህ እንግዲህ ተዋናይ መረጣ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ፍለጋን የመሰልቸት ስንፍና አሊያም እይታ የመድገም አባዜ ነው። አንድ ቀን ከታክሲው ውስጥ ያነበብኩትን ቀልድ ቢጤ አሽሙር ትዝ አለኝ። እንዲህ የሚል ነበር፤ “የኢትዮጵያ ፊልሞች በሁለት ይከፈላሉ፤ እነርሱም እንትና ያለበትና የሌለበት” በማለት የአንድ ተዋናይ ስም ተጠቅሶበታል። ለማሳቅ የተጻፈ ቀልድ ቢመስልም የፊልም ባለሙያዎቹ ግን እንዲያስቡበት የሚያደርግ ነው።
በአንድ ሰሞን በሚወጡ ፊልሞች ውስጥ ተከታታይ ድራማ እስኪመስል ድረስ ተደጋግሞ የሚታየው የአንድ ሰው ፊት ነው። የፈለገውን ያህል ከሌላው በተሻለ ቢተውነውም ከዛ በበለጠ የፊልሙን ተአማኒነትና ውስጣዊ ኃይል ይቀንሰዋል። “ማርም ሲበዛ…” የምትለዋን ሕገ ደንብ ቢያደርጓት ጥሩ ነበር፡፡
የመገናኛው መንገድ ለምን ጠበብ? ካሉ የሚያነሷቸው እልፍ ነጥቦች አሉ። አንዳንዶቹ ነጥቦች ጠባሳም ፈጥረዋል። ከሀገራችን ፊልሞች እርቆ በባህር ማዶ ለከረመውም አይፈረድበትም እንድንል የሚያደርጉም አሉ። ስንት ሕብረ ብሔራዊ ባህልን ከታሪክ እንዲሁም ከተፈጥሮ ስነ ምህዳር ጋር በታደለች ሀገር ውስጥ የፊልሞቻችን መቼት አብዛኛዎቹ ከአንድ ወንዝ በቀር አይሻገሩም። ሌላውስ ይቅር፤ ፊልሞቻችን ሲጀምሩ ለማልበሻነት የምንጠቀመው ምስል ምንድነው? የአዲስ አበባ መከረኛ ሕንጻዎች ናቸው። ፊልሙን ልንሠራባቸው ባንችል እንኳን ቢያንስ ለማልበሻው ከታሪካዊ ስፍራዎች ብንጀምር አንድ ጥሩ ነገር ነው፡፡
በፊልም ውስጥ የቦታ መረጣ (ሎኬሽን) የፊልሙ ዋነኛ ውበት ነውና የራሱ የሆነ ባለሙያ አለው። ችግሩ ግን ለገንዘብ ቁጠባ እየተባለ አብዛኛዎቹ ከአዲስ አበባና ከዙሪያዋ በስተቀር የሚታያቸው ነገር የለም። 80 ፐርሰንት ያህሉ ማኅበረሰብ በገጠር ገጥሮ ሳለ ከግማሽ በላይ ፊልሞቻችን የሚሠሩት በከተሜነት ውስጥ ባለ በቅንጡ የአኗኗር ዘዬ ውስጥ ነው። ያ ሁሉ የአኗኗር መልኮች ክንፋቸውን ዘርግተው በጣት የሚቆጠሩት ብቻ የሚኖሩትን ኑሮ መደጋገምን ምን ይሉታል…አንድ ቀን በአጋጣሚ ካገኘሁት ሰው ጋር ስለዚሁ አንስተን ስንጨዋወት፤ ለፊልም ሥራ ተብለው የሚከራዩ ውስን ቪላና ቅንጡ መኪናዎች እንዳሉ ከነገረኝ በኋላ፤ በብዙ ፊልሞች ውስጥ አንድ ዓይነት ቤት ከአንድ ዓይነት መኪና ጋር የምንመለከተው ለዚሁ ነው አለኝ። ነገሩ ክፋት ባይኖረውም ለማኅበረሰቡ ግን ቅንጡ መኪናና ቪላ ከመመልከት ይልቅ የራሱን ደሳሳውን ጎጆና ጋሪ ቢያይ ይመርጣል።
ሁልጊዜ ያልኖሩትንና የሌለውን ከመሙላት ትንሽም ቢሆን ካለችው ላይ መቅዳት ይሻላል። ከራሱ ኑሮ እንዲማር ከማድረግ ይልቅ በሌላው እንዲጽናና ማድረጉ አይበልጥም። ኑሮ ወዲህ ማዶ ፊልሙ ወዲያ ማዶ ከሆነ ምን ሊረባ…እንዲህ ብቻ እንሥራ አይደለም፤ እንዲህም መሥራት እንዳለብን እናስብ ነው።
እርምትን የሚሹ የታሪክና የማንነት ውክልናዎችንም እንመለከታለን። ይህኛውን ነጥብ ተመልካቹም ሆነ ባለሂሱ ልብ ያላለው አሊያም አምኖ የተቀበለው ይመስላል። ለአብነትም የባላገር ገጸ ሰብና መቼት አንዱ ነው። ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ባላገርና ባላገርነት የሚገለጹት በአንድ ዓይነት መንገድ ነው። አለባበስና የቋንቋ አጠቃቀሙ ጭምር ከአንድ አካባቢና ማኅበረሰብ ጋር ብቻ ተጣብቆ የሙጥኝ ብሏል። አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ከባላገርነት ጋር ተቃቅፎ በሚኖርባት ሀገር ውስጥ፤ ባላገሩ በአንድ ውክልና ብቻ ማስቀረት ማንነትን ማራቆት ይሆናል። ይህ ብቻም ሳይሆን የጋራ መሆን የነበራቸው እሴቶቻችንም ከአንደኛው ጋር ብቻ በማያያዝ በፊልም ደረጃ መንጸባረቅ የሌለባቸው ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡
አንድን ባህል እንዲዳብር አድርጎ ማውጣቱ መልካም ሆኖ ሳለ በዚያው ልክ ደግሞ ጥንቃቄ የሚሹ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ውለው አድረው ነገ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠራቸው አይቀርም። ስንቱን ሕብር አዋህዳ በያዘች ሀገራችን ውስጥ ያሉትን ልዩ ልዩ ባሕልና እሴቶች እንኳንስ ለመደጋገምና ሠርቶ ለመጨረስ እንኳ ተዝቀው የማያልቁ ናቸው። ፊልም ማለት የማኅበረሰቡ የፊት መስታየት እስከሆነ ድረስ ባለሙያዎቹ መገኘት ያለባቸው እታች ነው።
ሁሌም አዲስ ነገርና አዲስ እይታ ለሚፈልገው ተመልካችም ስንቁ ከወዲያና ወዲያ ብቻ ነው። ከሚጠይቀው የአቅምና ከገንዘብ ሁኔታ ብቻ በመነሳት በኢንዱስትሪውም ሆነ በማኅበረሰብና ተመልካቹ ላይ በድግግሞሽ መፍረድ የለብንም። አንዱን ምስር በቀይ በሀልጫ እያደረጉ ቢወጠውጡት ያው ምስር ወጥ ነው፤ ለመልክ እንጂ ለሰውነት የተመጣጠነ ሊሆን አይችልም።
የኢትዮጵያ ፊልሞች የችግር ነጠብጣብ መጠንና ደረጃው ከፉ በማለት ከበርሜል የሚፈስባቸው ቦታዎችም ብዙ ናቸው። ከወደ መንግሥት በፊልም ቁሳቁስ ላይ የሚጣለው የግብር ጫና ሳያንሰው እዚሁ በዚሁ ደግሞ እንግልቶች ይስተናገዱበታል። በቀረጻ ወቅትም ያለው ደጅ ጥናት እንኳን ቀላል አይደለም። ፊልም ሠሪዎቻችንም ካለባቸው የገንዘብ እጥረትም ሆነ የምልከታ ጥራት ታሪክና ታሪካዊ ስፍራዎችን መጠቀም አዳጋች ሲሆን ይስተዋላል። ተመልካቹም ቢሆን የራሱን ጎራ የያዘ ነው የሚመስለው፡፡
ፊልም ግን የሚሠራው ለገንዘብና ተዝናኖት ብቻ ነው? የፊልም ባለቤቶች መሥራት ያለባቸውን ሠርተው ይክሰሩ አይባልም፤ ግን ደግሞ እንደ ቡና ንግድ ጥበብ በአህያ ተጭኖ ገበያ አይወጣም። ለሀገርና ለዘርፉ፤ ለታሪክና ኪነ ጥበብ መስዋዕትነት ለመክፈል ካልተቻለ ቢያንስ በእኩል ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ከላይ ያነሳነው በየፊልሞቹ ውስጥ ተደጋጋሚ ፊት የመመልከት ችግር የሚመጣው አንድም ከዚህ የነጋዴነት መንፈስ የሚመነጭ ነው። አንዳንድ ጊዜ ከታሪኩ በላይ የምንወደው ታሪኩን የሚነግረን ሰው ሲሆን እንመለከታለን።
የሚወዱት ተዋናይ የሚተውንበትን ፊልም መምረጥ በየትኛውም ዓለም የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለ ቢሆንም አንዳንዶቻችን ጋር ደግሞ የበዛ ነው። አብዛኛዎቹ ሠሪዎችም ይህን የስነ አዕምሯዊ የፊልም ስበትን ስላወቁበት ይመስላል፤ በየፊልሞቻቸው ውስጥ ከፊት የሚያቆሙት ተወዳጅና ታዋቂዎቹን መሆኑ።
ከብቃቱ ጋር ኩርምት ብሎ የአንድ ቀን እድልና አጋጣሚውን የሚጠባበቅ ስንቱን ታዋቂ ማድረግ ስንችል አንዱን ይዞ እንደ ዳዊት መድገም ከንቱ ነው። ገና ለገና ተመልካች የሚወደውና ትርፍ የሚያስገኝበት መንገድ ነው ተብሎ በሰርጥና ሰንበሌጥ ውስጥ መሯሯጥ ለዘርፉ ጥበብ መዘዝ አለው። በፊልም ውስጥ ተመልካች ወሳኙ ነገር ቢሆንም፤ የደንበኛን ፍላጎት ብቻ መሠረት አድርጎ ማቅረብ ለሸቀጣ ሸቀጥ እንጂ ለፊልሙ ኢንዱስትሪ አይሆንም። ተመልካች ወደ ፊልም ይመጣል ወይንስ ፊልሙ ነው ወደተመልካች የሚሄደው? ተመልካችን ፍለጋ ሰዶ ማሳደድ ከተያያዝንማ ብዙ መወላገድ ያመጣል። ነገሩ የሚያስፈልግ ቢሆንም ዘለቄታዊ ግን አይሆንም፡፡
በአንድ ሰሞን አብዛኛው ተመልካች የሚወደው እያፈቀረ መሳቅ ነው አሉ። እናም በዚያ ሰሞን የሚሠሩ ፊልሞች ሁሉ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ነበሩ። ለምን ሲባል፤ ትራጄዲ የሆነ ኑሮ እየኖሩ ትራጄዲ ፊልም መመልከት በቃን የተባለ ዓይነት ድባብም ነበረው። የተመልካቹ ፍላጎት ወደ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ማዘንበሉ ለዚህ ብቻም ሳይሆን በትራጄዲው ውስጥ ተመልካችን ይዞ ማቆየቱ ትልቅ ሙያዊ ብቃትን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ከማሳቅና ከማዝናናት ይልቅ እያስተማረ ገንቢነቱና ታሪክ ነጋሪነቱ ይጎላል። ታዲያ ይህን አጣፍጦ ተመልካቹ እንዲወደው ሳቢ ለማድረግ ካልቻሉ ከሁሉ ከመውጣት ቢያንስ ስቆ መዝናናቱን ይመርጣል።
ተመልካቹን ማስከተል የነበረበት የፊልሙ ማኅበረሰብ፤ ተመልካቹን ተከትሎ ሄደ። ከባለሙያው እስከ ተመልካቹ ድረስ የአንድ ዓይነት የድግግሞሽ አባዜ የተጸናወተንም የዚህን ጊዜ ይመስለኛል። ታሪካዊ ሳቅ ስቀን ታሪካዊ የሆነ ፍቅርም ተመልክተን ይሆናል፤ ታሪካዊ የሆነውን ማንነታችንን እንድንመለከት ያደረገን ግን አይመስለኝም። በዚህ ዓይነቱ ፊልሞች ላይ መጠመዳችን ሌላኛውን ጎን ቢያዳክመውም በተናጠል ግን ስኬታማ ነበር። ምክንያቱም እንደ ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ዓላማ፤ ተመልካቹ ተዝናንቶ የፊልም ባለቤቶችም የሚፈልጉትን አግኝተውበታል።
እኚህን መሰል ስንክሳሮችና መሰሎቻቸው ተደማምረው በመጨረሻም የፊልም ኢንዱስትሪውን ባይተዋር አድርገውታል። መቅደስ እንደገባ ውሻ ከየአቅጣጫው ሲያበራዩት መገኘት ከነበረበት ሙክራቡ ደንብሮ ጠፍቷል። ከፍትፍቱ ፊቱ ነውና ባናደርግለት እንኳን ቢያንስ ፊት አንንሳው። ከመዝናናት ያለፈ ቁም ነገር እንድናገኝበት ጆሮና ዓይን ሰጥተን ትኩረታችንን እንቸረው። ማጀቱን ባንሞላው እንኳን አናጉድለው። እኚህ ሁሉም ያነሱና የተጨመሩ እንጂ የፊልሞቻችን መልኮች ናቸው ማለት እንዳልሆነ ግን አንርሳ፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2016 ዓ.ም