የአባቱ ልጅ ባለ ዜማ

“የአባት እዳ ለልጅ” ብለው ይላሉ አበው። ምን ነካቸው ባንልም ለዛሬው ግን ተረቱ እራሱ ተረት ሊሆን ነው። ይህን አባባል የሚያለዝቡ አባትና ልጆች ከወዲህ ግድም ሳይገኙ አልቀረም። ባይሆን ለዛሬው “ወንድ ልጅ ተወልዶ፤ ካልሆነ እንዳባቱ…” የሚለው የሚያስማማን ይመስላል። አይረሴው ሙዚቀኛ ተፈራ ካሳ የሙዚቃ ፈርጥ ለመሆን የቻሉ ሁለት ወንድ ልጆቹን አስከትሏል። አባት ዜመኛ፤ ልጅ ሙዚቀኛ፤ ወንድምም ዜመኛ…የድምጻዊ ልጅ ድምጻዊ … ከቤቱ ውስጥ ለልጅ የሚተርፈው የአባት እዳ ሳይሆን በረከት ነው። በአባት በረከት ልጅ እያስቀደሰ ወንድም ይሰልስበታል። የሙዚቃ ጥበብ እንደ ውርስ በተዋረድ እየተምዘገዘገ ከአባት ለልጅ በረከት ሲዘንብ፤ ያውም ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ የጥበብ በረከት ከመቶ መታደል ውስጥ የሚገኝ አንድ እድል ነው። የወይኖቹ ዘለላዎች ቢበረክቱም ለዛሬው አንዱን ጣፋጭ ዘንጋዳ ለመምረጥ የግድ ይለናል።በእንኮይ አቁማዳ እጣ ማውጣቱም ሳያስፈልገን የአይን እርግብግቢት ቅንድባችን ይመራናል።አባትን በላቀውና በሌላኛው የነገ ተስፋ አንጋፋውን የበኩር እንከተል። ግርማ ተፈራን ለማለት ነው።መቼስ የዚህን ጊዜ “ታድያለሁ በቃ” የምትለዋን ዜማ ያዜምልን ይሆናል። ለዛሬው ምርጫችን እንድናደርገው የገፋፋን አንድ ጉዳይ ስለመኖሩ ግን ከወዲሁ ጠቆም አድርገነው እንለፍ። ይኼውም የ2016ቱ የ”ለዛ አዋርድ” ነበር። ከቀናት በፊት 13ኛው የ”ለዛ አዋርድ” የሽልማት ሥነ ሥርዓት ስለመካሄዱ እንግዳ የምንሆን አይመስለኝም።ከነበሩት በርካታ የሽልማት ዘርፎች አንደኛው “የአመቱ ምርጥ አልበም” የሚል ነበር።ታዲያ ማን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት እሩቅ አይመስለኝም።ግርማ ተፈራ ካሳ እርሱ እራሱ ሆኖ ታይቷል። ከዳዊት ይፍሩ እጅ በክብር ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡

ደግሞ በሶምሶማው አንደኛው ሰፈር ደረስ መለስ አድርጎ ይመልሰን። ከእዚህ አዲስ አበባ፤ በአራት ኪሎ ስድስት ኪሎ አሳብረን ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ስንገባ ከወዴት ይሆን ግርማ ማለት አይቀርም። እዚያ ሠፈር እንደሆነ ፍሬው ቀርቶ እንክርዳዱን ቢዘሩት እንኳን ደርሶ አዝመራ ነው። ቄሱ ይሁኑ ሼሁ ማናቸው እንደባረኩት ባይታወቅም የመንደሩ የጥበብ አውድማ በጋ ክረምቱን አሽቶና አብቦ ጎተራውን እየሞላ ይፈሳል። ይህም ሀቅ ነው። ሠዓሊ ሙዚቀኛው፤ ጸሀፊ ጋዜጠኛው፤ ተዋናይና ስፖርተኛው ሁሉ ያለውን ጥበብ አንጠልጥሎ እየገባ ይሁን ከገባ ወዲህ…ብቻ ግን የኢትዮጵያን የኪነ ጥበብ ነጠላና ጋቢ የደረቡ ስመጥር ሁሉ ከወዴት ይሆኑ? ሲባል አንድና አንድ መገኛቸው ፈረንሳይ ሌጋሲዮን የሚል ነው።እዚያ ሠፈር ውስጥ ተወልዶ አድጎ፤ አሁንም ከዚያው የከተመው ግርማ ተፈራ ምናልባትም ሚስጥሩን ከማናችንም ደህና አድርጎ ያውቀው ይሆናል።ይህ ብቻም ሳይሆን በጥላሁን ገሠሠና በማህሙድ አህመድ እየተቆነጠጠ ያደገ ሰው በመሆኑ እድል ከነጅራቷ ዞራለታለች። እኚህን ሁለት ብርቱ ሙዚቀኞችን ሲወዳቸው መውደዱ መጠን የለውም። ስማቸውን ጠርቶም አይጠግበውም። ከፈረንሳይ የተተከሉት ሁለቱ የሙዚቃ ምሶሶዎች የተፈራ ካሳ የአባቱ ጓደኞች ነበሩ። ሙዚቃ ሲያጠኑ እንኳን አንድ ላይ ነውና የመገናኛ ታዛቸው በብዛትም ከነ ግርማ ቤት ውስጥ ነበር። ከፊትና ኋላ ከወደ አፍና አፍንጫ በተሰካካው የመኖሪያ ቤታቸው ቡናውን ተጠራርተው፤ ጸበል ጻድቁን ተቃምሰው በእድር ማህበሩ አብረው ተገኝተዋል። የአንዱ ልጅ ለሌላው ሲላላክ ሲያጠፋ ተኮርኩሞ ሲያለማ ተወድሶና ተሸልሞ አድጓል። እንግዲህ በዚህ ውስጥ ያደገው ግርማ ተፈራ ምን ዓይነቱ ልጅ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ እዳው ገብስ ነው፡፡

በኛ ሀገር ውስጥ በተለይ ደግሞ በቀደመው ዘመን ውስጥ ሙዚቀኛ ለመባል ካለሙት ለመድረስ ፈተናው ይህ ነው የሚባል አልነበረም። ልጆቻቸው አዝማሪና ዘፋኝ እንዳይባሉ አንካሴያቸውን ጨብጠው የሚቆሙ ወላጆችም ብዙ ነበሩ። ይህን ሳስብ ታዲያ፤ የሙዚቀኛው ልጅ ግርማ ተፈራስ ይህቺን ቦታ እንደምን ተሻገራት? ተቃውሞ ገጠመው ወይንስ በአባቱ ድጋፍ ሰተት ብሎ ወደ ሙዚቃው ገባ? ብዬ ባሰላስልም እራሱኑ የመጠየቁን እድል አላገኘሁምና ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ቃለመጠይቆቹ ውስጥ ምላሹን ለመቃረም ሞከርኩ። የሙዚቀኛ ልጅ ነውና ያለጥርጥር ተቃውሞ አይኖረውም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፤ ነገር ግን እንደዚያ አልነበረም። ልጁ የእርሱን የእግር ዳና ተከትሎ ሙዚቀኛ እንዲሆን አባት ፍላጎትም ሆነ ምኞት አልነበረውም። የሚያስገርም ቢመስልም ያለ እናት ላሳደገ ሙዚቀኛ አባት ግን በተራ ምክንያት የሆነ አይደለም። እርሱም በእርግጠኝነት ባያውቀውም ሊሆን የሚችለው ምክንያት ግን ከሙያው ፍቅር ጋር መሳ ለመሳ የቆመውን የመገፋትን የመከራ ገፈት እንዳይቀምስ ነበር። አባት በሙዚቃ ገመድ እያለፈበት ባለው በዚህ ከመንደር እስከ ሀገር በተቆለለው ድካምና እንግልት በበዛበት ተራራ እንዲንገላታ ካለመፈለግ የመጣ ነበር። ለውሳኔውም የቤተሰብ ሸንጎ ከጠረጴዛው ዙሪያ ተሰይሞ መከረበት። የመጨረሻውን የግርማን የሀሞቱን ልክና የፈነቀለውን ወኔ ሲመለከት አባት ውሳኔውን መቀየሩ አልቀረም። እንግዲያውስ አለ አባት፤ እንደኔ በልምድ ሳይሆን በዕውቀት እንድትገባበት በማለት የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲገባ አደረገው። ግርማ ተፈራ ከድምጹ ባሻገር ዛሬም ድረስ የሚጠቀምበትን የህይወት ዘመን የሙዚቃ ዕውቀት የሸመተው የዚህን ጊዜ ነበር። የሙዚቃን ዕውቀተ ስጋ “ተታሎ አይሰጥ ስጋ” እያለ መቅኔውን ከአጥንቱ እየሰረሰረ ሲበላ ከርሞ በአራተኛው ዓመት የሙዚቃ ቆቡን ደፋ።

ከዚህ በኋላ ወደሚወደው ሙዚቃ በኩራት ሲመጣ የመጀመሪያ ሥራው ስለ አባት ያዜመው ዜማ እንደሆነ ይናገራል። በጣም ስለተወደደለት ትላልቅ ሆቴሎች ሳይቀሩ እየሄደ እንዲዘፍንላቸው በጥሪ ቢያጨናንቁትም ምቾቱን የነሳው ጉዳይ እየገጠመው ተቸገረ። ጥሪው ደርሶት ማይኩን ጨብጦ በቆመ ቁጥር ሊዝናና ከመጣው መሃል አባቱን እያስታወሰ ሆድ የሚብሰውን ሰው በተደጋጋሚ መመልከቱ ሥራው ቢቀርስ አስባለውና ተወት አደረገው። እስከዛሬ ስለሠራቸው በርካታ የአልበምና የነጠላ ዜማ ሥራዎቹን ሳነሳ ስለ ድምጽና የአዚያዚያም ብቃቱ እያወራሁ ለቀባሪ አላረዳም። ቀልብን ከስሜት ጠፍረው ሽምጥ የሚያስጋልቡት ሙዚቃዎቹ ይናገራሉ። እንደ ሙዚቃ ግን፤ ግርማ የየትኛው ዘርፍ ተጫዋች ነው ብለን ካልን የአንድ ዓይነት ብቻ አለመሆኑ ነው። ከሥራዎቹ አኳያ ምድብ ከሰጠነው በአመዛኙ የሶል እና ሮክ ዓይነት ስልቶች ናቸው።

የአባቱ ልጅ የሆነው ግርማ ተፈራ አንድ የሙዚቃ ጎተራ ያለው ይመስላል።የራሱን አልበም ይዞ በመጣ ቁጥር ሁሉ ከዚህ ጎተራ ውስጥ እየዘገነ አንድና ሁለት ሙዚቃ የአባቱን ጨመር ያደርግበታል። “ሥራ ፈቶ ሲያይሽ ያንቺ ተመልካች፤ በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንቺ” በዚህ ሥራ ውስጥ ከእርሱ አልፎ ያለውን የአባቱን የተፈራ ካሳን ልክ አሳይቶበታል።ተፈራ ካሳ ያኔ ገና በክቡር ዘበኛ ባንድ ውስጥ ሳለ በማርሽ ባንዱ ታጅቦ የሠራው የዚህ ግሩም ዜማ ጥፍጥናው የሚጀመረው ገና ከሙዚቃው መግቢያ ላይ ነው። ከጅምሩ ነብስ ያስኮበልላል። በድጋሚ ግርማ ሲጫወተው ደግሞ ሙዚቃው የነበረው ውበትና ግርማ ኮለል እያለ ወጥቶ ኩልል ብሎ ታየ።“መቼ ትመጪያለሽ” የሚለውንም የቀድሞውን ደምግባቱን ሳይገፍ ከነባንድ ትዝታው ጋር በቅርቡ አስደምጦናል። ቀድሞ ከነበሩበት አንጻር በተደራጁ የሙዚቃ መሳሪያዎች በማዋሃድ በዘመናዊ መልኩ ከማቅረብ በስተቀር እንዳሻው በመሥራት ኃላፊነቱን አልዘነጋም። ከራሱ ሥራዎች በተጨማሪ በየጊዜው ቆንጠር እያደረገ ድንገት የሚያሰማን እኚህ ዜማዎች ከሙዚቃ ጋር በፍቅር እየጣሉ ፍቅርን የሚያሲዙ ናቸው። እርሱ እንደሆን አያልቅበት ነው፤ ወደፊትም የሚያሰማን ገና ብዙ ይኖረዋል። በዚህም አባቱን ዳግም እያስታወስን ግርማ ተፈራንም እያደነቅን እኛም እንዝናናለን። የአባቱ ልጅ ማለት እንግዲህ ለዚህ ዓይነቱ ልጅ ነው፡፡

“እርሱ ለኔ የተለየ ነው። ለርሱ ያለኝ ፍቅርም እጅግ ልዩ ነው። በህይወት ኖሮና ኖሮኝ ሁሉንም ነገር ባደርግለት ይሄን ፍቅሬን ብገልጥለት ደስ ይለኝ ነበር፡፡” የሚሉ የህይወት ዘመን ዐረፍተ ነገሮች አሉት። ይህ ታዲያ ለአባቱ እንጂ ለማንም አይደለም። የአባቱ መውደድ በልቡ ውስጥ ቃላት የማይቋጥሩት ስንኝ ነው። ደግሞ ስለ አባት አዚሟልና በዚያ የአባቶች ቀን ድምጹ እንደተስረቀረቀ ውሎ ያመሻል።ሁሉም ልጆች ከአባታቸው ጥላ ስር ግርማ ተፈራን አብረው እያስታወሱት ይውላሉ። ከአባት የተሰጠ ምርጡ የአባት ስጦታና ግብዣ ነው። ግርማ መቼስ አባቱን ሲወድ ፍቅሩ ወሰን አልባ ዳርቻው ሞላ ነው።“ኖሮ ላሳየው አልቻልኩምና የእርሱን ጥሩነት የምመልሰው ለልጆቼ ጥሩ አባት በመሆን ነው” ይላል ለጥሩነት ምላሹ ጥሩነት መሆኑን ተገንዝቦ። መውደዱ ገኖ ጣር ለመንካቱ ምናልባትም በልጅነት እናቱን በማጣቱ እንደ እናትም አባትም ሆኖ ያሳደገው ድንቅ አባት በመሆኑም ጭምር ነው። በልጅነት ያጣውን የእናቱን ፍቅር በመካሱ “እንደ እናት” የሚለው ጣፋጭ ሙዚቃ ሲያስደምጠን ግጥምና ዜማ ስላገኘ ብቻ አለመሆኑ አሁን ተገለጠልኝ። ያንን የእናትን ዓይነት ፍቅር ላሳየችው ውድ ባለቤቱ የተዜመ ዜማ ነበር። ግርማ በብዙ ለየት የሚያደርገው ይህ በፍቅራዊ መዓዛ የተቃኘው ልቡ መዳረሻው ወሰን አልባ መሆኑ ነው።በተገኘበት መድረክ ሁሉ ስማቸውን እየጠራ በፍቅር የሚያወድሳቸው አሊያም የሚያመሰግናቸው ቢያንስ ሁለትና ሦስት ሰዎች አይጠፉም።“የት ሀገር የሚለውን አልበሜ ተሠርቶ ለማየት እንደሚፈልግ ሁል ጊዜ በጉጉት ይናገረኝ ነበር። ነገር ግን፤ ማየት የሚፈልገውን ሳያይ በድንገት በሞት ተነጠቅኩኝ” በማለት በእርሱ ላይ የነበረውን የማዲንጎ አፈወርቅን የተስፋ ምኞት በእንባ ይገልጸዋል። ለሞት ክፋት ጥግ የለውም።እጅግ የሚሳሳለትን ሰው ድንገት በሞት ሲነጠቅ ማዲንጎ ሁለተኛው ነው።በወሊድ ወቅት በተፈጠረ የህክምና ስህተት አብዝቶ የሚወዳት ልጁ አያት አድርጋው በዚያው ቀረች። ልጇን እንዳስታቀፈችው ከሞት ጋር ሄዳለች። መሰበር አይሉትን ስብራት ተሰብሮ ወጌሻም የታጣለት ይኼኔ ነበር።

“ግን የት ሀገር?” የወዲህኛው የቅርብ ሥራው ነው። ከአራት ዓመታት በፊት ያለቀለት የነበረ ሥራ ቢሆንም በኮቪድ ወረርሺኝና ጦርነቶች ሳቢያ የመምጫ ጊዜው ተራዝሞ ከርሟል። 2015ን ግን ለመቅረት አልቻለምና በማለቂያው ደረሰ።“የኖህ መርከብ” የሚለውን ዜማም በመጀመሪያዎቹ ላይ አክሎ መጣ። በሙዚቃ ደረጃ ብቻ 20 ያህል ሙዚቀኞች ተሳትፈውበታል። የሚወደው ወዳጁ ማህሙድ አህመድም አንዲት ሥራ ሰጥቶታል። ጥራቱን ለመጠበቅ ሙያዊ ጉልበትም ፈሶበታል። የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ዜማም አንዲህ ነው፤

“በመልክሽ አይደል ወይ በቁንጅናሽ፤

የተረታው ልቤ ከብዶት ዝናሽ

ልሽሽ አልኩኝ ሳይሽ ከምቸገር፤

ልኑር ርቄ ካንቺ ግን የት ሀገር?”

በግጥም ቴዲ አፍሮና ይልማ ገ/ አብ ተዋህደውበታል። ዜማውን ደግሞ ቴዲ አፍሮ ሲሠራው በሙዚቃ ቅንብሩ ደግሞ አቤል ጳውሎስ ተጠቦበታል፡፡

የመላው ድምጻዊ የአልበም ሥራዎች ተደራሽነት ግን አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ ቀደም እንደምናውቀው ግርማ ተፈራ እንኳንስ አልበምና ነጠላ ዜማ ሲለቅ እንኳን ገጠር ከከተማው ሸሙናዬ ነበር። ድምጻውያኑ ከሰዋሰው መልቲሚዲያ ጋር ውል ማሰራቸውን ተከትሎ አዳዲስ የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን ልናገኝ የምንችለው ከመልቲሚዲያው የኢንተርኔት ማህደር ላይ በመግዛት ብቻ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። አሁን እንደ ድሮው በዩቲዩብና መሰል ጓዳዎች ውስጥ ማግኘት የለም። እንግዲህ ይህን ተከትሎ ድምጻውያኑ የተሻለ የልፋት ዋጋ ለማግኘት ቢችሉም እንደ ልብ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተከትሎ በአድማጩ ዘንድ ቅዝቃዜን መፍጠሩ አልቀረም።እየተቀባበሉ በየማህበራዊ ሚዲያው ለማራገብም የማይመች ሆኗል። በዚህም ምክንያት አልበምና ነጠላ ዜማ ባወጡ ቁጥር የሚዘመርላቸው መዝሙርም ቀርቷል። ከእነዚህም አንዱ ግርማ ተፈራ ነው። በቅርቡ በሠራው አልበም እንደቀድሞው ሆ! አልተባለለትም ለማለት ይቻላል። እጅግ ቆንጆ ቆንጆ የሆኑ የድምጽና ምስል ክሊፖችን ጨምሮ ለሽልማት ያበቃውን ምርጥ አልበም ቢሠራም ድምቀቱ ግን ተጓድሏል። ከለምንድነው የበፊት ሥራዎቹ አንጻር ማለት ነው። እንግዲህ በሁኔታው አድማጩ አኩርፎ አሊያም አልገጥምህ ብሎት ይሆናል። ዝምታው ከበዛ ደስታው ጭር ማለቱ አይቀርምና በዋዛ አይታለፍ። ድምጻውያኑም ሆኑ ሰዋሰው መልቲሚዲያ የተሻለውንና የሚበጀውን ሌላ መንገድ ቢያበጁ መልካም ነው።

በስተመጨረሻም የተፈራ ቤተሰብ ዜማቸው እንዲህ ይመስለኛል “አለ ገና፤ ገና አለ ገና…” ምክንያቱም ቀጣዩ የአልበም ሙሽራ የዜመኛው ልጅ የሙዚቀኛው ወንድም መሳይ ተፈራ ነው።በቀጣዩ ሰኔ 1 ቀን አዲሱን አልበሙን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ነው።“የልቤን” የአልበሙ መጠሪያ ነው። የልቡን ምንስ ሊነግረን ይሆን…ደርሰን የልቡን እንድናደምጥ ሳያጓድል የሰኔ ሰው ይበለን።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You