ኢትዮጵያ በርካታ ባሕላዊ እሴቶች ያሏት ሀገር ነች። እነዚህ እሴቶች የማህበረሰቡ መገለጫ ከመሆን አልፈው በቱሪስቶች ተመራጭ መስህቦች ናቸው። ከሁሉም በላይ ግን ባሕሉን፣ ወጉንና ማንነቱን ጠብቆ ለሚኖር የሀገሬው ሰው የኑሮ ዘይቤንና ራሱን የሚገልጽባቸው ሀብቶቹ ናቸው።
ማህበረሰቡ ካሉት አያሌ ባሕላዊ እሴቶች ውስጥ ቤተሰብ የሚመሰርትበትና ማህበራዊ ሕይወቱን ጠብቆ የሚያቆይበት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደመኖራቸው መጠን የጋብቻ ሥነ ሥርዓትና ባሕላዊ አንድምታዎቹም እንዲሁ ይለያያሉ።
ትዳር ለመመስረት ከመተጫጨት፣ እስከ ጋብቻ ጥያቄና ሽምግልና እንዲሁም የሠርግ ሥርዓት ድረስ የሚኖረው ሰንሰለት እንደባሕልና እንደየሀገሬው ወግ ልዩነት አለው። ይህ መሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዝሀ ባሕልና እሴት እንዲኖር አስችሏል። ይህንን ሀብት መጠበቅ እሴቶቹን በቀሪው ዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር የቱሪዝም ሀብት ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ላይም መሥራት ይገባል።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው ሀገርኛ አምድ በቅርቡ በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰስ ባሕላዊ ሀብትነት የተመዘገበው የሸዋል ኢድ ባህል ባለቤት ወደ የሆነችውን የሐረሪ ክልል ማህበረሰብ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት እንዳስሳለን። ለዚህም የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት ‹‹የሐረሪ ብሔረሰብ የማይዳሰሱ ቅርሶች፣ ክንዋኔዎችና ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ፣ ማህበራዊ ሥነ ሥርዓቶች›› በሚል በአቶ ገዛኸኝ ግርማ እና ቀለሟ መኮንን አዘጋጅነት የተጠናከረውን ጥናታዊ ጸሑፍ መሠረት አድርጎ ያዘጋጀውን የብሔረሰቡን የጋብቻ ባሕል እናስቃኛለን፡፡
አቶ ተወልዳ አብዶሽ የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ጋብቻ በሁለት የተለያዩ ወይም ተቃራኒ ፆታዎች መካከል በፍቃደኝነት ሕይወትን በጋራ ለመምራት የሚፈጸም በውል ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ከመሆኑም በላይ የቤተሰብ መሠረትና የኅብረተሰብ እድገት ዋስትና ነው፡፡ የሐረሪ ብሔረሰብ የጋብቻ ሥርዓትም የዚሁ ውጤት ነው። ዳይሬክተሩ ባደረሱን መረጃ መሠረትም ማህበረሰቡ በሚከተለው ባሕላዊ ክንዋኔ መሠረት ጋብቻው የሚፈጸምባቸውን የተለያዩ ሥርዓቶችን ይዘን ቀርበናል።
የመተጫጫ መንገድ
በሐረሪ ብሔረሰብ የተለያዩ የመተጫጫ መንገዶች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋናው የሸዋል ኢድ ቀን እንደሆነ ይነገራል፡፡ የሸዋል ኢድ በዓል ለብሔረሰቡ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የመተጫጫ መድረክ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የሸዋል ኢድ በዓል ዕለት ወጣት ወንዶች ቀልባቸው ያረፈባትን ልጃገረድ ለትዳር የሚመርጡበት ዕለት ነው፡፡
በዚህም ምክንያት በሸዋል ኢድ በዓል ልጃገረዶች (ጌይ ወሐቻች) ከምንጊዜውም በላይ አምረው፣ ተውበውና ደምቀው ይታያሉ፡፡ የታጨች ልጃገረድ የታጨችበትን ‹‹ ኩሻ ቡሩቅ›› የተባለ ባሕላዊ ቀሚስ ትለብሳለች፡፡
ጸጉሯን ደግሞ ‹‹ገማሪ›› በመባል የሚታወቀውን ባሕላዊ የጸጉር ስሬት በመሰራት ትለያለች፡፡ በዚህ መልኩ አለባበሳቸውን ካሳመሩና ባላቸው አቅም አጊጠው፣ ተውበውና ተሽቀርቅረው ከጨረሱ በኋላ በሙጋድ (በቡድን) በመሆን ወደ ክብረ በዓሉ ያመራሉ፡፡
ወጣት ወንዶችም በተመሳሳይ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ለመምረጥ ወደ በዓሉ በመሄድ ይታደማሉ፡፡ በሸዋል ኢድ በዓል የእጮኛ አመራረጥ ሂደት በሁለት መልኩ የሚከናወን ነው፡፡ የመጀመሪያው በዓሉ በሚከበርበት ‹‹አው ሹሉም አሕመድ›› እና ‹‹አው አቅበራ አዋቾች›› ላይ ጨዋታውን ለመመልከት ከሚመጡ ልጃገረዶች መካከል ዓይናቸው ያረፈ ባትን በመምረጥ ነው፡፡
ሁለተኛው የእጮኛ አመራረጥ ሥርዓት የሚፈጸመው በዓሉ የሚከበርባቸውን ሁለት ቦታዎች በቀጥታ የሚያገናኝ ‹‹አሚር ኡጋ›› (የሐረር ኢሚሬት መሪ ወይም አሚር) መንገድ ላይ ነው፡፡
ልጃገረዶችም ሆኑ ወጣት ወንዶች በዚህ ‹‹በአሚር ኡጋ›› የጨዋታውን ድምቀት እየተከታተሉ በተደጋጋሚ የሚመላለሱ በመሆኑ ወንዶች አመቺ ቦታ በመምረጥ ከሚመላለሱ ልጃገረዶች መካከል ዓይናቸው ውስጥ የገባችውን ወይም የወደዷትን የሚመርጡበትና የሚያጩበት ሂደት ነው፡፡
ወጣት ወንዶች በዚህ መልኩ ቀልባቸው ያረፈባትን ወይም የመረጧትን ልጃገረድ የራሳቸው ለማድረግ ይመኛሉ፡፡ በመመኘት ብቻ ሳይቀሩ ልጅቷ የማን ልጅ እንደሆነች እስከማጠያየቅ ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ማወቅ ካልቻሉ ወደቤታቸው ሲሄዱ ተከታትለው የማን ልጅ እንደሆነች ያጣራሉ፡፡
በሐረሪዎች በሸዋል ኢድ የበዓል ቀን ተያይቶ፣ ተመራርጦና ተዋውቆ ለጋብቻ መብቃት ዛሬም ህያው የሆነ የብሔረሰቡ ትልቅ እሴት ሲሆን፣ በዚህ ዕለት በበዓሉ ላይ መሳተፍ ያልቻለ ወይም ያልተገኘ ወጣት እንዲሁም በበዓሉ ላይ ቢሳተፍም ዓይን አዋጅ ሆኖበት እጮኛ ሳይመርጥ የቀረ እና ያልተሳካለትን ወጣት ጓደኞቹ ‹‹ሹዋሊድ አመለጤኽ›› ይሉታል፡፡ ይህም ማለት የማታ ማታ የበዓሉ ድምቀት አሞኝቶህ ሳትመርጥ ቀረህ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል በበዓሉ ላይ ተገኝቶ መምረጥ የቻለ እና የተሳካለት ወጣት ደግሞ ‹‹ሹዋሊድ ማረኼኝ›› እንደሚባል ወይዘሮ ኑሪያ ይገልጻሉ፡፡
ሽምግልና (የጋብቻ ጥያቄ)
በሸዋል ኢድ በዓል ዕለት የተሳካለት ወጣት ወደ ቤቱ ሲመለስ ለቤተሰቦቹ ስለወደዳት ልጅ በመግለጽ የአቶ እገሌን ልጅ የትዳር አጋሬ እንድትሆነኝ መርጫለሁና ሽማግሌ ላኩልኝ በማለት ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ የወንዱም ቤተሰቦች በልጃቸው ምርጫ ከተስማሙ ጥያቄውን ይቀበላሉ፡፡ ካልተስማሙ ግን ራሳቸው ሌላ ያጩለታል፡፡
የልጁ ቤተሰቦች የልጅቷን ቤተሰቦች ማንነትና ሰብዕና ካጣሩ በኋላ እና በልጃቸው ምርጫ ከተስማሙ ልጅቱ ቤተሰብ ጋር ሽማግሌ ይልካሉ፡፡ በሽምግልና የሚላኩትም ሴት አያት፣ እናት አልያም አክስት ወይም ከቤተሰቡ ከፍ ያለ ዕድሜ ያላቸው ሴት ይሆናሉ። እነሱም ዛሬ እናንተ ጋር መጥተናል ሲሉ ‹‹ርኸቡ›› (የመጣችሁበትን ጉዳይ አግኙ) ይባላሉ፡፡ ቤት ገብተው ‹‹ገብቲ ኤሔር›› መደባ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ለጥያቄው የሚኬደው በጠዋት ሲሆን ከቀናት በተለይ ሐሙስ እና ሰኞ ይመረጣሉ፡፡ ሌሎች ቀናት ገዳቸው ጥሩ አይደለም ተብለው ይታመናል፡፡
የልጅቷ እናትና ቤተሰብም በሽማግሌዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የረጅም ጊዜ ቀጠሮ ይሰጣሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ከዘመድ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር እና የልጁን ቤተሰቦች ማንነት እንዲሁም ስለ ልጁም ፀባይና ስለ ሥራው ክትትል ለማድረግ እና ለማጥናት ነው፡፡
የልጅቱ ቤተሰቦች ጋብቻውን ካልፈለጉት ‹‹አፍ ወጤና›› (ሌላ ሰው ቀድሟችኋል) ይሏቸዋል፡፡ ጋብቻውን ከፈለጉት ግን በቀጠሮው ቀን ሽማግሌዎች ጫት ይዘው እንዲመጡ ሌላ ቀጠሮ ይሰጧቸዋል፡፡ ይህም የጋብቻ ጥያቄ ያቀረበውን ወጣት ለልጃቸው የፈቀዱለት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
ቀነ ቀጠሮውም ሲደርስ የሙሽራው እናትና ሌሎች ሁለት ሴቶች የመተጫጫ የሐረሪ ጥቅል (ኩሻ ጫት) እና ብር ይዘው ወደ ልጅቱ ወላጆች ቤት ሲደርሱ ከልጅቷ ቤተሰቦች ሴቶች በአክብሮት ይቀበሏቸውና ሻይ ቁጢ (ከቡና ቅጠል የተዘጋጀ ሻይ) ይጋብዟቸዋል። የልጁ ቤተሰብ ያመጡትን ጫት ሽማግሌዎቹና የልጅቱ ቤተሰቦች የምርቃት ሥነ- ሥርዓት አድርገው ይፈቱና በቅድሚያ ለሽማግሌዎቹ ቀጥሎም ቤት ውስጥ ለተሰበሰቡት ለልጅቱ ዘመዶች ሁለት ሁለት እግር ጫት ይታደላል፡፡
የልጅቷን መታጨት ለማብሰር ቤት ላልመጡትም የልጅቱ ዘመድ አዝማድ ጫት ይላክላቸዋል፡፡ ጫት ያልተላከላቸው የልጅቷ ዘመዶች ተቀይመው በሠርጉ ሥነ-ሥርዓት ላይ ላይገኙ ስለሚችሉ በተቻለ መጠን ጫቱን ለሁሉም ለማዳረስ ጥረት ይደረጋል፡፡
በሀረሪዎች ጫት ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል። ለምሳሌም በጋብቻ ወቅት የልጁ ቤተሰብ ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ ለልጅቱ ቤተሰቦች ተይዞ የሚኬድ መሆኑ አንዱ ሲሆን ይህም የኩሻ ጫት ይባላል። ይህ በወንዱ ቤተሰብ የሚቀርበው የኩሻ ጫት የልጅቷ ቤተሰብም የራሳቸውን ጫት አክለውበት የፍጥምጥሙን ሥነ-ሥርዓት ለማስፈጸም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህ የኩሻ ጫት ሥርዓት ፍፃሜ ካገኘ የጋብቻ ጥያቄው ዕውቅና ያለው መላ ቤተሰብ ዘመድና ጎረቤት ያወቀው ይሆናል፡፡
የጋብቻ ውሉን ማሰሪያው ቁልፍ ጉዳይ ባል ለሚስቱ የሚሰጠውን ሀብት (ማህሪ) እንደ እርሻ መሬት፣ ገንዘብና ዕቃ በጋብቻው ወቅት በዝርዝር ማስፈር ይጠበቃል፡፡
የሠርግ ሥነ-ሥርዓት
የሠርጉ ቀን እንደተወሰነ በሁለቱም ቤተሰብ በኩል የድግስ ዝግጅት ይጀመራል፡፡ የሠርጉ ቀን ከመድረሱ በፊት የልጁ ጓደኞችና ዘመዶች ለሠርጉ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ከኤረር ወንዝ በመስበር በአህያ ጭነው ለልጅቱ ቤተሰብ ያቀርባሉ፡፡ ይህም ‹‹የዘገን›› (የቀለበት ሥነ-ሥርዓት) እንጨት ይባላል፡ ፡ የልጅቱ ቤተሰብም እንጨቱን ከተቀበሉ በኋላ ምላሹን በአንድ ቅል ወተት፤ በሌላኛው ቅል ደግሞ ብርዝ እንዲሁም አራት እስር ነጭ ሽንኩርት በሁለት ልጃገረዶች አስይዘው ወደ ልጁ ቤት ይልካሉ፡፡ ወተቱ፣ ብርዙና ነጭ ሽንኩርቱ በኤረር ወንዝ ሄደው እንጨቱን ላመጡት ወጣቶች ከወባ ለመከላከል ታስቦ የሚሰጥ ነው፡፡
የሠርጉ ቀን ሲደርስ ሙሽሮችና ቤተሰቦቻቸው ወዳጅ ዘመድ በሠርጉ ዕለት እንዲገኙላቸው ጥሪ ያደርጋሉ፡፡ ጥሪ በማድረጉ በኩል ግን ቀድሞ የሚጀምረው የሙሽራዋ ቤተሰብ ነው፡፡ ከሠርጉ ጥሪ በፊት ግን ሙሽራዋ ጓደኞቿን፣ ዘመዶቿንና ጎረቤቶቿን በየቤታቸው እየሄደች ‹‹ሚጫጩዊ›› (ነገ ልብስ እናጥባለን) ብላ ትጠራለች፡፡ በነጋታውም የተጠሩት በሙሉ የቤተሰቦቻቸውን ልብስና የሙሽራዋን ቤተሰብ ልብስ ጨምረው በመያዝ ወንዝ በመውረድ ልብሱን አጥበው እስኪጨርሱ እየተቀባበሉ ይዘፍናሉ። በዘፈናቸውም ሙሽራዋ ከእንግዲህ ከጓደኞቿ መለያየቷን፣ እንደበፊቱ ከነሱ ጋር ልብስ ለማጠብ ወንዝ መሄድ እንደማትችል የሚገልጽ ነው፡፡
ሙሽራውም በየቤቱ እየዞረ ጓደኞቹን፣ ዘመዶቹንና ጎረቤቶቹን ይጠራል፡፡ ልጃገረዶችን በእህቱ አልያም በዘመዶቹ ወይም በጎረቤት አማካይነት ያስጠራል። ወላጆቻቸውም በመልዕክተኛ ዘመዶቻቸውን፣ ዕድርተኞቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ያስጠራሉ፡፡
የሠርጉ ዕለት
የሠርጉ ዕለት እሁድ ቀን ሙሽራው ቤተሰብ ቤት የተጠሩት እድምተኞች እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት መውሉድ (የነብዩ መሀመድ /ሰ.ዐ.ወ) ከመወለዳቸው ጀምሮ ያለው ይቀራል፡፡ ይህ በወንዶች አፎቻ አማካኝነት የሚከናወን ነው፡፡ ከዚህ ሥነ-ሥርዓት በኋላ ለሠርጉ ሥነ-ሥርዓት የተዘጋጀው ምግብ ይቀርባል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሙሽራዋ ቤትም እንዲሁ ይደረጋል።
የሙሽራው ሚዜዎች ከሙሽራው ቤት ቀለበት ስለመምጣቱ እንደ ምልክት ተደርጎ የሚወሰደውን ጥጃ ወደ ሙሽሪት ቤት ይዘው ይመጣሉ፡፡ የሙሽሪት እናት የሙሽራዋ ቀለበት ሲደርሳቸው ጥጃዋን ሊጥ ይቀቧታል፡፡ ቀለበቱ መድረሱን ካረጋገጠች በኋላ ሙሽሪት ምሳዋን መብላት ትጀምራለች፡፡ ከዚህ ሥነ- ሥርዓት በኋላ ጥጃው ወደ ሙሽሮች ቤት የሚመለስ ነው፡፡
የሙሽራው አባትም ከዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ሙሽራዋ ቤት በመሄድ በግቢው በስተቀኝ በኩል በተነጠፈው ምንጣፍ ላይ ይቀመጣሉ። የሙሽሪት አባትም እና የተወሰኑ ጓደኞቻቸውና ዘመዶች ደግሞ በስተግራ በኩል በተዘረጋው ስጋጃ ላይ በመቀመጥ የሙሽራው ሚዜዎችና ጓደኞች ሙሽሪትን ይዘው ወደ ሙሽራው ቤት እስኪሄዱ ድረስ ያለውን ሥነ-ሥርዓት ይከታተላሉ፡፡
ከዚያም ብዙ ደጅ የጠኑት የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽሪትን እንዲወስዱ ሲፈቀድላቸው በቅሎ ይዘው ሙሽሪት ቤት ይገባሉ፡፡ በባሕሉም መሠረት የሙሽራዋ ወንድም ሙሽሪትን በቅሎ ላይ እንዲያስቀምጣት ይደረግና ጃንጥላ ከእራሷ ላይ ተይዞላትና በወንድሟ ተደግፋ ወንዶች ከበቅሎው ፊት ባሕላዊ ዘፈን እየዘፈኑና እየጨፈሩ ልጃገረዶች ከበቅሎው በስተኋላ በመሆን እየዘፈኑ ወደ ሙሽራው ቤት ይዘዋት ይሄዳሉ።
ከዚያም ሙሽሮች ወደተዘጋጀላቸው ‹‹አሩዝ›› (ጫጉላ ቤት) ይገባሉ፡፡ በዚህ መልኩ ሌሎች ተጨማሪ ሥነ ሥርዓቶች እየተካሄዱ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ይፈፀማል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም