አዲስ አበባ፡- የአመራርነት ሚናን በሳይንሳዊ እውቀት ላይ በማስደገፍ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ የኢፌዴሪ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አስታወቀ፡፡
የኢፌዴሪ መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እና የለውጥ አመራር›› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ሦስተኛው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በአካዳሚው በሚኒስትር ማዕረግ የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደምሴ ሽቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አካዳሚው ለውጡ የታለመለት ግብ ላይ ለማድረስ የሚያስችሉትን ወቅታዊ የአመራር ብቃትን የሚጠይቁ ጉዳዮችን እንደሚያስፈጽም፤ በየደረጃው ያለው አመራር በየወቅቱ የሚታይበትን የማስፈጸም ችግር መንስኤዎች በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በመለየት በትምህርትና ሥልጠና በማብቃት የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ያስቀጥላል፡፡
በፖለቲካዊ አስተዳደር፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በተለያየ መልክ የሚታዩ ችግሮችንና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ብቁ የሆነ አመራር አገሪቷ እንደሚያስፈልጋት የሚናገሩት አቶ ደምሴ፤ ምሁራን ነፃ በሆነ መድረክ ተሰባስበው ሀሳብ የሚያራምዱበትና አገራዊ ለውጡን የሚደግፉበት ተግባሮች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
በእውቀት ላይ የተመሰረተ የውሳኔ አሰጣጥ እንዲኖር የመደገፍ ሥራን በማከናወንና የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ በማድረግ ለአገሪቷ አመራሮች ጠቃሚ ግብዓቶች እንዲቀርቡ ተከታታይ የውይይት መድረኮች እንደሚመቻቹም አስታውቀዋል፡፡
የሀሳብ የበላይነት እንዲኖርና ከሁሉም አቅጣጫ እውቀትን በመቅዳት ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች በሚገባ እውን እንዲሆኑ የሚያስችል አቅጣጫን በመከተል ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል በአካዳሚው በኩል ያለሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ደምሴ አክለው ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ደምሴ ገለፃ፤ መሪ በአገራዊ ለውጥ ላይ ያለውን አዎንታዊ ሚና በማጉላት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ አካዳሚው በሩጫ ላይ ይገኛል፡፡ ጥረቱም ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማቅረብ ለውጡ እንዳይቀለበስ ማድረግ ነው፡፡
አካዳሚው በተደራጀ መልኩ በአግባቡ ከተቋቋመ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአገሪቷ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን አሰልጥኖ የማብቃት ሥራን በስፋት ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በአካዳሚክስ ዘርፉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ክፍተቶችን እየለየ ትምህርት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ በዶክትሬት ደረጃ ትምህር ለመስጠትም በዝግጅት ላይ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ በሚገኘው ሦስተኛው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች፣ የምርምር ተቋማት መሪዎችና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ታሳታፊ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
አዲሱ ገረመው