ከሒሩት ነጸብራቅ

በዘመን ጥበብ ውስጥ የተወለደ ትዝታ ይዞን ሊነጉድ ነው። መጥፎውን ትውስታ ባሳየን ወንዝ ፊት ቆመን ወዲያ ማዶም ልንዘል ነው። ስንሻገርም ዘመንና ኪነ ጥበብ፤ ጥበብና የጥበበኛዋ አስገራሚ አጋጣሚዎች ቆመው ይጠብቁናል። “ሒሩትን አንረሳም” ልንል ነው። አዎን…አንረሳም! ምክንያቱም እርሷ የአንጸባራቂው ኮከብ የኦርዮን ነጸብራቅ ናት።

ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ተነስቶ 70ዎቹን የተሻገረው የፖሊስና የጦር ሠራዊት ኦርኬስትራ ፍጥጫና በሁለት ማዕዘናት የተፈጠረው አብዮት ምን ነበር…በሁለቱም በኩል የተጠመደችው መድፍ ደግሞ ሒሩት በቀለ ነበረች። እሷ ከሄደች ይኸው ድፍን አንድ ዓመት ሞላት። የጠቢብ ሰው ሞቱም ጥበብ ነው። የ1ኛ ሙት- ዓመቷ ሌላ የጥበብ ሰፌድ ሰፍቶልናል።

ባሳለፍነው ሰኞ ግንቦት 19-2016 ዓ.ም በሻማ ጸዳል በጥበብ አትሮኖስ በተዘከረችበት በዚያ ቀን ግለ-ታሪኳን የያዘ መጽሐፍ ተመርቆ፤ ለስነ ጽሁፍ ቤት ልጅ ተወልዷል። “አንጸባራቂዋ ኮከብ” ሒሩትን አንረሳም፤ አዎን በእርግጥም እሷ ልትረሳ የምትችል አይደለችም። በስጋ እንጂ በህዝብና በጥበብ ልብ ውስጥ አልሞተችም። ሲሞት ብዙ ሆኖ እንደሚነሳው የስንዴ ፍሬ፤ ስትሞት በሌላ የጥበብ ዘለላ በርክታ ወጥታለች።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የ1952ቱን የጳጉሜ 5 ቀን የምሽት ፍጥጫ ማንም አይዘነጋውም። የክፍለ ዘመኑ ምርጡ የሙዚቃ አብዮትና ትዝታ ነው። የዚህ ሁሉ መንስኤ ደግሞ በዋናነት አንዲት ወጣት ድምጻዊት ነበረች። እርሷም ሒሩት በቀለ ናት። በወቅቱ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ድንኳን ውስጥ ነግሦ የነበረው የጦር ሠራዊት የሙዚቃ ባንድ አባል ነበረች። ጥላሁን ገሠሠንና ብዙነሽ በቀለን ጨምሮ በወቅቱ አሉ የተባሉ ምርጥ ስብስቦችንም የያዘ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ከተመሠረተ ገና 2 ዓመት ያልሞላው የፖሊስ ኦርኬስትራ ሀያልነቱን ወደራሱ በመቀልበስ የሙዚቃውን የክብር ወንበር ለመቀዳጀት የማይፈነቅለው ድንጋይ አልነበረም።

ከቀን ወደ ቀን ፉክክሩ እየጦፈ መጥቶ በ1952 መባቻና በ53ቱ የመስከረም 1 ዋዜማ ላይ አብዮትን የቀሰቀሰ ትንቅንቅ ተፈጠረ። የአዲሱን ዓመት ዋዜማ በታላቅ የሙዚቃ ትዕይንቶች ለመጀመር የቀረው ጊዜ በቀናት የሚቆጠር ነበር። ህዝቡም በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ነው። የሐምሌ 11 ቀኑ አዲስ ዘመን ጋዜጣም፤ “የሰንበት ኩርኮራ” በተሰኘው ገጹ “አዲሱ የሙዚቃ ጓድ” በማለት የፖሊስ ኦርኬስትራን ስለተቀላቀለው መስፍን ኃይሌ አስነበበ። ብዙ አዳዲስ ነገሮች ሊታዩ እንደሚችሉ በመጠቆም፤ የድምጻውያኑን ፍጥጫ ለመመልከት ያድርሰን ሲል ቋጨው።

“አዲሱ ጓድ” ጥላሁን ገሠሠን ተገዳድሮ እንዲያሸንፍና የንግሥናውን ዘውድ ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ እንዲዘውረው በማሰብ ነበር ያመጡት። የአሰላለፍ ቀመሩ በዚህ አላበቃም፤ ክፍሉን የሚመሩት ብርጋዴር ጀነራል ጽጌ፤ በህዝቡ ሁሉ ዘንድ ስሟ ለናኘው ለብዙነሽ በቀለ የምትሆን ሌላ አንዲት ንግሥትም ፈለጉ። ታላቁ ፍጥጫ የሚጀምረውም እዚህ ጋር ነው። ለዚህ ውሳኔ ትክክለኛዋ ድምጻዊት ሆና የተገኘችው ሴት የራሱ የጦር ሠራዊቷ ሒሩት በቀለ ነበረች። እርሷ ግን በዚያን ሰዓት በጦር ሠራዊት ክፍል ውስጥ ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ የሚሆኗትን የሙዚቃ ሥራዎቿን እያጠናች በዝግጅት ላይ ነበረች። የድምጻዊቷን ገመድ የክብሯን ክር የሳበ አንድ ሰው እዚህ ጋር ይመጣል። እርሱም ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ነው።

እናም፤ ይህን የአብዮቱን ዋነኛ ቀማሪ ለማግኘት ፈለኩና በአንድ ሰው መሪነት በቀጥታ ወዳለበት አመራሁ። ፒያሳ አሮጌው ፖስታ ቤት አጠገብ የማደሪያ መዋያው ምኩራብ ነው። ‹‹ፋዘር›› ዕድሜው ገፍቶ እርጅናው ተጫጭኖታል። ከመነጽሩ ውስጥ ያሉት እኚያ ተአምረኛ ዓይኖችም ደከም እንዳሉ ለመገንዘብ ቻልኩ። ሰውነቱ እንጂ መንፈሱ ግን አሁንም ጠንካራና ብርቱ ነው። የማስታወስ ችሎታው አንዳችም አልተነካም። አንደበቱም ጣፋጭ ነው። በአጠቃላይ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር፤ ለስጋው እንጂ ለውስጣዊ መንፈሱ ልዩ ድጋፍ የሚሻ አለመሆኑ ነው።

በድንቅ ሥራዎቹ የትውልዱ ሁሉ ማረፊያ እየሆነ መጥቶ ዛሬም በማረፊያው የኪነ ጥበባት ማሠልጠኛ መሥርቶ በሥራ ላይ ነው። ከተገናኘን በኋላ የሒሩት በቀለን የሙዚቃ ሀሁ ከአንደበቱ የመስማት ጉጉቱ ጠናብኝ። በመጀመሪያም ሁለቱን ስላገናኘው ታሪካዊ ድልድይ ጠየቅኩት። ፋዘር ቀጠለ፤ “ጊዜው 1952 ዓ.ም ነው። ያን ጊዜ በፖሊስ ኦርኬስትራ ክፍል ውስጥ ነበርኩ። የፖሊስ ሠራዊት ገና መቋቋሙ ነበርና በሰዓቱ የሚፈለገው ከነ ብዙነሽ በቀለና ጥላሁን ገሠሠ ጋር ለመወዳደር የሚችል ሙዚቀኛ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን አንዲት ልጅ የሀር ሸረሪት የሚል ዜማ ስትጫወት ድምጿ በጆሮዬ ጥልቅ አለ። የሰማሁትን ለማመን ከበደኝ። የዚያን ምሽት ሌሊቱን እንቅልፍ አልወሰደኝም ነበር። ሳጠያይቅ በጦር ሠራዊት የሙዚቃ ክፍል አዲስ የተቀጠረች ልጅ ስለመሆኗ ሰማሁ። የሙዚቃ አጨዋወቷ፣ የድምጿ ውበት፣ በዚያ ላይ ልጅነቷ…እጅግ የምትገርም ነበረች።

ድምጿ አሁንም አሁንም እያቃጨለብኝ አላስቻለኝም፤ ለኦርኬስትራው ኃላፊዎች ነግሬ እስከማሳምናቸው ቸኮልኩ። በኛ የሙዚቃ ክፍል ውስጥ ከነበሩት ሀላፊዎች አንዱ ኮሎኔል ታደሰ ብሩ ነበሩ። በቀጥታ ሄጄ ስለ ልጅቷ ነገርኳቸው። በመጨረሻም አሳመንኳቸው። እናም ልጅቷ የምትገኝበትን በስለላ ይጠና ተባለ። አድራሻዋ፤ የሥራ ቦታዋ…ብዙም ሳይቆይ ሁሉም መረጃዎቿ በእጃችን ገቡ። ከዚህ በኋላ ጊዜ ሳላጠፋ በማግስቱ የምትኖርበት ቤት አጠገብ ጠብቄ ላነጋግራት ወሰንኩ። ከጠቆመን ሰው ጋር ሆኜም ከእናቷ ቤት አቅራቢያ ቆሜ መጠባበቅ ጀመርኩ።

ያኔ የ23 ዓመት ወጣት ነበርኩ። እሷን ለማግኘት ስሄድም ዝንጥ ብዬ ለብሼ ነበር። ድንገት በቆምንበት ‹‹ያቿትና›› አለኝ፤ አብሮኝ የነበረው ሰው ሒሩት እየመጣች መሆኗን እያመለከተኝ። በአጠገባችን ልታልፍ ስትል ጠጋ ብዬ ላናግራት ስሞክር ለከፋ መሰላት። ኋላ እንደምንም ብዬ አግባብቼ ሁሉንም ነገር ነገርኳት። አሁን እኮ ለበዓል ዝግጅት ሙዚቃ ማጥናት ጀምሪያለሁ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ቢይዙኝስ… በማለት በውስጧ ፍራቻ አደረባትና ፈራ ተባ አለች። ግድ የለም አንዴ በኛ ፖሊስ እጅ ከገባሽ ምንም አትሆኚም፤ ሀላፊነቱን እኛ እንወስዳለን እያልኩ ከብዙ ሙግት በኋላ ላሳምናት ቻልኩ።

በማግስቱም እናቷን ይዛ መጣችና ለእሳቸውም በደንብ አስረዳኋቸው። እዚያ 50 ብር የሚከፈላትን ደሞዝ እጥፍ በማድረግ እኛ ጋር አንድ መቶ ብር እንደሚከፈላት ነገርኳቸው። ለደኅንነቷም የማያሰጋት መሆኑን እቤት ድረስ የሚወስዳት የመኪና ሰርቪስ ስለመኖሩም ጭምር ነግሬ እናቷንም አሳመንኳቸውና በሀሳቤ ተስማሙ።

የዚያኑ ዕለት ማታ ሻንጣዋን አዘጋጅታ እንድትጠብቀንና መጥተንም እንደምንወስዳት በመንገር እቅዱን ለሒሩት አስረዳኋት። ማታ በተቀጣጠርነው ሰዓት እናትየው ቤት ደርሰን በራቸውን አንኳኳን። የያዝነው መኪና ኡዚ የተሰኘውን ጂፕ ፓትሮል ነበር። ጀርባው ላይ መሳሪያ የያዘ ወታደር አስቀመጥን። ሌላ አንድ ሚሊቴሪ ፖሊስም አብሮን አለ። የፖሊስ ክፍሉ ሀላፊ ሻምበል ወርቅነህ ዘለቀም ከመኪናው ገቢና ውስጥ ተቀምጧል። ልክ በሩን ሲከፍቱ ሒሩት በቀለ ትፈለጋለች አልን ልክ እንደወንጀለኛ። በዚያ መንገድ እንዲሆን የፈለግነው ከነገሩ አስቸጋሪነት የተነሳ ነበር።

የሠፈሩ ሰው ደግሞ ከየቤቱ ግልብጥ ብሎ በመውጣት ተሰብስቦ የሚሆነውን ይከታተላል። ውጪ! የሚል ትዕዛዝ ተሰጣት፤ እኛ ግን ድራማ እየሠራን ነበር። ሒሩት ሻንጣዋን ይዛ ወጣች። በፓትሮሉ ጭነን በቀጥታ ወደ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወሰድናት። ሒሩት በቀለ የምትባለው ግለሰብ ባልታወቀ ጉዳይ በፖሊስ ተይዛለች የሚል ደብዳቤ ካጻፍን በኋላ ወዲያውኑ ኮልፌ ወደሚገኘው የፖሊስ ግቢ ወሰድናት። እርሷም እራሷን አረጋግታ በማግስቱ የሙዚቃ ሥራዋን ጀመረች።” በማለት ትዝታውን አጋራኝ።

የጦር ሠራዊት አዲሷን ባለተስፋ እንቡጥ ጽጌረዳ፤ አንጸባራቂዋን ኮከብ ገና ከመምጣቷ በፖሊስ ኦርኬስትራ ተነጠቁ። ይኸኔ ግን በሙዚቃ አብዮት ያሞቁት ፍጥጫ መንተክተኩ አልቀረም። ያ ሁሉ ዝግጅት የተደረገለት የአዲስ ዓመት ዋዜማ ደረሰ። በዚሁ የዋዜማ ዕለት የፖሊስ ኦርኬስትራው ብርጋዴር ጽጌ፤ ለመድረኩ ፍልሚያ ወኔያቸውን ለመቀስቀስ በማሰብ ለሙዚቀኞቻቸው የማዕረግ ዕድገት አደረጉ። ሞልቶ በፈሰሰው አዳራሽ፤ በአንድ መድረክ ላይ ለመንገሥ ሁለቱም ባንዶች በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ሒሩት ግን የማን ናት? የፖሊስ ኦርኬስትራ አንድ ችግር ከፊቱ ድቅን አለበት። ከዋናው ዝግጅት በፊት ከህዝቡ ጋር በሚደረገው ትውውቅ፤ ሒሩት በጦር ሠራዊቱ ዓይን ውስጥ እንዳትገባና ነገሩ ቀድሞ እንዳይበላሽ ማድረግ ነበር። ከዚህ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቲያትር አዳራሽ ውስጥ የሆነውን ነገር እንደወረደ ከፋዘር ንግግር ላይ እያነበብን እንስማው፤ “በዚያ የትውውቅ መድረክ፤ ለተንኮሉ ከኛ ቀጥሎ የሚቀርበው የጦር ሠራዊት ሆነ። ሒሩትን ይዘን ለመግባት ግራ ተጋባን።

እንድትከናነብ ካደረግናት በኋላ፤ በፊት ለፊት በር አስገብተን ከኦዲየንስ መሀል እንድትቀመጥ አደረግናት። ሁለት ባለጡንቻ ወጠምሻ ጋርዶችንም መደብንላት። እናም ዝግጅቱ ተጀመረና የመጀመሪያዎቹ አቅራቢዎች እኛ ሆንን። የጦር ሠራዊትም ሀገር አማን ነው ብሎ ከኋላ ቆሞ ይከታተለናል። ሰዓቱ ሲደርስ ከአንደኛው የመድረክ ጠርዝ ቀስ አድርገን አመጣናት። ከዚያ ሁለት ሙዚቃዎችን በሚገርም መልኩ ተጫወተች። ‘ቢስ ቢስ’ ተባለ በያኔው፤ ይደገም ይደገም እንደማለት ነው። እንደገባች የምትወጣበትንም ዘዴ መፈለግ ነበረብን” እናም ተሸፋፍና ዘፍና በፉጨትና ሆታ የታጀበችውን ሒሩት በቀለን ከጦር ሠራዊት ሸሽጎ ለማስወጣት ያገኙት መላ፤ መብራቱን አጥፍቶ በጨለማው መሀል ይዞ መሰወር ነበር። አጠፉትናም የመብራት ኃይል ችግር ነው ከይቅርታ ጋር ታገሱን በማለት ለታዳሚው አስተባበሉ።

ከውጭ ሞተሩን አስነስቶ በሚጠብቃቸው መኪና ውስጥ አስገቧትና ተፈተለኩ። የጦር ሠራዊት አባላት ሁሉም ነገር የገባቸው ዘግይቶ ነበር። ከዝግጅቱ መጨረሻ ላይ የፖሊስ ኦርኬስትራን መኪና ከበው ሒሩትን ውለዷት አሉ። ሒሩት ግን አልነበረችም። ከዚህ በኋላ ለረዥም ጊዜያት ያህል አለቆች በቃላት ስለመካረራቸው ፋዘር ተናግሮታል። ነገሩ ግን፤ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ዓይነት ነበር።

የጦር ሠራዊት ከመዳፉ የተነጠቀችውን የአልማዝ ፈርጥ አሜን ብሎ ለመቀበል አልቻለም። የዚህ ዳፋ ከሙዚቃው አብዮት አልፎ፤ በታህሳሱ ግርግር ስለመንጸባረቁ በእማኝነት የሚያስረዱ ብዙዎች ናቸው። በእርግጥም ወላፈኑ እየተጋጋለ ሄደ እንጂ አልተዳፈነም ነበር። ሒሩት በፖሊስ ኦርኬስትራ ከታሰበው በላይ ገናና ሆነች። የእሷና የፋዘር ግንኙነት ማስኮብለሉ ላይ አላከተመም። “ኢትዮጵያ ሀገራችን” የሚለውን ሙዚቃ፤ ግጥምና ዜማ ሠርቶ ሰጣት። የዚህ ሙዚቃ ጣዕም ከማንም አንደበትና ጆሮ የማይጠፋ ሆነ። የታላቅነቷን ደረጃ በብዙ ከፍ አድርጎ እንደ ሰንደቅ ዓላማው ሰቀላት።

የዘውዱ ሥርዓት ጀንበር ጠልቃ፤ የሶሻሊስት ጨረቃ ስትወጣ፤ ፖሊስ ባንድ በኮሪያ ተገኝቶ ዝግጅቱን ሊያቀርብ አቀደ። አንድ የኮሪያ ዜማ ሒሩት እንድትጫወተው ተደረገ። ምንም የማታውቀውን ቋንቋ አጥንታ መድረክ ላይም ወጣች። ከመድረኩ ፊት ለፊት የወቅቱ የኮሪያ ፕሬዝዳንት ኬኔዲ ሶንግ በክብር ተቀምጠዋል። ሒሩትን ያንን ዜማ አቀነቀነች መድረኩ ሌላ ሆነ። ፕሬዝዳንት ኬኔዲ ሶንግ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ወርቃማውን የእጅ ሰዓታቸውን በማውለቅ ሸለሟት። የኢትዮጵያ ሙዚቃ የወርቅ ዘንግ፤ በዚያን ዘመን ያልነካበት የዓለም ጫፍ አነበረም። ስለዚሁ የጀመርነው መንገድ ይሁንና፤ ባንዱ ከጥቂት ወራት በኋላ እንደገና ኩባ ገባ። ታሪክ ተደገመ።

ሒሩት የላቲን ሙዚቃ ይዛ በኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ፊት ቆመች። በድጋሚ ሌላ የወርቅ ሜዳይ ይዛ ተመለሰች። ሙዚቃ፤ በጦር ሜዳ ውስጥ ታላቁ ትጥቅ ስለመሆኑ ለኪነ ጥበብ እንደ ሒሩት ያስመሰከረለት የለም። በጦርነት ወቅት በጦር ቀጠናው ሁሉ ተገኝታ ስታዋጋ በወታደሩ ልብ ውስጥ በመግባቷ፤ “ሒሩት” የሚል ቀለሀ በስሟ ስለመሰየማቸው በማስታወስ ፋዘር ይናገራል። የፖሊስ ባንድን ይዛ በሙዚቃው አብዮት ጣራ የነካች ናትና፤ መቼም የሚረሳት አይደለችም። አምባሳደሩም ጭምር አድርጓታል።

እንግዲህ ጠቢቧ ብትሞትም ጥበቧ ግን አልሞተም። ያዜመቻቸው ሙዚቃዎቿ ዛሬ ይዘምሩላታል።

“እድሜ ሲገሰግስ ከንቱ ሰው ዘንግቶ፤

ነገ አልፎልኝ ይላል ማለፉን እረስቶ።

አይቀር መንፈራገጥ ያ ሆድ እስኪሞላ፤

ወድቃ እስክትሰበር ህይወት እንደ ሸክላ።”

አቤት! ሙዚቃ ነብስ ኖሮት ህይወትን እንዲህ ይተርከዋል። የዘመኑ ምርጥ የሙዚቃ ወለላ፤ ከሒሩት ልብ በድምጿ እየተንቆረቆረ “ቺርስ ለጆሮ!” ተብሎበታል።

ከሙዚቃ ሀሁ እስከ ህይወት ኤቢሲዲ፤ ከልጅነት እስከ ሽበት፤ ከውልደት እስከ እረፍት… መረዋ ድምጿን ስንስማ ኖረን፤ አሁን ደግሞ በተራ ልናነባት ነው። ከውልደት እስከ ሞት፤ ከሙዚቃ ድጓ እስከ መንፈሳዊ ህይወት የጉዞ ገጸ በርከቶቿን ይነግረናል። ፈታኝ የህይወት እንቆቅልሾች፤ በገጠመኝና በውጣውረዶች የታጀበውን የኑሮ ባቡሯን እያስከተለና እየከነፈ በሌላ ጊዜም ፍርጎውን እየገጨ ስኬትና ሳንካዎቿን ሊያስነብበን በመጽሐፏ መጥቶልናል። ዐብይ ፈቅይበሉ ጽፎ አሰናስኖታል።

ምረቃና ዝክረ ጠቢብ፤ በግንቦት 19ኙ የሰኞ አመሻሽ ላይ ነጸብራቋን በጥበብ አንጸባርቀዋታል። የፌደራል ፖሊስ የማርቺንግ ባንድ ኦርኬስትራና የዳዊት ፅጌ ባንዶች መድረኩን ደማቅ አድርገውታል። ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፤ ታዋቂ ግለሰቦችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ጨምሮ፤ ወዳጅ ዘመድ አድናቂዎቿ ሁሉ ተገኝተው ለእርሷ ያላቸውን ክብርና አድናቆት ከማዥጎድጎድ አልተቆጠቡም። “ሒሩትን አንረሳም” እንዳልነው ሁሉ፤ መጪው ትውልድም ላይረሳት ከመጽሐፉና ከሙዚቃ ሥራዎቿ ባሻገር ሌላ የዘመን መቀነት ታስሮላታል።

በመጨረሻው ሰዓት ሒሩት በቀለ የሞትን ጽዋ የተጎናጨችው በስኳር በሽታ ነበር። እናም ደግነት የወለደውን መልካምነቷን በማሰብና የእርሷን ስቃይ በወገኖቿ ላይ ያለማየት ምኞቷን እውን ለማድረግ፤ በስሟ የስኳር ሕሙማን ፋውንዴሽን ለመመሥረት ትልቅ እቅድ ተይዟል። ከመጽሐፉ የሚገኘው ገቢም፤ ሙሉ ለሙሉ ለዚሁ ማዕከል የሚውል ይሆናል። ሞተ ስጋ፤ ለጠቢብ ሰው ገና የህይወቱ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም። የአንጸባራቂ ክዋክብት ህያው ነጸብራቅ ይቀጥላል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም

Recommended For You