ፓሪስና ሁለተኛው ኦሊምፒክ ሲታወስ

ኦሊምፒክ በተወለደበት ግሪክ (አቴንስ) ትንሳኤውን በማድረግ በዘመናዊ መልክ ዳግም መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል። ፈረንሳዊው የሥነትምህርት ጠበብት ፒየር ደ ኩበርቲን (የዘመናዊው ኦሊምፒክ አባት) የኦሊምፒክን ጽንሰ ሃሳብ በመረዳትና ጠቀሜታውን በማመዛዘን በጥንት ተፈጥሮው ከመወሰን ይልቅ ዓለም ሊገለገልበት የሚገባ መሣሪያ በመሆኑ ዛሬ ባለው ቅርጽ እንዲቆም አድርገዋል። ይህንን ተከትሎም ሁለተኛው ኦሊምፒክ እአአ በ1900 ከግሪክ ውጪ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ተካሄደ።

ከመጀመሪያው ኦሊምፒክ አንጻር በርካታ ማሻሻያዎች የተደረገበት ይህ ኦሊምፒክ ምናልባትም ለዘመናዊው ውድድር መሠረት ያስያዘ ሊባል ይችላል። ይሁንና በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ሁኔታዎች አስደናቂና ፈገግታንም የሚያጭሩ ቢሆኑም፤ ትናንትን ማስታወስ ለዛሬ ማንጸሪያና ማሳያ ይሆናልና ይዘከራል። የኦሊምፒክ አዘጋጅ ሀገራት ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጡትና ከስፖርታዊ ሁነቶቹ ባለፈ ስለማንነታቸውና የታላቅነት ታሪካቸው በኪነጥበባዊ መንገድ ታግዘው ለታዳሚው የሚያሳዩት የመክፈቻ እና የመዝጊያ ትርኢት ፓሪስ ላይ አልነበረም። አስገራሚው ኦሊምፒክ እንዲሁ ጀምሮ ሲጠናቀቅ ከ26 ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺ226 የሚሆኑ ስፖርተኞች ተሳትፈውበት ነበር። ለ 14 ቀናት በተካሄደው ውድድርም 14 የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ነበሩ የተዘጋጁት። ከተሳታፊዎቹ መካከል 72 ከመቶ የሚሆኑት የአዘጋጇ ሀገር ፈረንሳይ ዜጎች ሲሆኑ የአብዛኛው ውድድር አሸናፊዎችም ራሳቸው ነበሩ። አሜሪካ እና እንግሊዝ ደግሞ በርካታ አሸናፊነትን በማስመዝገብ ተከታዮቹን ደረጃዎች የያዙ ሀገራት ናቸው።

በየትኛውም ስፖርት ይሁን አሸናፊ የሚሆኑ ተወዳዳሪዎች ሜዳሊያ ባያጠልቁም እንደየስፖርት ዓይነቱ ዋንጫ የሚሸለሙም ሆነ እስከ 3 ሺ ፍራንክ የሚደርስ ገንዘብ የሚበረከትላቸው ነበሩ። ውድድሩ በ19 የስፖርት ዓይነት ሲካሄድ፤ አንዳንድ ተሳታፊ ስፖርተኞች ፉክክር ላይ ስለመሆናቸው እንጂ ውድድሩ ኦሊምፒክ መሆኑን አለማወቃቸው አስገራሚ ነበር። በወቅቱ የኦሊምፒክ ስፖርት በሚል የተለዩ የስፖርት ዓይነቶች አለመኖራቸውን ተከትሎ ውድድሩ በተለያየ የስፖርት ዓይነት ይካሄድ እንጂ ከዚያ በኋላ ኦሊምፒክ ላይ ያልታዩ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል ዓሳ ማጥመድ፣ የሞተር ውድድር፣ ባሎን ማብረር፣ ክሪኬት፣ የ200 ሜትር ውሃ ዋና መሰናክል፣ ጥልቅ የውሃ ዋና ውድድር፣… ጥቂቶቹ ናቸው።

ውድድር ከተካሄደባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ አትሌቲክስ ሲሆን የመም እና የሜዳ ተግባራት ውድድሮችን ያካተተም ነበር። ይሁንና ውድድሩ መም ሊባል በማይችል፣ በዛፎች በተከበበና ሳር በበዛበት እንዲሁም በቂ ምልክት በሌለበት ሥፍራ የተደረገ ነበር። አስቂኝ የሆነው ጉዳይ ደግሞ በውድድሩ ሥፍራ ምቹ አለመሆን የተነሳ በውርወራ ስፖርቶች እንደ ጦር እና ዲስከስ ያሉ መሣሪያዎች መሬት ከመድረሳቸው አስቀድሞ ዛፎች ላይ ተሰክተው መቅረታቸው ነው።

የማራቶን ውድድር የሚካሄድባቸው መስመሮች በተገቢው ሁኔታ ምልክት ያልተደረገባቸው ስላልነበሩ አትሌቶች መንገድ እስከመሳት ደርሰዋል። ከሁሉ በላይ አስቸጋሪ የነበረው ግን ሩጫ በተሽከርካሪዎች፣ እግረኞች እና ብስክሌተኞች እንቅስቃሴ መረበሹ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ውድድሩ የተካሄደው ከሰዓት በኋላ በመሆኑ ሙቀቱ ውድድሩን ፈታኝ በማድረጉ አንዳንድ ተወዳዳሪዎች ወደ ሬስቶራንቶች ጎራ በማለት ቀዝቃዛና የአልኮል መጠጦችን ‹‹ፉት›› እያሉ ሩጫውን መቀላቀላቸውም ሳቅን የሚያጭር ገጠመኝ ነበር። ከውድድሩ በኋላ በአሜሪካ በኩል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን የያዙት የአዘጋጇ ሀገር አትሌቶች አቋራጭ መንገድ ተጠቅመዋል የሚል ክስ መቅረቡም ሌላኛው የኦሊምፒኩ አዝናኝ ትዝታ ነው።

በዚህ ኦሊምፒክ ከነበሩ ነገር ግን ዳግም ካልታዩ አስገራሚ ጉዳዮች መካከል አንዱ በሕይወት ያሉ እንስሳትን ማሳተፉ ነበር። ነገሩ አሳዛኝ ቢሆንም በወቅቱ ለዒላማ ተኩስ ውድድር ጥቅም ላይ የዋሉት ፔንግዊን የተሰኙት ወፎች ነበሩ። ይህም አስፈላጊ አለመሆኑን በመረዳት ከዚያ በኋላ ባሉ ኦሊምፒኮች እንስሳት በመሰል ሁኔታ ሕይወታቸው እንዳይጠፋ ተደርጓል።

አሻሚ የሆነው የሴቶች ተሳትፎ ታሪክ የሚጀምረውም በዚሁ ወቅት ሲሆን፤ የኒውዮርክ ከተማ ተወላጅ የሆነችው ሄለን ባርቢ ደግሞ ከዚሁ ጋር ስሟ የሚያያዝ አትሌት ናት። በቡድን የጀልባ ቀዘፋ ተሳታፊ የነበረችው አትሌቷ በጋራ በተገኘው አሸናፊነት ምክንያትም በተሳትፎ ብቻም ሳይሆን በድልም ስሟ ቀድሞ የሚጻፍ ተወዳዳሪ ልትሆን ችላለች።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You