የልጅነት ህልሙን ያሳካው የቱሪዝም አምባሳደር

‹‹የጠራ ዓላማ እና ያንን ከዳር ለማድረስ ውጣ ውረድን የመቋቋም አቅም ያላቸው ሰዎች›› የስኬታማነታቸው ዋነኛው መገለጫ ይሄው መሆኑ ይጠቀሳል። ስኬት ለራስ በተቀመጠ ግብና በሀገርና በማህበረሰቡ ላይ በሚያሳድረው በጎ ተፅእኖ ይመዘናል። ከዚህ መነሻ ግለሰቦች በሕይወት መስመር በመረጡት መስክና ሙያዊ እውቀት ላይ ተመርኩዘው ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለማህበረሰባቸው ይበጃል ያሉትን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ሁሉም እንደየተሰጥኦውና ጥረቱ ተደራርበው ሀገርን በሚሰሩ የሙያ ጡቦች ራሱን ያንፃል። ድምር ውጤቱ ኃያልነት፣ የማይበገር ስልጣኔ ይሆናል። የትውልድ ቅብብሎሹ ገናና ስልጡንና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ሀገር እንድትፀና ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

የዝግጅት ክፍላችን ለዛሬ ከላይ ባነሳነው መመዘኛ ውስጥ ከሚሰፈሩ ግለሰቦች መካከል በአንዱ የሙያ መስክ ላይ የተሰማራ ግለሰብ እንግዳ ለማድረግ ወድዷል። የቱሪዝም ባለሙያ (አስጎብኚ) ነው። ከልጅነት ህልሙ ጋር ለመገናኘትና ያሰበው ደረጃ ለመድረስ ፅናቱን፣ ቁርጠኝነትን፣ እውቀቱን ተጠቅሟል፤ አያሌ የሕይወት ፈተናዎችንም ተጋፍጧል። በሆቴሎች በእንግዳ ተቀባይነት ከመሥራት ተነስቶ የአስጎብኚ ድርጅት (Tour Company) እስከ መመሥረት ዘለቋል። ዛሬ ከደረሰበት የቀደመ ህልሙ ይልቅ ለራሱ የሰጠው የነገ የቤት ሥራ ድንቅ ነው።

ሳሙኤል ታደሰ ይባላል። የ‹‹ግራንድ ኢትዮጵያ ቱር ካምፓኒ›› መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ነው። የተወለደው ከጎንደር ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው በታች አርማጭሆ ገንበራ ጊዮርጊስ በምትባል የገጠር ቀበሌ ውስጥ በ1986 ዓ.ም ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ቦታው (ከ3ኛ እስከ 5ኛ ክፍል) በጎንደር በአንገረብ መለስተኛ ትምህርት ቤት (ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል ደግሞ)፣ በጎንደር አሸዋ ሜዳ (ከ6-8) ተከታትሏል።

ባለታሪካችን ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኘ ነው፤ እንደ ማንኛውም የአርሶ አደር ልጅ በልጅነቱ ወደ አስኳላ ከመሄዱ አያቶቹን በግብርና ሥራ ማገዝ ነበረበት። ይሁን እንጂ ለትምህርቱ ቀናኢ በመሆኑና ውሳኔውን ባለመቀበሉ ምክንያት ከዚያ ጠፍቶ ዘመድ ቤት እስከ መሸሸግ ደርሷል።

ተሸሽጎ ግን አልቀረም፤ የአያቶቹን እርግማን በመፍራት ወደ ቤተሰቦቹ ተመልሶ ከብትና ፍየሎችን በማገድ (በእረኝነት) አገልግሏል። ከፍተኛ የሆነውን የትምህርት ፍላጎቱን ያጤኑት ቤተሰቦቹ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ እንዲገባ ፈቅደውለት። ወጣት ሳሙኤል ትምህርቱን ለመማር የሚደጉመው ገንዘብ የሚያገኘው በራሱ ጥረት ነበር።

‹‹ክረምት ሲመጣ ወደ ቆላ በመሄድ ከዘመድ ጋር ሰሊጥ በማሳረስ እሱን እየሸጥኩኝ እማር ነበር›› የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ ወቅቱ ለእርሱ የፈተና ጊዜ እንደነበር ይገልፃል። ወደ ቆላ ሄዶ ገንዘብ የሚያገኝበት ሥራ በወባ በሽታ ምክንያት ፈተና ውስጥ ገባ:: ወባ ሥራውን በአግባቡ እንዳይሰራ አደረገው፤ ረጅም ጊዜውን የሚያሳልፈው በመሥራት ሳይሆን በመታመም ሆነ።

በዚህ ምክንያት የቆላማው ቦታ ሕይወቱን ተወው:: ለትምህርቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማግኘት ሌላ መላ ደግሞ ዘየደ:: ትናንሽ ሸቀጦችን መሸጥ ውስጥ ገባ። ወደ አስፋልት አካባቢ ወጣ በማለት ጫማና ሌሎች ቁሶችን በመሸጥ ለትምህርት የሚያስፈልጉት ሁሉ እየገዛ ተማረ። ንግዱም አልጋ ባልጋ አልሆንለት አለ፤ ፍቃድ ስላልነበረው ከደንብ አስከባሪዎች ጋራ መሯሯጥ የዘወትር ፈተናው ሆነ።

ወጣት ሳሙኤል ይህንንም ፈተና የሚያሻግረው እድል አገኘ:: ከ9ኛ እና 10ኛ ክፍልን በፋሲለደስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማር አንድ በጎ አጋጣሚ ተፈጠረለት:: አሁን በሕይወት የተለየው ወንድሙ አሜሪካ ሄዶ ከጠፋ ከረጅም ጊዜ በኋላ አድራሻውን አግኝቶ መጠያየቅ ጀመሩ፤ በመጠኑ ያግዘውም ጀመር:: አጋጣሚው ሳሙኤልን ወደ ህልሙ እንዲቀርብና ጥረቱን እንዳያቆም ትልቅ ብርታት ሆነው።

ወጣት ሳሙኤል 10ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ በቀጥታ የልጅነት ህልሙ ወደሆነው የሙያ ትምህርት ቤት አቀና። ልጅ እያለም የቱሪዝም ባለሙያ የመሆን አላማ ነበረው። አስተዳደጉ ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው። በተጨማሪ ወደ ጎንደር ይመላለስ በነበረበት ወቅት መስህቦችን የመመልከት አጋጣሚው ነበረው። ተራራማና ውብ የተፈጥሮ ቦታዎችን በእግር ጉዞ የማድረግ አጋጣሚው ለሳሙኤል የልጅነት የየእለት ድርጊቱ ነበር። ይህ ተፅእኖ ልቡ ለቱሪዝም እንዲቀርብ አስገደደው። እያደገ ሲመጣና ትምህርት ሲከታተል ስለ የቱሪዝም ፍላጎቱ ይበልጡኑ ጠነከረ።

‹‹የ10ኛ ክፍልን ፈተና እንደወሰድኩ በጎንደር ቴክኒክና ሙያ በቱሪዝም በቱር ጋይድ ትምህርት እየተከታተልኩ ጎን ለጎን ሥራ ጀመርኩ›› የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ ፎገራ ሆቴል በእንግዳ መቀበል ሥራ እንደተቀጠረ ያስታውሳል። በዚያም ለሁለት ዓመት ከሠራ በኋላ ወደ ጃንተከል ሆቴል በመሄድ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ያህል ሠራ።

በቱሪዝም ትምህርቱም በደረጃ 4 ተመርቆ የሚሰጠውን ምዘና ማለፉንና ወደሚወደው የሙያ ዘርፍ መሰማራቱን ይገልፃል። ከሙያ ፍቅሩ ባሻገር በትምህርቱ ያስመዘገበው ውጤት ተደምሮ በጎንደር ከተማ አካባቢ አስጎብኚዎች ማህበር የአስጎብኚ ማስታወቂያ ሲያወጣ ተወዳድሮ በማለፉ በጥር ወር 2009 ዓ.ም ወደ ቱሪዝም ይበልጥ ዘልቆ ገባ።

በውጣ ውረድ የተሞላው የወጣት ሳሙኤል ሕይወት ህልሙን እውን ለማድረግ እንቅፋት አልፈጠረበትም። ተግዳሮቶቹን ሁሉ በፅናት አልፎ የሚወደውን ሙያ ተቀላቀለ እንጂ። ዳግም በደረጃ 5 በቱሪዝም ማኔጅመንት ተመረቀ። በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ትምህርት ሁለተኛ ዓመት እየተማረ የነበረ ቢሆንም በሥራ መደራረብ ምክንያት ባያጠናቅቀውም፣ እፎይታ ሲያገኝ የሙያ ደረጃውን እያሻሻለ እንደሚቀጥል ይናገራል።

‹‹በጎንደር አስጎብኚ ማህበር ውስጥ ለስምንት ዓመት ሰርቻለሁ›› የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ አብረውት ከጀመሩት 18 ባለሙያዎች ውስጥ ልቆ መውጣት መቻሉንና በሥራውም ተቀባይነት ማግኘቱንም ያስታውሳል። ይህ ውጤታማነቱ የራሱን የአስጎብኚ ድርጅት እንዲያቋቁም በር እንደከፈተለትም ይገልፃል። የዓመታት ህልሙን በትምህርቱ ሙያውን ከማዳበር ጀምሮ ለዓመታት ባካበተው ልምዱ ተጠቅሞም የግል ኩባንያ መመሥረት እንደቻለም ያብራራል።

ወጣት ሳሙኤል ታደሰ አሁን ግራንድ ኢትዮጵያ የሚል የአስጎብኚ ድርጅት (tour and Travel) ከፍቶ በግሉ እየሠራ ይገኛል። በሥሩም 10 ሠራተኞችን ቀጥሮ ያስተዳድራል። ከበርካታ ወኪል ድርጅቶች ጋርም ግንኙነት መፍጠር ችሏል።

የእርሱ ህልም እሩቅ የሚጓዝ ነው። በልጅነቱ ያሳለፈው ውጣ ውረድ በሌሎች መሰል ህልም ባላቸው ወጣቶች ላይ እንዲከሰት ስለማይሻ በድርጅቱ ውስጥ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ለመቅጠር እየሠራ እንደሆነ ይናገራል። በተለይ ከቴክኒክና ሙያ የተማሩትን እድል ለመስጠት ፍላጎት አለው።

‹‹አዳዲስ ባለሙያዎችን እንደኛ ዓይነት ድርጅትና ሆቴሎች እድል ሰጥተው ማብቃት ይኖርባቸዋል›› የሚለው ወጣት ሳሙኤል፤ እርሱም አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ተምረው የሥራ ልምድ የሌላቸውን ባለሙያዎች እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ውጥን መያዙን ይናገራል። ለዚያ ግን አሁን እየተቀዛቀዘ የመጣው የቱሪዝም ሥራ ሰላሙ ተመልሶ መነቃቃት እንዳለበት ይገልፃል።

ግራንድ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ቱሪስቶችን እየተቀበለ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች እንደሚያስጎበኚ መሥራቹና ሥራ አስኪያጂ ወጣት ሳሙኤል ይናገራል። በዚህ ተግባሩ መልካም ስም መገንባቱንና በርካታ ቱሪስቶች ተመራጭ እንዳደረጉትም ይገልፃል። በዚህም የኢትዮጵያን ተወዳጅ መስህቦች የማስተዋወቅ ስኬታማ አፈፃፀም እንዳለው ይናገራል። የሀገር ገፅታን ከመገንባት ባሻገር የውጭ ምንዛሬ በማምጣት በኢኮኖሚው ላይ የድርሻውን ተፅእኖ በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ይናገራል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮሮናና በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች በተከሰተ ግጭት ሥራው መቀዛቀዝ ቢያሳይም ድርጅቱ ተፅእኖውን ተቋቁሞ እየሠራ እንደሆነ ይናገራል።

‹‹ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ሀብት አላት፤ ነገር ግን ተደራሽ አድርገነው እየሠራንበት አይደለም›› የሚለው የግራንድ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ፤ እርሱ በአካባቢ ሳይወሰን ራሱን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ መስህቦችን ለዓለም ለማስተዋወቅ እና አዳዲስ ፅንሰ ሃሳቦችን ለማስረፅ እየሠራ መሆኑን ይናገራል።

በተለይ ከዚህ ቀደም ተደራሽ ያልሆኑ ሀብቶች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተቆራኙ የጉብኝት ዓይነቶችን በማስለመድ (ማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም) የሀብቱ ባለቤት የሆኑ ዜጎች ቀጥታ ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል ለመፍጠር እየሠራ መሆኑን ይናገራል። ቱሪስቶችም የገጠሩን ሕይወት በተግባር የሚያዩበትና ራሳቸውም ልክ እንደ ሀገሬው ሰው ለተወሰኑ ቀናት የሚኖሩበትን የጉብኝት ዘይቤ ከዚህ ቀደም የሠራበት እንደነበረ አስታወሶ፣ አሁንም ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልፃል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝም በበቂ ሁኔታ እንዳልተሰራበት የሚገልፀው ወጣት ሳሙኤል፤ ድርጅቱ በዚህ ዘርፍ ላይ ለመሥራት እቅዶችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይናገራል። በተለይ ከመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ጋር ቀጥታ ግንኙነት በመፍጠር ጎብኚዎች ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ በሥራ የተጨናነቀ አእምሯቸውን እንዲያፍታቱ አድሉን እየፈጠሩ መሆናቸውንም ጠቁሟል። ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን የተፈጥሮ፣ የባህል፣ የታሪክና ልዩ ልዩ እሴቶች የመጎብኘት ልምድ እንደሌላቸው በመግለፅ የድርጅቱ ቀዳሚ አላማ ይህንን ባህል መቀየር እንደሆነ ይናገራል።

የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወጣት ሳሙኤል በቱሪዝም ዘርፍ ላይ አንድ ድርጅት ብቻ በማሰብ ተጠቃሚ ለመሆን እንደማይሰሩ ይናገራል። ይልቁንም አስጎብኚ ባለሙያዎች፣ ሆቴሎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ከቱሪስቱ በሚገኝ ገቢ እንደየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትና በጥቅል በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ የሚመጣበት መሠረት ለመጣል እየሠሩ መሆኑንም ያስረዳል።

እንደ ሳሙኤል ገለፃ፤ ግራንድ ቱር ለቱሪስቶች ሙሉ የጉብኝት ጥቅል ያቀርባል። ይህም የመኪና ኪራይ፣ የሆቴል፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የምግብ፣ በየአካባቢው ለሚገኙ አስጎብኚ ባለሙያዎች እና የአጃቢዎችን ያካትታል።

ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አስቀድመው ለድርጅቱ እንደሚያሳውቁና አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት እንደሚያደርጉ በመጥቀስም፣ ዋናው የጉብኝት መርሃ ግብር ከመጀመሩ 10 እና 15 ቀናት በፊት ዝግጅቱ እንደሚጠናቀቅ ይናገራል። ይህም ይበልጥ ተመራጭ እንደሚያደረገው ያስረዳል። ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና የአርኪዮሎጂካል አካባቢዎችን መጎብኘት ሲፈልጉ በቀጥታ ከግራንድ ኢትዮጵያ የአስጎብኚ ድርጅት ጋር እንደሚገናኙም ይናገራል።

ሥራ አስኪያጁ ድርጅቱ የማህበረሰቡን እሴቶች በማስተዋወቅ፣ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር የራሱን ዐሻራ እየጣለ እንደሆነም ይገልጻል። ይህ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመዳረሻ ልማት ከሰጠው ትኩረት ጋር ሲደመር የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ለማድረስ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ይናገራል።

‹‹እኛ ዲፕሎማት ነን፤ ከአንድ አምባሳደር አንተናነስም›› የሚለው የግራንድ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ፤ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ መሥራት፣ የሀገራችን ገፅታ እንዳይበላሽ ከቱሪስቶች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠርና በጎ በጎውን ስለ ሀገር ማሳየት እንደሚጠበቅ ይስገነዝባል። የእርሱ ድርጅትም ይህንን እንደ ዋንኛ እሴት ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ጠቅሶ፣ ላለፉት 13 ዓመታትም ይህንኑ ተግባር በስኬት ሲያከናውን መቆየቱን ነግሮናል።

በግሉ ወጣቶች ሥራ እድል እንዲያገኙና በእውቀት ራሳቸውን እንዲያበቁ እንደሚያግዝ ጠቅሶ፣ በተለይ በበርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር እንደሚሳተፍ ወጣት ሳሙኤል አስታውቋል፤ ሁሉም የድርሻውን ሲያበረክት ሀገርን ማሳደግ ይቻላል የሚል መልእክቱንም አስተላልፏል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You