አሽሙር

ሹል አፍ.. ከስሟ ቀጥሎ፣ ሁሉም ከሚያውቀው ሰማያዊ ፈገግታዋ ቀጥሎ መታወቂያዋ ነው። ስም ከማንነት ጋር ልክክ ያለላት ሴት ናት። እድል ሳይሰጣት ባተሌ ሆና ቀረች እንጂ እግዜር ሲሰራት ለንግስትነት አስቦ ከመሰለኝ ሰንበትበት ብያለው። ባለሰማያዊ ፈገግታ ነፍስ አላት። ስትስቅ ከጉሮሮዋ አፈትልኮ ገጽዋ ላይ የሚበተን ሰማያዊ መሳይ ፈገግታ አለ። ይሄ እንዴት እንደሆነ አላውቅም። ማንም ባለቀለም ሳቅና ባለህብር ፈገግታ ከውስጡ ሲተፋ አይቼ አላውቅም። እነ በዓሉ ውበትን ሲገልጹ፣ እነ አዳም ረታ ሳቋ ፈገግታዋ ሲሉ የነፍስን ህያው መልክ አለመናገራቸው ምን ነክቷቸው ነው እንድል ያደርገኛል። ሼክስፔር በውበት ላይ ሲዘባነን፣ ዴዝዴሞና ሃምሌትን፣ ሮሚዮና ጁሌትን በህያው ቱባ ብዕሩ ከነፍስ ስጋችን ሲቀላቅላቸው የሳቅን መልክ መቀለም እንዴት ጠፋው? ሎሬቱ ጸጋዬ ቢሆንስ፣ በጠራ ጨረቃ በእኩለ ለሊት፣ አይኖቿ እያበሩ እንደከዋክብት ሲል መንግስቱ ለማ የሳቅ መልክን ለምን አለፈው? ደበበ ሰይፉ..ትካዜ ባጠላው ልብ ‹ጠብቄሽ ነበረ› ብሎ ሲገጥም የጠበቃትን ሴት ፈገግታ ለምን ችላ አለው?

ለእኔ ሳቅ ቀለም አለው..ፈገግታ ህብር አለው። ያለቀለም የተፈጠረ ምን አለ? ሰማይ ሰማያዊ፣ ምድር አረንጓዴ ናቸው። ሰው በቀይና ጠይም፣ በጥቁርና ቀይዳማ በአራት አይነት ቀለም የተዠጎደጎደ ነው። ፈገግታ ግን ምን መሳይ ነው? እንደእንኮይ በሰላ ቀይ ፊት ላይ የተሳቀ ጸሀያማ ሳቅ፣ በደግነት በቆነጀ ልብ በኩል የተፈገገ ፈገግታ ምን መልክ ነው? ገና ልትስቅ ስትል ጀምሮ እንደእስስት የምትጋራው የሰማይን ቀለም የሚመስል ነገር አላት። ይቺ ሴት ሹል አፍ ናት። ደግነቷን የከለለ፣ ትህትናዋን የደበቀ ለመቶ ሜትር የቀረበ እንዥርግ አገጭ አላት። ሰማያዊ ፈገግታዋን የጋረደ፣ ንግስትነቷን የሰወረ እንደቀስት የሾለ አፍ አላት።

አፍ እንደዛ ሲሾል፣ አገጭ በዛ ልክ ሲመዘዝ በምድር ላይ እሷን ብቻ ነው የማውቀው። ሾላ ሹል አፍነትን አተረፈች። እንደእኛ ሰው በእግዜር ፍጥረት ላይ የሚያላግጥ ማን አለ!.? በእንከናችን እንጂ በስማችን በማይጠራን ማህበረሰብ መሀል ነን። በሙላታችን ሳይሆን በጉድለታችን ሊያውቀን በሚፈልግ አእምሮ ጋር የተነካካን ነን። የሚጎዳን ተፈጥሮ ሳይሆን ፍጡር ነው። በማይረባ ጎናችን በኩል ሆን ብለው ይጠጉናል..እየሰደቡን መጥተው እየሰደቡን ይሄዳሉ። አፉ የሾለ ሰው ነገረኛ ነው የሚባል ተለምዷዊ አባባል አለ። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እውነት ነው ስል ተቀብዬዋለው። እውነት ሆኖ ይሆን አጋጣሚ ሹል አፍ የሆኑ ሁሉ ለነገረኛነት የቀረቡ ሆነው ተመልክቻለው። ንግስትን ስጠጋ ግን የነበረው ሁሉ ግጥምጥሞሽ እንጂ እውነት እንዳይደለ ገባኝ። እንዳውም የእዝነትና የጽድቅ መንፈስ የሞላባቸው ሆነው ነው ያገኘኋቸው።

ስም ይወጣ ከቤት ይከተል ጎረቤት ሆነና እንጂ ንግስትነት የሚያንሳት ነበረች። ክፉ አማቾች አሏት..በባሏ ቤተሰቦች በኩል የወጡላት እንደረኸጥ፣ ሹል አፍ፣ ገልቱ የመሳሰሉ ነውረኛ ስያሜዎች አሏት። ከሁሉም ጎልቶ የወጣው ግን ሹል አፍ የሚለው ቅጥያዋ ነው። የባሏ እናት ስለማይወዷት ‹ይቺን ምኗን ሴት ብሎ አገባት? ከምን ቀላቀለኝ..ይሄ መድረሻ ቢስ? የሆ ነገር አስነክታው እንጂ በደህናው እዚች ገልቱ ላይ አልወደቀም..ምን ያለችው ሹል አፍ ናት? ሲሉ ሊጠይቃቸው ለመጣ ሁሉ ክፉዋን ይናገራሉ። በምራቷ የተጀመረው የሹል አፍ ሽሙጥ ጎረቤት ደርሶ ሰፈሩ ውስጥ ሹል አፍ ሆና ቀረች።

ግን እኮ ክፉ አይደለችም..ያለነውር የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ለሁሉ እንደእግዜር ናት። የባለቤቷ ቤተሰቦች ለምን እንደጠሏት አታውቅም። ከእናቱ የጀመረ እስከ መጨረሻ ወንድሙ ድረስ እንከናም ናት። የሆነ ዘር ከዘራቸው እንደተቀላቀለ አይነት ሲጸየፏት ለጉድ ነው። ለበዓል ቤታቸው ዝር ከማይሉ ሁለት ሰዎች አንዷ እሷ ስትሆን ሌላኛው ደግሞ ጎረቤታቸው ጥላዬ አንዱ ነው። እሷስ ሹል አፍ ሆና ነው የጥላዬ ግን ማንአለብኝነት የወረረው ነው። የሆነ ጊዜ ወሰን የሚጋራውን የቤቱን አጥር ሲያሳጥር ወሰን ገፍተሀል ብለው እንዳኮረፉት 20 ዓመታት ተቆጠሩ። ጉርብትናዬ ይበልጣል ወሰን ካለፍኩም እክሳለው ብሎ ባለሙያ አምጥቶ ወሰኑን ሲያስለካ ድንበር ገፊዎቹ እነሱ ሆነው ተገኙ። የሚሉት ሲያጡ እንዴት ሕግ ትጠራብናለህ ሲሉ አይንህ ላፈር አሉት። ይሄው ሃያ ዓመታቸው ቡና ከተጠራሩ። መጥፎ ሚስት እንዳለው ወንድ ምን እድለቢስነት አለ? የባል ደግነቱ ባትናገር ሚስቱ አይደል ወትሮስ አባባሉ? ጋሽ ፍታወቅ ከሚስታቸው ጋር ካልሆኑ ሰላም ብለውት የሚያልፉ ናቸው። መቼም ፍታወቅ ማን እንደሆኑ አይጠፏችሁም፣ የክፉዋ ሴት ባለቤት ናቸው። አብረዋቸው ካሉ ግን መለስ ቀለስ የለም ወደፊት እንደተባለ ወታደር ወደፊት ብቻ።

የሴት ክፉ አይጣልባችሁ! ሴት ካሰኛት መላዕክትነቷን ገፋ በክፋቷ ሰይጣንን ያስቀናች መሆን ትችላለች። ጋሽ ፍታወቅ ግን በምኗ ተማርከው የታገቢኛለሽ ጥያቄን አቀረቡላት? እርግጥ ወጣት ሳሉ ቆንጆ መሆናቸው ዘመን ካጠላው እርጅናቸው መታዘብ ይቻላል። ቢሆንም ይሄን ያክል ጭካኔ በሴት ነፍስ ላይ ተጭኖ አንዲትን ኮረዳ ለታገቢኛለሽ ማጨት እብደት ካልሆነ ምንም ሊባል አይችልም። ነው ወይስ ጋሽ ፍታወቅ ቆንጆ ትሁን እንጂ አመሏ ያጋንት ቢሆንም እችለዋለው በሚል የአፍላነት ፍልስፍና ውስጥ ሆነው ይሆን?

የሆነው ይሁን ጋሽ ፍታወቅና እማማ ትዋብ (እማ ሲባሉ እንደማይወዱ ሰምቻለው ቢሆንም ከእማማ በቀር በሌላ አልጠራቸውም..እርር ድብን ይበሉ..እኚህ አዛውንት ዲያቢሎስ) መንገድ ላይ ሲያዩዋት መንገድ ከመቀየስ ጀምሮ አሽቀንጥሮ እስከሚወረውር ግፍተራ ድረስ ያደርሱባታል። ግልምጫን በየአይነቱ የቀመሰችው ከባለቤቷ ቤተሰቦች ዘንድ ነው። ወደቤታቸው የመጣ ስለእሷ ክፉ ነገር ሳይሰማ ተመልሶ አያውቅም። ‹ይቺ ረኸጥ ልጄን በመዳኒት አደንዝዛ አገባችው..እንጂማ ማን በጨው ይቀምሳት ነበር› በሚል ወሬ ጀምረው..ማብቂያቸው ‹ብዙ ርግማንና ማጣጣል ያለበት ሹል አፍ ነው።

ባሏ ግን እንደነሱ አይደለም አለ የተባለ ባሏ ሆኖ ጎኗ የቆመ ነው። እዛ ማህጸን ውስጥ እንዴት እንደበቀለ አይገባትም። እዛ ቤተሰብ ውስጥ፣ በነዛ እህትና ወንድሞቹ መሀል እንዴት ሰው እንደሆነ አታውቅም። ብቻ ክብሯ ነው..ጠልሽታና ነውራ መውደቂያዋ ተራራማ ልቡ ነው። ተሰድባና ተንቋሻ ማረፊያዋ ሃሳቡ ነው። ሙሽራዬ ብሎ ነው የሚጠራት። የዛችን ሴት ጡት ጠብቶ፣ በክንዷ ታቅፎ፣ በከንፈሯ ተስሞ እንዲህ መጥራት፣ እንዲያ ማፍቀር እንዴት እንዳወቀ አታውቅም። ክፋቷን ሳታጋባበት እንዴት እንደተረፈ ይገርማታል። ሙሽራዬ ሲል ከወደቀችበት እንጦሮጦስ ያወጣታል። በብዙ መከራ ውስጥ እንዳለፈች እመበለት ከማንም የላላ፣ ለማንም የሚነሆልል ስስ ልብ አላት። ቤቷ የሄደን አብልታ፣ የታመመ ጠይቃ፣ በእድርና በማህበር ማን እንደእሷ የተባለላት አገልጋይ ናት። ድሀ ቤቷ የማይጠፋ፣ ጎረቤቶቿ ቅዳሜ ገበያ እስኪደርስ ያሻቸውን የሚያገኙባት ሆና መገፋቷ፣ ሹል አፍ መባሏ ለሰሚው ግራ ነው።

ግን ሚስትና የባል ቤተሰብ እንዳይግባቡ ተፈጥሮ ከመሀከላቸው የሆነ ስንጥር አጉድላ ይሆን? የባልና የሚስት ቤተሰብስ መች ተፋቅረው ያውቃሉ? በየሄድኩበት ሁሉ ሚስት በባል ቤተሰብ የክብር ምንጣፍ ሲነጠፍላት፣ እንደ ቤተሰብ ባይሆንም ባልም በሚስቱ ቤተሰቦች በኩል መድፍ ሲተኮስለት አላየሁም..አልሰማሁም። ተናንቆና ተሰጋግቶ ትዳር አለ?

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You