ትኩረት ለዓይነ ስውራን ሙአለ ሕፃናት ትምህርት ቤት

ወይዘሮ በትረወርቅ ለማ በአዲስ አበባ ከተማ ዘነበ ወርቅ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የሚኖሩት። ሮኢ ያሬድ የሚባል የስድስት ዓመት ልጅ አላቸው። ሮኢ ለወይዘሮ በትረወርቅ ብቸኛ ልጃቸው ነው። ከብዙ ፀሎት፣ ልመናና ስለት በኋላ የተገኘ ልጃቸው ነው። ሮኢ ገና እንደተወለደ ልክ እንደማንኛውም ሕፃን ሙሉ አካል ያለው ነበር የሚመስለው። ይሁንና ወይዘሮ በትረወርቅ እናት ናቸውና የልጃቸውን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ ሮኢ ማየት እንደማይችል አረጋገጡ። በጊዜው የተሰማቸው የሀዘን ስሜትም እጅግ ከባድ ነበር። እንዲህ አይነቱ ክስተት ከዚህ ቀደም በቤተሰባቸው ውስጥ ተከስቶ ስለማያውቅ ለመቀበልም ተቸግረው ነበር።

በኋላ ግን ወይዘሮ በትረወርቅ ሮኢ ማየት አለመቻሉን አምኖ ከመቀበል ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም። ሮኢም በቤት ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደውም ማየት ከሚችሉ ሕፃናት የበለጠና ፈጣን እየሆነ መጣ። አስተውሎ የሚያደርጋቸው ነገሮችም ቤተሰቡን ያስደምም ጀመር። እድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ግን ወይዘሮ በትረወረቅ በአንድ ነገር እንደገና መጨነቃቸው አልቀረም። ይኸውም የት ትምህርት ቤት እንደሚያስገቡት ነበር ጭንቀታቸው። እርሱን ለመርዳት ሲሉ የበርካታ ትምህርት ቤቶችን ደጃፍ ረግጠዋል።

ወይዘሮ በትረወርቅ መጀመሪያ ላይ ጀርመን ትምህርት ቤት ሮኢን የማስገባት አጋጣሚ ቢፈጠርላቸውም ከስምንት ዓመት ጀምሮ ብቻ እንደሚቀበሉ ስለተነገራቸው ልጃቸውን ትምህርት ቤት ለማስገባት ሳይችሉ ቀርተዋል። በኋላ ላይ ግን ቪዥን በሶሻል ሚዲያ አማካኝነት ቪዥን ማየት የተሳናቸው ሕፃናት ወላጆች የመሰረቱት በጎ አድራጎት ድርጅት ያቋቋመውን የሙአለ ሕፃናት ትምህርት ቤት አይተው ልጃቸው ሮኢን ማስመዝገብ ቻሉ። ከዛን ቀን ጀምሮ ወይዘሮ በትረወርቅ በልጃቸው ላይ ለውጥ እያዩ መጡ።

አሁን ሮኢ ወደ ቪዥን የዓይነ ስውራን ሕፃናት ትምህርት ቤት ደርሶ ሲመለስ በየቀኑ አዳዲስ ለውጦችን ማምጣት ችሏል። ንግግሩ ላይም ጥሩ ለውጥ አምጥቷል። ከሰው ጋር የመግባባት አቅሙም ከፍ ብሏል። በዚህም ወይዘሮ በትረወርቅ እጅግ ደስተኛ ናቸው። የሙአለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ ብዙም ትኩረት ያላገኙና ተደራሽነታቸውም እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ታዲያ መንግሥት ፣ ማህበረሰቡና ሌሎችም ረጂ ድርጅቶች ለትምህርቱ ትኩረት መስጠትና ተባብረው ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንዳለባቸው ነው በዚሁ አጋጣሚ ወይዘሮ በትረወርቅ መልእክታቸውን የሚያስተላልፉት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ገና በእድገት መነሻ ባሉ ሀገራት ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው ትኩረት ያን ያህል አይደለም። የሚገነቡ ሕንፃዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ መንገዶችና ትምህርት ቤቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት አካል ጉዳተኞች በተለይ በትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ከሌላው ህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ እየሆኑ አይደለም።

አካል ጉዳተኞች የትምህርት እድል ቢያገኙም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለእነርሱ አመቺ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል ሲቸገሩ ይስተዋላል። እንዲያም ሆኖ ግን በመንግሥት፣ በአንዳንድ ረጂ ድርጅቶችና መልካም ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የአካል ጉዳተኞች ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ በቢሾፍቱ ከተማ ድጋፍና እንክብካቤ በአካል ጉዳተኞች ማህበር አማካኝነት ተመርቆ የተከፈተውና የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤትና በክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት ተገንብቶ ባሳለፍነው እሁድ የተመረቀው የሼይካ ፋጢማ ቢንት ሙባረክ የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ለዚህ አስረጂ ነው። በሀገሪቱ ከሚገኘው ከፍተኛ የዓይነ ስውራን ቁጥር አንፃር ግን ይህ በቂ ነው ማለት አይደለም። በተለይ የሕፃናት ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ከማስፋፋት አንፃር ገና ሥራ አልተሠራም ማለት ይቻላል።

ቪዥን ማየት የተሳናቸው ሕፃናት ወላጆች በጎ አድራጎት የተሰኘው ድርጅት ግን የአይነ ስውራን ሙአለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ከፍቶ ቢያንስ ጅምሩን አሳይቷል። ወይዘሮ ፈለቀች ወልዴ የድርጅቱ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው። ድርጅቱን ሊመሰረቱ የቻሉት እርሳቸውም ልጃቸው ማየት የተሳነው በመሆኑና ትምህርት ቤት ለማስገባት በመቸገራቸው ነው። እርሳቸው እንደሚሉት የዓይነ ስውራን ሙአለ ሕፃናት ትምህርት ቤቱ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በሰባት ወላጆች ነው የተከፈተው። በወቅቱ ወላጆቹ ትምህርት ቤቱን ሲመሰርቱ ሰባቱም ወላጆች ዓይነ ስውራን ሕፃናት ልጆች ነበሯቸው። ትምህርት ቤቱን ለመመስረት ያበቃቸው ዓላማም ይህ ነው።

እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ዓይነ ስውራን መሆናቸውን ቃወቁበት ጊዜ አንስቶ ልጆቻቸውን ለማስተማር እረፍት የላቸውም ነበር። ልጆቻቸው ትምህርት እንዲማሩ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በመጨረሻ አንድ ላይ ሆነው በመምከር አንድ ትምህርት ቤት ለልጆቻቸው መክፈት እንዳለባቸው ከስምምነት ላይ ደረሱ። ከሁለት ዓመት በፊት በመሰረቱት የሙአለ ሕፃናት ትምህርት ቤት አማካኝነት እድሜያቸው ከአራት ዓመት ጀምሮ ያሉ ዓይነስውራን ሕፃናትን በመቀበል እስከ ሰባት ዓመት እድሜአቸው ድረስ ተምረው እንዲወጡ የማድረግ ሥራ እየሠሩ ነው።

እነዚህ ሰባት እናቶች ትምህርት ቤቱን ሲያስጀመሩ የነበራቸው ሃሳብ ብቻ እንጂ እውቀቱም ሆነ ገንዘቡ አልነበራቸውም። በአንዳንድ ቅን ግለሰቦች ድጋፍና በራሳቸው መዋጮ ነበር ሥራውን እያከናወኑ የነበረው፤ አሁንም ያለው።

እንደ ቦርድ ሰብሳቢዋ ገለፃ፤ ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ 30 ተማሪዎችን ተቀብሎ ከክፍያ ነፃ የትምህርት አገልግሎት ይሰጣል። የተማሪዎቹ ወላጆችም በዚህ አገልግሎት በጣም ደስተኛ ናቸው። ሕፃናቱም ትምህርት የመቀበል አቅማቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። በትምህርት ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታም የብሬል አፃፃፍ ትምህርትና ሌሎች ለዓይነስውራን አስፈላጊ የሆኑ ተጓዳኝ ክህሎት ማሳደጊያ ትምህርት ይከታተላሉ።

ተማሪዎቹን የሚያስተምሩ ስምንት የልዩ ፍላጎት መምህራን ተቀጥረው እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ሁለቱ በሞግዚትነት አራቱ ደግሞ በመምህርነት ያገለግላሉ። ትምህርት ቤቱ ስራውን እንደ ሙአለ ሕፃናት አድርጎ የጀመረና መሠረታዊ የዓይነ ስውራን የብሬል አፃፃፍና ተያያዥነት ያላቸው ትምህርቶችን እየሰጠ የሚገኝ ቢሆንም በቅርቡ ግን ቅድመ መደበኛ ትምህርትን ለማስጀመር የሚያስችለውን ፍቃድ እየጠየቀ ነው።

ድርጅቱ ቋሚ የገቢ ምንጭ የሌለውና አሁንም ድረስ በጥቂት ደጋግ ኢትዮጵያውያን የሚደገፍ እንደመሆኑ ከመንግሥት፣ ከግል ተቋማትም ሆነ ከሌሎች ግለሰቦችና ባለሀብቶች ተጨማሪ ድጋፍ በማሰባሰብ በ2030 ከሙአለ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋት ራእዩን እውን ማድረግ ይፈልጋል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You