መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል ከአንድ ዓመት በፊት፣ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም፣ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እንደተመዘገቡበት ተገልጿል። የአምራች ዘርፉ ዋና ተዋናይ የሆነው የግሉ ዘርፍ በንቅናቄው ቀዳሚ ተጠቃሚ ሆኗል።
በንቅናቄው የመጀመሪያ ዓመት ሀገር አቀፍ ጉዞ ከ352 በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል። 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ምርት ማምረት ጀምረዋል። አዳዲስ አምራቾችም በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸው የንቅናቄው ውጤት ነው። በንቅናቄው የመጀመሪያ ዓመት አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል። በንቅናቄው በተከናወኑ ሥራዎች፣ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 55 በመቶ ማድረስ ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል።
ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል። በሀገሪቱ በአምራች ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ ተቋማት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ እቅዶች ላይ ተመሥርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን፣ ንቅናቄው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው ይገኛል። አምራቾች ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱም ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በንቅናቄው በኢንዱስትሪ ደረጃ ከተለዩ 2167 ችግሮች (የግብዓት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመሥሪያና የማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት … ችግሮች) መካከል፣ 1034 የሚሆኑት መፍትሔ እንዲያገኙ ተደርጓል፤ በቀሪዎቹ 1133 ላይ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፤ ችግሮቻቸው ከተፈቱላቸው አምራቾች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ አምራቾች ናቸው።
ክልሎች በኢንቨስትመንት አቅሞቻቸውና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ላይ ተመስርተው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄን ተግብረዋል፤ ንቅናቄው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያጋጠሙ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዳስቻላቸውና በንቅናቄው ትግበራም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ መሆናቸውንም ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል።
ንቅናቄው አምራቾች ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል።
የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ሁለተኛው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ከግንቦት አንድ እስከ አምስት 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። በኤክስፖው 130 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ 80 መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች (በድምሩ 210 ኢንዱስትሪዎች) ተሳታፊዎች ሆነዋል። ከ100ሺ በላይ ጎብኚዎች ኤክስፖውን ጎብኝተዋል። 157 ዲፕሎማቶች እንዲሁም ከ57 ሀገራት የመጡ ድርጅቶች ተሳትፈዋል። ከ830 በላይ ሰዎች የተሳተፉባቸው የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል፤ በዚህም አምራቾች ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝተው እንዲመካከሩ ተደርጓል። 5188 ግብይቶችና የግብይት ትስስሮች ተከናውነዋል። 74 አብሮ የመሥራት ስምምነቶች ተደርገዋል። የሀገር ውስጥ አምራቾች ከሰባት ሀገራት ከመጡ ድርጅቶች የግዢ ትዕዛዞችን ተቀብለዋል። በኤክስፖው ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈፅሟል።
የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅምና ዘርፉ የደረሰበት ደረጃ በተዋወቀበት በዚህ መድረክ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምርቶችን ለማስተዋወቅና ዘላቂነት ያላቸውን ትስስሮችን ለመፍጠር እንዲሁም ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለውን መተማመን ለማሳደግና አማራጭ ገበያ ለመፍጠር ጥረቶች ተደርገዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያግዙ አማራጭ ሃሳቦችን የማሰባሰብና ግንዛቤ የመፍጠር ዓላማ ያላቸው የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል።
በኤክስፖው ላይ የተሳተፉ አምራች ድርጅቶች በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ እቅዶች ላይ ተመስርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን፣ ንቅናቄው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው እንደሚገኝና በትግበራውም አበረታች ውጤቶችን እያገኙ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚረዱ ማሽኖችን የሚያመርተው የ‹‹ኢሜክ ኢንጂነሪንግና አግሮ-ኢንዱስትሪ ትሬዲንግ›› የቢዝነስና ማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ለገሰ፣ ኤክስፖው ለአምራቾች የገበያ ትስስር እንደሚፈጥር ይገልፃሉ። እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ፣ ድርጅቱ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ ላይ ሲሳተፍ የዘንድሮው ሁለተኛው ነው። በመጀመሪያው ኤክስፖ ላይ መሳተፉ የድርጅቱን ምርቶች ለማስተዋወቅና ገበያ ለማግኘት እድል ፈጥሮለታል። የዘንድሮው ኤክስፖም ለድርጅቱ እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
‹‹ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ዘመናዊና አስተማማኝ የሆኑ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን በመተካት የውጭ ምንዛሬ የማዳን ሚናም ያላቸው ማሽኖችን የሚያመርት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ የማያውቁ ብዙ አካላት አሉ። ኤክስፖው ምርቶቻችንን ለእነዚህ አካላት ለማስተዋወቅ አስችሎናል። ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር እንድንፈጥር አግዞናል፤ ግብዓቶችን እንዴት ማግኘት እንደምንችል አቅጣጫ ጠቁሞናል። በኤክስፖው ላይ ከተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በተሰማራንባቸው ዘርፎች ስላሉ ችግሮች ለመወያየትና የሚያስፈልጉንን ድጋፎች ለመጠየቅ እድል ፈጥሮልናል›› በማለት ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የዘንድሮው ኤክስፖ ባለፈው ዓመት ከተካሄደው ኤክስፖ በብዙ ነገሮች የተሻለ ነው። የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶታል፤ በርካታ ድርጅቶችን አሳትፏል፤ የጎብኚዎችም ቁጥር ካለፈው ኤክስፖ የበለጠ ነው። በቀጣይ ጊዜያት ኤክስፖው አሁን ካለው የበለጠ ሰፋ ባለ ቦታ ላይ ቢዘጋጅና እንደ እኛ ትልልቅ ማሽኖችን የሚያመርቱ ድርጅቶች ማሽኖቻቸውን ለማሳየት የሚያስችላቸው ቦታ ቢዘጋጅላቸው የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ›› በማለት ኤክስፖው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት›› አቶ ቴዎድሮስ ይገልፃሉ።
የ‹‹ቤቴል ኢንጂነሪንግ›› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ አቶ መኮንን በጋሻው፣ ድርጅቱ በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ ላይ ሲሳተፍ የዘንድሮው የመጀመሪያው እንደሆነ ጠቁመው፣ በኤክስፖው ላይ መሳተፉ ድርጅቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተሻለ እንዲታወቅ እንደሚረዳውና ሰፊ የገበያ ትስስር እድል እንደሚፈጥርለት ይናገራሉ። ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ በቀጣይም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ መሳተፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ የሚናገሩት ሌላው የአምራች ዘርፍ ተዋናይ በ‹‹ቴዎድሮስ ፍቅሩ ፕላስቲክ ሪሳይክሊንግ›› ፋብሪካ የማርኬቲንግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍፁም ዘውዴ ናቸው። እሳቸው እንደሚገልፁት፣ ድርጅቱ በመጀመሪያው ኤክስፖ ላይ መሳተፉ ተጨማሪ የገበያ እድሎችን እንዲያገኝ አስችሎታል። ‹‹ድርጅታችን በየአካባቢው በተለምዶ ቆሻሻ ተብለው የሚጣሉ የፕላስቲክ እቃዎችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የመገልገያ ቁሳቁሶችን (ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ እቃ ማስቀመጫ…) ያመርታል። ባለፈው ዓመት የተካሄደው ኤክስፖ ላይ መሳተፋችን የገበያ እድሎችን አስፍቶልናል፤ ብዙ ግለሰቦችና ተቋማት ኤክስፖው ላይ አይተውን ፋብሪካችንን መጎብኘት እንደሚፈልጉ ነግረውን ነበር፤ ከብዙ ሰዎች ትዕዛዞችን ተቀብለን ሰርተናል›› በማለት በኤክስፖው መሳተፍ ስለሚኖረው ፋይዳ ያስረዳሉ።
የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ተዋንያን በሆኑ በበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚተገበር ቢሆንም ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ንቅናቄው የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት ረገድ ያስገኛቸው ውጤቶች በአምራች ዘርፉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ እገዛ የሚያደርጉ እንደሆኑ ያስረዳሉ። ‹‹ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሯል፤ ባለሀብቶችን የመደገፍ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ ተግባራት ተከናውነዋል። ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ የመሬትና የሼድ አቅርቦቶች እንዲሻሻሉ ተደርጓል። እነዚህ ተግባራት የግሉ ዘርፍ ችግሮች እንዲቃለሉ እገዛ አድርገዋል›› ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ለአምራች ዘርፉ እድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩና ውጤትም ያስገኙ ርምጃዎችን የሚያብራሩት አቶ መላኩ፣ ርምጃዎቹ የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲኖረው የሚያስችሉ እንደሆኑ ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚያስረዱት፣ አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተዘጋጅተውና ጸድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጋቸው፤ የመንግሥት ተቋማት የሚያስፈልጓቸውን እቃዎች ከሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲገዙ አቅጣጫ መቀመጡ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ መወሰኑ፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆ ዘላቂና ተቋማዊ በሆነ መልኩ በቅንጅት ለመፍታት የኢንዱስትሪ አስተባባሪ እንዲሁም የቢዝነስ ከባቢ ሪፎርም ኮሚቴ (Business Climate Reform Steering Committee) መቋቋማቸው የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት የማሳደግ ዓላማ ያላቸው ርምጃዎች ናቸው።
‹‹እነዚህ ርምጃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 395 ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በትግራይ ክልል 217 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ አስችሏል። የአምራች ኢንዱስትሪ የማምረት አቅም አጠቃቀም በ2013 በጀት ዓመት ከነበረበት 47 በመቶ በ2016 በጀት ዓመት አጋማሽ ወደ 56 በመቶ አድጓል። የኢንዱስትሪ ምርት በ2013 ከነበረበት 36 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ በዚህ ዓመት አጋማሽ ወደ 39 በመቶ እንዲሁም ዘርፉ በየዓመቱ ይፈጥረው የነበረውን 172ሺ ቋሚ ሥራ እድል ወደ 256ሺ ማሳደግ ተችሏል›› ብለዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም