ሱዳን ከጀነራል አልበሽር ሥልጣን መልቀቅ ማግስት የሲቪል መንግሥት ይመሰረታል የሚል ተስፋ ሰንቃ በደስታና ሆታ በጭፈራም ተውጣ ነበር። ውሎ ሳያድር ተቃዋሚውና ሕዝቡ የጠበቀው ተስፋ በጨለማ ግርዶሽ ተዋጠ። የተለያዩ ተቃዋሚዎች ከወታደራዊው የሽግግር መንግሥት ጋር ድርድር ቢያደርጉም ያሰቡትን ማሳካት አልተቻላቸውም። ዳግም ሕዝቡን በማስተባበር በአመጽና በተቃውሞው ገፉበት።
የሽግግሩ ወታደራዊ መንግሥት ካርቱም ላይ ተቃውሞአቸውን ለማሰማት አደባባይ በወጡ ሲቪሎች ላይ እርምጃ በመውሰዱ ከ100 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱ እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ መስጠቱን እንዳመነ አልጀዚራ ቢዘግብም ብሉምበርግ የዜና ወኪል በበኩሉ የሱዳን ወታደራዊ ምክርቤት ምክትል መሪና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አዛዥ መሀመድ ሀምዳን በሲቪሎች ላይ ጥቃቱን ያደረሰው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሳይሆን ዩኒፎርሙን ያገኙ ሌሎች ኃይሎች ናቸው ሲሉ ማስተባበላቸውን ዘግቦአል።
ዛሬ ሱዳን በማያባራ ትርምስ እየተናጠች ትገኛለች። የመላው ዓለም ትኩረት ሱዳን ላይ አርፎአል። የአፍሪካ ሕብረት በበኩሉ ሱዳንን ከሕብረቱ አባልነት ማገዱን ብሉምበርግ የዜና ወኪል ዘግቦአል። የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ካርቱም ላይ ለተቃውሞ አመጽ በወጡ ሲቪል ሱዳናውያን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ግድያ በማውገዝ፤ ከተቃዋሚዎች ጋር የነበረውም ድርድር በመቆሙ፤ ሱዳን በሲቪል የሚመራ መንግሥት እስካልመሰረተች ድረስ ከአፍሪካ ሕብረት አባልነት መታገዷን አስታውቋል።
የሱዳን አብዮታውያን ከኢንተርኔት መስመር ውጭ ቢሆኑም በዝምታ አልተዋጡም ሲል ቢቢሲ ዘግቦአል። ከአፍሪካ ጋዜጠኞች በደረሱን እጅግ በጣም በርካታ ደብዳቤዎች መሰረት ምላሽ ለመስጠት ዘይነብ መሀመድ ሳሊህ ለሱዳን አብዮታውያን ከኢንተርኔት ውጭ ሕይወት ምን እንደሚመስል ትገልፃለች። ሱዳናውያን የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚው ላይ ከወሰዱት ዘግናኝ እርምጃ ወዲህ አሁንም ብርክና ድንጋጤ ላይ ናቸው። አልተረጋጉም።
ዶክተሮች እንደሚገልፁት ከሞቱት ከ100 በላይ ሰዎች ውስጥ 40ዎቹ በናይል ወንዝ ተጥለው ተገኝተዋል። ልዩ ኃይሉ በሲቪሎች ላይ ጭፍጨፋውን ሲያካሂድ ኢንተርኔት በሽግግሩ ወታደራዊ መንግሥት ተዘግቶአል። ጉዳዩ ከብሔራዊ የደሕንነት ጉዳዮች ጋር የተየያዘ መሆኑን ገልፆአል። ቀደም ሲል ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርን ለማውረድ ሰፊ የተቃውሞና የአመጽ እንቅስቃሴ ሲደረግ እያንዳንዱ የካርቱም ነዋሪ የሞባይል ስልኩን እንደያዘ ነበር።
ሰላማዊ ሰልፉን ያስተባበረው ዋነኛው አካል የሱዳን ሙያተኞች ማሕበር ጥሪውን ያስተላለፈው ከ800.000 በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስ ቡክ ገፁ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ወደ ሲቪል መንግሥት ሽግግር ይደረግ የሚለውን መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ግፊት የሚያደርጉት የትዊተርና ፌስ ቡክ ገፆቻቸውን በመጠቀም ነው።
ብሉምበርግ የዜና ወኪል የሕብረቱ የሰላምና የደሕንነት ምክርቤት በሰጠው መግለጫ የሲቪል መንግሥት መመስረት ሱዳን አሁን ካለችበት ቀውስ ለመውጣት ክፍት የሆነው ብቸኛ መንገድ ነው ማለቱን በዘገባው ገልፆአል። በሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ላይ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጫናና ተቃውሞ በርትቷል። በካርቱም ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ አብሮ ተሰልፎ የነበረው የዶክተሮች ቡድን 108 ሰዎች እንደተገደሉ ሲገልጽ የሱዳን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የሞቱት 61 ሰዎች ናቸው ማለቱን ብሉምበርግ በዘገባው አስፍሮአል።
የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች በቅርቡ እንደገለፁት በካርቱም ሲደረግ የነበረው የመቀመጥ አድማ የካርኒቫል መልክ ያለው በመሆኑ ለሕዝብ ሰላምና ፀጥታ አደጋ ነው ሲሉ መግለፃቸውን የብሉምበርግ ዘገባ ያስረዳል። በሱዳን ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ለማፈላለግ የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ቀጥሎአል።
ኦሜር አልዲጊያር የተቃዋሚው ጥምረት የሆነው ኮንግረስ ፓርቲ የቀድሞ አመራር ለድርድር በሚደረገው ጥረት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ጋር ካርቱም ላይ እንዲገናኙ ተጋብዘው እንደነበር ለብሉምበርግ ገልፆአል። የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚካኤል ቦጋዶናቭ ሞስኮ በሱዳን ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከሱዳን ወታደራዊ መሪዎችና ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት ፈጥራ እየሠራች ነው ሲሉ መግለፃቸውን ብሉምበርግ ዘግቦአል።
የሱዳን ተቃዋሚዎች ሕብረት በበኩሉ ለተቃውሞ በወጡት ሲቪሎች ላይ ለተፈፀመው ግድያ ወታደራዊ ምክርቤቱ ኃላፊነቱን ይወስዳል ብሎአል። ማክሰኞ ዕለት በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ሩሲያና ቻይና፤ በጀርመንና በእንግሊዝ የወጣውን የሲቪሎችን መገደል የሚቃወምና ለቀውሱ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግ በሚል የሰጡትን መግለጫ ማገዳቸውን አንድ ዲፕሎማት ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጊዜያዊነት አንዳንድ ሠራተኞቹን ከሱዳን ወደሌላ ቦታ ማዛወሩን የዋናው ጸሐፊ ቃል አባይ የሆኑት ስቲፋኔ ዱጃሪክ መግለፃቸውን ብሉምበርግ በዘገባው አስፍሯል። የሱዳን ሠራዊት የሱዳናውያንን ሕይወት እጠብቃለሁ፤ ሕዝቡ ግን ከወታደራዊ ተቋማት መራቅ አለበት በሚል ያወጣውን መግለጫ የሱዳን ኦፊሴላዊ የዜና ኤጀንሲ የሆነው ሱና መዘገቡን ብሉምበርግ ገልፆአል።
ሱዳን መጪውን ጊዜ ለመተንበይ በሚያስቸግር መልኩ ባልታወቀ ጎዳና ላይ ትገኛለች። የዓለም ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ የትኩረት አጀንዳ ዛሬም ሱዳን ነች። ለ30 ዓመታት የዘለቀውን የአልበሽር መንግሥት በሕዝብ አመጽና በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በማስወገድ የተቆጣጠሩት የሱዳን ጀነራሎች ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ቢመሰርቱም ለሲቪል መንግሥት ምስረታ የገቡትን ቃል መጠበቅ አልቻሉም።
በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የነበሩት ተቃዋሚዎች በስተኋላ መደራደሩን አቁመው አጠቃላይ የሲቪል አመጽና የሥራ ማቆም አድማ እስከ መጥራት ተሻግረዋል።
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዛሬም ባልተቋጨውና ወዴት እንደሚሄድ በማይ ታወቀው፤ በአመጽና በተቃውሞ በሚናጠው የሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዕለታዊ ዜናዎችና ትንተናዎችን በስፋት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ቢቢሲ፤ አልጀዚራ፤ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ፤ ኤንቢሲ ኒውስ፤ ሱዳን ትሪቡን፤ ፍራንስ 24፤ ሲኤን ኤን፤ ዶቼቬሌ፤ ዴይሊ ኤክስፕሬስ፤ ዘ ኢንዲፔንደንት፤ ዘ ጋርድያን በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው።
የመላው ዓለም ትኩረት ሱዳን ሆናለች። ተቃዋሚዎች በደቡብ ሱዳን አመጽ ዘመን ከፍተኛ እልቂት ያስከተሉት የጃንጃዊድ ሚሊሺያ ኃይሎችና ልዩ ኃይሉ ከ100 በላይ ሲቪሎችን (ሰላማዊ ሰዎችን) በመግደላቸው ካርቱምን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል። ወታደራዊው የሽግግር መንግሥት ለተቃዋሚውና ለውጭ አደራዳሪዎች የሲቪል መንግሥት ለመመስረት ይቻል ዘንድ ምርጫ እንዲደረግ ቃል የገባ ቢሆንም የሱዳን ውስብስብ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ሥልጣኑን ለመልቀቅ ፍላጎት እንደሌለው በተለያየ መልኩ እያሳየ ነው።
በካርቱም ከሕዝባዊ አመፁ መቀጣጠል በኋላ በርካታ መስመራዊና ከፍተኛ የሠራዊቱ መኮንኖች ለእስር ተዳርገዋል። የተለያዩ መንግሥታት በሱዳን ያለው ውጥረት እንዲረግብ ወታደራዊው የሽግግር መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር ተደራድሮ የሲቪል መንግሥት እንዲመሰረት ሰፊ የማግባባት ሥራዎችን ቢሰሩም የተጨበጠ ውጤት አልተገኘም። የአፍሪካ ሕብረትም አገሪቱን ከአባልነት ያገደው በዚህ ምክንያት ነው።
የቢቢሲ ዘገባ በተቃውሞው የተገደሉት ሰዎች በካርቱም የአባይ ወንዝ ውስጥ ወድቀው መገኘታቸውን ያስረዳል። የጃንጃዊድ ሚሊሺያ በተለይም በደቡብ ሱዳን ውስጥ በጨፍጫፊነቱ የታወቀ ሲሆን ሰሞኑን ፀጥታ በማስከበር ስም በካርቱም ከተማ ሴቶችን ሲደፍሩ መታየታቸውን ቢቢሲ ዘግቦአል። የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስና ምስቅልቅል ጣሪያ በነካበት በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ መሪው ሌተና ጀነራል አብዱልፈታህ አብዱላሂ አልቡርሀን በተለያዩ ጎረቤት አገሮች ጉብኝት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
በሌላም በኩል የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የአፍሪካ ጉዳዮች ሴክረተሪ ቲቦር ናጊ በወቅታዊው የሱዳን ሁኔታ ላይ ከወታደራዊው መሪዎች ጋር በመገናኘት ለሁለት ቀናት መክረው ተመልሰዋል። ሰሞኑን በቀደመው ዘመን በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉት ነባሩና አንጋፋው ዲፕሎማት ዶናልድ ቡዝ ዳግም በቦታው ተሹመዋል።
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ሞርጋን ኦርታገስ የሱዳን ኃይሎች በሲቪሎች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ማቆም፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይላቸውን ከካርቱም ማስወጣት አለባቸው ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል። ዛሬም ሱዳን ውሉ ባልታወቀ ጎዳና በትርምስና ሁከት፤ በአመጽና በከረረ ተቃውሞ ታጅባ ጉዞዋን ቀጥላለች። ሁለት ምርጫ አላት። አንድም የለየለት ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት ይፈጠራል ወይንም በሰላማዊ ምርጫ የሲቪል መንግሥት ይመሰረታል።
በአጠቃላይ የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤት ሱዳን አሁን ካለችበት አጣብቂኝ ማውጣት ትልቅ አደራው ብቻ ሳይሆን አህጉራዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል። በመሆኑም ወታደራዊው ምክር ቤት ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡ ዜጎችን ከመጨፍጨፍ ተቆጥቦ አገሪቱ በሲቪል መንግሥት እንድትመራ ያደርጋት ይሆን የሚለው ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ወንድወሰን መኮንን