ጋዜጠኞች የሙያ አጋሮቼ እንደሚሉት አካባቢን ቀይረው ወደ ሥራ ሲመለሱ ጥሩ ሙድ ወይም መነቃቃት ይፈጠራል፡፡ ወጣ ሲሉ ወጣ ያለ ነገር ይገኛል፡፡ ተስማሚ የሆነ ወይም የሚጎዳ የአየር ፀባይ ያጋጥመዎታል፡፡ አይንዎም እንዲሁ ጥሩም መጥፎም ያያል፡፡ ጆሮም ደግና ክፉውን ይሰማል፡፡ ከሰዎች ባህሪ ጀምሮ ወጣ ብለው አብረው ውለው ሲያድሩ ብዙ ያያሉ። ይታዘባሉ፡፡ በሚታዘቧቸው ነገሮችም ወይ ይዝናናሉ፡፡ ወይም ያዝናሉ፡፡
ወደ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አምቦ መስመር ነበር ጉዞዬ፡፡ ወደ ጊንጪ መንገድ ይታጠፋል፡፡ ከሙያ አጋሮቼና ከሌሎች ጋር ረፋድ አራት ሰዓት ላይ በዕለተ አርብ ነበር ከአዲስ አበባ ከተማ የወጣነው፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ነበር ወደ ስፍራው ይዞን የሄደው፡፡
በጉዞ ወቅት ምቾት ከሚነሳው አንዱ የጉዞ ቅድመ ሁኔታ አለመመቻቸት እና የመናበብ ችግር ነው፡፡ የጉዞ አስተባባሪዎች በአንድ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ የሆነ ቋንቋ የላቸውም፡፡ እናቶች እንደሚሉት ‹አረረም መረረም ማህበሬን ተወጣሁት› አይነት ሩጫ ነው የሚታይባቸው። አክብረው የወሰዱትን ባለሙያ አክብረው መመለስ ላይም እንዲሁ ችግር አለባቸው። በዚህ የአንድ ቀን አዳር ጉዞዬ ያነሰኋቸውን ነጥቦች ነበር በባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ላይ ያስተዋልኩት፡፡
ከተማውን ለቀን ወደገጠሩ ስንገባ ምድሪቷ የተቀበለችን በልምላሜ፣ በቀዝቃዛ አየርና ዝናብ ነበር፡፡ በአካባቢው ክረምቱ ከገባ የከረመ እንጂ ገና የጀመረ አይመስልም፡፡ ወደ ሥፍራው ያመራነው ሰኔ ግም ሊል አንድ ቀን ሲቀረው ስለነበር ቅዝቃዜ ይኖራል ብዬ አልገመትኩም። በተለይ ‹ጭልሞ› ተብሎ የሚጠራው ደን ‹ውበቴ ቅዝቃዜና ዝናብ ነው› ያለ ይመስላል። ጥቅጥቅ ያለ የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ ደኑን አልፈን ስንሄድ ዝናብ አልነበረም፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ስንመለስ ‹ዶፍ› አይነት ዝናብ ነበር የጣለው፡፡ የነበረንን የመንገድ ሥራ ጉብኝት ፕሮግራምም አስተጓጎልብን፡፡
ተፈጥሮን እያደነኩ ወደማሳዎቹ ሳማትር ደግሞ ለየት ያለ ነገር አስተዋልኩ፡፡ ወይንጠጅና ነጭ ቀለም ያለው አበባ በማሳው ላይ ልዩ ውበት ተጎናጽፎ ትኩረቴን ሳበው፡፡ የአበባ እርሻ ልማት ነው እንዳልል ‹ግሪን ሀውስ› በሚባለው ውስጥ አይደለም፡፡ ጥቂት ከተመራመርኩ በኋላ ምን እንደሆነ ስጠይቅ የድንች ተክል እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ እንዲህ ያለ አበባ እንዳለው አለማወቄ ለግብርና ሥራ ምን ያህል እሩቅ እንደሆንኩ ተረዳሁ፡፡
ውስጥ አዋቂ የሆነ ሰው ሲያጫውተኝ በዚህ ወቅት ድንች በአካባቢው በስፋት ይመረታል። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ይደርሳል፡፡ ነዋሪው የአካባቢውን ብርድ የሚቋቋመው በድንች ነው። በእንስራ ተቀቅሎ ሰብሰብ ብሎ መብላት የተለመደ ነው፡፡ በአካባቢው ‹ቡትሌ› ተብላ በምትጠራ ጠርሙስ አብሮ አረቄ ይቀርባል። ውስጥ አዋቂው አጣፍጦ ሲያወራኝ እኔም ብርድ ብርድ ያለኝን ለማጥፋት ተመኘሁ፡፡ ምና ዋጋ አለው ድንቹ ገና በአበባ ላይ ነው፡፡
እንዲህ እያወጋን ቅዝቃዜውን ለማምለጥ ብንሞክርም እየመሸ ሲሄድ ቅዝቃዜው ባሰበት። እህል ውሃ ልንል ከሽኩቴ እስከ ጩሉጤ 62 ነጥብ ሁለት ኪሎሜትር የሚሸፍነውንና ሦስት ወረዳዎችን የሚያገናኘውን አስቸጋሪውን መንገድ ለመሥራት በተረከበው ገምሹ በየነ ተቋራጭ ካፕ ጎራ አልን፡፡ ከመመገቢያው አቅራቢያ በሚገኝ ዋርካ ላይ በአሮጌ ቆርቆሮ የተሸፈነ በመካከሉ ደግሞ በነጭ ወረቀት ላይ በትልቅ ፊደል ጽሁፍ ተንጠልጥሏል፡፡
ትኩረቴን ስለሳበው ጠጋ ብዬ ሳነበው ‹እዚህ ውስጥ ኮንዶም ይገኛል› የሚል ነበር፡፡ ማስታወቂያው ከተለጠፈበት አቅራቢም በራሱ ብረት ካልሆነ በእጅ ቢመቱት ድምጽ የማይሰጥ ብረትም ተጠልጥሏል፡፡ ደውል ሳይሆን አይቀርም፡፡ ኃላፊነትን መወጣት እንዲህ ነው፡፡ ‹ዝምታው ይሰበር› ተብሎ ኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ላይ ርብርብ እንዳልተደረገ ዛሬ መልሶ ማሰራራቱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ እንደመንገድ ሥራ ባሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ለወራት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ሥራው ባለበት አካባቢ በመሆኑ ትኩረቱ አስፈላጊ ነውና ይበል የሚያስብል ተግባር ነው፡፡
በነገራችን ላይ ለኤች አይቪ ቫይረስ በጣም ተጋላጭ ከሆኑ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ወይም ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ እና መሰል አካባቢዎች የግንዛቤ ሥራው እንዳለ ሆኖ በልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚመጣውን የቫይረሱን ስርጭት በእንዲህ መልኩ መቀነስ ይቻላል የሚለውን ተሞክተሮ መውሰድ ብልህነት ነው፡፡
‹‹እዚህ ውስጥ ኮንዶም ይገኛል›› ብሎ የካምፑን ሠራተኞች መንገር ቢያንስ ባስፈለገ ጊዜ እንኳ ‹‹የለም›› ብሎ በመዘናጋት በቫየረሱ ከመጎዳት ይታደጓል፡፡ ለዚህም ነው በካምፑ የተተገበረው ሥራ ይበል የሚያስብል ምርጥ ተሞክሮ ነው ያልኩት፡፡
በዚህ ረገድ ከተሜው በየመዝናኛ ቤቱ ይህን በመሰለ ሁኔታ ሳይሆን በነፃ ጭምር በተለያዩ የሆቴል ኮርነሮችና ኮሪደሮች ቢቀመጥም ‹‹እምቢኝ›› ብሎ አይኑ እያየ ራሱን በቫይረሱ ሲያስለክፍ ማየት በዝቶ ነው ዛሬ መንግሥት ‹‹በቸልተኝነት የኤች አይቪ ቫይረስ ስርጭት ዳግም አገርሽቷል›› ሲል መግለጫም ሆነ ስለጠና ለመስጠት የተገደደው፡፡ እናስ ከእኛ ምን ይጠበቃል ብሎ ራስን መጠየቅ ግድ ነው። በመሆኑም የጎበዘ ራሱን ማቀብ፤ ካልተቻለ ደግሞ መጠቀም ግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በካምፑ ውስጥ የታዘብኩት ይህ መልካም ሥራ በአቅራቢያው በሳሉ የአርሶ አደሮች መንደር ውስጥ ድረስ መዝለቅ ችሎ ይሆን ስል መየቅ ወደድኩ፡፡ እውነት ነው ቢያንስ እዛው ግቢ ውስጥ ተቀጥረው ያሉ ወጣቶች ለመኖራቸው አልጠራጠርም፡፡ እናም አገልግሎቱ ለእነዚህም የአካባቢው ነዋሪዎችም በሚሆን ልክ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡
በአንድ ወቅት በዚህ ካምፕ ሳይሆን በሌላ ሥራ አጋጣሚ ወደ አንድ የገጠር አካባቢ ውስጥ ብዛት ያላቸው ሠራተኞች ያሉበት ካምፕ ውስጥ እንዲሁ ለሥራ እግር ጥሎኝ ነበር፡፡ በካምፑ የደረስነው ፕሮግራሙ ሊከናወን አንድ ቀን ሲቀረው ነበር፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ባለበት ወቅት ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ካምፑን መቃኘት ያዝን፡፡
በአጋጣሚ አንዳንድ በቆርቆሮ በተሠሩ ቤቶች ጥጋጥግ ትላልቅ ካርቶኖች አልፎ አልፎ ተሰቅለው አየን፡፡ በዚያም አካባቢ ስናልፍ፤ አንድ ነጭ ጋወን የለበሰ ሰው ብዛት ያላቸውን ኮንዶሞች ከፌስታል እያወጣ በካርቶኖቹ ውስጥ ያስገባል፡፡
እንደ ድንገት አንድ የጊቢው ሠራተኛ የሚሆነውን ነገር አይቶ ሲገሰግስ መጣና ‹‹ቢሮ ድረስ መጥተን ስንጠይቅ የለም ያልከው ኮንዶም ዛሬ ከየት መጣ›› ሲል አቧረቀበት፡፡ አንድ አንድ ሲሉም ለጠብ ተዳርገው ለማገላገል የደረስንበትን አጋጣሚ አልዘነጋውም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ልክ እንደዚህ ለታይታ ኃላፊ ይመጣል በሚል የሚሠራ ሥራም እንዳለ ማወቅም ይገባል፡፡
ይህን እና መሰል ተያያዥ ሁኔታዎችን እቆዘምኩ ምሽቱ መጣ፤ ድካም ቢጤ ስላለኝ በጊዜ መኝታ ብንፈልግም ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በፊት አልተሳካልንም፡፡ በጊዜ ወደ አዳር አለመሄዳችን ሲገርመን ንጋት 11 ሰዓት ላይ ለጉዞ ዝግጁ መሆን እንዳለብን ተነገረን። 60 ኪሎሜትር አባጣና ጎርባጣ መንገድ ስለሚጠብቀን ነበር ጉዞአችን በማለዳ የሆነው። ኪሎሜትሩን በእጥፍ ተጉዘን ነበር ከአቡና ግንደበረት ወረዳ የደረስነው፡፡
እኛ በአንድ ቀን እንዲህ ያለ ስሜት ከተሰማን የአካባቢው ነዋሪዎች ምን ሊሉ እንደሚችሉ መጠየቅ አይገባም፡፡ ከአቡና ግንደበረት እስከ ጊንጭ ድረስ ይሠራል ብለው ሲጠብቁና ሲጠይቁ ዓመታት ተቆጥሯል። ወረዳው በምዕራብ ሸዋ ዞን ከሚገኙ 22 ወረዳዎች አንዱ ሲሆን፣ በሰሜን አባይ፣ በምሥራቅ ሙርጋና ሙገር፣ በምዕራብ ጉደር፣ በደቡብ ደግሞ ቃሌና ቀላጤ በተባሉ ትላልቅ ወንዞች የተከበበ ነው፡፡
ነዋሪው በአንድ መንገድ ብቻ ነው የሚወጣውና የሚገባው፡፡ ‹በረት ውስጥ እንዳለ ከብት ነው ያለነው› ያሉንም ነበሩ። በመንገድ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ለከተማ ባዳ ሆነው ዘመናትን ማስቆጠራቸውን ነበር የሰማነው፡፡ ለአንድቀን እንዲህ ያማረረን መንገድ እነሆ መፍትሄ ሊያገኝ ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ተቆርጦለታል፡፡ ዕድሜ ለሰጠው 2014 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ መንገዱ አስፓልት ሆኖ አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ለማቅረብ እና ከከተማ ወዳጅ ዘመዱ ጋር እንደልቡ ለመጠያየቅ ይበቃል፡፡ እኔም ለመመረቅ እበቃ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011
ለምለም መንግሥቱ