በቢሾፍቱ የተገነባው የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት

በትምህርት፣ ጤና፣ ሥራና በልዩ ልዩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች እምብዛም ትኩረት ካላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ በዋናነት አካል ጉዳተኞች ይጠቀሳሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በተለይ ዓይነ ስውራን ዜጎች በነዚህ ዘርፎች የተሰጣቸው ትኩረት ከሌሎች የህብረተሰበ ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ዓይነ ስውራን መንግሥት ከሚያደርግላቸው መጠነኛ ድጋፍ ውጪ ለእነርሱ አመቺ የጤና ትምህርትና የሥራ ሁኔታ እንዲመቻች ድጋፍ የሚያደርጉት በአብዛኛው የሀገር ውስጥና የውጭ የረድዔት ድርጅቶች ናቸው፡፡

ከነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹ድጋፍና እንክብካቤ ለአካል ጉዳተኞች›› የተሰኘው ማህበር ይጠቀሳል፡፡ ማህበሩ በ2005 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የተመሠረተ ሲሆን አካል ጉዳተኞች ከተቀረው የህብረተሰብ ክፍል እኩል ትምህርት፣ ጤና፣ የሥራ ስምሪትና ሌሎች መስኮች ተጠቃሚዎች የሚሆኑበት አካታች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መደላድል ፈጥሮ የማየት ራዕይ በመሰነቅ ላለፉት አስራ አንድ ዓመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በነዚህ ዓመታትም በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

ማህበሩ ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በኋላ በቢሾፍቱ ከተማ ባቋቋመው የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምሀርት ቤት ውስጥ በቢሾፍቱ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎችና ከተለያዩ ክልሎች ለሚመጡ አይነ ስውራን ህፃናት የትምህርት አገልግሎት መርሃ ሀግብር ዘርግቶ ባለፉት አስር ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓይነ ስውራንና የእይታ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ህፃናትና ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ትምህርት ቤቱ በመሠረታዊነት ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸው ዓይነ ስውራን ህፃናት መደበኛ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ገብተው ትምህርታቸውን በተሳካ ሁኔታ መከታተልና ማጠናቀቅ እንዲችሉ የሚያዘጋጃቸውን የቅድመ መደበኛ ትምህርት መርሃ ግብር ያካሂዳል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የጤና፣ የገቢ ማስገኛ፣ የአቅም ግንባታና የአካል ጉዳተኞች መብት ውትወታ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ከሰሞኑ ደግሞ እያካሄደ የሚገኘውን የትምህርትና የተጓዳኝ አገልግሎቶችን ለማሳደግ የሚያግዘውን የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ህንፃ ከቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር በተረከበው 1 ሺ 800 ካሬ ሜትር ላይ አስገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፡፡

ድጋፍና እንክብካቤ ለአካል ጉዳተኞች ማህበር መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ አስፋው፣ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡት ገና የአራት ዓመት እድሜ እያሉ ነው፡፡ በርግጥ በንጉሡ ዘመን በለስ ቀንቷቸው ትምህርታቸውን የመማር እድል አግኝተዋል። ግን ደግሞ ትምህርታቸውን ተከታትለው ዛሬ ላይ ለመድረስ ነገሮች  ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም፤ በብዙ ተፈትነዋል፡፡ ያንን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው ዛሬ ግን ለብዙ ዓይነ ስውራን መማሪያ የሚሆን ትምህርት ቤት ከረድዔት ድርጅቶችና ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር በቢሾፍቱ ከተማ ለመከፍት በቅተዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚናገሩት፣ በቢሾፍቱ ከተማ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት የተገነባው በኔዘርላንድ ድርጅቶችና በኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ግንባታውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ የስምንት ወር ጊዜ ወስዷል፡፡ ለግንባታውም አስር ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኗል፡፡

ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች እዛው እየኖሩ የተሟላ የትምህርት አገልግሎት የሚያገኙበት ነው፡፡ በአንድ ጊዜም 30 ዓይነ ስውራንና የእይታ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ እድሜያቸው ከስድስት እስከ አስራ ሶስት የሚሆኑ 30 ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ ከቅድመ መደበኛ እስከ አራተኛ የክፍል ደረጃም ያስተምራል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ተማሪዎች በኪራይና በተበጣጠሰ መልኩ የሚያገኙትን የትምህርት እድል በማስቀረት በአንድ ቦታ ሆነው የተሟላ የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታ ከሚያገኙት መደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የብሬል ፅሁፍና ማንበብና ሌሎች የክህሎት መገንቢያ ትምህርቶችን ይማራሉ፡፡ በተጨማሪም ለመቀንሳቀስ የሚያስችላቸው የአካል ብቃት ትምህርት፣ የመግባባት /social skill/ እና የመዝናኛ ትምህርቶች ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህም ትምህርት ቤቱን ለመገንባት የረዱት የኔዘርላንድ ድርጅቶች ተጨማሪ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ እስከ አራተኛ ክፍል በዚህ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በሌሎች መደበኛ ትምህርት ቤቶ ውስጥ ገብተው ከተማሪዎች ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ ይደረጋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት ቀደም ሲል በነበረው ጊዜ አይነስውራን ትምህርት ለማግኘት በእጅጉ ይቸገሩ ነበር፡፡ በፈተና ውስጥ አልፈው ትምህርት እድል ያገኙትም ቢሆኑ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ለእነርሱ አመቺ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ምክንያት የሚፈልጉትን ያህል ትምህርት አያገኙም፡፡ ለዓይነስውራን ብቻ ታስበው የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ውስን ነበር፡፡

ይሁንና አሁን ላይ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች በየቦታው እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን የዓይነ ሥውራን የትምህርት እድል የማግኘት ችግር በመጠኑም ቢሆን እየቀረፈው መጥቷል፡፡ ማህበሩ በቢሾፍቱ ከተማ አስገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገው የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤትም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በቀታይም ትምህርት ቤቱ ዓይነ ስውራን በዘላቂነት የሚማሩበት ቦታ ነው፡፡

ከድሮው ጋር ሲነፃፀር በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡ ለዓይነ ስውራን ያለው አመለካከት እየተለወጠ መጥቷል፡፡ ለዚህም በርካታ ዓይነ ስውራን ተማሪዎች በራሳቸውም ጥረት ይሁን የሌሎች ድጋፍ ታክሎበት በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባትና በከፍተኛ የሥራ ዘርፎች ላይም ጭምር ተሰማርተው መታየት ነው፡፡ ይሁንና አሁንም የህብረተሰቡ አመለካከት በሚፈለገው ልክ አልተለወጠም፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ትምህርት ቤት በየቦታው ቢከፈትና ትኩረት ቢሰጥ አመለካከቱን መቀየር ይቻላል፡፡

በቀጣይ ምንም እንኳን እነዚህን ትምህርት ቤቶች ማስፋፋት የሚከብድ ቢሆንም ዓይነ ስውራን ህፃናት ከማንኛውም በደበኛው ትምህርት ትምህርታቸውን ከሚከታተሉት ህፃናት የማያንሱና በነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው የመማር አቅም ስላላቸው ህብረተሰቡም ይሁን ወላጅ ይህን በመረዳት ልጁ ወደመደበኛ ትምህርት ቤት እንዲሄድ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ወይም ወደ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች በመላክ ተገቢውን ሥልጠናና ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የዛኑ ያህል ደግሞ የህብረተሰቡ አመለካከት እንዲቀየር ሰፊ የግንዛቤ ስራ መስራት ይገባል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You