በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ 500 በላይ የሙስና ጥቆማዎች ቀርበዋል

አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ሙስናን የተመለከቱ ጥቆማዎች መቅረባቸውን የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የሙስና መረጃ አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፈርዳ ገመዳ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከፌዴራል ተቋማት እንዲሁም ከክልሎች ሙስና ነክ የሆኑ ጥቆማዎችን እየተቀበለ ይገኛል።

በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አንድ ሺህ 451 ሙስናን የተመለከቱ ጥቆማዎች መቅረባቸውን አቶ ፈርዳ ተናግረዋል።

ለክልል የሚደርሱ የሙስና ጉዳዮች ወደ ኮሚሽኑ ሳይደርሱ ከክልሉ የሕግ አካላት ጋር በመሆን እንዲመረመሩ ይደረጋል ያሉት አቶ ፈርዳ፤ ከፌዴራል ተቋማት በቀጥታ ለኮሚሽኑ ከደረሱት 80 የሙስናን ጥቆማዎች መካከል 65ቱን ጥቆማዎችና መረጃዎቹን ለፌዴራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት የማጣራት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ወደ ኮሚሽኑ መረጃ ክፍል ከሙስና ጥቆማዎች በተጨማሪ የተለያዩ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ቅሬታዎች እንደሚመጡ ጠቁመው፤ በዚህም ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 265 ቅሬታዎችን ተቀብሎ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው አካላት መምራቱን አስረድተዋል።

ወደ ኮሚሽኑ የሚመጡ ጥቆማዎች ሁሉም የተረጋገጡ የሙስና ወንጀሎች ናቸው ማለት እንደማይቻልና አንዳንዶች ያለምንም ማስረጃ የግል ፀብን በመያዝ የሚቀርቡም ይኖራሉ ብለዋል፡፡

አንዳንድ ጥቆማዎችን መሠረት አድርጎ ጉዳዮች ሲመረመሩ ምንም አይነት ማስረጃ የማይገኝበት ከሆነ በሥራችን ላይ ጊዜ ያባክናል በመሆኑም የተረጋገጠ መረጃን ይዞ ጥቆማ ማቅረብ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ችግሩም የሙስና መከላከል ርምጃን ወደ ፊት ለማራመድና ተጠያቂነትን ለማስፈን አስቸጋሪ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች የኮሚሽኑን የሥራ ኃላፊነት በአግባቡ ካለመገንዘብ የተነሳ ኮሚሽኑ የማይፈታቸውን የተለያዩ ቅሬታዎችን ይዘው የሚመጡበት ሁኔታ ሌላኛው የኮሚሽኑ ሥራ ላይ ችግር እየፈጠረ የሚገኝ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አቶ ፈርዳ እንዳመለከቱት፤ በሀገሪቱ የሙስና ፈጻሚዎች ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን በየጊዜው እየተሠሩ ያሉ ጥናቶች ስለሚጠቁሙ ህብረተሰቡ ከሙስና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመስጠት ያለው ተባባሪነት ሊጠናከር ይገባል።

ሙስና ሀገርን የሚጎዳ ጸያፍ ተግባር መሆኑን በመረዳት ሁሉም ዜጋ ለሕገወጥ ድርጊቱ ተባባሪ ባለመሆንና ሙስና ፈጻሚዎችን ለይቶ በማውጣት ተሳትፎውን ማሳደግ እንዳለበት አመላክተዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You