መቼም ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ በርከት ያሉ በረከቶች አይጠፉም። ሁሌም ሰኔ ግም ባለ ቁጥር ብዙ የሚባሉ በጎ ነገሮችን ስናይ ቆይተናል። ማየትም ብቻ ሳይሆን እኛው ራሳችን ተሳትፈን ሌሎችንም ጭምር በማስከተል የድርሻችንን ተውጥተንም ሊሆን ይችላል።
ወዳጆቼ! ይህን ጉዳይ ሳነሳላችሁ «ደግሞ ለበጎነት ምንስ ቢሆኑለት ምን አለበትና» ትሉ ይሆናል። እውነት ብላችኋል። ከበጎነት በላይ ምንም የለም። ሁሌም መልካምነትን የያዘ አዕምሮና ልቦና መልካም ፍሬን ለማፈስ የቀረበ ነውና ብዙ ቢባልለት የሚያንሰውና የሚያስገርም አይሆንም።
ወደቀደመው ነገሬ ልመለስ። ወደ ክረምቱ በረከት። አዎ! ክረምት ሲታሰብ ሁሌም በረከት አይታጣም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብዛኛውን የሀገሬ ሰው ከልቡ ተነሳስቶ በየቦታው፣ በየጉድባውና በየሸንተረሩ ችግኞችን መትከል ባህሉ እያደረገው ነው። ይህ ደግሞ አሁንም «እሰዬው» የሚያስብል ተሞክሮ ነው። አዎ! ዛሬም ይህን ለሚያደርጉ በጎ አሳቢዎች ሁሉ «በርቱልን ተበራቱልን» ማለትን አንተውም። አንዘነጋምም።
ባሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትራችን አሳሳቢነት መላውን ሀገር ለችግኝ ተከላ የሚያነሳሳ ዘመቻ ተካሂዷል። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ለመልካምነት የሚያበረታ ነውና «እሰይ! ይሁን» ከማለት የበለጠ መልካም የሚባል አርአያነቱን ያጎላዋል። ልክ እንዳለፉት ወራት የጽዳት ዘመቻ ሁሉ በመሪ የተመራው የችግኝ ተከላም ውጤታማ የሚባልና የተለየ ሙቀት የነበረው ሆኖ ሰንብቷል።
ወዳጆቼ! እስከዛሬም ቢሆን እኮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሀገር በቀል ችግኞችን በዘመቻ ተክለናል። በተለየ ወኔ ተነስተንም አላማውን አድንቀንና ብዙ ተባብለን ከስምምነት ደርሰናል። ይህ ስምምነት ደግሞ ችግኙ ሞቃታማው አየር ለውጥ፣ ለውሃ መገኛ፣ ለበርሃማነት መቀነሻና ለደን ሀብታችን መጠበቂያ ጭምር መሆኑን አመላክቶናል።
ተደጋግሞ ሲነገር እንደምንሰማውና እኛም ሁልጊዜ እንደምንመሰክረው ችግኝ የመትከልን አስፈላጊነት የምንዘነጋው አይደለም። እንዲያውም በአንዳንዶቻችን ተቋማት ዘንድ ይህን የችግኝ መትከያ ጊዜ የዓመቱ የመገናኛና የሠራተኞች ቀን አድርገን በተለየ ስሜት እናስበዋለን። በዚህ ቀን ችግኝ ከመትከል በዘለለ ቀናችንን ብሩህ በማድረግ የዓመቱን ልፋታችን በችግኝ መትከሉ ሰበብ አስውበነው እናልፋለን።
«በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ» እንዲሉ የችግኝ ተከላ ቀናት በሌሎች ቁምነገሮች ጭምር ተዋዝቶ ማለፉ እየተለመደ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ አንድም ለአረንጓዴው ቀናችን ሌላም ለዓመቱ ልፋታችን የተለየ ትዝታና ጠቀሜታን አስጨብጦ ያልፋል። ይህ ሁሉ መሆኑ አሁንም ቢሆን «እሰዬው» የሚያስብልና የሚያበረታን ነው።ይህን ቀን አስቦ ደስታን ቢያጭሩና ቁምነገርን ቢገበዩም መልካምነቱን ያጎላል። ዕለቱን በተለየ ትዝታ አስቦም ለከርሞው አረንጓዴነት ቅርስና አሻራን ትቶ ማለፍ ያስችላል።
ወዳጆቼ! ለእኔ ግን ይህ ብቻ መሆኑ በቂ ይሆናል አልልም። ችግኞችን መትከሉና አፈር አልብሶ መመለሱም ለተነሳንበት ዓላማ ግብ አይደለም፡፡ ጀምረነዋል ለምንለው የአረንጓዴማነት አካባቢ ማስፋት ማረጋገጫችን አይሆንም። በየዓመቱ ችግኞችን ለመትከል ቦታ መምረጡና አገር ቆርጦ መጓዙም በቂ የሚባል አይሆንም።
አሁን ደግሞ እጆቻችንን በእርጥብ አፈር ለውሰን ችግኝ ተክለን መጣን የምንልበት ብቻ አይደለም። እንደዋዛ ከመሬት አገናኝተን በርቀት የምንለያቸው ችግኞችም ታሪካችንና የድርሻችን አሻራ እንዳሳረፍን የምንመካበት ሆኖ ሊሰማንም አይገባም። እውነት ነው! ሁሌም ችግኞችን ከመትከል በዘለለ የተከልናቸው እጽዋት የት ደረሱ ልንል ይገባል።
አዎ! ርቀት ተጉዘንና በእግራችን ኳትነን የተከልናቸው የምንላቸውን አሻራዎች በዓመቱ ተመልሰን ስንመጣ ሕይወት ዘርተው፣ በቁመታቸው አድገውና በቅጠላቸው ለምልመው እንደምናገኛቸው እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን በየዓመቱ ተዘጋጅተው በሚጠብቁን ጉድጓዶች ላይ እንደዋዛ ተከል አድርገን የምንመለሰውን ችግኝ አጸደቅን ለማለት ይቸግረናል።
ሁሌም ቢሆን ችግኞቹ ማደግና መብቀላቸውን ካላወቅን ለእኛ በስፍራው ደርሶ አፈር መቆፈሩ ብቻ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ለስሙ አደረግነው ብሎ መናገሩም ታሪክና ቅርስ አይሆንም። እንዲህ ማድረግም ለማንም አይበጅም። ችግኞችን በየዓመቱ እየተከሉ የት መድረሳቸውን ያለማወቅ በእኔ ግምትና እሳቤ ወልዶ እንደመጣል ይቆጠራል። ልክ ተወልዶ በአባቱ እንደተካደ፣ አልያም ደግሞ ባልተገባ ግንዛቤና ጭካኔ ከመንገድ እንደተጣለ ጨቅላ ሕፃን ዓይነት። አበቃሁ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2011
መልካምስራ አፈወርቅ