የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሞርሲ ሰኞ ዕለት ካይሮ ከተማ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው ሳለ ራሳቸውን ስተው ከወደቁ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሞርሲ ከወደቁ በኋላ በሰውነታቸው ላይ ጉዳት እንዳልደረሰባቸውና ሆስፒታል ውስጥ እንደሞቱ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
መሐመድ ሞርሲ ወደ ወህኒ ከወረዱበት እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ ተገቢውን የጤና እንክብካቤና ክትትል እያገኙ እንዳልነበር ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሞርሲ የስኳር፣ የጉበትና የኩላሊት በሽታዎች ታማሚ ነበሩ፡፡ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ሰውየው በወህኒ ቤት ውስጥ ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸውና ሕክምና እንደማያገኙ ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ የመሞታቸው ዜና እንደተሰማም ደጋፊዎቻቸው የሞርሲ ሞት መንስኤ በተፈፀመባቸው ስቃይ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሦስት የብሪታኒያ ምክር ቤት አባላት ከተለያዩ አካላት ባሰባሰቡት መረጃ ሞርሲ ተገቢ ሕክምና አለማግኘታቸው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው ነበር፡፡ የፓርላማ አባላቱ በወቅቱ ታሳሪውን መሀመድ ሞርሲን ለመጎብኘት ለግብፅ መንግሥት ጥያቄ ቢያቀርቡም ፈቃድ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ስለሆነም የፓርላማ አባላቱ ማስጠንቀቂያዎች ከተለያዩ አካላት በተገኙ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡
ክርስፒን ብለንት የተባሉ የፓርላማ አባል «መሀመድ ሞርሲ እንዳያገኙ የተከለከሉት መሠረታዊ የጤና እንክብካቤዎች ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት መሆኑ አይቀርም፡፡ ፕሬዚዳንት አብደልፋታህ አልሲሲን ጨምሮ ሁሉም በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ አካላት ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል» በማለት በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሞርሲ በቀን ለ23 ሰዓታት ያህል ለብቻቸው እንደሚታሰሩ ገልፀው፤ ድርጊቱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች መመዘኛ መስፈርቶች አሰቃቂ ቅጣት ከሚባሉት ወገን እንደሚመደብ ጠቁመው ነበር፡፡
ሕልፈተ ሕይወታቸውን ተከትሎ «ኢንድፔንደንት ድቴንሽን ሪቪው ፓነል» (Independent Detention Review Panel) በተባለው የምርመራ ቡድን በኩል ባወጡት መግለጫም የሞርሲ ሞት የግብፅ መንግሥት በአገሪቱና በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት እስረኞችን መያዝ እንደማይችል ያሳያል ብለዋል፡፡ የግብፅ መንግሥት ስለሁኔታው ግልጽ ማብራሪያ መስጠት እንዳለበትና ስለሞርሲ አሟሟት ገለልተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ምርመራ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአልጀዚራው ዘጋቢ ጀማል ኤልሻያል እንደሚያስረዳው፣ የሞርሲ ችሎት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የሚተላለፍ አልነበረም፡፡ ከጠበቆቻቸው ጋር ለብቻቸው መነጋገር አይችሉም ነበር፡፡ ቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኟቸውም አይፈቀድላቸውም፤ ከዚህ በተጨማሪም ሰውየው የሚያስፈልጋቸውን የሕክምና አገልግሎት አያገኙም፡፡
መሐመድ ሞርሲ በግብፅ ታሪክ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሕዝብ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት እንደሆኑ ይነገር ላቸዋል፡፡ የአረብ አብዮት ለ30 ዓመታት ያህል ግብፅን የገዙትን ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክንና አስተዳደራቸውን ማስወገዱን ተከትሎ በግብጽ ምርጫ ሊካሄድ ችሏል፡፡ እ.አ.አ በ2012፣ ወደ ሥልጣን የመጡት ሞርሲ፣ በፈርኦኖቹ መንበር ላይ መቆየት የቻሉት ለአንድ ዓመት ያህል ብቻ ነው፡፡ እ.አ.አ በ2013 በግብፅ ዳግም በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመፅ ምክንያት በአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ከሥልጣናቸው ተነሱ፡፡ ወዲያውም በቁጥጥር ስር ዋሉና በርካታ የክስ መዝገቦች ተከፈቱባቸው፡፡ እ.አ.አ በ2012 ሕዝባዊ አመፅ ለተገደሉት ሰዎች የ20 ዓመታት እስራት ተፈረደባቸው፡፡ ከኳታር መንግሥት ጋር ምስጢራዊ የመረጃ ልውውጥ አድርገዋል ለተባሉበት ክስ ደግሞ ዕድሜ ይፍታህ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ ከእስር ቤት ለማምለጥ ሞክረዋል፣ ፍርድ ቤትን ተሳድበዋል እንዲሁም በሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈዋል የሚሉ ክሶችም ቀርበውባቸዋል፡፡
በስድስት ዓመታት የእስር ቤት ቆይታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተገናኙት ለሦስት ጊዜያት ያህል ብቻ ነው፡፡ ከእዚህም መካከል ባለፈው መስከረም ወር የፀጥታ ኃይሎች ባሉበት ሁሉም ቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኟቸው እንደተፈቀደላቸው ይጠቀሳል፡፡
የሞርሲን ሞት ተከትሎ የአገራት መሪዎችና ልዩ ልዩ ተቋማት የኀዘን መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከሟቹ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የነበራቸው የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን የኀዘን መግለጫ ለማሰማት የቀደማቸው መሪ የለም፡፡ ሟቹን ሰውዬ «ሰማዕት» በማለት የገለጿቸው ኤርዶጋን «ሞርሲ ታስሮ እንዲሰቃይና እንዲሞት ያደረጉት አካላት ከታሪክ ተወቃሽነትና ተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ አላህ የሰማዕቱን የወንድማችንን ነፍስ በሰላም ያሳርፋት» ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ በሚገኘው ፋቲህ መስጊድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞርሲ ጸሎት አድርገውላቸዋል፡፡
የኳታሩ ኢሚር ሸህ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታሃኒ «የዶክተር መሐመድ ሞርሲን ሕልፈት የሰማነው በከባድ ኀዘን ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለግብፅ ሕዝብ መፅናናትን እመኛለሁ» ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይም ለሞርሲ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡ የ«ሂዩማን ራይትስ ዎች» (Human Rights Watch) የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ ቀጣና ኃላፊ ሳራ ዊትሰን የሞርሲ ሞት አሰቃቂና አሳዛኝ እንደሆነና የግብጽ መንግሥት ለሞርሲ የሚያስፈልገውን የሕክምና ክትትል ባለማድረጉ ሕልፈታቸው የሚጠበቅ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
«ባለፉት ዓመታት ካሰባሰብናቸው መረጃዎች እንደታዘብነው ሞርሲ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ቆይተዋል፡፡ ሁልጊዜም ዳኞች ፊት በቀረቡ ቁጥር ሕክምና እንዲያገኙ ይጠይቁ ነበር፡፡ በቂ ምግብና ሕክምናም አያገኙም፡፡ ራሳቸውን እየሳቱ በተደጋጋሚ ወድቀዋል፤የታሰሩት ከሰዎች ተለይተው ብቻቸውን ነው፡፡ የግብፅ መንግሥት ይህን ሁሉ ያውቅ ነበር» በማለት ኃላፊዋ ለአልጀዚራ ገልጸዋል፡፡ የግብፅ ባለሥልጣናት ከደሙ ንጹህ ለመሆን ሲሉ ስለሰውየው አሟሟት አስፈላጊውን ምርመራ እንደማያደርጉም ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅታቸው «ሂዩማን ራይትስ ዎች»ም በሞርሲ ጤንነት ላይ ያተኮረ ሪፖርት አዘጋጅቶ እያጠናቀቀ እንደነበር በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡
ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የታገደውና የቀድሞው ፕሬዚዳንት የመሐመድ ሞርሲ የፖለቲካ ማኅበር የሆነው የሙስሊም ወንድማማችነት (Muslim Brotherhood) ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የመሐመድ ሞርሲን ሞት «ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግድያ» ሲሉ በጥብቅ ኮንነውታል፡፡ ፓርቲው ደጋፊዎቹና አባላቱ በመላው ዓለም በሚገኙ የግብፅ ኤምባሲዎች ዙሪያ በመገኘት ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ለሞርሲ ቅርበት የነበራቸውና በእርሳቸው የፕሬዚዳንትነት ወቅት በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ፖለቲከኞች በበኩላቸው የሰውየውም አሟሟት የሚያጣራ ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል፡፡ የመሪያቸውንም ሞት «መንግሥታዊ ግድያ» ብለውታል፡፡
«አምነስቲ ኢንተርናሽናል» (Amnesty International) የግብጽ ባለሥልጣናት ስለሞርሲ ሞት ምርመራ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የግብፅ መንግሥት ግልፅ፣ ዝርዝርና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቋል፡፡
የጋዛን ሰርጥ (Gaza Strip) የሚያስተዳድረውና ለመሐመድ ሞርሲ ቅርብ የነበረው ሃማስ (Hamas) መሐመድ ሞርሲ ለግብፅ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ብዙ እንደሆነ በኀዘን መግለጫው አውስቷል፡፡ ለፍልስጤማውያን መብት መከበርም የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቅሶ የተሰማውን ኀዘን ገልጿል፡፡
ማሌዢያም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ኀዘኗን ገልፃለች፡፡ አንድ የፓኪስታን ሃይማኖታዊና የፖለቲካ ቡድን በበኩሉ ሞርሲ በመላው ፓኪስታን ጸሎት እንደሚደረግላቸው ገልጿል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሥርዓተ-ቀብር ትናንት ካይሮ ውስጥ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት የተፈፀመ ሲሆን የደጋፊዎቻቸው ተቃውሞ በአገሪቱ ውጥረት እንዲነግስ ምክንያት ሆኗል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የመሐመድ ሞርሲ ሞት የአረብ አብዮትን ተከትሎ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ለማገገም ለምትጥረው ግብፅ ችግር እየጎተተባት መምጣቱ አይቀርም እየተባለ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 12 /2011
አንተነህ ቸሬ