ፕሮጀክቱ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችንና የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ ያደርጋል

  • በፕሮጀክቶቹ የተገዙ 77 የመስክ መኪናዎች ለፌዴራል ተቋማትና ለክልሎች ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፦ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበረው የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ምዕራፍ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችንና የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት እና በአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት በጋራ በመሆን 289 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 77 ተሽከርካሪዎችን ለክልሎችና ለፌዴራል ተቋማት ርክክብ አድርገዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር )በወቅቱ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበረው የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት 54 ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት 23 ተሽከርካሪዎችንና አንድ ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ክሊኒከ 289 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ ለክልሎችና ለፌዴራል ተቋማት ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የስደተኛ ተመላሽ ፕሮጀክት 265 ሞተር ብስክሌቶች ገዝቶ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ የልማት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ ንጋቱ ቦጋለ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በስድስት ክልሎች፣ በ30ወረዳዎች፣ በ330 ቀበሌዎች እና በ25 የስደተኛ መጠለያዎች ላይ እየተተገበረ ይገኛል።

በዚህም ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብንና ከ750ሺ በላይ ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

አቶ ንጋቱ ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት በ180 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚተገበር ሲሆን በአሁኑ ጊዜም ፕሮጀክቱ ለሚከናወንባቸው ክልሎች 145 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተገዙ 54 ተሽከርካሪዎችን ማበርከቱን ገልጸዋል።

አቶ ንጋቱ ፕሮጀክቱ በምእራፍ አንድ ትግበራው ስደተኞችን ባስጠለሉ 5 ክልሎችና 16 ወረዳዎች ላይ በዓለም ባንክ በተገኘ 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰቦችን እና ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎችም መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ ጀማል አልዬ በበኩላቸው፤ ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ለደቡብ ኢትዮጵያ፣ ለሶማሊያ እና ለአፋር ክልሎች እንዲሁም ሥራውን ለሚያስተባብሩ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ለኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የሚሰራጩ 23 የተለያዩ ዓይነት ቶዮታ ሃርድ ቶፕ እና አንድ ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ህክምና መስጫ ክሊኒክ ግዥ መፈፀሙን ተናግረዋል።

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You