የምሥራቅ ሸዋ ዞን በመኸር እርሻ 528 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን አቅዷል

– በክረምት ከ250 ሚሊዮን በላይ የአረንጓዴ አሻራ ችግኞች ይተከላሉ

አዲስ አበባ፡– ዞኑ በመጪው የመኸር እርሻ ወቅት 528 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ማቀዱን የምሥራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ቢሮ አስታወቀ፡፡ በዘንድሮው ክረምትም ከ250 ሚሊዮን በላይ በአረንጓዴ አሻራ ችግኞች እንደሚተከሉም ተገልጿል፡፡

የዞኑ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለመጪው የመኸር እርሻ ከጥር ጀምሮ ለአርሶ አደሮች፣ ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት እንዲሁም የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት ዝግጅት ተጀምሯል፡፡

በዚህም በዘንድሮ የመኸር እርሻ ዞኑ 528 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ማቀዱን ገልጸው፤ ከዚህም 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የመሬት ዝግጅት የመጀመሪያ ዙር እርሻ መታረሱን የገለጹት ኃላፊው፤ እስካሁንም 200 ሺህ ሄክታር መሬት ማረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ከሚለማው መሬት 50 በመቶ የሚሆነው ስንዴ ሲሆን፤ የተቀሩት በሌላ ሰብሎች የሚሸፈን ይሆናል ያሉት አቶ መስፍን፤ በዞኑ የበቆሎ ዘር ቀድሞ የሚዘራ በመሆኑ የዝግጅት ሥራው ተጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮ መኸር እርሻ ለየት የሚያደርገው የሜካናይዜሽን ሥራዎችን አጠናክሮ ለመሥራት መታቀዱ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፤ አምና 81 በመቶ የነበረውን የቴክኖሎጂ ሽፋን ዘንድሮ 90 በመቶ ለማድረስ ይሠራል ብለዋል፡፡

ኃላፊው፤ ዞኑ አምና የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ሆኖበት መቆየቱን አውስተው፤ ዘንድሮ ድጋሚ ችግሩ እንዳይከሰት ከጥቅምት ጀምሮ ማዳበሪውን የማስገባት ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡

የመጣውን ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ የማሰራጨት ሥራዎች እየተከናወ ነው ያሉት አቶ መስፍን ፤ለማግኘት ከታቀደው ማዳበሪያ 90 በመቶ የሚሆነው ወደ ዞኑ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገለጻ፤ በዘንድሮ ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሩ በዞኑ 279 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዷል፡፡ በሁለት ሺህ 800 የችግኝ ጣቢዎች ችግኞችን ዝግጁ የማድረግ ሥራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡

ከሚተከሉት ችግኞች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ለደን ልማት የሚያገለግሉ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ሁለት ጥቅም በሚሰጡ ችግኞች ፣ ፍራፍሬና አትክልት እንዲሁም ለተፋሰስ ልማት በሚያገለግሉ ችግኞች የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You