አካዳሚው ለአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፦ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የአመራር ልማት ፕሮግራም ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

አካዳሚው ከትናንት በስቲያ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ወቅት የአካዳሚው ርዕሰ አካዳሚ አቶ ዛዲግ አብረሃ እንደገለጹት፤ አካዳሚው በኢትዮጵያ የአመራር ልህቀት እንዲመጣ ከሚሰራው ሥራ በተጨማሪ የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የአመራር ልማት ፕሮግራም ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የአፍሪካ ለውጥ አራማጅ አመራሮችን በማብቃት የአፍሪካ ውህደት እንዲሳካ ተመሳሳይ የእሳቤ ደረጃ ላይ የሚገኙ አመራሮች እንዲፈጠሩ አካዳሚው እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ብዛት ያላቸውን አፍሪካዊ አመራሮች ማሰልጠንና ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከአካዳሚው ምክትል ፕሬዚዳንቶች ውስጥ አንዱ ከሌላ የአፍሪካ ሀገር እንዲሆን መፈቀዱንና አፍሪካዊያን በጋራ ሊሰሩ የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑን የገለጹት አቶ ዛዲግ፤ በጋራ በመሥራት እርስ በእርስ የሚተሳሰሩበትን መንገድ መፈለግ እንዳለባቸውና አካዳሚው ለዚህም ሁነኛ ማስፈፀሚያ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

አካዳሚው አፍሪካዊ ተቋም እንዲሆን ተድርጎ በመገንባቱ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የምርምር ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመው፣ አፍሪካዊያን የሚጋሯቸው በርካታ ተመሳሳይ ነገሮች በመኖራቸው ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ አካዳሚውን መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ዛዲግ ገለጻ፤ ቀድሞም ኢትዮጵያ ጆሞ ኬንያታን፣ ኒልሰን ማንዴላንና ሌሎችንም የአፍሪካ መሪዎች አሰልጥናለች፡፡ አሁን በተሻለ ቁመና ላይ የምትገኝ በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ለራሱ ችግር ብቻ ግድ የሚሰጠው ሳይሆን የአፍሪካ ችግርም እንዲቃለሉ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ከ11 የአፍሪካ ሀገራት ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት መደረጉንና ይህንንም የማስፋት ሥራ እንደሚከናወን ያነሱት አቶ ዛዲግ፤ አካዳሚው በትንሹ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለተወጣጡ 120 ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና መስጠቱን ገልጸዋል።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው አካዳሚው ይዞት የተነሳው እጅግ የሚደነቅ ሃሳብ በመሆኑ እንደሚደግፉት በመግለፅ፤ የተያዘው ውጥን ከግብ እንዲደርስ ከመሰል አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You